>

የምድራችን ታሪካዊው ምርጫ!!! (በዲያቆን ዶክተር ያየህ ነጋሽ)

የምድራችን ታሪካዊው ምርጫ!!!

በዲያቆን ዶክተር ያየህ ነጋሽ
ከ1,979 ዓመት በፊት በዛሬው ዕለት ኢየሩሳሌም ታሪካዊ ምርጫ አደረገች። ምርጫዋ በሚገባ ተከብሮላታል። ከዚያ በኋላ ላለፉት 1,979 ዓመታት ምናልባትም ለወደፊቱ እስከ ምጽዓተ ክርስቶስ ድረስ የምርጫዋን ትሩፋት እየተቀበለች ትኖራለች። አዎ! ያኔ ሁለት ተመራጮች ቀርበውላት ነበር። ይበጀኛል ያለችውን መረጠች።
#አንደኛው ተመራጭ በፊቷ ቆሟል። በሮማውያን ወታደሮች ተደግፎ እጆቹ ወደኋላ የታሰሩ፣ ፊቱ በደም የተጨማለቀ፣ ገላው የተተለተለ፣ ከደሙ መፍሰስ የተነሳ በውሃ ጥም የተቃጠለ፣ ከንፈሮቹም ክው ብለው የደረቁ፣ ችሎ መቆም እያቃተው ሊወድቅ ሲንገዳገድ ቀና በል እያሉ ወታደሮቹ የሚወረውሩት፣ መከራው ቢበዛበትም አንዳች ቃል የማይተነፍስ፣ ምረጡኝም ብሎም የማይናገር፣ ወዳጆቹም በዕለቱ በእርሱ ላይ ለምን እንዲህ ይደረጋል? ብለው የማይከራከሩለት፣… ነበር።
ይህን ሰው ባለፋት 3 ዓመታት በሚገባ ታውቀዋለች። ኢየሩሳሌም ብቻ ሳትሆን መላዋ እሥራኤል በደንብ ታውቀዋለች። አዎ! እርሱ በመካከሏ ሲመላለስ መጠን የሌለው በጎነት እንጂ አንዳች ክፋት ያላገኘችበት፣ ልጆቿ ሲራቡ ያበላቸው፣ ሲጠሙ ያጠጣቸው፣ ከደዌአቸው የፈወሳቸው፣ ጎባጦቻቸውን ያቀናላቸው፣ እውሮችን ያበራላቸው፣ በትምህርቱ ያጽናናቸው፣ የዘላለም ተስፋም የሰጣቸው ደገኛ፣ ሰላማዊ አባት ነበር።
#ሁለተኛው ተመራጭ ወኅኒ ውስጥ ነበር። እርሱም ኢየሩሳሌምን በማወክ የታወቀ ነበር። ሰላም የለውም። እርሱ መጣ ከተባለ ሰላም ይርቃል። ከተማው ይታወካል፣ ይረበሻል። ሰውን ማዳን አያውቅበትም፣ መግደል እንጂ። በዓመፅም ነፍስ ከገደሉ ጋር አብሮ ከዓመፀኞች ጋር የታሰረ ነበረ።
ኢየሩሳሌም በዚህ አድራጎቱ በሚገባ ታውቀው ነበር። ሲታሠር እንጂ ሲፈታ እፎይታ እንደማይኖራት ታውቃለች። ወንበዴዎችን አሰማርቶ ሲያሰቃያት ኑሯል። ልጆቿ በሰላም ውለው እንደማገቡ ለኢየሩሳሌም የተሰወረ አይደለም። ሴቶቿ ገበያ ወጥተው በጤና አይመለሱም። ሱቆቿ በሰላም አያድሩም። ከብቶቿ ከስምሪት በደህና ወደ ጋጣቸው አይመለሱም።
እናም በየቀኑ እርሱን ለመክሰስ ወደፖሊስ ጣቢያ እንደተመላለሰች ነው። ሊያበላት ቀርቶ እየዘረፈ ያስራባት፣ መድኃነት ሊሆናት ቀርቶ በየጊዜው እያስጨነቀ አረጋዊያኗን በሽታ ላይ የጣለ ነበር። ለምርጫ ሲቀርብ ግን ጮኸችለት። ድጋፏን አሰማች።
ኢየሱስ ክርስቶስና እና በርባን እንዲህ ለምርጫ ቀረቡ። ኢየሩሳሌም በርባንን መረጠች። አስመራጩ ጲላጦስ ደነገጠ። ምርጫው ፈጽሞ አልተጭበረበረም። ግልጽና ታማኝ ነበር። ኢየሩሳሌም የፈለገችው በርባንን ነው።
የመረጠችውም እርሱን ነው። እናም ይፈታልኝ አለች። እንዲታሰርላት የሮማን ባለስልጣን እንዳላስጨነቀች ሁሉ ዛሬ ፍታልኝ አለች። ጲላጦስ ኢየሱስን ምን ላድርገው? አላት። ስቀለው አለች። ራሷ ከሳሽ፣ ራሷ ፈራጅ ሆነች።
ጲላጦስ ምርጫዋን ማመን አቅቶት ደጋግሞ ጠየቃት። እርሷ ግን አስረግጣ በርባንን ፍታ፣ ኢየሱስን ስቀል አለች። ስቀለው! ስቀለው! ስቀለው!…አለች። ድምጿ በቀራንዮ፣ በደብረዘይት ተራሮች ላይ አስተጋባ። በርባን ይፈታ! በርባን ይፈታ! በርባን ይፈታ! ጩኸት…ጩኸት…ጩኸት…ኢየሱስ ይሰቀል! ኢየሱስ ይሰቀል! ኢየሱስ ይሰቀል! ጩኸት…ጩኸት…ጩኸት…ቃሏ በረታ!!!
እናም ዐይኗ እያየ፣ ጆሮዋ እየሰማ፣ ልቧ እያወቀ፣ በርባንን አስፈትታ ክርስቶስን እንዲሰቀል አደረገች። ምርጫዋም ተጠናቀቀ።
የምርጫ ታዛቢዎቹ እነ ፀሐይ፣ ጨረቃ፣ ከዋክብት፣ ነፋሳት፣ መሬት፣ ወዘተ ተቃውሟቸውን አሰሙ። ኢየሩሳሌም እንደገና ደነገጠች። ግን ምርጫው አልቋል። ውጤቱም ተነግሯል። ማኅተም ተመትቶበታል። ሀዘንም ድንጋጤም ስህተቷን ሊያርሙላት አልቻለችም።
————————
ወገኔ አንተ፣ አንቺ፣ እኔ ዛሬ ማንን መረጥን? አዎ ብዙዎቻችን በቃል ኢየሱስን ብለን ይሆናል። ኢየሱስን መምረጥ በቃል ብቻ ሳይሆን የሚገለጠው በተግባር ጭምር ነው። በሥራ ጭምር ነው። በውሎ እና አዳር ጭምር ነው። በሥራ ቦታ ጭምር ነው። በገበያ ውስጥም ነው። በታክሲ፣ በአውቶቡስ ተራ ጭምር ነው። በትምህርት ቤት፣ በፍርድ ቤትም ጭምር ነው።
ውሎህ የት ነው? በክፋት አደባባይ፣ በስርቆት ዋሻ፣ በዝሙት ጓዳ፣ በተንኮል ሸንጎ ከሆነ ምርጫህ በርባን ነው ማለት ነው። የራስህን ምቾት ብቻ እያሰብክ፣ ለራህ ድሎት ስትል ሌላውን በደይን ውስጥ ለማኖር የምትጥር ከሆንክ ምርጫህ የአይሁድ ምርጫ ነው።
የመንግሥት ስልጣን ተገን አድርገህ ሕዝብንም ቤተክርስቲያንም ለመበደል ቀንና ሌሊት የምትተጋ ከሆንክ አንተ ምርጫህ በርባን ነው።
ስለዚህ ምርጫህን አስተካክል…! ምርጫን ማስተካከል ትችላለህ። ምርጫው ተጠናቅቋል፣ ታትሟል ተብሎ አትከለከልም። ግን እንዳይመሽብህ!!!
መቼውንም መርጠነው ብንሄድ እኛን ለመቀበል ዝግጁ የሆነው፣ ቢከዳም ጨርሶ የማይቀየመው፣ ፊቱን በይቅርታ የሚያዞረው ጌታ ይርዳን!!!
ወደ ፈጣሪ እንጸልይ
እጆቻችንንበሳሙናእንታጠብ
አፍናአፍንጫችንንእንሸፍ
Filed in: Amharic