የብሄር ፖለቲካው ቫይረስ!!!
ኤፍሬም ለገሰ
በአሁኑ ወቅት በዓለም ዙሪያ እያነጋገረ፣ እያሳሰበና እያዋከበ የሚገኘው የኮረና ቫይረስ እያደረሰ ያለው ቢሆንም በአገራችን ሌላው በተጨማሪ ለረዥም ጊዜ ጤናና ሰላምን የነሳን የብሄር ፖለቲካ የሚባለው አስከፊው ወያኔና ኦነግ ያመጡብን ቫይረስ ነው።
በሰው ህይወት ላይ የሰሩት በደልና የሕዝብ ንብረት ዘረፋ ወንጀሎች የተረሱላቸው መስሏቸው በትግራይ ውስጥ ከሁለት ዓመት በፊት መሽገው የሚገኙት የብሄርን ፖለቲካ በመሰሪው ባህሪያቸው በትረካና በጥላቻ ላይ ተመርኩዘው የኢትዮጵያ ጠላቶችን ዓላማ ለማሳካት ህሊናቸውንና ማንነታቸውን ለጊዜዓዊ ጥቅም ሸጠው አገራችንን በጣም አስከፍፊ በሆነው የብሄር ፖለቲካ የተበተቧት፣ ያለ ባህር ያስቀሯት፣ እነሱ ባመጡት ጦርነት ከ100 000 በላይ ወገኖቻችንን ያጣንበት ከዚያም በኋላ እስከ ዛሬ ድረስ በባድመ ጉዳይ በውሸቱ እየቀጠሉበት፣ በሰፈር ልጆች ለሌብነት ተደራጅተው ሲዘርፉን የቆዩ፣ አማራውንና ኦሮሞውን እሳትና ጭድ ሲሉ የነበሩ፣ የኦሮውን ሕዝብ ዛራም ያሉ፣ ከመሬት ንብረቱ በሆድ አደሮች ትብብር ያፈናቀሉ፣ ለስደት የዳረጉ፣ አንድ ሰዓት ባልሞላው ጊዜ በኢሬቻ በዓል ቀን የገደሏቸው ከ800 በላይ የሚሆኑት ወገኖቻችን፣ አማራውን ሕዝብ ከመነሻቸው ጀምሮ ጠላት ብለው ፈርጀውት ቁጡሩን ለመቀነስ የተለያዩ ስልቶችን የተጠቀሙ፣ በሀይማኖት በባህል በጋብቻ በስራ በታሪክ በአጠቃላይ በብዙ መንገድ ትስስር ያላቸውን የአማራውንና የትግራይን ሕዝብ በጠላትነት እንዲተያይ የሰሩት የ 666 አገልጋዮች የሆኑት፤ ዛሬ የኦሮሞውና የአማራው ሕዝብ ተቆርቋሪ መስሎ መቅረብን እንኳን የበደሉ ሰለባ የሆኑት ቀርቶ እናንተም ማታምኑት ” አበድረኝና አህያህን ልግዛህ” ነገር ነው።
ለመሆኑ በህወሃት ዘመን እራሱ ሕዝቡ በመረጣቸው ሰዋች የተዳደረ “ክልል” ነበረን? አሁንም ያው ቢሆን።
ለመሆኑ ከፅንፈኛው ኦነግ ጋር የጥፋት ጋብቻ ፈጥሮ ሰላም የሚነሳ፣ ህይወት የቀጠፈ፣ ሰዋች እንዲሰወሩ ያደረገ ማን ሆኖ ነው?
ፖለቲካን እንደ አክሶን ማህበር ተጠቃሚ ማን ሆኖ ነው? የሰውን ህይወት ከምንም ሳይቆጥር ኤድስን ለገንዘብ መሰብሰቢያ ያደረጉው ማን ሆኖ ነው?
ማን ሆኖ ነው ለ27 ዓመታት የደርግን፣ የሐይለ ሥላሴንና የሚኒልክን ዘመናት በየቀኑ በሃሰተኛ መረጃዋች ሲወቅስ የቆየው?
የቀረው ቀርቶ የውጭ ጠላት የትግራይን ሕዝብ በወረረበት ወቅት ከደረሱለት ሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በሃሰተኛ ትረካዋች ለማነጣጠል የሰራችሁትና እየሰራችሁት ያለው መሰሪ ተግባር ምነው ተረሳችሁ?
በ1978 ዓ፡ም በደረሰው ድርቅ የተራበውንና የተጠማውን ሕዝብ ለፖለቲካ ንግድ እንደተጠቀማችሁ እንዴት ተረሳችሁ?
ዝም ስለ ተባላችሁ ነው ይህንን ከኮሮና ቫይረስ የባሰውን መሰሪ የብሄር ፖለቲካችሁን መርጨት የተያያዛችሁት። የብሄር ፖለቲካ የጠቀመው ቢኖር የኢትዮጵያን ሕዝብ የማይወክሉትን 1% እንኳን የማይደርሱትን ህሊና ቢሶችን ነው።
ህወሃቶች እና ኦነጎች ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተከሰተ ላለው ችግር ተጠያቂ እንጂ ከሳሽ መሆን አይችሉም ። መቼም ቢሆን የሕዝባችን ችግርና ፍልጎት አጀንዳቸው ሆኖ አሳስቧቸው አያውቅም በሕዝብ መኖርን እንጂ ለሕዝብ መኖር አይመቻቸውም።
የህወሃት አመራሮች ከአጀማመራቸው በጥላቻ ተሞልተው ያደጉ፣ በቢልደርበርግ ክለብ ታጭተው ተደራጅተው ታጥቀው የኢትዮጵያን አንድነት ለማናጋት ቃል የገቡ የ666 ተላላኪዋች ናቸው። ብሄርተኞች በውስጣቸው የስልጣን ሽኩቻ ሊኖር ይችላል እንጂ የነሱን ቡድን በሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ በላይነት መጫንን አምነው የተቀበሉ ናቸው። ብሄርተኞች ድርጅታቸውንና የብሄራቸውን ሕዝብ በፍፁም ነጥለው የማያዩ አስተሳሰባቸው ከጊዜው ጋር የማይሄዱ የዘራፊዋችና የነፍስ ገዳይ ስብስቦች ናቸው።
የሴራ ፖለቲካችሁ የአደባባይ ምስጢር ከሆነ ውሎ አድሯል እና አሁን የኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ሕዝብ ተቆርቋሪና አሳቢ ሆኖ መቅረብ እራስን ለማታለል ካልሆነ ወይም ደግሞ Amnesia በሽታ ካልሆነ በስተቀር ሌላ ሊባል አይችልም።
ይህ በዚህ እንዳለ በአሁኑ ሰዓት የመንግስትን ስልጣን ቦታ የተቆጣጠረው ቡድን በህወሃትና በኦነግ ፅንፈኞች ላይ እርምጃ መውሰድ አለመቻሉ አቅመ ቢስነቱን የሚያሳይ ወይም እራሱ የሴራው አካል እንደሆነ የሚያጠራጥር ነው። ለምሳሌ በኦነግ ሸኔ ቁጥጥር ስር ነበር የተባለውን የምዕራብ ወለጋን ክፍል በቁጥጥር ስር አውያለሁ የሚል ከሆነ አምስት ወር አካባቢ የሞላቸው ተማሪዋቻችን የታሉ? የትግሉ ሰለባ ሆኑ እንዴ? ወይንስ ለፖለቲካ ፍጆታ ጓሮ ደብቃችኋቸው ነው?
እስከ መቼ ነው የትግራይን ሕዝብ ምርኮኛ አድርጎ የመሸገውን የህወሃትን ድርጅት እሹሩሩ የምትሉት?
ወይንስ ፖለቲካችን የሴራ ፖለቲካ ስለሆነ የነሱ መጥፋት አያስፈልግም ነው ነገሩ?
በአጠቃላይ በብሄር ፖለቲካ ተከፋፍለን፣ እያንዳንዱ”ክልል” እንደ አንድ ልዓላዊ አገር የራሱን ልዩ ሃይል እያደራጀና እያስታጠቀ፣ የመገንጠልን መግለጫ እየሰጠ፣ የመንግስትን ስልጣን እየተጋፋ፣ የፌደራል ወታደሮችን በቁጥጥር ስር እያደረገ የመንግስትን ስልጣን የያዘው ግን ምንም ማድረግ አለመቻሉና ዝምታን መምረጡ አንዳንዴ አ፡አበባ ተቀምጦ በውሸት ላይ ውሸት የተሞላበት መግለጫ መስጠት ካልሆነ በስተቀር የሚታየው ጉዳይ አሳሳቢ ጉዳይ ነው። ስለዚህ መንግስት እራሱንም ሆነ ሕዝብን ለማከበርና ለማረጋጋት እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል። ከዚህ በፊት ሕወሃት የኢህአዴግን ጭምብል እጥልቆ ሲገዛ እንደነበረው አሁን ደግሞ የብልፅግናን ጭምብል እጥልቆ እየገዛ ወይም ከጀርባ ሆኖ እየዘወረ የሚገኘው ኦነግ እንደ ሆነ ያሳያል ምክንያቱም እስካሁን ድረስ የኦነግ አፈቀላጤዋች እንደነ ጃዋር መሐመድ፣ ብርሃመስቀል አበበ ሰኚ፣ ስዩም ተሾመ፣ “ቀሲስ” በላይ መኮንን ወዘተ የመሳሰሉት በተለያየ ቦታና ወቅት በአገራችን ያስነሱት ግጭትና ሞት እንኳን ለፍርድ ሊቀርቡና የማውገዝ መግለጫ እንኳ አለመስጠቱ አቅመቢስ መሆኑን ወይም የችግሩ አካል መሆኑን ያሳያል። በህወሃት በኩልም በአለም ላይ የተከሰተውን ግር ግር በመጠቀም “ግር ግር ለሌባ ያመቻል” እንደ ሚባለው እነ መስፍን ስዩም፣ ጌታቸው ረዳ፣ ደብረፅዮን፣ ሆድ አደሩ ያየሰው ሽመልስ ወዘተ የመሳሰሉት የሚነዙት የሴራና መሰሪ አላማቸው ሊጠቀሱ ይችላል።
በአጠቃላይ ህወሃትና ኦነግ በስም ተለያዩ እንጂ በፀረ-ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የተልዕኮ ዓላማ አንድ መሆናቸውን በእነዚህ 40 ዋቹ ዓመታት በግልፅ አይተነዋል እያየነውም ነው። ይህ የብሄር ፖለቲካ በዚህ ከቀጠለ “ጅብ ካለፈ ውሻ ጮኸ” ሊሆን ይችላል።
ፈጣሪ ኢትዮጵያን እንደጠበቃት ይጠብቃት!!!