>
5:13 pm - Wednesday April 19, 4254

ኑ...ዛ....ዜ... ! ! ! (መስፍን ማሞ)

ኑ…ዛ….ዜ… ! ! !

 

መስፍን ማሞ
– ጌታ ሆይ መኖሪያዬ መሥሪያ ቤቴ ነው አልንህ ፣ መሥሪያ ቤቱም እንዳትመጡብኝ ብሎ ዘጋ ።
 –   አዋቂዎች ስለ እኛ እየተመራመሩ ነው እንተኛ አልን ፣ እነርሱም ከአቅማችን በላይ ነው አሉን ።
– ሰንበትን ሽረን ትምህርት ቤቶችን ከፈትን ፣ ስድስት ቀን የሠራነው ሳይበቃን በሰባተኛውም ቀን እንሥራ አልን ፤ ትምህርት ቤቱም ፤ ለወራት ተዘጋ ። አንድ ሰንበትን ሽረን ሰባቱንም ቀን ሰንበት አደረግኸው ።
– ከምርጫ ግርግር ለመዳን ብለን ውጭ አገር ኮበለልን ፣ እዚያም ሞት ቀድሞ ጠበቀን ።
– ይህ መሬት የእኛ ነው ውጣልን ተባባልን ፣ እጃችሁ የእናንተ አይደለም አፋችሁን አትንኩ ተባልን ።
– ጎዳናው ማረፍ ፈልጎ ለመነህ ፣ አንተም ሰምተኸው ጸጥ አደረግከው ።
–  ሰማዩን በተበከለ አየር ጋረድነው ፣ እኛን እቤት ስታስቀምጥ ውበቱ ፈክቶ ይኸው እየሳቀ ነው ።
– በሽታውን ከእንስሳ መጣብን አልን ፣ በልተውን ሳይሆን በልተናቸው መሆኑን ረሳን ።
– ጭጋጉ ያደጉ ከተሞችን ሸፍኖ ነበር ፣ ይኸው ከዋክብት ሊያበሩ መጡ ።
– አንድ በሽታ ሲመጣ የሚያጠቃው ጥቁሮቹን ነው አልን ፣ ሁሉም የሚያቃስትበትን በሽታ አመጣህ ።
– እግዚአብሔር አላመጣውም ሰዎች ለቀውብን ነው አልን ፣ ክፉዎችን በክፉዎች እንደምትቀጣ ረሳንህ ። – እኛን አይነካንም ብለን ተመጻደቅን ፣ እምነታችን ከካዱት የተለየ እንዳልሆነ አሳየኸን ።
– ጸሎታችን ልዩ ነው አልንህ ፣ የወንድም ቀባሪዎችን ጸሎት መስማት መቼ ጀምረህ ነው 
– ያልታመመውን ካልፈወስን እያልን ነገድን ፣ የታመመ ሲመጣ አዳራሹን ለቀን ወጣን ።
– እግዚኦ ብንል አልን ቅዱሶቹን አርክሰን ፣ አማኞቹን አውግዘን ፣ ንጹሖቹን ስም ሰጥተን የምትሰማን መስሎን ተታለልን ።
– አቤት ፣ አቤት እያልንህ እህል እንደብቃለን ። እየጸለይን ሰውን እንዘርፋለን ።
– የእኔ ዘር ያልሆነ አልይ አልን ፣ እናትና ልጅን የማያስተያይ በሽታ ተማለን አወረድን ።
– ሰው ዘቅዝቀን ሰቀልን ፣ አየር የሚያሳጣ ጉድ መጣብን ።
–  ያለ ፍርድ ሰውን እንደ እባብ ቀጥቅጠን ገደልን ፣ ፍርድ ቤት የሚያዘጋ የበሽታ ባለሥልጣን ከተፍ አለብን ።
– የገደልነውን ሬሳ አይነሣም ብለን ፎከርን ፣ ቀባሪ የሚያሳጣ ደዌ ጎተትን ።
– ጠግበን ነበረ ፣ የምንናገረውን መመጠን አቅቶን ነበረ አፍስሰነው ነበረ።
– በሰማይ ደመና እንጂ ዙፋን አልታየንም ነበር ።
 ጌታ ሆይ እንዴት ታዘብከን ።
– በጣም ተገፋፋን ፣ አብሮ አደጎች ተካካድን ፣ በሚያራርቅ ሕመም አትነካኩ ተባልን ።
– ሥልጣኔአችንን የሚያቆመው ኃይል የለም ብለን ተናግረን ሳንጨርስ ጉንፋን አቆመን ።
– የአንዲት አገር በሽታ ነው ብለን ስንሳደብ የሁሉም አገር እንዲሆን አደረግን ።
– ተፋፍገው የሚኖሩ ድሆች በሽታ አያጣቸውም አልን ፣ ቤተ መንግሥት የሚኖሩ ሲጠቁ አየን ።
– ፈረንጅ አገር ሂዶ መምጣት ልዩ ነገር መሰለን ፣ ዛሬ የሚያሳስበን ሆነ ።
– ግደለኝ እያልንህ ስንለምንህ ከረምን ፣ ዛሬ አልኮል ለመግዛት ተሰለፍን ።
የዛሬውን ችግር ሳናይ የትላንቱን አደነቅን ፣
ይባስ እንደማያልቅ አስተማርከን ።
ሁሉም ነገር አንድ ቀን ቀጥ እንደሚል ዋዜማውን አሳየኸን ። ቃልህን ለመስማት ኮራን ፣ የተማርኩት በቂ ነው አልን ፤ ስብከተ ወንጌል የለም ተባልን ። ቅዳሴ ለማስቀደስ ተፈተንን በየቤታችሁ ሁኑ ተባልን ። ሰው ሰብስቦ ማስተማር ሰለቸኝ አልን ፣ ባዶ ቤት መስበክ ጀመርን ። ሰው ሰላም እንዳይለን እንሸሽ ነበር ፣ በአዋጅ አትጨባበጡ ተባልን ። የጠላነው መነካካት ዛሬ ሕግ ሆኖ መጣ ። መተቃቀፍ አስጠላን ፣ የሚተቃቀፉትን ፖሊስ ይለይ ተባልን ። ጨረቃ ላይ ደርሰናል ብለን ስንኮራ ገና እጃችሁን ታጠቡ የሚል ምክር እንሰማለን ። ጠላት አለብኝ እያልን ስንለፈልፍ በእጃችሁ ዓይናችሁን እትንኩ ፣ እጃችሁ ነው ጠላታችሁ ተባልን ።
ለትዳራችን የሚሆን ጊዜ አጥተን ተረሳስተን ነበር ፣ አሁን ሃያ አራት ሰዓት አብረን ስንቀመጥ ተፋጠጥን ። ሥራችንን ጠልተን ጥቁር ሰኞ እንል ነበር ፣ ዛሬ መሥሪያ ቤቱ ናፈቀን ። ሰዓቱ ሳይሞላ ከሥራ ወጥተን ነበር ፣ ዛሬ ትርፍ ሰዓት መሥራት አማረን ። ከሠራነው ላይ አሥራት ለመስጠት ተፈትነን ነበር ፣ ዛሬ ግን ያስቀመጥነውን ያለ ደስታ እንበላለን ።
ጌታ ሆይ ጣትህን ብትዘረጋ እንዲህ የሟሸሽን ክንድህን ብትዘረጋ የት ልንገባ ነው  ብናኝ ልጆችህን ይቅር በለን ። አክብረኸን ማረን እንጂ አክብረኸን እንዳትጣላን ። እኛ ሰው ፣ አንተ አምላክ ነህ ። እባክሀ ይቅር በለን ። በመልካም አስበን ።
ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ክብር ምስጋና ይሁን ። ከምታልቀዋ ከዛሬዋ ቀን እስከማይፈጸም ዘመን ። ከደካማው ልባችን እስከ ጸናው ሰማይ ። ለዘላለሙ አሜን
Filed in: Amharic