>
5:16 pm - Tuesday May 24, 8670

የአሐዳዊና የፌዴራል ሥርዓት አራማጆቹ እነማን ናቸው? (አቻምየለህ ታምሩ)

የአሐዳዊና የፌዴራል ሥርዓት አራማጆቹ እነማን ናቸው?

አቻምየለህ ታምሩ
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ እንደ ኦሮሞና ትግሬ ብሔርተኞች ግብዝ፣ ራሳቸውን  የማያውቁ፣ የእውቀት ጾመኛና ነውር ጌጡ የሆነ የፖለቲካ ተዋናይ በአፍሪካ ምድር መኖሩን እጠራጠራለሁ። ራሳቸውን  እንደ ፌዴራሊስት ኃይል የሚቆጥሩት እነዚህ ሁለት የአፓርታይድ ሥርዓት አራማጆችና  ነውረኛ ብሔርተኞች መድረክ ፈጥረው በተገናኙ እንዲሁም  የሌላውን ድርሻ ሲቀራመቱ ርስበርሳቸው በሚፈጥሩት ጠብ  ሲሻኮቱ ሙሾ ባወረዱ  ቁጥር አማራውን ባልዋለበት ሲከሱ የሚውሉት በአሐዳዊ ሥርዓት አራማጅነት ነው።
እውነት የኦሮሞና የትግሬ ብሔርተኞች ፌዴራሊስት ኃይሎች ናቸውን? እውነትስ አማሮች አሐዳዊ ሥርዓት አራማዎች ናቸው? እስቲ እውነታው ምን እንደሚመስል እንመርምር።
ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ኦሮሞና ትግሬ ብሔርተኞች ጸረ-ፌዴራላዊ፣ አሐዳዊ ብቻ ሳይሆን እጅግ ፍጹም የሆነ አሐዳዊ  የአፓርታይድ ሥርዓት አራማጅ የሆነ ቡድን የለም። በተቃራኒው ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ አማራው ፌዴራላዊ የሆነ እሳቤ ያለውና የፌዴራል ሥርዓት የሚያራምድ ቡድን የለም።
የኦሮሞና የትግሬ ብሔርተኞች ባሕሪያቸው ስላልሆነው ፌዴራላዊነትና ስለ መብት አጎናጻፊነቱ አብዝተው ሲሰብኩ ይሰማሉ። በተግባር ሲፈተሹ ግን እንደነሱ ልሙጥ የሆነ አሐዳዊዳ የአፓርታይድ ሥርዓት አራማጅና ጸረ ፌዴራላዊ ሥርዓት ተከታይ የለም።
በኦነጋውያንና በወያኔዎች ትንተና፣ ትርጉምና መስፈርት ፌዴራሊዝም ማለት ለማንነት እውቅና መስጠትና ራስን በራስ ማስተዳደር ማለት ነው። በዚህ መስፈርት መሰረት በፌዴራል ስርዓት ከፍተኛው የአስተዳደር አደረጃጀት ቀበሌ ነው። በዚህ የኦሮሞና የትግሬ ብሔርተኞች እሳቤ፣ የፌዴራሊዝም ትርጉምና አደረጃጀት መርሆ መሰረት የሚያራምዱት ፖለቲካ ሲፈተሽ እንደነሱ ፌዴራሊዝም የሚሰጠውን መብት ገፋፊና ፍጹም አሐዳዊና እጅግ የተማከለ ስርዓት አራማጅ የለም።
የኦነግና የወያኔ ፕሮግራም በወለደው ሕገ መንግሥት ተብዮ መሰረት ከተከፋፈሉ የኢትዮጵያ አካባቢዎች መካከል ኦሮምያ፣ ትግራይና አማራ የሚባሉት ክልሎች ሶስቱ ፌዴሬሽን የሚባለው አደረጃጀት አካሎችና ዋና ዋና የሕገ መንግሥት ተብዮው ውሉድ የሆኑ ክልሎች ናቸው። አሐዳዊ ስርዓት አራማጅ ነው ተብሎ የሚከሰሰው አማራ ያስተዳድረዋል በሚባለው የአማራ ክልል በሚባለው ውስጥ በኦሮሞና በትግሬ ብሔርተኞች የፌዴራሊዝም ትርጉምና መስፈርት መሰረት ቢያንስ ስድስት ለማንነት እውቅና የተሰጠባቸውና ራሳቸው በራሳቸው የሚያስተዳድሩ የፌዴራል አደረጃጀቶች [federal units] አሉ። እነሱም የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የዋግ፣ የአዊ፣ የቅማንትና የአርጎባ የፌዴራል አደረጃጀቶች ናቸው። በነዚህ አማራ ያስተዳድረዋል በሚባለው ክልል ውስጥ የሚገኙ የፌዴራል አደረጃጀቶች ውስጥ ስድስቱም የፌዴራል አደረጃጀቶች የራሳቸው ፓርላማ ያላቸው፣ በኦሮሞና በትግሬ ብሔርተኞች መስፈርት ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩ፣ ለማንነታቸው እውቅና የተሰጠጣቸውና በቋንቋቸው የሚማሩ፣ የሚዳኙና የሚሰሩ ናቸው።
አማራውን በአሐዳዊ ሥርዓት አማራጅነት በሚከሱት የኦሮሞ ብሔርተኞች የሚተዳደረው ኦሮምያ በሚባለው ክልል ውስጥ በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠር አማራ፣ በሚሊዮኖች፣ በመቶ ሺዎችና በአስር ሺዎች የሚቆጠር ጉራጌ፣ አርጎባ፣ ትግሬ፣ ዝይ፣ ዳዋሮ፣ ጌዲዮ፣ ሐድያ፣ ካፊቾ፣ ከምባታ፣ ኮንሶ፣ ማኦ፣ ሲዳማ፣ ሲልጢ፣ ሶማሌ፣ ዎላይታ፣ የም፣ ወዘተ ይኖራል። በኦሮሞ ብሔርተኞች የፌዴራሊዝም ትርጉምና መስፈርት መሰረት እነዚህ ሁሉ ኦሮምያ ክልል በሚባለው “ፌዴራላዊ” ክልል ውስጥ የሚገኙ «ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች» ማንነታቸው እውቅና ተሰጥቶት ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር ነበረባቸው።
ሆኖም ግን ኦሮምያ በሚባለው ክልል ውስጥ ከላይ ከክልል እስከ ታች ቀበሌ ድረስ ከኦሮሞ በስተቀር ማንነቱ የታወቀና ራሱን በራሱ የሚያስተዳድር አንድም የኢትዮጵያ «ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ» የለም! ይህ ማለት ኦሮምያ የሚባለው ክልል በአሐዳዊ ሥርዓት የሚተዛ እንጂ በፌዴራላዊ ስርዓት የሚተዳደር አይደለም ማለት ነው። ኦሮምያ የሚባለውን ክልል የጻፈውን ሕገ መንግሥትም ብንወስድ ሕገ መንግሥቱ እውቅና የሰጠው ለኦሮሞ ብቻ ነው። በመሆኑም ኦሮምያ የሚባለው ክልል ፍጹም በሆነ አሐዳዊ የአፓርታይድና ያልተማከል አገዛዝ የተዋቀረ፣ ማንነቶች የታፈኑበት፣ ራስን በራስ ማስተዳደር ፈጽሞ የማይቻልበትና በዋለልኝ ቋንቋ ክልሉ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እስር ቤት ነው ማለት ይቻላል።
የትግራይን ክልልም ብንወስድ ያው ነው። ዛሬ ትግራይ ክልል በሚባለው ውስጥ ኢሮብ፣ ኩናማ፣ አገው፣ ኦሮሞ፣ አፋርና በግፍ ወደ ትግራይ በተካተቱት በወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምትና ሁመራ እንዲሁም በራያ አማራ ይኖራል። የትግራይ ክልል የሚባለው ሕገ መንግሥት ግን የእነዚህን ነገዶች ቋንቋ የስራ ቋንቋ አድርጎ እውቅና አልተሰጠውም፣ የራሳቸውን ምክር ቤት እንዲያቋቁሙ አይፈቅድላቸው፣ ራሳቸው በራሳቸው እንዲያስተዳድሩና በራሳቸው ቋንቋ እንዲዳኙ አይፈቅድም። የትግራይ ክልልን የፍርድ ቤቶች ቋንቋ የሚደነግገው የክልል ሕግ የክልል የፍርድ ቤት ቋንቋ ትግርኛ እንደሆነ ጠቅሶ በኢሮብ ወረዳም ቢሆን የሳሆ ቋንቋ ተናጋሪዎች ትግርኛ ካልቻሉ በወረዳቸው ላይ የሚያጋጥማቸውን የፍርድ ቤት ጉዳይ ለመከታተል አቤቱታቸውን ወደ ትግርኛ ማስተርጎም ይጠበቅባቸዋል ይላል። በክልላቸው ያለውን የኢሮብን ሕዝብ ልሳን እንደ አንድ የክልሉ የስራ ቋንቋ ማካተት ያቃታቸው የትግራይ ብሔርተኞች ናቸው እንግዲህ የፌዴራሊስት ኃይሎች ቁንጮ ሆነው ስለ ፌዴራሊዝም ጉባዔ እየዘረጉ የፌደራል ሥርዓትን እነሱ እንደፈጠሩት የሚፈሰኩሩትና ከጥንት ጀምሮ የተፈተነውን የፌዴራል ሥርዓት አራማጅ አማራውን በአሐዳዊ ሥርዓት አራማጅነት የሚከሱት።
እንግዲህ! ከኦሮሞና ትግሬ ውጭ ክልላችን በሚሉት ውስጥ የሚኖርን አንዱንም የኢትዮጵያ «ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ» ማንነት እውቅና ያልሰጡ፣ የራሱን ፓርላማ እንዲያደራጅ ያልፈቀዱ፣ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር ያላደረጉ፣ በቋንቋው እንዲማር፣ እንዲዳኝና ቋንቋው የስራ ቋንቋ እንዳይሆን በሕግ ያገዱና እጅግ የጠጠረና ልሙጥ የሆነ አሐዳዊ የአፓርታይድ ሥርዓት የገነቡና የሚያራምዱ የኦሮሞና የትግሬ ብሔርተኞች ናቸው በነሱ የፌዴራሊዝም መስፈርት ማንነታቸው ታውቆ፣ የራሳቸው ፓርላማ ያላቸው፣ ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩ፣ ለማንነታቸው እውቅና የተሰጠጣቸውና በቋንቋቸው የሚማሩ፣ በቋንቋቸው የሚዳኙና ቋንቋቸው የስራ ቋንቋ የሆነ ቢያንስ ስድስት የፌዴራል አደረጃጀት [units] የተዋቀሩበትን የአማራ ክልል የሚባለውንና መላውን አማራ በአሐዳዊ ሥርዓትና በተማከለ አስተዳድር አራማጅነት የሚከሱት!
ባጭሩ የፌዴራሊዝም ጠብቆች ነን የሚሉን አፈ ጮሌዎች የኦሮሞና የትግሬ ብሔርተኞች በተግባር አክራሪ የአሐዳዊ አፓርታይድ ስርዓት አራማጆች ናቸው። ቀደም ሲል የዘረዘርኳቸው ጨምሮ ዛሬ ኦሮምያና ትግራይ በሚባሉት ክልሎች ውስጥ የፌዴራል ሥርዓት አራማጅ ነን በሚሉን የኦሮሞና የትግሬ ብሔርተኞች መብታቸው ተገፎ ኦሮምኛና ትግርኛ ብቻ እንዲናገሩ የተገደዱ፣ ራሳቸውን በራሳቸው የማያስተዳድሩ፣ በቋንቋቸው የማይማሩና የማይዳኙ «ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች» ቁጥር ከ60 ይበልጣል። በተቃራኒው የአሐዳዊ ስርዓት አራማጅ ተደርጎ የሚከሰሰው የፈረደበት አማራ በተግባር ሲፈተሽ በእንደራሴነት የተሾሙትን ጨምሮ መላው የአማራ የፖለቲካ ማኅበረሰብ የፌዴራል ስርዓት አራማጅ ነው።
ሆኖም ግን ነገሩ ጩኸቴን ቀሙኝ ሆኖ ከኦሮሞና ከትግሬ ውጭ ላንድም «ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ» እውቅና ሳይሰጡ፣ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር ሳይፈቅዱንስ እስከ ቀበሌ ድረስ አንድ አይነትና ልሙጥ የሆነ አሕዳዊ የአፓርታይድ  አገዛዝ የዘረጉት የኦሮሞና የትግሬ ብሔርተኞች የፌዴራል ሥርዓት ተግባሪና አስተማሪ የሆነውን የአማራውን የፖለቲካ ማኅበረሰብ የእነሱ መገለጫ በሆነው የአሐዳዊ ስርዓት አራማጅና በጸረ ፌዴራል ስርዓት አራማጅነት ይከሱታል!
Filed in: Amharic