>

ትራምፕ የአለም ጤና ተቋም ድጎማን አገዱ! መመሪያ ሰጡ!!! (ታምሩ ገዳ/ህብር ራዲዮ)

ትራምፕ የአለም ጤና ተቋም ድጎማን አገዱ! መመሪያ ሰጡ!!!

 

 

ታምሩ ገዳ/ህብር ራዲዮ
 
* በተጨማሪም “WHO” የኮሮና ቫይረስ ለመጀመርያ ግዜ በቻይና ሲከሰት ለመደበቅ በመሞከሩ፣ ቫይረሱን ለመቆጣጠር እንደ ተቋም ድክመት በማሳየቱ እና ለቻይና መንግስት ወገንተኛ በመሆኑ ተጠያቂ መሆን አለበት ብለዋል! 
 
“…በሽታው ቻይና ውስጥ ሲከሰት ተቋሙ ባለሙያዎችን ልኮ አስፈላጊውን ክትትል ቢያደርግ እና እርምጃ ቢወስድ ኖሮ ዛሬ ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወት አያልፍም፣ በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በበሽታው አይጠቁም፣ የገጠመን ኢኮኖሚያዊ ቀውስም የአሁኑን እና የወደፊቱን ያህል አይሆንም ነበር!…” ብለዋል!
በኮሮና ቫይረስ፣ሳንባ ቆልፍ ወረርሺኝ  ሳቢይ ከአለማቀፉ የጤና ተቋም(WHO)ጋር ሰሞኑን የቃላት ጦርነት ውስጥ የገቡት የአሜሪካው ፕ/ት ዶናል ትራምፕ አገራቸው ለተቋሙ የምታፈሰው አመታዊ  የገንዘብ ድጎማን ማቆማቸውን ገለጹ።
 ትራምፕ ዛሬ ማክሰኞ  በዋይት ሀውስ ቤተመንግስታቸው በሰጡት  ጋዜጣዊ መግለጫ    ”  በአለማችን ላይ በርካታ ሰዎች እንዲሞቱ ምክንያት ለሆነው ለኮሮና ቫይረስ  ወረርሺኝ ምላሽ ዙሪያ ተቋማዊ ስህተት ለፈጸመው ለWHO የምንሰጠው የገንዘብ ፈሰስ እንዲቋረጥ እና በተቋሙ ላይም ምርመራ እንዲደረግ ለአስተዳደሪ መመሪያ ስጥቻለሁ” ብለዋል።
የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ እና አፍሪካዊ የድርጅቱ መሪ ፣ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የሚመሩት ተቋም ሰምን  በመጥራት ካብጠለጠሉት የአለም መሪዎች ቀዳሚው የሆኑት ፕ/ት ትራምፕ ” እኛ በቻይና እና በተቀረው አለም ላይ  አለማቀፋዊ የጉዞ እገዳ እንዳናደረግ ማከላከሉ ትልቅ ስህተት ነበር፣ይሁን እንጂ እኔ በቻይና ላይ በወሰድኩት እገዳ የበርካታ ሰዎች ህይወትን አተረፍኩኝ ”  በማለት በምክንያትነት ጠቅሰዋል።
እንደ ሲ ኤን ቢ ሲ(CNBC) ዘገባ በአለማቀፉ የጤና ተቋም ላይ የገንዘብ ፈሰስ እገዳ እጥላለሁ ያሉት ፕ/ት ትራምፕ በአሜሪካ ኮንግረስ የተፈቀደ ገንዘብን ከፈቃጁ( ከኮንገረስ) ይሁንታ ውጪ ምን አይነት  የተናጥል እርምጃ እንደሚወስዱ ግልጽ አይደለም፣ስልጣኑም የላቸውም  ተብሏል።ይሁን እንጂ እኤአ በ1974 የወጣው ህግ “ኮንግረስ አስከ ሚወስን  ድረስ ፕ/ቱ ገንዘቡን ለአርባ አምስት ቀናት ሊያቆመው ይችላል።ኮንግረሱ ውሳኔ ካልሰጠ  ገንዘቡ ለተለገሰው ተቋም ይመለሳል” ይላል ።
ፕ/ት ትራምፕ የ አለም ጤና ተቋሙ በኮሮና ወረርሺኝ ዙሪያ በቅድሚያ የሰጠው መረጃ”ወረርሺኝ አይደለም፣ተላላፊ በሽታ  አይደለም፣የጉዞ እገዳም አያሻውም በማለት ከቻይና የተገኘ መረጃን  በመጠቀም አሳስቶናል፣ቻይናን በግልጽነት አወድሷል “ሲሉ ይወቅሳሉ።በአሜሪካ  ውስጥ በአሁኑ ወቅት  በወረርሽኙ  ከስድስት መቶ ሺህ በላይ  ሰዎች የተጠቁ ሲሆን፣ ከሀያ አምስት ሺህ በላይ ሞተዋል፣ይህ አሃዝ አሜሪካኖችን  እና ፖለቲከኞቿን በእጅጉ አንገት አስደፈቷል።
በአሜሪካ የተወካዬች ም/ቤት የአንስተኛው ም/ቤት (Senate Minority Leader )  ተጠሪ የሆኑት የኒዮርኩ ዲሞክራት   ሴንተር ቻክ ሹመር ዛሬ ከ ኤሜ ሲ ኤን ቢ ሲይ(MSNBC) ቴሌቭዥን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ” ፕ/ት ትራምፕ ሁሉም አሜሪካዊ ዜጋ እንደ ደ/ኮሪያ የምርመራ እድል እንዲያገኝ የሚያስችል  የቤት ስራቸውን መስራት ትተው  የአለም ጤና ተቋምን እየተከታተሉ  መወረፉ በአሜሪካ ያለው ነባራዊ ችግሩን አይቀርፈውም፣አያሻሽለውም “በማለት ቅሬታቸውን አሰምተዋል ።
  በአለማችን ሁለት  ሚሊዮን የሚጠጉ  ሰዎችን ያጠቃው፣ከአንድ መቶ ሃያ አምስት ሺህ በላይ  የገደለው፣የአለም ኢኮነሚን እና የሰዎች እንቅስቃሴን ጸጥ ረጭ ያደረገው ፣የሳምባ ቆልፍ  ወረርሽኝ በቻይናዋ ውሃን ከተማ  ከተቀሰቀሰ በሁዋላ እኤአ ጥር/ጀነዋሪ 30, 2020  በአለም ላይ ገና አስራ ስምንት አገራትን ሲመታ ፣ስምንት ሽህ ሰዎችን ሲያጠቃ የመንግስታቱ የጤና ተቋም ”  በሽታው አለማቀፋዊ ምላሽ ያሻዋል” ካለ ከአንድ ወር በሁዋላ  ፕ/ት ትራምፕ በወቅቱ “የኮሮና ቫይረስ  ለአሜሪካ ስጋት አይደለም፣ተቆጣጥረነዋል” ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ላይ ማስፈራቸው እና ባለፈው ጥር/ጀነዋሪ 24 “ቻይና በሽታውን በመቆጣጠር ረገድ በበርትታ ሰርታለች፣ ለግልጽናቸውም አሜሪካ በጣም ታደንቃለች /The United States greatly appreciates their efforts and transparency.”
” ማለታቸው  ዛሬ ድረስ በአሜሪካ ፖለቲከኞች ፊት ለብርቱ ትችት አጋልጧቸዋል።
ፕ/ት ትራምፕ ዛሬ በሰጡት  አስተያየት ዙሪያ አለማቀፉ የጤና  ተቋም የሰጠው  አፋጣኝ ምላሽ ባይኖርም  ዶ/ር ቴድሮስ ባለፈው ሚያዚያ/አፕሪል 8, 2020 እኤአ  ለጋዜጠኞች በሰጡት አስተያየት  ”  የአስክሬን   ክምር እንዲበራከት ካልፈለግን በቀር፣ፖለቲካውን ወደ ጎን አድርገን ይህ  ሃይማኖት፣ ፖለቲካ  ….ወዘተ የማያውቀው ወረርሽኝን በጋራ እንዋጋው”ማለታቸው አይዘነጋም። የኮሮና ወረርሺኝ  አለማቀፋዊ ስጋት ከሆነ ጀምሮ  ዶ/ር ቴድሮስ እና የሚመሩት ድርጅት በሽታውን በመቋቋም እና የመረጃ ፍሰት ዙሪያ  የተከተሉት ፖሊሲ በርካታ ትችቶችን እና ድጋፎችን እያስተናገደ ይገኛል።
Filed in: Amharic