>

ይድረስ ለአቶ ደመቀ መኮንን እና ለአቶ ተመስገን ጥሩነህ (ሀብታሙ አያሌው)

ይድረስ ለአቶ ደመቀ መኮንን እና ለአቶ ተመስገን ጥሩነህ

ሀብታሙ አያሌው
አማራ በሚል በተከለለው ‹‹ክልል›› ውስጥ የተለያዩ ቡድኖች  ከፋኝ/ፋኖዎች ጦር መሳሪያ አንስተው ዱር ቤቴ ብለው ‹የከረሙት ህዝባችን ተጠቃ›፣ ‹የሚቆምለት መንግስት ጠፋ› ብለው ነው፡፡ እርስዎና ፓርቲዎ ለህወሓት ገብረው በአማራ ህዝብ ላይ ያ ሁሉ ግፍ ሲፈፀም አስፈፃሚ ሆነው እጅዎ በደም ሲነከር የእናንተን ሐጢያት ተሸክመው በህወሓት የጥይት አረር ለመሰዋት ዱር ገደሉን ቀራንዮ ያደረጉ አርበኞች ዛሬ እንደገና ተሳዳጅ እና  በየዱሩ ሟች መሆናቸው ያሳዝናል።
የእናንተ የፖለቲካ ድኩማንነት በፈጠረው ችግር ክልሉ ተፍረክርኮ ትላንት ለህወሓት ዛሬ ለኦነጋውያን ገብሮ የሚያድር  የአስተዳደር ቡድን በህዝቡ ላይ እየቀለደ ይገኛል።  የአዴፓ ምኩን አመራር  የህዝብን ልማት፣ ደህንነትና ሰላም ማረጋገጥ ችሎ ቢሆን ይህ ሁሉ ወጣት ከህወሓትና ከኦነግ የአማራን ህዝብ ለመታደግ ፋኖ ተሰማራ ብሎ ዱር ገደል ባልወረደ ነበር፡፡  ታሪክ እራሱን ይደግማል እንዲሉ  እናንተ የከዳችሁትን ህዝብ ጣሊያንን ጭዳ እዳደረገው እንደ ትላንቱ የጀግኖች ቁንጮ  በላይ ዘለቀ አርበኛ ሆነው ከህወሓት እና ኦነጋውያን ህዝባቸውን የታደጉ አርበኞች በአደባባይ ይሰቀሉ ጀመር።
አንድ መቶ አመት ያልሞላው የተጋድሎ ታሪካችን እንደሚያስታውሰን፤ ታላቁ አርበኛ በላይ ዘለቀና የዘመን ተጋሪው አርበኞች፣ ወራሪውን ጣሊያን የሚመክት የመንግስት አካል ስላልነበረ ህዝብ የማደራጀት ግዴታ ውስጥ ገቡ፡፡ መደራጀቱ ነፍጥን በማንሳት የጀመረ ነበር፡፡ ይሄ የአርበኞች አደረጃጀት በየአካባቢው እየሰፋ ሂዶ ወራሪውን ኃይል የሚፋለሙ ቡድኖች ሊበራከቱ ችለዋል፡፡ ቁም ነገሩ ያለው እነአርበኛ በላይ ዘለቀ ኃላፊነት ወስደው ራሳቸውንና ሀገራቸውን ከጥቃት ለመከላከል የተደራጁበት ዋና ምክንያት ላይ ነው! መንግሥት ፈርሶ ነበር፡፡ ጠላትን ለመመከት የሚያስቸል የተማከለ አደረጃጀት አልነበረም፡፡ ዛሬም  በየቦታው ኢ-መደበኛ አደረጃጀቶች የመበርከታቸው አንዱ ገፊ-ምክንያት ክልሉ አዴፓ በሚባል የሰላቶዎች ስብስብ ሲመራ በመቆየቱ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡
የተረገመው ፖለቲካችን  የደረሰበት የክህደት ቁልቁለት ከአዴፓ አመራሮች ክህደት ተሻግሮ እነዚህ እድሜያቸውን በረሃ የበላው የአማራ ህዝብ ልጆች እምንቱን ቀርጥፎ የበላው (የግንቦት ሰባት)  ዳግም መዘበቻ መሆናቸውም የፖለቲካችን ሰበላነት ደረጃ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ የሚገባው ነው።
ግንቦት ሰባት በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ከዳያስፖራው ለማለብ በረሓ ላይ ፊልም መስሪያ ያደረጋቸው እነ አርበኛ መሳፍንት አፅማቸውን የሚያነሳ እንኳን የሞከረ የለም። “በስድስት ወር አዲስ አበባ ለመድረስ በነፍስ ወከፍ 500 ዶላር ስጡን”  ብለው እልፍ ዶላር የሰበሰቡ እና ጭቡ የሰሩ አካላት ቤተመንግስቱን ከብበው የአማራ ህዝብ ልጅ ትላንት መነገጃቸው ዛሬ ደግሞ በጥይት አረር የሚያስቆሉት በየዱሩ ወዳቂ መሆኑ በቀላሉ የሚታለፍ ተራ ነገር ይሆናል ብለው ካሰቡ በእጅጉ ተሳስተዋል።
አቶ ደመቀ መኮንን እና አቶ ተመስገን ጥሩነህ የዳግመኛ ውድቀታችሁ መጀመሪያ የሰኔ 15ቱ ሴራ ቢሆንም የሃያ ዘጠኝ አመታት ልምዳችሁን ተጠቅመችሁ በማሰር በመግደል ስልጣን ለማስቀጠል የጀመራችሁት ዘመቻ ደግሞ የከፋ ውድቀታችሁ መጀመሪያ ሁለተኛ ምዕራፍ መሆኑን ልታውቁት ይገባል።
የምትረሱት አይመስለኝም ጌታችሁ ህወሓትን ሳልፈራ ባህርዳር መጥቼ ( እመኑኝ ደርግ ወድቋል ህወሓት ይወድቃል ብያችሁ ነበር ) አሁንም እመኑኝ የአማራን ህዝብ ትጥቅ የማስፈታት ስውር ዘመቻ ከቀጠለ በማሰር በመግደል የምታስቀጥሉት ስልጣን አይኖርም። አወዳደቃችሁ ብቻ ሳይሆን አሟሟታችሁንም ይከፋል።  እመኑኝ የጀመራችሁት መንገድ ለጊዜው የሚያዋጣ ይመስላችሁ ይሆናል።  ለጊዜው  የግንቦት ሰባት መዋቅር አይዟችሁ ግፉ እያለ በልጆቻችሁ ደም እጃችሁን ያጨቀየው ይሆናል። ኋላ ግን እናንተንም ግፋ በለው የሚሏችሁ የሴራውን አካላትም ጠራርጎ የሚበላ ማንም የማያቆመው አብዮት ይወለዳል።
Filed in: Amharic