>

የዶ/ር ዐብይ ህዝበኝነት (populism) እና የ'ደረቅ' አመራር አስፈላጊነት (ያያ አበበ)

የዶ/ር ዐብይ ህዝበኝነት (populism) እና የ’ደረቅ’ አመራር አስፈላጊነት

ያያ አበበ
[የዶ/ር ዐቢይ የረመዳንም ሆነ የትንሳኤ ንግግራቸው የማረካችሁ ወገኖች ባታነቡት ይመረጣል። ብታነቡት ግን ደስ ይለኛል።]
የጠቅላይ ሚኒስትራችን የፋሲካ ንግግራቸው የክርስትያኑን ስሜት እንዳማረከው ሁሉ ፣ የረመዳኑ ንግግራቸውም የሙስሊሙን ስሜት እንደማረከው እገምታለሁ።
ንግግራቸው የፈጠረው የስሜት ምቾት ጊዜያዊ ነው። በጎ ስሜትም በራሱ ችግር አይደለም።
ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትራችን እምነት ውስጥ ጠልቀው ገብተው የሚያደርጉት ንግግር (የፋሲካውም ይሁን የረመዳኑ) ተቋማዊ ገደብንና ድርሻን ያለፈ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንኳን ለረመዳን በዓል አደረሳችሁ የሚል መልዕክት ዛሬ በማለዳ አስተላልፈዋል፡፡  ለመልካም ምኞቱ እናመሰግናለን፡፡ ነገር ግን ‹‹እንኳን ለረመዳን ጾም አደረሳችሁ!›› ለማለት ስለረመዳን የ10 ደቂቃ ቡራኬና ትምህርት ማስተላለፍ ያለባቸው አይመስለኝም፡፡
ከዚህ ቀደምም ብዬው ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሴኩላር ሀገር መሪ ናቸው፤ እንደ መንግሥት ከሃይማኖት ጋር ያላቸው ግንኙነት ያልተመጠነና ገደቡን ያለፈ መኾን የለበትም፡፡ ሃይማኖታዊ በዓል በመጣ ቁጥር ቅዱሳን መጻሕፍትን እያጣቀሱ፣ የነቢያትና ጻድቃን ንግግርን በዋቢነት እያቀረቡ ከመንግሥት ይኹን ከሃይማኖት ተቋም መሪ እንደተላለፈ ለመለየት የሚቸግር መልዕክት ማስተላለፍ አሰፈላጊ አይደለም ብቻ ሳይኾን ተገቢም አይደለም፡፡ ለዚህ ዓይነቱ መልዕክት ቄሶቹና ሼኾቹ የሚሰንፉ አይመስለኝም፤ ትክክለኛ ኋላፊነቱም የእነሱ ነው፡፡
መንግሥት ለእምነት ተቋማት አዎንታዊ አመለካከት እንዳለው ለማሳየትም ከኾነ ሚዛኑን የጠበቀ መስተጋብር ነው ማድረግ ያለበት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይኼን መሰሉን ነገር የሚያደርጉት በቅንነትም ይኹን ለሽንገላ ተገቢ እንዳልኾነ ተረድተው ቢያርሙት መልካም ነው፡፡ ሕዝቡም ከመልካም ምኞቱ በዘለለ የሀገሩ መሪ ሃይማኖታዊ ቡራኬ እንዲሰጡት የሚጠብቅ አይመስለኝም፡፡ የእሳቸውን ሥራ የተመለከተ የሰፈር ካድሬ በአቅራቢያው የሚገኝ መስጂድ ወይም ቤተ ክርስቲያን ኼዶ እኔ ላሰግድ እንዳይልም ያሠጋል፡፡ የምሬን ነው!
***** የህዝበኝነት አደጋው ******
የሀገራችን ህዝብ ስሜታዊ ነው። ስሜቱን በቀላሉ ማግኜት ይቻላል።
ለምሳሌ በሺዎች የሚቆጠረው ወገናችን ባድመ ላይ ሄዶ የተሰዋው ስሜቱ ተነሳስቶ እንጂ የባድመ ጉዳይ ገብቶት ወይንም የጦርነቱን ትርጉም የለሽነት ተረድቶት አይደለም።
አንድ ጸሃፊ ስለ ህዝበኝነት ሲጽፍ ‘ህዝበኝነት የሚያቀነቅነው ፓሊሲ ላለው አዋጪነትም ሆነ ዋጋ ግድ የለውም’ ይላል። በሌላ መልኩ ህዝበኝነት የአጭር ጊዜ ውጤት ላይ ብቻ ያተኩራል ማለቱ ነው።
ህዝበኝነት (populism) ተቋማትን ከመገንባት ይልቅ ግለሰቦችን ያገዝፋል። ጠቅላይ ሚኒስትራችን የህዝበኝነትን ስልት ጀምረው መተው የማይችሉበት አጣብቂኝ ውስጥ እየገቡ ነው።
ህዝበኝነት ለዘመናት አብረውን የኖሩትንና ዛሬም የሚያደቁንን ጥልቅ ፣ ነባርና ውዝፍ ተግዳሮቶቻችንን ቀላል መፍትሄ ያላቸው እንዲመስለን ያማልላል።
ጠቅላይ ሚኒስትራችን የህዝበኝነት ስልቶቻቸውን መግታት ያለባቸው ከዚያ አደጋ የተነሳ ጭምር ነው።
******* ደረቅ አመራር *******
ዶ/ር ዐቢይ ህዝቡን የስሜት ቆርቋሪ ንግግር ሱሰኛ እያረጉት ነው። ስሜቱን እዲያሻሹለትና እንዲዳብሱለት ጥበቃ (expectation) እየፈጠሩበት ነው።
ከዚህ ይልቅ ህዝብ እውነትን እንዲለምድ ፣ እውነታን እንዲቀበል ፣ ድርሻውን እንዲያውቅ ፡ ከዚያም አልፎ የነባራዊውን እውነታ መራርነትና ድርቅና እንዲረዳ ማድረግ ወሳኝ ነው። ያ አይነት አመራር ስሜታዊ ሳይሆን ‘ደረቅ’ አመራር ነው።
የአቶ መለስ ዜናዊን ርዮታለማዊ ዝንባሌያቸውንና አንዳንድ ፓሊሲዎቻቸውን መቃወም እንዳለ ሆኖ፣ አቶ መለስ ለገሀዱ አለምና እውነታ ወግነው ይሰጡት የነበረው አይነት ደረቅ አመራር ህዝብን የሚያሰክን አመራር ነው።
ካለንበት ጠመዝማዛ ፣ ጨለማና ገደላማ ሀገራዊ መንገድ አንጻር ፣ ዛሬ ከመቼውም በላይ ደረቅ አመራር ያስፈልገናል።
እስከዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ስሜትን የመማረክና የማማለል ስልታቸው ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል። “እንታገስ” የሚለው ስሜታዊ ስልት ውድ ወገኖቻችንን (እነ ዶ/ር አምባቸውን፣ ጄ/ል ሰዓረን፣ ሌሎች ወገኖችንና ተማሪዎችን) እንድናጣ መዘናጋት ፈጥሮብን ነበር።
ዛሬም እምነት ውስጥ ገብተው ስለ ረመዳን ጾም ባደረጉት ንግግር ለስሜት ምቹ ቢሆንም ፡ የመንግስትን ተቋማዊ ድርሻና ገደብ እየናዱት ነው። (ስለ ፋሲካ ንግግራቸው ተመሳሳይ ሂስ ማቅረባችን ይታወስልን።)
ይሄ አይነት የተቋማዊ ሚና ብክለት ወደፊት የሚያመጣው ያልተጠበቀ ውስብስብነት (unintended complications) እንደሚኖር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ተገንዝበት ፡ እምነት ውስጥ ጠልቀው ከመዋኜት ይልቅ ፡ ደረቅ ያለ አመራር ቢሰጡ ዘለቄታዊ ፋይዳው ሰፊ ነው።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ፡ የረመዳንን ጉዳይ ለተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጅ ኡመር ይተውት። ፋሲካን ለአቡነ ማቲያስና ለሌሎች ቤተዕምነት መሪዎች ይተዉት።
አክብሮት ጋር!
Filed in: Amharic