>

ዐፄ ዮሐንስ እና የትግራይ ብሔርተኞች ምንና ምን ናቸው?! (አቻምየለህ ታምሩ)

ዐፄ ዮሐንስ እና የትግራይ ብሔርተኞች ምንና ምን ናቸው?!

 

አቻምየለህ ታምሩ
በዚህ ጽሑፍም ኾነ በሌላ እኔ የትግራይ ብሔርተኞች የምላቸው የትግራይ ተወላጆችን ወይንም የትግራይ ፖለቲከኞችን ሁሉ አይደለም። እኔ የትግራይ ብሔርተኞች የምላቸው የሕ.ወ.ሓትን የፖለቲካ ፕሮግራም የሚያቀነቅኑና ሀገር ለመመሥረት የሚንቀሳቀሱ መንደርተኞችን ነው። ስለዚህ የትግራይ ብሔረኞች ስል ኢትዮጵያዊ ብሔርተኛ የኾኑ የትግራይ ተወላጆችን እንደማያጠቃልል ይታወቅልኝ።
በኢትዮጵያ ምድር የሲዖልን በር በርግዶ የከፈተው የፋሽስት ወያኔ  የአፓርታይድና የግፍ  አገዛዝ  በኢትዮጵያውያን ላይ ሲፈጽመውን  የኖረውን ግፍና መከራ  ላለፉት 27 ዓመታት ስናወግዝ የትግራይ ብሔርተኞች  ሁሉ በግፈኛ ወያኔዎች ላይ የሚሰነዘረውን ሁሉ  የሚረዱት ትግሬነታቸው ስለተጠላ የደረሰባቸው ተቃውሞ  አድርገው እንጂ አንድም ጊዜ  የሚያስጠላ ስራ ስለሰሩ የተከተላቸው  ውግዘት አድርገው ተሳስተው እንኳ አስበውት  አያውቁም። በአለም መድረክ ኢትዮጵያን ወክለው በሚሰሩት ነውር የሚደርስባቸው ተቃውሞ ደግሞ እንደኩሩ ኢትዮጵያዊ በኢትዮጵያዊነታቸው የደረሰባቸው አድርገው ለገበያ ያቀርቡታል። ዘመናዊቷን ኢትዮጵያን እንደገና  ለቋቋም  ዘመናቸውን  የፈጁትን ታላላቆቻችንን  እነ ዐፄ ዮሐንስን፣ ራስ አሉላን፣ ራስ ወልደ ሥላሴን፣ ደጃዝማች ስባጋዲስ ወልዱን፣ ደጃዝማች አባይ ካሳን  ወዘተ እያነሱ የነሱ ልጆች እንደሆኑ  አድርገው ይናገራሉ።
ፋሽስት ወያኔ ከአዲስ አበባ ከተባረረና መቀሌ ከመሸገ ወዲህ ደግሞ ዐፄ ዮሐንስ የተሰዉበት ቀን በታወሰ ወይም በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን በተለይም የሰሜኑ ኢትዮጵያ አካል በነበረችው ባሕር ምድር (የዛሬዋ ኤርትራ) የተደረጉት እንደ ጉንደት፣ ጉራና ሰሐጢ ዓይነት ድሎች በታወሱ ቁጥር ታሪኩን የራሳቸው ለማድረግ በመሽቀዳደም ረገድ የትግራይ ብሔርተኞችን የሚቀድማቸው የለም። ይኹን እንጂ በዐፄ ዮሐንስ ዘመን የተፈጸመው አኩሪ የኢትዮጵያውያን ታሪክ ሊያኮራው የማይገባው ቡድን ቢኖር፣ ባለፉት አርባ አምስት ዓመታት የመጣንበት መንገድ እንዳሳየን በዐፄ ዮሐንሷ ኢትዮጵያ ላይ ሲዘምቱ ለኖሩት የትግራይ ብሔርተኞች ነው።
የትግራይ ብሔርተኞች ከሁሉ በላይ የዘመቱበት፣ የዱቄት መጠቅለያ ያደረጉት ዐፄ ዮሐንስ መተማ ሲሰዉ ተጠቅልለው የወደቁበትን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ነው። ብዙ ሰው አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀዩን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የዐፄ ዮሐንስ አሻራ አድርጎ ቢቆጥርም፣ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ግን ከዐፄ ዮሐንስ በፊት ከ1770– 1808 ዓ.ም. ትግራይን ይገዙ የነበሩት ራስ ወልደሥላሴ የሚያውለበልቡት ሰንደቅ እንደነበር ራስ ወልደሥላሴን በ1793 ዓ.ም. ጨለቆት ሥላሴ የጎበኛቸው እንግሊዛዊው ሄንሪ ሳልት ነግሮናል።
ሄንሪ ሳልት የትግራይ ገዢ ራስ ወልደሥላሴ ያውለበልቡት ስለነበረውና ተከታዮቻቸው ይለብሱት ስለነበረው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ሲገልጽ እንዲህ ሲል ጽፏል፡-
“…  Round their heads, they wore bandages formed of Yellow, green [and] red satin tied behind long and streaming loosely as they rode…” (ምንጭ፡-George, V. V. (1802). Voyages and Travels to India. Ceylon, the Red Sea, Abyssinia and Egypt (London, 1811), Vol. 3, Page 124.)
ሕ.ወ.ሓ.ት ጫካ ሳለ ዱቄት የቋጠረበትና በአገዛዝነት ከተሠየመ በኋላ ደግሞ እንዳይውለበለብ በሕግ ያገደው ሰንደቅ ዓላማ ሄንሪ ሳልት እንደሚነግረን የትግሬው ገዢ ራስ ወልደሥላሴና ተከታዮቻቸው በ1790ዎቹ ያውለበልቡት የነበረውን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ነው።
ከራስ ወልደሥላሴ በኋላ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርገው ያውለበለቡት የትግራይ ገዢና የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ዐፄ ዮሐንስ ናቸው። ከታች የታተመው ሰንደቅ ዓላማ በዐፄ ዮሐንስ ፬ኛ ዘመነ መንግሥት ይውለበለብ የነበረው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ነው። ይህ የዐፄ ዮሐንስ ሰንደቅ ዓላማ አሁንም ድረስ መቀሌ በሚገኘው የዐፄ ዮሐንስ ፬ኛ ቤተ መንግሥት ውስጥ ይገኛል። ይህን ታሪካዊ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በካሜራዬ ያስቀረሁት መቀሌ ዩኒቨርስቲ በማስተምርበት ወቅት የዐፄ ዮሐንስ ፬ኛን ቤተ መንግሥት በጎበኘሁበት ጊዜ ነበር።
በሰንደቅ ዓላማው መሀል ላይ ያለው ምልክት የሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሥዕል ነው። ቅዱስ ጊዮርጊስ በብዙ ሀገሮች ዘንድ የታወቀ እንደመኾኑ በኢትዮጵያም የታወቀ ስመጥር ሰማዕት ነው። ለዚህ እንደ አስረጂ በእንግሊዝን፣ በግሪክ፣ በግብጽ፣ በሶርያና በሌሎች 37 የዓለም ሀገሮች ውስጥ የሚገኙትን የቅዱስ ጊዮርጊስ አብያተ ክርስቲያናት ማውሳት እንችላለን። እንግሊዝ ውስጥ ብቻ በ37 ከተሞች ውስጥ የቅዱስ ጊዮርጊስ አብያተ ክርስቲያናት ይገኛሉ።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አማኞች ዘንድም ቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ጠባቂ ሰማዕት ተደርጎ ይወሰዳል። የቅዱስ ጊዮርጊስ ጽላት ወደ ኢትዮጵያ የገባው በ፲፫ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በዐፄ ዐምደ ጽዮን ዘመነ መንግሥት እንደነበር ከክብረ ነገሥቱ መረዳት ይቻላል። ክብረ ነገሥቱ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳም ውስጥ ብዙ ዓመታት የኖሩ አባ ልዑለ ቃል የተባሉ መነኩሴ ከሶርያ ደብረ ይድራስ ከሚባለው ገዳም የቅዱስ ጊዮርጊስን ጽላት ከገድሉ ጋር አምጥተው ለዐፄ ዐምደ ጽዮን እንዳስረከቡ፣ ዐፄ ዐምደ ጽዮንንም ቤተ ክርስቲያን አሠራለት እንዳሉትና ገድሉን ከዐረብኛ ወደ ግዕዝ እንደተረጎሙ ያትታል።
የዘመኑ ታሪከ ነገሥት ዐምደ ጽዮን የጊዮርጊስን ጽላት አስይዘው ከጠላቶቻቸው ጋር በመግጠም ዐሥር ታላላቅ ዘመቻዎችን በድል አድራጊነት እንደተወጡ፣ ንጉሠ ነገሥቱ «ቅዱስ ጊዮርጊስ አማላጄና ረዳቴ ስለሆነ የኢትዮጵያ ጠላቶች ድል ሊያደርጉኝ አይችሉም» እያሉ በቅዱስ ጊዮርጊስ አማላጅነትና ረዳትነት አብዝተው ያምኑ እንደነበር ያስረዳል።
የዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ጸሐፌ ትእዛዝ እንደነበሩ የሚታመነው መርቆርዮስም አርዌ በድላይ የተባለ ጠላት ብዙ ወታደሮች አሰልፎ ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብን ሊወጋቸው ሲነሣ ንጉሡ የቅዱስ ጊዮርጊስን ጽላት ይዘው ሠራዊታቸውን አስከትተው በመዝመት የኢትዮጵያን ጠላት ድል መትተው ተመልሰዋል ሲሉ ጽፈዋል።
ባጠቃላይ በኢትዮጵያ ነገሥታት ዜና መዋዕል እንደሚነበበው ነገሥታቱ በሚዘምቱባቸው ታላላቅ ዘመቻዎች ሁሉ የቅዱስ ጊዮርጊስን ጽላት ትተው አይንቀሳቀሱም ነበር። ይህንን እውነት ለማረጋገጥ ቢፈለግ በዓድዋ ላይ ከኢጣልያ ጦር ጋር በተደረገው ውጊያ ማለትም በዓድዋ ጦርነት ወቅት ቅዱስ ጊዮርጊስ አደረገው በተባለው ተሳትፎ «ኢትዮጵያን በዓለም ታሪክ በጦር ኃይል ስምንት ጊዜ እጥፍ የሚበልጣትን ሀገር አሸንፋ ታዋቂ የነፃነት ሀገር እንድትባል አድርጓታል» በሚል የሚቀርበውን ታሪክ መመልከት ይበቃል።
የዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ጸሐፌ ትእዛዝ የኾኑት ገብረሥላሴ እንደጻፉት ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ወደ ዓድዋ ሲዘምቱ በአራዳ ገነተ ጽጌ ቤተ ክርስቲያን የሚገኘውን የቅዱስ ጊዮርጊስን ጽላት አስይዘው ነው የዘመቱት። ጦርነቱም ቅዱስ ጊዮርጊስ የእርዳታ እጁን በመዘረጋቱ ኢትዮጵያ ድል እንዳደረገችና ብዙ የጠላት ሠራዊት እንዳለቀ አትተዋል።
በወቅቱ የነበረ አንድ የኢጣሊያ ጋዜጠኛ ወደ ሀገሩ ባስተላለፈው መልዕክት አንድ በነጭ ፈረስ ላይ የተቀመጠ ጀግና እንደፈጃቸውና ይህ በነጭ ፈረስ ላይ የተቀመጠው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ ሠራዊት ጎን ተሠልፎ የኢጣሊያን ሠራዊት እንዳርበደበደው የምንዋጋው ከሰው ጋር ብቻ ሳይኾን ከእግዚአብሔርም ጋር ስለኾነ በጦርነት ድል ልንመታ ችለናል ሲል ዘግቧል። በዚህም የተነሣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ተራዳኢነቱን፣ ፈጥኖ ደራሽነቱን፣ ስለት ሰሚነቱንና አማላጅነቱን የሚያምኑት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምእመናን የቅዱስ ጊዮርጊስ ጽላት በተተከለበት፣ ቤተ ክርስቲያኑ በተሠራበት፣ በዓሉ በሚከበርበትና ስሙ በሚጠራበት ሥፍራ ሁሉ እየተገኙ በጸሎትና በምሥጋና ያስቡታል፤ ፍጡነ ረድኤት ይሉታል።
ይህንን ሁሉ ሀታተ መዘርዘሬ በዐፄ ዮሐንስ ዘመነ መንግሥት በነበረው የኢትዮጵያ ሰንደ ዓላማ መሀል ያለውን የቅዱስ ጊዮርጊስ ሥዕል ከሃይማኖታዊነቱ ባሻገር ትርጉሙ ጠባቂ ሰማዕት ለኢትዮጵያ መኾኑን አጽንዖት ለመስጠት ነው።
የቅዱስ ጊዮርጊስን መስቀል በሰንደቅ ዓላማቸው መካከል ባደረጉት በእንደ እንግሊዝ፣ ዴንማርክ፣ ስዊድን፣ ኖርዌይ፣ ፊንላንድ፣ ወዘተ ሀገሮች የየሀገሩን ሰንደቅ ዓላማ ለማክበርና ከሰንደቁ በፊት ለመውደቅ እንደ ሃይማኖታቸው ሥርዓት ቃለ መሀላ በመፈጸም ዜጋ የሚኾኑት የመላው ዓለም የእስልምና እምነት ተከታዮች፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ መስቀል ላለባቸው ሰንደቅ ዓላማዎች ቃለ መሀላ የሚፈጽሙትና ለማሉበት ሰንደቅ በጦር ሜዳ ሕይወታቸውን የሚሰጡት የቅዱስ ጊዮርጊስን መስቀል ትርጉም በሃማኖታዊ ምልክትነቱ ሳይኾን በሀገር ጠባቂነቱ ወስደውት ነው። ኢትዮጵያውን ክርስቲያኖች ጭምር ነቢዩ መሐመድ ስለ ኢትዮጵያ በተናገሩት መልካም ነገር የሚኮሩትና የሚጠቅሱት ሃይማኖታቸው እስልምና ስለኾነ ሳይኾን ነቢዩ «ኢትዮጵያን አትንኩ» ያሉት የኢትዮጵያ ጠባቂ የአደራ ቃላቸው ሀገራዊ ፋይዳ ስላለው ነው።
ባጭሩ በዐፄ ዮሐንስ ዘመነ መንግሥት የነበረው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ መሀል ያለው የቅዱስ ጊዮርጊስ ምልክት ትርጉምም፣ ልክ ከተለያየ ዓለም ወደ እንግሊዝ፣ ዴንማርክ፣ ስዊድን፣ ኖርዌይ፣ ፊንላንድ፣ ወዘተ ሀገሮች የሚሄዱ የእስልምና እምነት ተከታዮች የሚምሉበት ሰንደቅ ዓላማ መሀል እንዳለው መስቀል ዓይነት ሀገራዊ ትርጉምና ፋይዳ ነው ያለው።
ይህን በዐፄ ዮሐንስ ዘመነ መንግሥት ብሔራዊ ምልክት የነበረውን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አጥብቀው ከሚጠሉት ብሔርተኞች መካከል ቀዳሚዎቹ የትግራይ ብሔርተኞች እንደኾኑ ቀደም ብዬ አውስቻለሁ። አስገራሚው ነገር በዐፄ ዮሐንስ ሰንደቅ ዓላማ ላይ ከሁሉ በላይ የዘመቱት የጉንደት፣ ጉራ፣ ዶጋሊና ሰሐጢ ድሎችን የራሳቸው ለማድረግ የሚቃጣቸውና ‹የዐፄ ዮሐንስ ልጆች ነን› የሚሉን የትግራይ ብሔርተኞች ናቸው። ዐፄ ዮሐንስ እድል አግኝተው ቀና ቢሉ ከሁሉ በላይ የሚያፍሩት የዐፄ ዮሐንስ ልጆች ነን በሚሉት በትግራይ ብሔርተኞች ይመስለኛል።
የትግራይ ብሔርተኞች የዘመቱበት ሌላኛው የዐፄ ዮሐንስ አሻራ የአማርኛ ቋንቋ ነው። ዐፄ ዮሐንስ በተደራቢነት የሚናገሩትን ቋንቋዬ ነው ብለው ብሔራዊ ቋንቋ ያደረጉትን አማርኛን ‹በትግሬ ላይ የተጫነ› ብለው ከሁሉ በላይ የዘመቱት ነውር ጌጡ የኾኑት የትግራይ ብሔርተኞች ናቸው።
የትግራይ ብሔርተኞች በዐፄ ዮሐንስ ታሪክ ላይ የዘመቱበት ሌላኛው አሻራቸው ኢትዮጵያን የዳግማዊ ምኒልክ ስሪት አስመስለው በወረራና በቅኝ ግዛት የተፈጠረች ኢምፓየር አድርገው ይህን ትርክታቸውን በመንግሥትነት ሲሰየሙ ብሔራዊ ታሪክ አድርገው ትውልዱን ማበላሸታቸው ነው።
የኢትዮጵያን ወሰን በሚመለከት ዐፄ ዮሐንስ ከሰመራ ከተማ በካቲት 11 ቀን 1873 ዓ.ም. ለጀርመኑ ንጉሥ ቀዳማዊ ዊልሄለም በጻፉት ደብዳቤ እንዲህ ሲሉ ጽፈው ነበር፡-
«[ሀገሬ] በምሥራቅ በደቡብ ወገንም ዲካው [ድንበሩ] ባሕር [ሕንድ ውቅያኖስን ማለታቸው] ነው። በምዕራብ በሰሜን ወገንም ባሕር በሌለበቱ ከኑብያ፥ ከካርቱም፣ ከስናር፣ ከሱዳን በስተቀር ጋላ፣ ሻንቅላ፣ እናርያ፣ አዳል የያዘው ሀገር ሁሉ የኔ ነው። አሁን እንኳ በቅርብ ከሸዋ በታች ያለው ሐረር የሚባል ሀገሬ በቱርክ ተይዟል። ይህን ሁሉ መጻፈ ያገሬ ድንበሩ ይታወቅ ብዬ ነው።»
በዚህ መልክ ተመዝግቦ የሚገኘውን የዐፄ ዮሐንስ ዘመን የኢትዮጵያ ድንበር አፍርሰው የዛሬዋን ኢትዮጵያ ‹ምኒልክ ነጻ የነበሩ የአፍሪካ ሀገሮችን ወርሮ የፈጠራት የብሔር፣ ብሔረሰቦች እስር ቤት የሆነች ኢምፓየር ናት› ብለው ከሁሉ በላይ በዐፄ ዮሐንስ ሀገር ላይ የዘመቱት፣ የዐፄ ዮሐንስን ኢትዮጵያ ያፈረሷትና ያደሟት ‹የዐፄ ዮሐንስ ልጆች ነን› የሚሉን ጉደኞቹ የትግራይ ብሔርተኞች ናቸው። እነዚህ ማፈሪያዎች ‹አባታችን ናቸው› የሚሏቸው ዐፄ ዮሐንስ ቀና ቢሉ የትኛውን የአባታቸውን ራእይ ወረስን ብለው ይነግሯቸው ይኾን?
ማፈሪያዎቹ የትግራይ ብሔርተኞች በዚህ አላበቁም። አዲስ አበባን እንደ ኦ.ነ.ጋውያን ሁሉ ፊንፊኔ እያሉ በመጥራት ከኦሮሞ ውጭ ያለው የአዲስ አበባ ነዋሪ (ትግሬን ጭምር) እንደ ኦ.ነ.ጋውያን ሁሉ ሰፋሪ እያሉ ሲሳደቡ የሚውሉት ግራኝ አሕመድ ኢትዮጵያን በወረረ ጊዜ የበረራን የዐፄ ዳዊት ቤተ መንግሥት ላለማስደፈር በአማራው አዛዥ ደገልሃን የሚመራው የባሌ ጦር በዛሬው አዲስ አበባ ዙሪያ ተጋድሎ ሲያደርግ አብረው ሲፋለሙ የወደቁት የትግሬ መኳንንት ሮቤል ደም የፈሰሰበትን ምድር ነው።
ታሪኩን ለማታውቁ፣ የትግሬ ገዢ የነበሩትና በዘመነ መሳፍንት አንጋሽ የነበሩት ራስ ሚካኤል ስሑል በረራን ከግራኝ አሕመድ ለመከላከል በተደረገው ተጋድሎ የወደቁት የትግሬ እንደርታ ተወላጁ የትግሬ መኳንንት ሮቤል ዘር ናቸው። እፍረተ ቢሶቹ የትግራይ ብሔርተኞች የስሑል ሚካኤል ልጆች ነንም ይላሉ። ይህን የሚሉን እነዚህ አሳፋሪ ፍጡራን ግን የስሑል ሚካኤል እንሽላት (ስምንተኛ ትውልድ) የኾኑት ትግሬ መኳንንት ሮቤል የወደቁበትን የዛሬውን አዲስ አበባ አካባቢ የትግሬ መኳንንት ሮቤል ትውልዶችና አብረዋቸው የወደቁት የአዛዥ ደገልሃን ልጆች ርስት አይደለም ብለው የትግሬ መኳንንት ሮቤልንና የአዛዥ ደገልሃንን ትውልዶች ሰፋሪ እያሉ ከኦ.ነ.ጋውያን ጋር ሲሳደቡ ይውላሉ። እንደሚኮሩባቸው ሁሉ እነ ዐፄ ዮሐንስን ‹አባቶቻችን ናቸው› እያሉ ‹አባቶቼ ናቸው› በሚሏቸው ቀደምት የኢትዮጵያ አባቶች ታሪክና ሥራ ላይ
እነ ግራኝ፣ ፋሽስት ጣሊያንና ግብጽ/ቱርክ እንኳ እንደ ትግራይ ብሔርተኞች የዘመተበትና የእነዚህ ቀደምት ታላላቆችን አሻራ ያወደመ ፍጡር በታሪክ ውስጥ ስለመኖሩ እጠራጠራለሁ።
እነዚህ አይነት ፍጡራን ናቸው እንግዲህ ነጮችን ያሳፈሩትን አባቶቻችንን ሲያዋርዱና አሻራቸው ሲፍቁ ኖረው ዛሬ ላይ የወያኔው ማፍያ በኢትዮጵያውያን ላይ ሲሰራው የኖረውን  ግፍ በአለም ፊት አጋልጦት ተቃውሞ ሲደርስበት በጥቁርነቱ  የደረሰበት ጥላቻ አድርገው ሊያቀርቡት የሚሞክሩት። በነጮች  ቡራኬ  በመንግሥትነት ሲሰየሙና የነሱ አገር በቀል ወኪል ሆነው  ከነሱ በሚያገኙት ዘመኑ በወለደው ደፍጥጦ የሚያነድ የጦር መሳሪያ ጥቁሮችን 27 ዓመታት ሙሉ ሲረሽኑና ሲያዋርዱ ሲኖሩ ግን  ያንጋሾቻቸው ነጭነትና ሲበድሏቸው የኖሯቸው ግፉዓን  ኢትዮጵያውያን ጥቁርነት አልታያቸውም ነበር።
Filed in: Amharic