ዓለም በሩንም ደብሩንም ዘግቶ ያከበረው የትንሳኤ በአል!!!
አ.አ
በጥንታዊቷ ቅድስት ከተማ እየሩሳሌም እየሱስ ክርስቶስ ከተቀበረበት ቦታ አቅራቢያ የሚገኘውና በ326 ዓ.ም እንደተሰራ የሚነገርለት ስመጥር ቤተ ክርስቲያን፣ ከዚህ ቀደም በትንሳኤ ሰሞን ከመላው አለም በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሚጎርፉበት ቅዱስ ስፍራ እንደነበር ይነገራል፡፡ ይህ ቤተ ክርስቲያን እ.ኤ.አ ከ1349 በኋላ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በትንሳኤ ሳምንት በሮቹ መከርቸማቸውንና ያለ ምዕመናን ጭር ብሎ ማሳለፉን ፎክስ ኒውስ ዘግቧል!
የጸሎተ ሐሙስ የካህናት ተምሳሌታዊ እግር አጠባና ቅዳሴ፣ ብዙዎችን የሚያሰባስበው አስደማሚው የዕለተ ስቅለት ስግደት፣ ማራኪው የቅዳሜ ሌሊት የቤተ ክርስቲያን ስነ ስርዓት፣ ደማቁ የትንሳኤ በዓል፣ የዓውደ አመት ሰሞን ሃይማኖታዊ ስርዓትና በሽር ጉድ የታጀበ የበዓል አከባበር ዘንድሮ፣ ለአብዛኛው የአለም ህዝበ ክርስቲያን የሚታሰብ አልነበረም፡፡
ኢትዮጵያውን ነገ የምናከብረውን የዘንድሮ የትንሳኤ በዓል፤ በአብዛኞቹ የዓለም አገራት የሚገኙ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ የክርስትና እምነት ተከታዮች ባለፈው እሁድ ኤፕሪል 12 ነበር፣ ከወትሮው በተለየ መልኩ በየቤታቸው ተዘግተው በተቀዛቀዘ ስሜት ያከበሩት፡፡
አለምን ክፉኛ እየፈተነ በሚገኘው የኮሮና ቫይረሰ ወረርሽኝ ሳቢያ በተለያዩ አገራት የሚገኙ እጅግ በርካታ የእምነቱ ተከታዮች፣ የዘንድሮውን ትንሳኤ በዓል፣ በአብያተ ክርስቲያናት ታድመው በድምቀት ያከብሩት ዘንድ አልታደሉም:: ካህናትና ቀሳውስት ያለ ወትሯቸው አንድም ሁለትም ሆነው የሚፈጽሙትን ስርዓተ ቅዳሴና ስብከት፣ በየቤታቸው ሆነው በቴሌቪዥን መስኮት እየተከታተሉ፣ ከመጣው የጥፋት ማዕበል እንዲያተርፋቸው፣ ለፈጣሪያቸው ጸሎታቸውን ከማድረስ ውጭ አማራጭ አልነበራቸውም፡፡
ከአውሮፓ እስከ አሜሪካ፣ ከእስያ እስከ አፍሪካ በበርካታ የአለማችን አገራት በትንሳኤ ሳምንት በተለየ ሁኔታ በምዕመናን ይጥለቀለቁና ድምቀትን ይጎናጸፉ የነበሩ እጅግ በርካታ አብያተ ክርስቲያናት፣ ዘንድሮ ግን በሮቻቸው ተዘግተው አልያም ባልተለመደ መልኩ ጭው ጭር ብለው ነው ሳምንቱን ያሳለፉት፡፡
ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በተለያዩ የአለም አገራት መንግስታት፣ ዜጎች ርቀታቸውን እንዲጠብቁ፣ ከቤታቸው እንዳይወጡ ወይም መሰል ሃይማኖታዊ ስነስርዓቶችን በጋራ እንዳይከውኑ አስገዳጅ ህግ በማውጣታቸው፣ በአብዛኞቹ አገራት አብያተ ክርስቲያናት ተዘግተዋል፤ ምዕመናንም አምልኳቸውን በቤታቸው ሆነው እንዲፈጽሙ ተገድደዋል፡፡
በጥንታዊቷ ቅድስት ከተማ እየሩሳሌም እየሱስ ክርስቶስ ከተቀበረበት ቦታ አቅራቢያ የሚገኘውና በ326 ዓ.ም እንደተሰራ የሚነገርለት ስመጥር ቤተ ክርስቲያን፣ ከዚህ ቀደም በትንሳኤ ሰሞን ከመላው አለም በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሚጎርፉበት ቅዱስ ስፍራ እንደነበር ይነገራል፡፡ ይህ ቤተ ክርስቲያን እ.ኤ.አ ከ1349 በኋላ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በትንሳኤ ሳምንት በሮቹ መከርቸማቸውንና ያለ ምዕመናን ጭር ብሎ ማሳለፉን ፎክስ ኒውስ ዘግቧል፡፡
የኮሮና ወረርሽኝ ከአውሮፓ አገራት መካከል እጅግ የከፋውን ጥፋት ያደረሰባትና ከ21 ሺህ በላይ ዜጎቿን በእንባ ወደ መቃብር ሸኝታ፣ ከ163 ሺህ የሚበልጡትን እያስታመመች በምትገኘዋ ጣሊያን፤ አሁን አውደ አመትና አዘቦት ብዙም ልዩነት የላቸውም፤ እያንዳንዱ ሰዓት የሞትና ህመም መርዶ የሚሰማበት፣ እያንዳንዱ ዕለት በጭንቅ መጥቶ በጭንቅ የሚያልፍ የመከራ ጊዜ ሆኗል፡፡
በጣሊያኗ ቫቲካን ከተማ ውስጥ የሚገኘው ግዙፉ የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ድሮ ድሮ፣ በስቅለት፣ በቅዳም ሹርና በትንሳኤ ዕለት ማለዳ በአስር ሺህዎች በሚቆጠሩ ምዕመናን ከአፍ እስከ ገደፉ የሚጥለቀለቅ ታላቅ ስፍራ ነበር:: በዘንድሮ የፋሲካ ሰሞን ግን፣ ይህ ስፍራ ያለ ወትሮው ጭው ጭር ብሎ ነበር የታየው፡፡
የሮማው ሊቀጳጳስ ፍራንሴስ ከኦና ካቴድራል በቀጥታ ስርጭት ባስተላለፉት መልዕክት “ለብዙዎች የዘንድሮው ትንሳዔ የሀዘን፣ የባይተዋርነትና የፈተና ነው፡፡ አሁን ከምንጊዜውም በላይ በአንድነት የምንቆምበትና የጋራ ፈተናችንን በጋራ ለመወጣት የምንተጋበት ነው፡፡ አለም በጋራ ተረባርቦ ይህንን ቫይረስ በቁጥጥር ስር ማዋል ይገባዋል” ሲሉ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፣ ለታመሙት ምህረትን ያወርድ ዘንድ ለአምላካቸው ጸሎት አድርሰዋል፡፡
በአንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ከዚህ ቀደም በበርካታ ቀሳውስትና ዲያቆናት ይካሄድ የነበረው ስርዓተ ቅዳሴና ጸሎት፤ በዘንድሮው የትንሳኤ ሰሞን ባልተለመደ ሁኔታ በአንድ ወይም በሁለት ቀሳውስት ብቻ እንዲከናወን የተደረገ ሲሆን፣ ምዕመናንና ሌሎች ካህናት ግን ክፉ ቀን፣ በቤታቸው ተዘግተው እንዲቀመጡ ቢያስገድዳቸውም፣ ፎቶግራፎቻቸው በአብያተ ክርስትያናቱ ውስጥ ተደርድረው አስቀድሰዋል፤ ቡራኬ ተቀብለዋል፡፡
የሩስያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሞስኮ ውስጥ በሚገኝ አንድ ካቴድራል በዓሉን እንደ ወትሮው በደመቀ መልኩ ባይሆንም እንደነገሩ ያከበረች ሲሆን፣ በአሜሪካም በተለያዩ ግዛቶች በርካታ ቁጥር ያላቸው አብያተ ክርስቲያናት ለምዕመናን ዝግ ሆነው በዓሉን ማሳለፋቸውን ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡ እስራኤልን ጨምሮ በበርካታ የአለማችን አገራት አብያተ ክርስቲያናት በራቸውን ለምዕመናን ዘግተው፣ የጸሎት ስነስርዓትና ሌሎች ክንውኖችን ፌስቡክን ጨምሮ በተለያዩ ድረገጾች በቀጥታ ማሰራጨታቸውን የዘገበው ብሉምበርግ፤ አንዳንድ መለኛ ሰባኪያን ደግሞ በርካታ ቁጥር ያላቸው ምዕመናን በሰፋፊ ክፍት ቦታዎችና አደባባዮች ላይ በየራሳቸው መኪና ውስጥ ተቀምጠው ስብከታቸውን በድምጽ ማጉያ እንዲያዳምጡና አብረዋቸው እንዲዘምሩ ማድረጋቸውን አስነብቧል፡፡
በፓናማ አንድ ሊቀጳጳስ በሄሊኮፕተር እየተንቀሳቀሱ ፈጣሪ ለህዝባቸውና ለአገራቸው ምህረትን ይልክ ዘንድ ቡራኬ የሰጡ ሲሆን አንድ ፖርቹጋላዊ ቄስ በበኩላቸው፤ በክፍት መኪና መንገድ ለመንገድ እየዞሩ፣ ለምዕመናን የሃይማኖት ትምህርት መስጠታቸውን የዘገበው ደግሞ ዘ ኢንዲፔንደንት ነው፡፡
የዘንድሮውን አያድርገውና በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ እንግሊዛውያን የትንሳኤ ዕለት ከመቼውም በበለጠ መልኩ ከቤተሰቦቻቸውና ወዳጅ ዘመዶቻቸው ጋር ሰብሰብ ብለው የሚያሳልፉት ተናፋቂ ቀን ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን፣ ተያይዞ ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድም፣ ተሰባስቦ የአውደ አመት ማዕድ በጋራ መቋደስም ሆነ ወጣ ብሎ መንሸራሸር እንኳን ሊደረግ ሊታሰብም የሚከብድ እጅግ አደገኛ ድርጊት ሆኗል፡፡
በበርካታ የአለም አገራት የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት፣ የትንሳኤ ሰሞን ሃይማኖታዊ ትምህርትና የጸሎት ስነስርዓቶችን ጨምሮ የተለያዩ የአውደ አመት ፕሮግራሞችን ከቴሌቪዥንና ሬዲዮ በተጨማሪ፣ በድረገጾች አማካይነት በቀጥታ ለምዕመናን ማስተላለፋቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ በርካታ ቁጥር ያላቸው የማህበራዊ ድረገጾች ተጠቃሚዎችም ከአብያተ ክርስቲያናት በቴሌቪዥን በቀጥታ የሚተላለፉ የጸሎት ስነስርዓቶችንና ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን ትዊተርና ኢንስታግራምን ጨምሮ በተለያዩ አማራጮች ለወዳጆቻቸው በስፋት ማሰራጨታቸው ተነግሯል፡፡
ኮሮና ቫይረስ በመላው አለም የሚገኙ እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸውን የክርስትና እምነት ተከታዮች፣ የዘንድሮው የትንሳኤ በዓል ከወዳጅ ዘመድ፣ ጓደኛና ቤተሰብ ተነጥለው በየቤታቸው ተከትተው እንዲያሳልፉ ቢያስገድዳቸውም፣ ብዙዎች ግን ዘመኑ በደረሰበት የዲጂታል ኮሙኑኬሽን ቴክኖሎጂ መጽናናታቸው አልቀረም፡፡
“ኦንላይን ጸሎት”፣ “ኦንላይን ቡራኬ”፣ “ኦንላይን ዘመድ ጥየቃ”፣ “ኦንላይን እንኳን አደረሳችሁ መባባል” እንዲህና እንዲያ ያሉ ርቀትን የሚያጠብቡ ቴክኖሎጂ ወለድ መላዎች፣ ለብዙዎች የዘንድሮውን “የየብቻ ትንሳኤ” በተወሰነ መልኩም ቢሆን ፈታ ያደርጉባቸው ዘንድ እንደጠቀሙ ይነገራል፡፡
ናሽናል ሪቴል ፌዴሬሽን የተባለው የአሜሪካ ተቋም፣ የትንሳኤ በአል አከባበራቸውን በተመለከተ ከበዓሉ ሳምንት በፊት ጥናት ካደረገባቸው አሜሪካውያን መካከል፣ 34 በመቶ የሚሆኑት ከቤታቸው ሳይወጡ በኢንተርኔት አማካይነት ቤተሰባቸውን ወይም ጓደኞቻቸውን በመጠየቅ “ኦንላይን ዘመድ ጥየቃ”፤ 32 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በኢንተርኔት አማካይነት ቤታቸው ሆነው ቤተ ክርስቲያን በመሳምና በማስቀደስ በዓሉን ለማክበር እንዳሰቡ መናገራቸውን ዲጂታል ኮሜርስ ድረገጽ ከሰሞኑ ባወጣው ዘገባ አስነብቧል፡፡
የትንሳኤ ሰሞን በአብዛኞቹ የአለማችን አገራት ከፍተኛ መጠን ያለው ግብይት የሚፈጸምበት ወቅት እንደሆነ በዚሁ ዘገባው ያስታወሰው ድረገጹ፤ በበርካታ አገራት ዜጎች የትንሳኤን በዓል ሰበብ አድርገው ለፍቅረኞቻቸው፣ ለጓደኞቻቸው፣ ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው በብዛት ስጦታዎችን የመስጠት ልማድና ባህል እንዳላቸው ገልጧል፡፡
በበዓሉ ሰሞን ከሚዘወተሩ ስጦታዎች መካከል ቸኮሌት፣ ከረሜላ፣ “ጢቢኛ”፣ “የፋሲካ ቀሚስ” እና “የወይን ጠጅ” እንደሚገኙበት የሚገልጸው ዘገባው፤ ዘንድሮ ግን በመላው አለም ታዋቂ የሆኑ የኤሌክትሮኒክ ግብይት ኩባንያዎች የትንሳኤ ሰሞን ሽያጫቸው ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በእጅጉ እንደቀነሰባቸው ማስታወቃቸውን ያትታል፡፡
በጎረቤት አገራት ኡጋንዳና ግብጽ በተመሳሳይ ሁኔታ የዘንድሮው ትንሳኤ በዓል፣ ከወትሮው በተለየ መልኩ መከበሩን ዘገባዎች ያመለክታሉ:: በኬንያ ክርስትና ወደ አገሪቱ ከገባበት ዘመን አንስቶ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የትንሳኤ በዓል “በዝግ” መከበሩን የዘገበው ዴይሊ ሞኒተር፤ በፕሬዚዳንታቸው ከቤት እንዳይወጡ ጥብቅ ትዕዛዝ የተሰጣቸው ኡጋንዳውያን የእምነቱ ተከታዮችም፣ በየቤታቸው ሆነው በቴሌቪዥንና በሬዲዮ የሚተላለፉ የጸሎት ስነስርዓቶችን እየተከታተሉ በዓሉን ማክበራቸውን ጠቁሟል:: የግብጽ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ሃይማኖታዊ መሪ የሆኑት ፖፕ ቴዎድሮስ ሁለተኛ፣ ብዙም ሰው ባልታደመበት አንድ ገዳም በተከናወነ ስነስርዓት በአሉን በተመለከተ ሃይማኖታዊ መልዕክት ማስተላለፋቸውን የዘገበው አሶሼትድ ፕሬስ፤ ናይጀሪያና ኮንጎን ጨምሮ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት፣ የትንሳኤ በዓል ከቤተ ክርስቲያን ውጭ፣ በየቤቱ ተከብሮ ማለፉንም አመልክቷል፡፡
አብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ የአምልኮ ቦታዎች እንዲዘጉ መወሰናቸውን የዘገበው ኦል አፍሪካን ኒውስ፤ ከዚህ ጋር በተያያዘ የትንሳኤ በዓል ሃይማኖታዊ ስነስርዓቶች በኦና አብያተ ክርስቲያናት ከተካሄዱባቸውና ዜጎችም በቴሌቪዥንና ሬዲዮ የቀጥታ ስርጭት እየተከታተሉ፣ በዓሉን ከቤት ሳይወጡ ካከበሩባቸው አገራት መካከል ኬንያና ሩዋንዳ እንደሚገኙበትም ገልጧል፡፡
“ኮሮና ቫይረስ እንደ ሰው ልጅ ለበዓል እረፍት አይወጣም፤ በአውደ አመትም የጥፋት ስራውን አያቋርጥም፡፡ ቫይረሱ በዓል አዘቦት ሳይል ሰዎችን በመቅጠፍ ላይ ነውና፣ መጪውን በዓል በየቤታችን ሆነን እናክብረው!” በማለት ነበር የአውስትራሊያ የጤና ሚኒስትር ግሬግ ሃንት፣ ከቀናት በፊት ለዜጎች ጥሪ ያቀረቡት፡፡
በበርካታ የአለማችን አገራት ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ መንግስት የጣለውን የእንቅስቃሴ ገደብና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማክበር በዓሉን በየቤታቸው ያከበሩ የመኖራቸውን ያህል፣ በእምቢተኝነት ከቤታቸው ወጥተው በለመዱት መልኩ በአሉን ያከበሩ አንዳንዶችም አልጠፉም፡፡ ከእነዚህም መካከል ከባህር ዳርቻ አለማቸውን እየቀጩ የትንሳኤን በዓል በድምቀት ያከበሩት በርካታ ቁጥር ያላቸው የሆንግ ኮንግ ዜጎች እንደሚገኙበት ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡ በተለያዩ የአውሮፓ አገራት ዜጎች የትንሳኤን ሳምንት እንደ ወትሯቸው ወጣ ብለው የጸደይ ወቅትን ማራኪ አየር ለማጣጣምና ሽርሽር ለማለት እንዳይሞክሩ መንግስታት፣ መንገዶችን መዝጋትና ቅጣት መጣልን ጨምሮ የተለያዩ ስልቶችን ቢጠቀሙም፣ የእንቅስቃሴ ገደብን በመጣስ በዓሉን በፈንጠዝያ ለማክበር የሞከሩ አልታጡም፡፡
መንግስት ያወጣውን ህግም ሆነ ቫይረሱን ከቁብ ባለመቁጠር በትንሳኤ ማለዳ በቤተ ክርስቲያን “ምዕመናንን ሰብስበን እንሰብካለን፣ እናስተምራለን፣ እንጸልያለን” ያሉ የተወሰኑ የአሜሪካ ቄሶችና ፓስተሮችም በፖሊስ ተይዘው መታሰራቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
የሚገርመው ግን…
እነዚህኞቹ የአሜሪካ ቄሶችና ፓስተሮች “ቫይረሱ አደገኛ ነውና ርቀታችሁን ጠብቁ፤ ተሰብስባችሁ ማምለክ ለጊዜው ይቅርባችሁ” የሚለውን ምክር ከቁብ ሳይቆጥሩ በእምቢተኝነት ለሰበካ በወጡባት በዚያች የትንሳኤ ዕለት ማለዳ፤ በዚያው በአሜሪካ የእነሱ ቢጤ ሲመከሩ አልሰማ ያሉ ሌላ እምቢተኛ ፓስተር መርዶ መሰማቱ ነበር፡፡
“ወህኒ ካልተወረወርኩ አልያም በጸና ታምሜ ሆስፒታል ካልገባሁ በስተቀር፣ ምዕመናንን ሰብስቤ መስበኬን በፍጹም አላቋርጥም!…” በማለት በአደባባይ የተናገሩትና ከኮሮና ቫይረስ እንዲጠነቀቁ በተደጋጋሚ የቀረበላቸውን ምክር አልቀበልም በሚል አቋማቸው የጸኑት የቨርጂኒያው ፓስተር ጄራልድ ግሌን፤ በኮሮና ቫይረስ ተጠቅተው በተወለዱ በ66 ዓመታቸው፣ በትንሳኤ ዋዜማ ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል፡፡