>

የዶክተር አብይ ፒኮክና የይሁዳ አንበሳ (ገለታው ዘለቀ)

የዶክተር አብይ ፒኮክና የይሁዳ አንበሳ 

 

 

ገለታው ዘለቀ

 

 

ወደ ዛሬው ርእሴ በቀጥታ ከመግባቴ በፊት ወቅቱ የኮረና ቫይረስ ሃገራችንን ስጋት ላይ የጣለ በመሆኑ ህዝቡ ራሱን እንዲጠብቅ እንደ ዜጋ እየጠየኩ በውነት እግዚአብሄር ሃገራችንን ከዚህ በሽታ ይታደግልን።

ይህንን ካልኩ በሁዋላ ዛሬ ወደ ተነሳሁበት ርእስ ልምጣ። እንደምታውቁት ሃገሮች  የየራሳቸው የእንስሳ ብሔራዊ ምልክት አላቸው ፡፡ ለምሳሌ  አሜሪካ  ብሔራዊ  ምልክቷ ንስር ነው ፡፡ ቻይና ደግሞ ፓንዳ ነው ምልክቷ፣ ሩስያ ድብ፣ ቬትናም ወተር ቡፋሎ፣ አንዳንድ  አገሮች  ነብር  ታላቁዋን ብሪታኒያን ጨምሮ ኬንያና አንዳንድ  ሃገሮች  ደግሞ የእንስሶች ንጉስ የሆነውን አንበሳን መርጠዋል፡፡ ኢትዮጵያ ሃገራችን አንበሳን ከመረጡትና በአንበሳ ጥንካሬ ከተማረኩት የመጀመሪያዋ ሀገር ናት፡፡  የዓለም ሃገራት ከእንስሳቱ ዓለም ምልክት ሲሹ የዚህ  ምልክት  ዓላማ  ከእንሰሳቱ  ጠንካራ  ጎን  በመውሰድ  ያንን  ጠንካራ  ጎኑን   ለማህበረሰቡ ሀይል፣ ሃሴትና ርካታ  ይሆናል  ከሚል  ስሌት ነው ፡፡  ይህ  የየሃገሩ  ምልክት  ዘመን  ተሻጋሪ ነው ፡፡  መንግስት ሄዶ መንግስት ሲመጣ፣ ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ ፣ ብሄራዊ ምልክቶች ይኖራሉ ፡፡ ወደ ሃገራችን ኢትዮጵያ ስንመጣ የረጅም ዘመናት ታሪክ ያለው፣  እልፍ  ዘመን  ተሻግሮ የመጣው፣ ብሔራዊ ምልክት  አንበሳ  ነው ፡፡ ኢትዮጵያዊ  በባህሉ  ጥንካሬን ፣ ጥረትን፣ ጉብዝናን፣ በዚህ እንስሳ በኩል ይገልጻል ፡፡ ከዚህም በላይ  በኢትዮጵያ  ሃገረ መንግስት  ታሪክ ውስጥ  አንበሳ  የጥንካሬ፣ የሃይል ፣ የብርታት ምልክት ብቻ  ሳይሆን ለረጅም ዘመን የቆየው  የሰለሞን  ስርወ መንግስት ምልክት ነው፡፡ ሞአ አንበሳ ዘእም ነገደ ይሁዳ የሚለው የነገስታቱ ማእረግ የዘመናት መጠሪያ ነው፡፡ በሌላ በኩል ከሃይማኖት አንፃር ደግሞ የይሁዳ አንበሳ የተባለውን ኢየሱስ ክርሰቶስን የሚያሳይ ነው፡፡ መጽሃፍ ቅዱስ ክርስቶስን የይሁዳ አንበሳ ይለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ክርስትናን ለረጅም ዘመን  ከቤተ-መንገስት ጋር አያይዛ ስለኖረች አንበሳ ምልክቴ ነው ስትል ሞአ አንበሳ ትላለች፡፡ ሞአ ማለት አሸናፊ ማለት ሲሆን አሸናፊው አንበሳ ክርስቶስ ነው ከሚል የመጣ ትርጓሜ  ነው፡፡ በአንድ በኩል የሰለሞንን ስርወ መንግስት  እያሰበች  በሌላ በኩል ደግሞ አሸናፊውን ክርስቶስን ሃይሌ ነው እያለች የምትኖርበት ምልክት ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ደግሞ በዘመናት መሃል አንበሳ የኢትዮጵያውያን የጀግንነት፣ የሰራተኝነት ምልክት ነው፡፡

በ1966 ለውጥ ሲመጣና የሰለሞን ስርወ መንግስት በሃይል ሲቋረጥ ወታደራዊው መንግስት  ብዙ እሴቶቻችንን የሰበረ ቢሆንም በህዝቡ ልብ ውስጥ ይህ ምልክት ግን ህያው ነበር ፡፡ ምንም እንኳን ስርወ መንግስቱ ቢቋረጥም ብሔራዊ ምልክታችን አልተነካም፡፡ ህብረተሰቡም ለአንበሳ ምልክት ትልቅ ክብር ሁልጊዜም አለው፡፡

በቅርብ ቀን ከአንድ ቦታ ታክሲ ይዤ ወደ ፒያሳ ስመጣ አንድ አካባቢ ተቀየረብኝ፡፡ የት እንዳለን ማወቅ አቃተኝ፡፡ ወደ ግራ ወደ ቀኝ  እያማተርኩ የት ነን አሁን?  ብዬ ታክሲ ውሰጥ እያለሁ ጠየኩ፡፡

“ቤተመንግሰት ነን “ አለችኝ አንዷ ተሳፋሪ፡፡

ዘወር ስል ሁለት አንዳች የሚያካክሉ የወፍ ዘሮች አየሁ፡፡ እነዚህ የወፍ ዘሮች ፒኮክ የተባሉት ወፎች ሲሆኑ  ቤተ-መንግስቱ በር ላይ ግራና ቀኝ ተፋጠው ይታያሉ፡፡ ግዙፍ ሃውልት ነው የተሰራላቸው፡፡ በውነት ተገረምኩ፡፡

ከዚህ በፊት <<ርካብና መንበር>> የተሰኘውን  የዶ/ር አብይን መጽሃፍ  አንብቤ እጅግ አዝኜ ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንበሳ ላይ ያላቸው ጥላቻ ምንም ስም የለውም፡፡ ይህንን ስነ ልቡና ከየት እንዳመጡት መገመት ከበደኝ፡፡ በኢትዮጵያ ህዝብ እምነት፣ ባህል፣ ሰነ-ቃል ውስጥ አንበሳ መልካም ምልክት ነው፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩ አንበሳን መጥላት ብቻ ሳይሆን ይህንን እንስሳ ለማስጠላት መጽሃፍ ጽፈዋል፡፡ የአንበሳን ደካማ ጎኖች እየፈለጉና አንበሳ የሌለውን ተፈጥሮ አለው እያሉ የኢትጵያን ህዝብ ከዚህ ምልክቱ ለማፋታት ያልሆኑት የለም፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ አኚህ ሰው አንበሳን ህዝቡ እንዲጠላ በመሞከራቸው አዝኜባቸው ነበር ከልቤ፡፡ ያሳዘነኝ ለእንስሳት ሰብአዊ መብት በመቆሜ ሳይሆን ከምልክቱ ባሻገር ያለውን እሴት ለመስበር ያላቸውን መሰሪ ጥረት  በመረዳቴና ትውፊታችንን በምናብ በማየቴ ነው።

አሜሪካውያን ንስርን ሲመርጡ ከዚህ ፍጡር ያዩት ብርታት ለህብረታቸው ጥንካሬ በጎ ምሳሌ ስላለው ነው። ንስር ከፍ ብሎ ይበራል፣ ንስር በእርጅናው ወራት ሃይሉን ያድሳል፣ ንስር ከካይ እየበረረ ከታች ምድር ላይ ያለውን ረቂቅ ነገር ያያል። በዚህ ፍጥረቱ የተደነቁ አሜሪካውያን እኛም እንደዚህ ሃይላችንን እናድሳለን ፣ ከፍ ብለን እንበራለን፣ ረቂቅ ነገሮችን እናያለን፣ ብሩህ ነን ለማለት ንስርን ብሄራዊ ምልክት አደረጉት፤ ይሄ የአሜሪካውያን እሴት ነው። ኢትዮጵያውያን ደግሞ የተደመሙት በአንበሳ ነው። አንበሳ ያሉትን ጠንካራ ጎኖች ወስደን ለማህበራችን ምልክት ካደረግን ሽህ አመት ሆነን። አንበሳ እሴታችን ነው። ትውፊታችን ነው። ገበሬው አገላብጦ ሲያርስ አንበሳው ይባላል፣ ሩዋጩ ሩጦ ሲያሸንፍ አንበሳ ይባላል። ተማሪው በትምህርቱ ሲሳካለት አንበሳ ይባላል። ጅግናው ወታደር ጀብዱ ሲፈጽም አንበሳ ይባላል፣ መሪው ጀግኖ ሲገኝ አንበሳው ይባላል።  ጅግናዋ ሴት ስታሸንፍ አንበሲት እንላታለን። ምልክታችን ነውና ዘወትር አንበሳን ከፍ አድርገነው  እንኖራለን። በባህሎቻችን፣ በሃይማኖታችን፣ በትውፊታችን ሁሉ አንበሳ የጥንካሬና ድፍረት ምልክት ነው።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ይህንን እሴታችንን ለማጣጣል ብዙ ጥረዋል። “ርካብና መንበር” በሚለው መጽሃፋቸው ላይ አንበሳ ምልክት መሆን አይችልም እያሉ የሚታገሉ አስገራሚ ሰው ናቸው። በአስተዳደር በኩል የገጠሙንን ችግሮችና እልቂቶች ሁሉ አንበሳን ብሄራዊ ምልክት ከማድረጋችን ጋር ያያይዛሉ። ይገርማል። ሌላ እንስሳ መፈለግ አለብን እንጂ አንበሳ ብሄራዊ ምልክት  አይሆንም ብለዋል። ትውፊታችንን የተዳፈሩ የመጀመሪያ መሪ ናቸው።

 

በእሴታችን ላይ ጥላቻ ያላቸውና “ርካብና መንበር” የሚለውን መጽሃፍ የጻፉት እኚህ ሰው  ወደ ስልጣን መጡና እነሆ ዛሬ አንዲት እንስሳ ይዘውልን መጡ ማለት ነው። ዶክተር አብይ እነሆ ዛሬ በቤተ መንግስቱ በር ላይ ፒኮክ ለተባለችው ወፍ በአንበሳው ምትክ ሃውልት አቁመዋል። እኚህ ሰው ስለምን አንበሳ ጠሉና ፒኮክ ወደዱ ብሎ መጠየቅ ይገባል። ምን አልባት አንበሳ ደካማ ጎኖች ስላሉት ነው እንዳንል ፒኮክ የተባለችው ወፍም ብዙ ደካማ ጎኖች አሉዋት። ፒኮክ ነጭናጫ ወፍ ናት ይባላል። ከሌሎች ወፎች ጋር አብራ መኖር አትችልም። ሲበዛ ግዛታዊ ናት። ወደ ክልሉዋ አታስገባም። ስስታም ናት ማለት ነው። ከሁሉ በላይ ንቃተ ህሊናዋ ዝቅተኛ ነው። ፒኮክ ራሱዋን በመስታወት ብታይ ከራሱዋ ምስል ጋር ካልተደባደብኩ ብላ አምባጉዋሮ የምትገባ ፍጡር ናት። ከአንበሳ ጋር በኢንተለጀንስ አይገናኙም። ሳይንቲፊክ አሜሪካን የተሰኘው መጽሄት ሳይንስ ስለ አንበሳ የደረሰበትን ሲገልጽ አንበሳ የፐዝል ጥያቄ መመለስ የሚያስችል አእምሮ እንዳለው ገልጹዋል።

በርግጥ ህንዶች ይህቺን ፒኮክ የተባለች እንሰሳ ምልክት ሲያደርጉ ቀለሙዋ ከነሱ ቀለም ምርጫ ጋር ይሄዳል መሰለኝ። ትውፊትም አላቸው ይሆናል። በባህላቸውም ደግሞ ፒኮክ ትወደዳለች። እኛ መጀመሪያ ነገር ስሙዋንም አናውቅም። ስንት ኢትዮጵያዊ ፒኮክ የምትባል ወፍ እንዳለች እንደሚያውቅ አላውቅም። በስነ-ቃላችንም ሆነ በባህላችን የለችም። ትውፊታችን አንበሳ ነው። አንበሳ በኢትዮጵያውያን ብሄሮች ዘንድ በጎ ምሳሌ ነው። ከሰማይ በራሪ ሌላ የብሄራዊ ምልክት ብንጠየቅ ርግብን ነው የምንመርጠው። ኢትዮጵያውያን ርግብ የሰላም፣ የቅድስና፣ የርህራሄ ምልክት አድርገው ያያሉና። ነገር ግን ጠቅላይ ሚንስትሩ ይህቺን ወፍ በአንበሳው ቦታ ሲያኖሩ አንደኛው ነገር እሴትን መስበር ነው አጀንዳቸው። ይሄ ነው አሳዛኙ ነገር። መደመር ማለት ይሄ ነው። ሁለተኛ ነገር እኚህ ሰው የራሳቸውን አሻራ መተዋቸው ነው መሰለኝ። ይህ በውነት ተገቢ አይደለም። አንደኛ ነገር እኚህ ሰው በህዝብ አልተመረጡም። ሁለተኛ በየዘመኑ የመጣ መሪ ሁሉ ብሄራዊ ምልክታችንን እየለወጠ የራሱን እንስሳ ሃውልት አይሰራም። እኚህ ሰው ሲወርዱና ነገ ሌላው መሪ ሲመጣ ሰጎን የተሰኘችውን ወፍ ቢያቆም፣ ቀጥሎ የሚመጣው ወይፈን ቢያቆም ቀጥሎ የሚጣው ጉሬዛ ቢያቆም ቤተ-መንግስቱ የእንስሳት ሙዚየም ከመሆኑ አልፎ ብሄራዊ ምልክት አይኖረንም።  የአንድን ማህበረሰብ እሴት መጠበቅ የሁላችን ድርሻ ነው፡፡ እሴቶች በዘመናት መሃል አይነኩም፡፡ አሜሪካውያን መሪ በመረጡ ቁጥር ብሔራዊ አንስሳቸውን አይለውጡም፡፡ ኦባማ ይህንን አላደረጉም። እሴቶቹ ታሪኮች ናቸውና ይጠበቃሉ፡፡

አንበሳ ጠሉ ዶ/ር አብይ ፒኮክ በቤተመንግስቱ በር ላይ ማድረጋቸው እንደ ትንሽ ነገር አይታይም፡፡ ትውፊትን መስበር ነው። እኚህ ሰው በአንድ በኩል መደመር እያሉ በሌላ በኩል ግን ትውፊታችንን እሴቶቻችንን እየሰበሩ ይገኛሉ። ቤተ መንግስት እያስዋብኩ ነው እያሉ የታሪካችንን ቀለም እያጠፉ ነው። ሃይ ሊባሉ ይገባል። ከፍ ሲል እንዳልኩት ኢትዮጵያውያንን ፒኮክ የምትባለውን ወፍ ምንም አያውቁም፡፡ ስሟንም አያውቁም፡፡  ይሄ ትውፊታችንን ማቅለል ብሔራዊ ስሜትን መጉዳት ነው፡፡ ቤተንግስት ታሪካዊ ቦታ ነው፡፡ እንደፈለግን የፈለግነውን የምንገነባበት የምናፈርስበት የግል ቤት አይደለም፡፡ ታሪካዊ ውበቱን ጠብቆ ሊቆይ ይገባል፡፡

የዶ/ር አብይ ወፍ ቤተመንግስቱን ግርማ ሞገስ አሳጥቶታል፡፡ ለታሪካችን ስድብ ነው። ሃይማኖትን ማቅለል ነው። ከሁሉ በላይ እኚህ መሪ ህዝብ እስኪመርጣቸው እንኳን አልታገሱም፡፡ እኒህ ሰው ፒኮክ የተባለችውን ወፍ ከወደዱ ወይ በራሳቸው ግቢ  ወይ በሆነ ስፍራ ሃውልት ሊያሰሩ ይችላሉ። ነገር ግን ይህ ቤተ መንግስት የግል ቤታቸው አይደለም። በዚህ ቤት ብሄራዊ ምልክታችን ነው ከፍ ብሎ መታየት ያለበት። ሌላ እንስሳ የተባለ ነገር ቤተ መንግስት አይታይ ሳይሆን ጠቅላይ ሚንስትሩ በመጽሃፋቸው አንበሳ ብሄራዊ ምልክት መሆን የለበትም ባሉት መንፈስ በምንም አይነት ሊሆን አይገባም ለማለት ነው። ክብር ለትውፊታችንና ለእሴቶቻችን።

 

  እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ

  Email;  geletawzeleke@gmail.com

Filed in: Amharic