>

ቆንስላ ጄኔራል ዶር ብርሀነ መስቀል ሰኚ ከዲፕሎማቲክ ስልጣናቸው ተባረሩ !!! (ኢትዮ 360) 

ቆንስላ ጄኔራል ዶር ብርሀነ መስቀል ሰኚ ከዲፕሎማቲክ ስልጣናቸው ተባረሩ !!!

ኢትዮ 360 
በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ግዛት የኢትዮጵያ  ቆንስላ ጄኔራል በመሆን ላለፈው አንድ አመት በለውጡ አስተዳደር የተሾሙት ዶር ብርሀነመስቀል አበበ ሰኚ ከስልጣናቸው መባረራቸውን የዲፕሎማቲክ ምንጮች ለኢትዮ 360 ገለፁ::
 ቆንስላ ጄኔራል ዶር ብርሀነ መስቀል ሰኚ ከዲፕሎማቲክ ተልዕኮአቸው ባፈነገጠ መልኩ ፅንፈኛ የኦሮሞ ብሄርተኛ ፅሁፎችን በማህበራዊ ሚዲያ በማስተጋባት እና በዘረኝነታቸው ይታወቃሉ::
 ዶር ብርሀነመስቀል ስኚ ከሀላፊነታቸው መነሳታቸውን የፃፈው የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የሰው ሀብት ልማት ፅህፈት ቤት ሲሆን አምባሳደሩ እስካሁን ላገለገሉት ጊዜ ምስጋና ከማቅረብ ውጭ የተባረሩበትን ምክንያት አልገለፀም::ሌላ ቦታ ስለመመደባቸውም ያለው ነገር የለም::
    ይህም ሆኖ ግን አምባሳደሮች በአዲስ አበባ ስልጠና ሲወስዱ በማጠቃለያው  ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ አንዳንድ ዲፕሎማቶች ከተሰጣቸው ሀገራዊ ተልዕኮ ይልቅ የብሄር አጀንዳ የሚያስተጋቡትን በስም ሳይጠቅሱ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበው ነበር::
ዶር ብርሀነ መስቀል ግን ብሄር ተኮር  እና ፅንፈኛ ፅሁፎችን ከማውጣት እንዳልተቆጠቡ መረጃዎች ያመለክቱ እንደነበር የኢትዮ 360 ዲፕሎማቲክ ምንጮች ገልፀዋል::
እናም በአቶ ገዱ እንዳርጋቸው የሚመራው የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በአቶ ብርሀነመስቀል ላይ እርምጃ ለመውሰድ መገደዱን ምንጮች ጨምረው ገልፀውል::
 በካሊፎርኒያ ሎስአንጅለስ የኢትዮጵያ ቆንስላ ጄኔራል የነበሩት ዶር ብርሀነመስቀል ሰኝ በቀድሞው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዶር ወርቅነህ ገበየሁ በአቶ ለማ መገርሳ ጎትጏችነት ሹመቱን እንዳገኙ ይነገራል:: ዶር ብርሀነመስቀል ሹመቱ ሲሰጣቸው አክቲቪስት እንደነበሩ እና የአሜሪካ ዜግነታቸውንም እንደያዙ መሆኑም አይዘነጋም::
አምባሳደር ብርሀነመስቀል ከሃላፊነት መነሳታቸውን በተመለከተ እርሳቸውን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም::
Filed in: Amharic