>
5:18 pm - Friday June 15, 1668

"ዲስኩሩና ፉከራው ይብቃ!" (አበበ ገላው)

“ዲስኩሩና ፉከራው ይብቃ!”

አበበ ገላው
አዲሶቹ የአደባባይ ፎካሪዎች ለህወሃት አድረው ህሊናቸውን እንደ አሞሌ ጨው ለዳቦ ሸጠው ኦሮሞን ጨምሮ ጭቁን የድሃ ልጅ ሲገርፉና ሲያስገርፉ፣ ሲገድሉና ሲያስገድሉ ነበር። ይህን ሃቅ ችላ ያልነው ጠፍቶን ሳይሆን ለውጥ መጥቷል፣ እኩልነት ታውጇል በሚል የይቅርታ መንፈስ ነበር። እድል ይሰጣቸው ብለን የተከራከርነው የተስፋ ብርሃን ፈንጥቋል በሚል እምነት እንጂ ገና በተግባር ያልተፈተነ ሰበካ አስደስቶን፣ ዲስኩሩ አስደምሞን አልነበረም።
ነጻት፣ እኩልነት፣ ፍትህና አንድነት በመልካም ቃላት ሲታውጅ በደስታ ያነባነው ግፍና በደል፣ ጭቆናና ዘረፋ፣ ዘረኝነና ጎጠኝነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ያከተመ መስሎን ነበር። የእስር ቤት በሮች ተሰብረው በጨለማ ብዛት ብርሃን ማየት የተሳናቸው አይኖች ዳግም ሲበሩ ማየት ያስፈነጠዘን ወንድሞቻችና እህቶቻችን በግፍ ተመልሰው ወደ ጨለማ ቤት አይወረወሩም በሚል እምነት ነበር። ከትናንት ዛሬ ይሻላል፣ ከዛሬ ነገ የተሻለ ይሆናል ብለን እምነት ያደረብን የሰጡን ተስፋ ዋጋ አለው በሚል እንጂ ከንቱ ሽንገላ አማሎን አልነበረም።
አገርና ህዝብን ያከበረን ማክበር፣ ነጻነትን ያወጀ እልል ብሎ መቀበል ይገባል በሚል እምነት ለጉብኝት ሲመጡ በነቂስ አደባባይ ወጥተን ከበሮ እየደለቅን እንደ ታቦት አነገስናቸው። ከውሃት ኢትዮጵያን ታደጓት ብለን “የለውጥ ሃይል፣ የለውጥ ሃይል” ብለን ዘመርን። እነርሱ ግን ቃላቸውን አረከሱት። ከጥላቻ ሃዋሪያት ጋር ተሰልፈው በህወሃት ዘመን ያንገሸገሸንን የጥላቻ ዲስኩር በየአደባባዩ በኩራት ደጋገሙብን። የእነ OMNን የጥላቻና የዘር ቅስቀሳ 24 ሰአት ህዝብ ላይ ለቀው ተራ ትችት ያሰሙን ሁሉ ለቃቅመው ማሰር ጀመሩ።
ታሪካችን የትግል ቢሆንም ትግል አብቅቶ በውይይትና በመግባባት የጋራ አገራችንን አጠንክረን እንድንገነባ የተመኘነው ለውጡ የምር መስሎን ነበር። ከዚህ በሁዋላ ለውጥ አትስበኩን። ለውጥ እንዲመጣ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ልጆቹን ገብሯል፣ ደሙን አፍሷል አጥንቱን ከስክሷል።
ለውጥ የአንድ ጠባብ ቡድን ፍላጎት ማርኪያ፣ ጥላቻ መስበኪያ፣ ድምጽ የሚያሰማን ማፈኛ፣ ሌሎችን አንኳሶ እራስን ማወደሻ፣ ያልበደለን ድሃ ህዝብ በጅምላ ማውገዣ ከሆነ ይቅርብን። ጭቁኑ የኢትዮጵያ ህዝብ የናፈቀው ሰባኪ ሳይሆን የተግባር ሰው ነው። እናንተ ህዝብ ስትጨቁኑና፣ ስታስጨቁኑ፣ ስትገርፉና ስታስገድሉ፣ ህዝቡ ለነጻነቱ ሲታገል ነበር።
ህዝቡ በትግሉ ከሎሌነት ነጻ አወጣችሁ እንጂ እናንተ ከማንም ነጻ እንዳላወጣችሁት ግልጽ ይሁንላችሁ። በኩራት የቆማች ሁበት አደባባይ ሁሉ የቆማችሁበት አደባባይ ሁሉ ለነጻነትና እኩልነት የታገሉ የአንድ ጎሳ አባላት ሳይሆኑ የመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ልጆች ደምና አጥንት እንደገበሩበት ይግባችሁ። ህዝብ ስታስጭቁኑና ስትጨቁኑ ኖራችሁ ባለቀ ሰአት ማይክሮፎን ስለጨበጣችሁ እንዴት ነጻ አውጪ ልትሆኑ ትችላላችሁ?
ከዚህ በሁዋላ ይበቃል! ስብከትን በተግባር ማሳየት ስለተሳናች ህዝብ ተቀይሟል። እንደነ ጃዋር አይነት መርዘኛ የዘር ፖለቲካ ነጋዴዎች ታቅፋችሁ እሽሩሩ እያላችሁ የኢትዮያን ህዝብ መሸንገል አትችሉም።
ይልቅ የሚቻላችሁ ከሆነ ሳይመሸ የተምታታ የእኩልነትና የጥላቻ፣ የፍትህና የእብሪት ዲስኩር በየአደባባዩ ማሰማት ትታችሁ በግፍ ያሰራችሁትን የድሃ ልጅ ሁሉ ፍቱ። ለውጥን በስብከት ሳይሆን በትግባር አሳዩ። በዚሁ ከቀጠላችሁ ግን ውድቀታች ከፈጣሪዎቻችሁ የከፋ እንደሚሆን ፈጽሞ አትጠራጠሩ።”
እናመሰግናለን!
ትግሉ ይቀጥላል!
Filed in: Amharic