>

የሰንበት ወግ;- ጣዖሷ ጦስ አመጣች¡¡ [ቢቢ ሽጉጤ]

የሰንበት ወግ

ጣዖሷ ጦስ አመጣች¡¡

ቢቢ ሽጉጤ
   እንደው ‘ተነታረኩ፣ተጨቃጨቁ ።’ ብሎ የፈጠረን ህዝቦች። 
 እቺን ሁለት ቀን ፒኮክ በአማርኛ የጣዖስ ሃውልት ቤተመንግስት መግቢያ ላይ “ለምን ቆመ ” እና “እሰይ ቆመ” በሚል፤ ህዝቤ ኮሮናን እርስት አድርጎ እንካሰላምትያ ገጥሟል።
  ካነበብኳቸው አስተያየቶች  ” …ታሪክን ለማጥፋት አቅደው ነው የተነሱት፣ አብይ የ666 ተከታይ ነው መሰለኝ፣ ፒኮክ የጌዎች ምልክት ነው፤ ፒኮክ የውበት መገለጫ ነው ..ወ ዘ ተ…”
  የገረመቺኝ አንድ የመንግስት ሰው የሰጣት አስተያየት ናት  ” የፒኮክ ቀለም የተለያየ ስለሆነ ሃገሪቷ የተለያዩ ውበት ያላቸው ብሄረሰቦች ሃገር ስለሆነች ብሄሮችን ለመወከል ነው”
 ወይጉዴ ! ወይ እኝህ ብሄረሰቦች ! “ብሄረሰብን የሚወክል ኮከብ ነው ” ብላችሁን ባንድራው ላይ ለጥፋችሁ ፤ስታነታርኩን ኖራችሁ። አሁን ደግሞ ኮከብ አይደለም ፒኮክ ነው ብሄረሰቦችን የሚወክል ብላችሁ ባንድራው ላይ እንለጥፍ እንዳትሉን በእናታችሁ።
  ብሄረሰቦች ሚወክላቸውን ሲምቦል እንዲመርጡ ቢጠየቁ “አንበሳን” እንደሚመርጡ እርግጠኛ ነኝ።
  ሁሉም ብሄረሰብ በሚባል ደረጃ የሚዘፍኑት ዘፈን ውስጥ እራሳቸውን “አንበሳ ” እያሉ አድንቀው ነው የሚዘፍኑት። ይሄውም ከጥንት ጀምሮ አንበሳን የጀግንነት፣የጥንካሬ፣የአልበገር ባይነት ምሳሌ አድርገው ስለሚስሉት ነው።  የየትኛውም ኢትዮጵያዊ ብሄር ዘፈን ውስጥም፣ባህል ወስጥም ፒኮክ የለችም።
  እኔን የሚጠይቀኝ የለም እንጂ ፤ቢኖር ፡ በቤተመንግስትም ሆነ ሌላ የጋራ ቦታ የሚሰሩ ሃውልቶች ፡ የሃገሪቷን ታሪክ፣የህዝቡን ስነ-ልቦና ያገናዘበ ለትርጉም አሻሚ ያልሆነ ትዕምርት ወይም ሲምቦል ቢሆን ፤ በመንግስት መንጋ ደጋፊ እና በጭፍን ተቃዋሚ ለሚነሳው አቧራ የሚርከፈከፍ ወኃ ይሆናል ። እል ነበረ ። ስለ ፒኮኳ ግን  ከኢትዮጵያውያን ጋር ምን እንደሚያገናኛት፡አባቴ ይሙት ምንም አላውቅም፤ ዲ.ዳንኤል የፃፍት እራሱ አልገባኝም። የማልክደው ” አዋሳ ፒኮክ ጫማቤት ” አሪፍ ጫማ ገዝቼ መዘነጤን ነው።
  ነገስታቱ በሃይማኖት ይሁን በክፉ ሚሊኪ ወይ በሌላ ተመርተው ፡ የኢየሱስን ስም ወስደው “ሞ አንበሳ አምነገደ ይሁዳ ” ብለው እራሳቸውን ጠርተው፡አስጠርተው፣ተቀባብተው ፣ነግሰው፣የአንበሳ ሃውልት አሰርተው፣አንበሳ ጊቢ ብለው ፡አንበሳ አርብተው፣”መኩሪያ” የሚባል አንበሳ አሳድገው ኖረው፣ኖ ረ ው፣ ኖ     ረ     ው ፣  ተገለው ተቀበሩ። ግን እንደ ይሁዳ አንበሳ አልተነሱም።
   ፕሮቴስታንቱ የአህመድ አሊ ልጅ “አንበሳ ሁሉ ሞ አንበሳ እምነገደ… ነው” ብሎ አይመስለኝም የአንበሳውን ሃውልት ያፈረሰው።
  አንበሳውስ እሺ ፈረሰ ግን በምን መስፈርት ነው ኢትዮጵያውያኑ ጅግራ፣ቆቅ፣ዝዬ፣እርግብ ፣ዋኖስ፣ንስር ወዘተ…እያሉ ፤ህንዳዊቷ ፒኮክ የተመረጠችው?
  መቼም በሚሊኪ ተመርተው ፣መዳፍ አንባቢ ነግሯቸው ነው ብዬ አይምሮዬን ተጠራጠር አልለውም፤’መልኳ ስለሚያምር ነው’ ብዬ ቅን ከማሰብ ውጪ።
 ፒኮክ ግን ቤተመንግስት መግቢያ ላይ ሃውልት እንደተሰራላት ሰምታለች፤ አንበሶችስ እዛው እየኖሩ ሃውልት መኖሩን ሳያውቁ ፈረሰ ። ምፅም
  አንዳንዱ ደግሞ የሃውልቱን ተገቢነት ለማስረዳት የሚሄድበት እርቀት፡ አጃኢብ ነው።
  ለምሳሌ መ/ር ታዬ ቦጋለ የፒኮክን ልዩ ባህሪ ለማሳየት የፃፉትን ፤ለፒኮኳ ለራሷ ቢነበብላት ” ይሄ ሁሉ እውቀት እና ችሉታ ካለኝ፤ ለምን የአውሬ መጫወቻ ሆንኩ?” ብላ እግሯን አንስታ የምትስቅ ይመስለኛል።
  እናላችሁ ጓዶች ፦ ኢትዮጵያ ውስጥ በኮሮና የተያዘው ሰው ብዛት 117 ፤ስለ ኮሮና የዘፈነው ዘፋኝ ብዛት 207 ደርሷል አላችሗለው።
  የአንዳንዱ ማንቋረር ደግሞ (ዘፈን ለማለት ስለሚከብደኝ ነው) ሌላ እራሱን የቻለ አዲስ በሽታ ያመጣል። ጎበዝ እራሳችሁን ጠብቁ።
  ይሄ ደግሞ ዘፋኝ እና ዘማሪ ተቀላቅለው ያደረጉት ነገር ፤ዘፈኑ ነው ዘመሩ ነው የምንለው ወይስ ዘፈኑ + ዘመሩ = ዘፈሩ ነው የሚባለው።  እግዜሩንም ግራ እያጋቡት መሰለኝ።
አድነነ ከመአቱ !!  ሮመዳን ሙባረክ!!
Filed in: Amharic