>

ባህላዊ  ...!!! (በእውቀቱ ስዩም)

ባህላዊ  …!!!

 

በእውቀቱ ስዩም
ወይዘሮ አልጣሽ  ስመጥር  የባህል ህክምና አዋቂ ናቸው ፤ አምስት መቶ በላይ ብራናዎችን መርምረዋል:: ከምስጢራዊ ጠቢባን ተምረዋል- ይባላል፤
የሆነ ጊዜ ላይ  ወደ ቤታቸው ሄድኩ፤ ለካርድ አምስት መቶ ብር አስቀድሜ ከፈልኩ፤ካርዱ ራሱ ባህላዊ እንዲሆን ታስቦ ከሰኔል የተሰራ ነው፤
ወይዘሮ አልጣሽ ደርበብ ያሉ ውብ  ሴትዮ ናቸው፤ አፈወርቅ ተክሌ ስእል  ውስጥ ከሚታዩት እናቶች አንዲቱን ይመስላሉ::
“ምንህን ነው የሚያምህ?” ሲሉ ጠየቁኝ::
“ ራሴን! ራሴን  በጣም ያመኛል”
“ ህምም  …መች መች ነው እሚነሳብህ?”
“ማለዳ ከንቅልፌ ስነሳ”
 ወይዘሮ አልጣሽ  በዙፋን ቅርፅ በተሰራው ሶፋቸው   መከዳ ላይ ተለጥጠው  ተመቻቹና እንዲህ አሉ፤
“  በሰው ልጆች ታሪክ የመጀመራው ራስ ምታት ታማሚ ናምሩድ ነው፤ ናምሩድ  የተወለደው ባቢሎን ውስጥ  ነው ይላሉ ፤ ስተት ነው ፤ትውልዱ ፊንቃዊ ለመሆኑ ጥርጥር የለኝም!!   እስከ ሰላሳ ዘመኑ  ድረስ ኢትዮጵያ  መጥቶ ተቀምጦ ነበር:: ባመመው ቁጥር  በራሱ ዙርያ እሚጠመጥማት  ነጭ ሻሽ ለብዙ ዘመን   ባክሱም  ኖራለች:: ልኡል ራስ  መንገሻ ዮሀንስ  ጠምጥመዋት  ፎቶ ተነስተዋል፤ በነገርህ ላይ የልኡሉ ማእረግ ንጉስ ነው! ራስ መንገሻ ይባሉ የነበሩት   ጥኑ ራስ ምታት ስለነበረባቸው  ነው:: አጤ ምኒልክ ራስ መገሻን ድል ካደረጉ በ ሗላ ሻሺቱን ራሳቸው ይጠመጥሟት ጀመር! “
እምለው ቸግሮኝ ዝም አልኩ::
“ አባትህ   ራስ ምታት አለባቸው”?
“ የለበትም ” ብየ መለስኩ::
አልጣሽ ቀጠሉ:-
“ ህምም!  ንጉስ ናምሩድ ሁለት ልጆች ነበሩት፤ አንደኛው ዱርየ ሲሆን  ፤ ሌላኛው  ጭምት ነበር! ዱርየው ልጅ አባቱ ለዘመቻ በወጣ ቁጥር የቤቱን እቃ   ጆሮውን  እያለ ፈጀው ፤ ጭምቱ ልጅ ግን  ዱርየው የሸጠውን እቃ  እንደገና በውድ  ዋጋ ገዝቶ  ወደ ቤቱ ይመልሳል፤   ናምሩድ ሊሞት ሲል ለጨዋ ልጁ  ዘውዱን ከራሱ አውልቆ ሲሰጠው  ለዱርየ ልጁን ደግሞ ራስ ምታቱን አወረሰው ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ  መንግስትም ራስ ምታትም በዘር እሚተላለፉ  ሆነዋል!  ይህንን ነገር መፅሀፈ ኩፋሌ አምልቶ አስፍቶ ፅፎታል፤ ለመሆኑ ራስህን ሲያምህ ምን ታደርጋለህ?”
“ ቡና ጠጣለሁ”
“ ቡና ይቅርብህ! “ አሉ ወይዘሮ አልጣሽ “  በነገራችን ላይ  በሰው ልጆች ታሪክ የመጀመርያው የቡና ሱሰኛ አፄ  ሱስ-ንዮስ ነበር፤ ኢሉምናምንቴዎች   ፖርቱጋሎች የቡናን አመል  ከታች ማዶ አምጥተው  አለመዱት!  ሱስ-ንዮስ  አገራችንን  ለፖርቱጋሎች ትቶ : ቡናውን አስፈልቶ ፤ ፈንድሻውን አስቆልቶ፤ አጫጭሶ ከልጁ ጋር አብሮ ፏ-ሲል ይውል ነበር፤ፏ-ሲል የሚለው አነጋገር በጊዜ ብዛት ” ፋሲል “ሆኗል“
ራስ ምታቴ እየጨመረ  ሲመጣ ይሰማኝ ጀመር!
በመጨረሻ በጉጉት ስጠብቀው የነበረውን  መዳኒት የሚያዙልኝ ጊዜ ደረሰ ፤  የሆነ የሰለሞን እፅ ይሰጡኛል ብየ  ጠብቄ ነበር፤ ፓራሲታሞል እንዳዘዙልኝ  ስመለከት  ግን  ውሃ ሆኘ  ቀረሁ::
” ምነው?” አሉኝ  መደናገጤን አጢነው፤
“ ባህላዊ መድሃኒት ነበር  ከርስዎ የጠበኩት”
“ ጃኖ ወይም በርኖስ ለብሰህ ከዋጥከው ባህላዊ መሆኑ መች ይቀራል?”
Filed in: Amharic