>

የሕግ ባላሙያዋን እና ጋዜጠኛውን ፍቷቸው! ዋስትና ማግኘት ሕገ መንግሥታዊ መብት ነው! (ያሬድ ሀይለማርያም)

የሕግ ባላሙያዋን እና ጋዜጠኛውን ፍቷቸው! ዋስትና ማግኘት ሕገ መንግሥታዊ መብት ነው!

 

ያሬድ ሀይለማርያም
ፍርድ ቤት ይፈታል ፖሊስ “አልለቅም!” ይላል !!!
 
መንግስት በጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ እና በሕግ ባለሙያዋ ኤልሳቤት ከበደ ላይ እየፈጸመ ያለውን የመብት ጥሰት ሊያቆም ይገባል። ሁለቱም ግለሰቦች ተጠርጥረው የታሰሩበት የወንጀል አይነት በምንም መልኩ የዋስትና መብት የማያሳጣቸው መሆኑ እየታወቀ ፖሊስ ከቅድመ ምርመራ ጊዜ ጀምሮ ግለሰቦቹን አስሮ ማንገላታቱ ግልጽ የመብት ጥሰት ብቻ ሳይሆን የሕግ የበላይነትንም መደፍጠጥ ነው።
ጋዜጠኛ ያየሰው በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በቁጥጥር ከዋለ በኋላ ፍርድ ቤት ቀርቦ የሃሰት መረጃ በማሰራጨት ወንጀል ተጠርጥሮ መያዙ ተገልጾ ትናንት ፍ/ቤት በ25,000 ብር ዋስ ከእስር እንዲወጣ ወስኖለት ነበር። ይሁን ፖሊስ ግለሰቡን ከእስር መልቀቅ ሲገባው የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ወደጎን በመተው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሌላ የክስ ፋይል በመክፈት በፍርድ ቤት የተረጋገጠለትን የዋስትና መብቱን ነፍጎታል። የሕግ ባለሙያ እና የመብት ተሟጋች የሆነችው ኤልሳቤትም ታስራ በምትገኝበት የሃረሪ ክልል ፖሊስ የዋስትና መብቷን ተነፍጋ በእስር ላይ በመጉላላት ትገኛለች።
በሁለቱም ጉዳይ ላይ በግልጽ እንደሚታየው በወንጀል ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች በዋስትና ተለቀው ጉዳያቸውን የመከታተል መብት እና በፍርድ ቤቶቹ የሚሰጡም ትዕዛዞች ዛሬም እንደትላንቱ በመንግስት ሹማምንት የሚጣሱ መሆናቸውን ነው።
መንግስት ሁለቱንም ግለሰቦች ከሕግ አግባብ ውጭ አስሮ የሚያጉላላበት መንገድ የአገሪቱን ሕግ የጣሰ እና በሕገ መንግስቱም የተረጋገጡ የዜጎች መብት እና ነጻነቶችንም የጣሰ ነው። አሁንም ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ሁለቱ ግለሰቦች ከእስር እንዲፈቱ እና የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅ ለማሳሰብ እንወዳለን።
ፍትህ ለሕግ ባለሙያዋ ኤልሳቤት እና ለጋዜጠኛ ያየሰው!
Filed in: Amharic