>

እዚሁ አዳራሽ ውስጥ …  (አሌክስ አብርሃም) 

እዚሁ አዳራሽ ውስጥ … 

(አሌክስ አብርሃም) 
  እዚሁ አዳራሽ ውስጥ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ የአገር ባህል ልብስ ለብሰው  በአንጋፋው ሱዳናዊ ዘፋኝ መሃመድ ዋርዲ ዘፈን ከመላው ህዝብ ጋር  ጨፈሩ  …
እዚሁ አዳራሽ ውስጥ…የትግል አጋራቸው የአገር መከላከያ ሰራዊትኢታማዦር ሹም ሳእረ መኮነን አስከሬን በእንባ ተሸኘ …
እዚሁ አዳራሽ ውስጥ …እነኦነግና ግንቦት ሰባት አገር አፍራሽ ተብለው ህዝብ በጭብጨባ ውግዘቱን ደገፈ …እዚሁ አዳራሽ ውስጥ ኦነግም ግንቦት ሰባትም ቁመው አገር አዳሽ ተብለው ተጨበጨበላቸው
 …እዚሁ አዳራሽ ውስጥ ከቀመር ዮሱፍ እስከ አጫሉ  ሚኒሊክ  ህዝብ ጨፍጫፊ ሂትለር ነው አሉን …እዚሁ አዳራሽ ውስጥ ቴዲ አፍሮ ሚኒሊክ ጥቁር ሰው ከጨፍጫፊ አዳነን  ብሎ አወደሰ ….
….እዚሁ አዳራሽ ውስጥ አገራችን አድጋ ወደ ኢንዳስትሪው አለም እየገሰገሰች ነው ተብሎ ትልቅ ባዛርና የንግድ ኤግዚቪሽን ተደረገ
….እዚሁ አዳራሽ ውስጥ  ተርበናልና እርዱን የሚል ጥሪ ተደረገ !
….እዚሁ አዳራሽ ውስጥ  ታረቅን ተብሎ እንባ ተራጨን
 …እዚሁ አዳራሽ ውስጥ እርስ በእርስ ተጫረስን ብለን አለቀስን ! እዚሁ አዳራሽ ውስጥ
 …ኦርቶዶክስ እና ጴንጤ ሙስሊምና ካቶሊክ በየፊናቸው ፈጣሪያቸውን አመለኩ ምድሪቱ የተቀደሰች የፈጣሪ ግዛት  ናት አሉ
….እዚሁ አዳራሽ ውስጥ ቢዮንሴ ከነኢሉምናቲ ተጠርታሪነቷ እርቃኗን ፈነጨችበት
 …እዚሁ አዳራሽ ውስጥ ቀጠናውን የሚያምሰው የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አይንህን ላፈር ተባለ …እዚሁ አዳራሽ ያው ኢሳያስ የክብር ካባውን ለብሶ ‹‹ኢሱ ኢሱ ›› እየተባለ ተሞገሰ ተከበረ
 ….እዚሁ አዳራሽ ውስጥ …ኢሃዴግ ሌባ አይወድም ተባለ እዚሁ አዳራሽ ኢሃዴግ ሌባ ተባለ !
ይሄ ሁሉ ልዩነት በህይዎት የመኖር ምልክት ነበር …በሃሳብ የመለያየት ጤናማ ሂደት ነበር …ዛሬ ግን አስከፊው እውነት ጋር ተፋጠናል! ከነልዩነታችን ፣ ከነአመለካከትና እምነታችን ከነዘር እድሜና ቋንቋችን አንድ ላይ በአንድነት የመኖር ወይም ያለመኖር ጥያቄ ጋር ተፋጠናል ….እዚሁ አዳራሽ ውስጥ ሁላችንም የጋራ ጠላታችን ሰለባ ከሆንን ካለልዩነት ልንተኛ ብዙ አልጋዎች ተዘጋጅተውልናል !((((ለፍስሃ በደስታ ተቃቅፈን ወደገባንበት አዳራሽ ብቻችንን በቃሬዛ እንዳንገባ )))) ያለን አማራጭ አንድና አንድ ነው …ያንን የፍስሃ ጊዜ ዳግም እናይ ዘንድ …ራሳችንን ብሎም ቤተሰብ ጎረቤትና መላውን ህዝብ ከዚህ ክፉ ወረረሽኝ መጠበቅ !! እንራራቅ ፣እጃችንን ካለመሰልቸት በሳሙና እንታጠብ ፣ ቸልተኛ አንሁን … ጊዜውን እንመልከት ከጊዜው ጋር እንቀየር !!እና ተስፋ እናድርግ !
Filed in: Amharic