>

ሙስጠፌ እና አብዲሃፊዝ Hard-talk !!! (ሙክታሮቪች) 

ሙስጠፌ እና አብዲሃፊዝ Hard-talk !!!

(ሙክታሮቪች) 
መሰረቱን እንግሊዝ ሀገር ያደረገው ዩኒቨርሳል ቲቪ በሶማሌው ማህበረሰብ ሰፊ ተመልካች ያለው የመገናኛ ብዙሀን ነው። በርካታ ፕሮግራሞች ሲኖሩት ጋዜጠኛ አብዱልሃፊዝ መሀመድ የሚያዘጋጀው የቃለመጠየቅ ዝግጅት በሞጋችነቱ እና ስሱ ጉዳይን አንስቶ በማፋጠጥ አቀራረቡ ዝናን ያተረፈ፣ በርካታ ታዋቂ የፖለቲካ ተክለስብዕና ያላቸው እንግዶች የሚቀርቡበት “ሀርድ ቶክ” አይነት ሾው ነው።
ፕሬዝዳንት ሙስጠፌ ኦማር ከዚህ ሞጋች ጋዜጠኛ ፕሮግራም ላይ እንደሚቀርብ ከተነገረ ጀምሮ በርካቶች በጉጉት ጠብቀውታል። እንደተገመተው የሞቀ ዱላ ቀረሽ፣ በስሜት የተሞላ እና ኋላም በመከባበር የተቋጨ ቆይታ አድርገዋል።
በቆይታቸው የተነሱትን ሁሉ ጥያቄዎች አላቀርብም። ሆኖም አንኳር አንኳር ጉዳዮችን ለመሸፈን ጥረት አደርጋለሁ። ብታነቡት እንደምታተርፉበት ቅንጣት ያህል አልጠራጠርም።
ወደ ጥያቄ እና መልሱ በቀጥታ ልግባ።
ጋዜጠኛው: ⇓
ክቡር ፕሬዝዳንት አቶ ሙስጠፋ ኦማር፣ ለቃለመጠየቅ ፍቃደኛ ስለሆኑ ከልብ አመሰግናለሁ። በርካቶች በተለይ በስልጣን ላይ ያሉ ሰዎች በፕሮግራሜ ላይ ስጋብዛቸው እሺ አይሉኝም። እርስዎ ፍቃደኛ በመሆንዎ ለድፍረትዎና የራስመተማመንዎ ሳላመሰግን አላልፍም።
ወደ መጀመሪያ ጥያቄዬ ልግባ እና ክልሉን እርስዎ ከመምራቶ በፊት የነበረበትን አጠቃላይ ሁኔታ እስቲ ለተመልካቾቻችን ጠቅለል ያለ ምስል ይስጡልን።
ሙስጠፋ:
በአላህ ስም እጅግ ሩህሩህ እጅግ አዛኝ በሆነው እጀምራለሁ መልሴን። እኔም በዚህ በርካታ የተከበሩ ሰዎች ሲቀርቡበት በነበረው ዝግጅትህ ላይ እንደቀርብ ስለተጋበዝኩ አመሰግናለሁ። ፍቃደኛ የሆንኩትም በአንተ ሚዛናዊ እና ሞያዊ ስነምግባር አድናቆት ስላለኝ እና ዩኒቨርሳል ቲቪ የክልላችንን ጉዳይ በዋነኝነት ሲዘግብ ስለነበረ፣ አሁን ያለውን የሽግግርና የለውጥ ሁኔታ ለህዝባችን መረጃ ለመስጠት የእናንተን ፕሮግራም ምርጫዬ ስላደረግኩ ነው።
ወደ ጥያቄህ ስመጣ፣
ክልሉን እኔ ከመረከቤ በፊት የነበረበት ሁኔታ እጅግ ለመናገር በሚከብድ ደረጃ የሶማሌ ህዝብ የተዋረደበት፣ እንደማህበረሰብ ቅስሙ የተሰበረበት፣ የሰውልጅ መሆኑ የተካደበትና ከፍተኛ እንግልት የደረሰበት፣ ከአውሬ ጋር የታሰረበት፣ አካላዊና መንፈሳዊ ማሰቃየቶች የተፈፀመበት፣ ያለፍርድ ሰዎች በአሳቃቂ ሁኔታ የተገደሉበት፣ ሴቶች የተደፈሩበት እንዲሁ በጅምላ ሰዎች በአንድ መቃብር እየተረሸኑየሚቀበሩበት ክልል ነበረ።
ይህም የአለም ሰብአዊ መብት ተማጋች ድርጅቶችን ሪፖርት፣ የተቀረፁ ምስሎችን ጭምር በማየት ማረጋገጥ ማንም ሰው የሚችለው ነው።
ክልሉን ስንረከብ እንደ መንግስታዊ ተቋም የሚሰሩ የመንግስት መስሪያቤቶች አጠቃላይ የሉም። መዋቅራቸው ፈርሶአል። አጠቃላይ የክልሉ ቢሮክራሲን ሊያቀላጥፉ የሚችሉ መንግስታዊ ድርጅቶች ወድመዋል። በጣም በሚያሳዝን ደረጃ የነበረ ክልልን እና መንፈሱ የተሰበረ ህዝብን ነው ስንመጣ ያገኘነው። እንዲሁ በቀላሉ ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም።
ጋዜጠኛ:
እርግጥ ነው የገለፁት ሁሉ እውነት ስለመሆኑ፣ ክልሉን በቅርበት ስለምከታተል ልክ ነዎት። ለውጥ መጥትዎ፣ እርስዎ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ያሳኳቸው ቁልፍ ተግባራትን እባክዎ ሊዘረዝሩልኝ ይችላሉ?
ሙስጠፋ: በርካታ ተግባሮችን እና ስኬቶችን በተጨባጭ አስመዝግበናል። ዝርዝሩ ብዙ ነው። ምናልባት ኋላ በሚነሱ ጥያቄዎች ዘርዘር አድርጌ እመለስበታለሁ።
በአጠቃላይ ግን ለማስቀመጥ:
የክልሉ ህዝብን አጠቃላይ ክብር ነው ወደ ቀድሞ ቦታው፣ ወደ የተከበረ እና የሚገባው የነበረ ስፍራ የመለስነው።
የወጣቶች ምናብና መንፈስን ነው አድሰን በሀገራቸው ተስፋ እንዲኖራቸው የራስ መተማመን እንዲኖራቸው፣ ማለም እንዲችሉ የተገፈፉትን ሰብአዊ ክብር መልሰን ለሀገር ልማት እንዲተጉ ወደሚያስችል ቁመና ከፍ አድርገናል ሞራላቸውን።
የሶማሌን ህዝብ ክብር በኢትዮጵያ ከፍ እንዲል፣ ሀገራችን ሰላሟ የተጠበቀ እንዲሆን፣ የሶማሌ ህዝብ ሰላም ወዳድ ህዝብ መሆኑን የቀጠናውን ሰላም በማስከበረ ምሳሌ እንዲሆን አድርገናል። በርግጥም የሶማሌ ህዝብ ሀይማኖተኛ፣ ሰው አክባሪ፣ ሰላም ወዳድ፣ ሀገር ወዳድ እንደሆነ እንዲያረጋግጥ እድሉን አመቻችተንለት ለኢትዮጵያም፣ ለምስራቅ አፍሪካም መልካም እሴቱን አሳይተናል። ስርዓት ሲስተካከል ህዝብ የዘመናት የሰላም ጥማቱን በተግባር አሳይቷል። ይህ እኛ በሀላፊነት በቅንነት በሰራነው የተቀናጀ ስራ የመጣ ውጤት ነው።
+—
የሴቶቻችንን ክብር አስጠብቀናል። ከሁሉ በላይ በነፃነት መኖርን፣ ያለፍራቻ ወጥቶ መግባትን በክልሉ አስፍነናል።
እስከ ሶስተኛ ዲግሪ ድረስ የተማሩ የክልሉ የተማሩ ሰዎች፣ በመማራቸው እና በማወቃቸው መከበር ሲገባቸው የሚሸማቀቁበትን ስርዓት ለውጠን እውቀታቸውን ለማህበረሰባቸው እንዲያውሉ አስችለናል። ወደ ህዝብ አገልግሎት ስንጠራቸውም በችሎታ እና በችሎታ ብቻ መስፈርት ባደረግነው መሰረት አካታች የሆነ የሲቪል ሰርቪስ ስራን ተግባራዊ አድርገናል።
ከፈቀድክልኝ ትንሽ የማክለው ደግሞ
ከዚህ ቀደም በአብዲሌ የዘረፋ ቡድን የተዘረፉ መሬቶች እና ያለህግ የተዘረፉ ንብረቶችን አስመልሰናል ለህዝብ። የህዝቡን ንብረት መዝረፍ የሚባል ነገር ተወግዷል። በጥቅም ትስስር እና በሞኖፖሊ የመንግስትን ስልጣን በመጠቀም ይደረግ የነበረውን የኢኮኖሚ የበላይነት ለአንድ ወገን ማመቻቸትን አስቀርተናል።
በተለይም የሰራነው ቁልፍ ተግባር፣ የሶማሌን ህዝብ ጥያቄ ወደ መሀል ሀገር ወስደን ከሀገሩ ሀብት በፍትሃዊነት የሚገባውን እንዲጠይቅ ወክለነው የሚያኮራ ስራ ሰርተናል። የሶማሌ ህዝብ መሰረታዊ ጥያቄን ወደ መሀል ሀገሪቱ አጠቃላይ ፖለቲካ አምጥተን በመሞገት ከተፈጥሮ ሀብቱ የሚጠቀምበትን መንገድ በእስትራቴጂ እና በእውቀት ታግዘን በኩራት አቅርበናል። በዚህም የኢትዮጵያውያንን ክብር እና ፍቅር አረጋግጠናል። የሶማሌ ህዝብ የሚገባውን ክብር እንዲያገኝ፣ የፖለቲካው የዳር ተመልካች ሳይሆን የመሀል ተጫዋች እና በሚወሰኑ ውሳኔዎች ድምፅ ሆነነዋል።
+—
በመሰረተ ልማት ደረጃም በርካታ ተግባሮች ጀምረናል። የተጠናቀቁ እና በጅምር ላይ ያሉ በርካታ ናቸው። የክልላችን ህዝብ ዋነኛ ችግር መንገድ እንደሆነ ግልፅ ነው። በህጋዊ መንገድ ስርአታቸውን ጠብቀው ሰባት ረጃጅም ደረጃ አንድ አስፋልት ተጀምረዋል። እንግዲህ እነዚህ ፕሮጄክቶች ሲጠናቀቁ የምንመሰገንበት እንደሚሆን አምናለሁ። አየህ፣ መሰረተ ልማት ጊዜን ይወስዳል። ፍሬው ለመታየት ጥቂት አመታት ሊወስድ ይችላል። ለፖለቲካ ትርፍ አያገለግልም። ለሀገር ለወገን የሚሰራ ነው።
ወደ ሰላሳ ከተሞች የሀያአራት ሰዓት መብራት አስገብተናል። የጤና ሴክተሩንም ለማሻሻል ከዚህ ቀደም ከፌዴራል የሚላክልንን ብቻ የምንጠብቀው አሁን 150 አምቡላንሶችን በራሳችን ወጪ ገዝተን ለራቅ ራቅ ላሉ ወረዳዎች አስረክበናል።
ወደ 450 ት/ቤቶችን አስሩ ከፍተኛ ደረጃ ትምህርቤት፣ ሶስት ቴክኒክ ኮሌጅ ሰርተናል።
ወረዳን ከወረዳ የሚያገናኝ መንገድ፣ የከተሞች የውስጥ መንገዶችን አሰርተናል።
አዲስ ሆስፒሎች እና እየታደሱ ያሉ ሆስፒታሎች፣ የደንብ ባንኮች፣ የፓርላማ ህንፃ እና የዞነን አስተዳደሮችን ህንፃዎች በአመት ከስምንት ወር ቆይታችን ውስጥ እያሰራን ነው። እውነት ለመናገር በአስር የመጨረሻ ወራት ከፍተኛ ስራዎችን አከናውነናል። ፖለቲካውን ካረጋጋን በኋላ ሰላም ካሰፈንን በኋላ የሰራነው ብዙ ነው።
ዝርዝሩ ብዙ ነው። ከሁሉ በላይ ለልማት አመቺ የሆነውን ሰላም በክልሉ እውን ማድረጋችን ትልቁ ስኬታችን ነው።
ጋዜጠኛ:
በዘረዘሩልኝ ስኬቶች ላይ የማነሳቸው ጥያቄዎች አሉኝ። ከዚያ በፊት፣ ከጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር ያላችሁ ግኑኝነት እንዴት ነው?
ሙስጠፋ:
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር መልካም ግኑኝነት ነው ያለን። በሀገሪቱ ህገመንግስት በተቀመጠው የፌዴራል እና የክልል የአሰራር እና የግኑኝነት ስርዓትና ደንብ ነፃነታችን ተጠብቆልን ነው የምንሰራው። አሁን ደግሞ በአንድ ፓርቲ፣ ብልፅግና፣ ስር በፓርቲ ደረጃ ስለምንሰራ መልካም የሆነ ገንቢ የሆነ ግኑኝነት ነው ያለን።
ጋዜጠኛ:
ካነሱት አይቀር ይህ የብልፅግና ፓርቲ ነገር፣ በርካቶች ጥያቄ ያነሱበታል። የሶማሌ ህዝብን መብት ያስጨፈልቃል እያሉ አስተያየት የሚሰጡ አሉ። ክብር ፕሬዝዳንት፣ ብልፅግና ስትባሉ፣ የተባለው ብልፅግና እውነትም ብልፅግና ስለመሆኑ በምን አረጋግጠው አመኑ? በፓርቲዎ ውስጥም ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ ሽኩቻ እና እስር ተካሂዷል፣ ከምዕራብ ሶማሌ ህዝብ ፓርቲ ጋርም ግጭት ውስጥ ገብታቹሀል።
ሙስጠፋ:
አንድ በአንድ ዘርዘር አድርጌ እንድመልስልህ ጥያቄዎችህን በቅደም ተከተል አስቀምጥልኝ።
ጋዜጠኛው:
እሺ ከብልፅግና ፓርቲ እንጀምር
(ሙግቱ ተጀመረ! በክፍል ሁለት እመለስበታለሁ።
እህሳ! አብረን ነን?
Filed in: Amharic