>

ፓለቲካችን እና ውስጣዊ ቁስሎቹ (ያያ አበበ)

ፓለቲካችን እና ውስጣዊ ቁስሎቹ

ያያ አበበ
1. በግፍ መታሰር ፣ በመርማሪዎች መሰቃየት ፣ ከቤተሰብ መለየት … የሚያስከትለው ጉዳት ግልጽ ነው። ነገር ግን ከ1960ዎቹ ጀመሮ እስከ አሁን ድረስ በተለያየ የፓለቲካ ቅራኔና ግጭት ወቅት የተጎዱ ወገኖቻችን በእርግጥ ከደረሰባቸው ስነ-ልቦናዊ ጉዳት ምን ያህሎቹ አገግመዋል?
2. የደረሰባቸውን ጉዳት በሚመለከት በዕርቅ ሂደት ውስጥ ሳያልፉ ፣ በደሉን ያደረሰው አካልም ሳይናዘዝ ፣ በደለኞችም የደረሰባቸውን ጉዳት ባደባባይ ሳይመሰክሩ ስንቶቹ ናቸው ዛሬ ስነልቦናቸው በጎ ናቸው ሊባሉ የሚችሉት?
3. ባሰቃዮቻቸው ይቅርታ ሳይጠየቁ «ይቅር ብያለሁ» የሚሉት ወገኖችንሽ እናምናቸዋለን? ይቅርታ ሳይጠየቁ «ይቅር» ብያለሁ ማለታቸውስ ለነሱም ለሌሎቻችንም አደጋ የለውምን?
4. በስሜታቸውና በትውስታቸው ውስጥ ያለውን ቁስልና ጠባሳ በሚያራምዱት ፓለቲካ ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽዕኖ ተጎጂ ወገኖች ይረዱታልን?
5. ከብሔር ማንነታቸው ፣ ከእምነታቸው ፣ ከፓለቲካ ርዮታቸው ወዘተ … የተነሳሥ በተለያየ መንገድ ቤተሰባቸው ፣ ስሜታቸውና ሰብዓዊ ክብራቸው በስም ማጥፋት ዘመቻ የተጎዱና እየተጎዱ ያሉት ወገኖችስ ፓለቲካቸው ምን ያህሉ ከህመምና ከመጎዳት የመነጬ ነው?
እነዚህን ጉዳዮች እንደ ህብረተሰብ ልዩ ትኩረት ካልሰጠንና ፓለቲካችን ስነምግባር (ethics) እንዲኖረው ካልሞከርን ፡ ስነልቦናችን በቆሰለና በተጎዳ ወገኖች የሚቀነቀን ፓለቲካ ዉጤቱ ቁስልን በቁስል ፣ በደልን በበደል የመተካት ሂደት ነው።
ሰዎች ተጎድተው ጉዳታቸውን እውቅና ሳይሰጡ ፣ ጎጂዎችም ላደረሱትን ጉዳት ኃላፊነት ሳይወስዱ እንዴት የፓለቲካችን ስነምግባር እንደሚሻሻል አይገባኝም።
መጠቃትና መጎዳት የሚያደርስብንን የውርደትና የሀፍረት ስሜት ወደ ቁጣ (rage) እና ወደ በቀል ከመለወጥ ያለፈ ፣ ለተጎዳው ስሜታችን ጠጋኝ መፍትሄ አለማበጀታችን ፓለቲካችንን በጣም ጨካኝና አምካኝ አድርጎታል።
አንዲት የስደተኞችን ስነልቦና ያጠናች ስውዲናዊት የስነ-ልቦና ባለሙያ ፡ አንዳንድ ህብረተሰቦች “emotionally dishonest” (ስሜታቸውን የሚክዱ፣ ለስሜታቸው እውቅና የማይሰጡ) ናቸው ትላለች።
ስሜትን የመካድ ባህሪ ፓለቲካችንንም እኛንም በአግባቡ የሚገልጸን ይመስለኛል።
Filed in: Amharic