.. ብዬ አሰብኩና፤ ማጣፊያው ሲያጥር ተውኩት!!!
ያሬድ ሀይለማርያም
– ለ86 ንጹሃን ዜጎች ሞት ምክንያት የሆነው እስክንደር ቢሆን ብዬ አሰብኩና፣
– መንግሥት የደለደለውን የኮንደሚንየም እጣ ሜጫ የያዙ ደጋፊዎቹን ይዞ አደባባይ በመውጣት ወይ ፍንክች አታረጓትም ብሎ የፎከረው እሰክንድር ቢሆን ብዬ አሰብኩና፣
– ለሲዳማ ወጣቶች በአደባባይ የአመጽ ጥሪ አቅርቦ ለ50 በላይ ሰዎች መሞት እና በሚሊዮኖች ለሚገመት ንብረት መውደም ምክንያት የሆነው እስክንድር ቢሆን ብዮ አሰብኩና፣
– በቡራዩና በሰበታ ከተፈፈጸመው ጭፍጨፋ ጀርባ እጃቸው እንዳለበት የሚያሳይ ፎቶዎችን በማን አለብኝነት ሲለጥፋ የነበሩት የእስክንድር ደጋፊዎችና አጃቢዎች ቢሆኑ ኖሮ ብዬ አሰብኩና፣
– በቡራዩ የሞቱትን ሰዎች ቁጥር በተመለከተ የሃሰት መረጃ የሰጠው እና ፖሊሶችን በመዝለፍ ማስፈራሪያ የሰነዘረው እስክንድር ቢሆን ብዬ አሰብኩና፣
– የውጭ አገር ፖስፖርት ይዞ የፖለቲካ ስራዎች ሲሰራ፣ የምርጫ ቅስቀሳ ሲያደርግ እና ምርጫ ቦርድም ማስጠንቀቂያ ቢሰጠው የቦርዱን ሰብሳቢ መድሎኛ ብሎ ሰድቦ ያልተፈቀደ ቅስቀሳውን የቀጠለው አስክንድር ቢሆን ብዬ አሰብኩና፣
– በራሱ ሚዲያ ሕዝብ እና መንግስትን፤ በተለይም ጠቅላዩን ሲያብጠለጥል፣ ሲሳደብ፣ ሲዝትና ሲያስፈራራ የነበረው፣ ሁለት መንግስት አለ ያለው፣ የአዲስ አበባን ጉዳይ ወይ በምርጫ ወይ በጉልበት እንፈታዋለን ያለው አስክንድር ቢሆን ብዬ አሰብኩና፣
– በተደጋጋሚ የሃሰት መረጃና የአመጽ ቅስቀሳ በሚያስተዳድረው ሚዲያ ሲያሰራጭ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ቢጻፍለትም ይቅርታ እንኳ ለመጠየቅ ያልዳዳው እና መልሶ መንግስ ላይ ዛቻ የሚሰነዝረው እስክንድር ቢሆን ብዬ አሰብኩና፣
– መንግሥት የመደበለትን ጠባቂ ወታደሮች ያስኮበለለው እና በመንግስት ላይ ክህደት ኤዲፈጽሙ ያደረገው እስክንድር ቢሆን ብዬ አሰብኩና፣
ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም ሰው በሕግ ፊት እኩል የሚዳኝበት ቀን ቢርቅብኝ ጊዜ ቢሆን እያልኩ ማሰብ ጀመርኩ።
ለፍትህ እሩቅ ነን፣
ለሕግ የበላይነት መከበር እሩቅ ነን፣
ለእኩልነት እሩቅ ነን፣
ለዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብም እሩቅ ነን፣
በደልን በእኩል ለመጠየፍም እሩቅ ነን፣
ከግፋአን ጎን በድፍረት ሳናወላውል ለመቆምም ገና እሩቅ ነን፣
እንደዜጋ እኩል የምንተይ ሳይሆን ባፈረጠምነው ጡንቻ፣ ባደራጀነው ቲፎዞ እና ባካበትነወ ሀብት ልክ የምንሰፈርበት ዘመን ፍጻሜ ካላገኘ ጉዟችን ሁሉ እዘጭ እንቦጭ ነው የሚሆነው።
መንግስት ታጋሽነቱም ሆነ ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ ያለው ቀናይነት ወጥ እና ሁሉንም ዜጋ በእኩል የሚሰፍር መሆን አለበት። አይን ያወጣ ኢፍትሃዊነት ከማስተዛዘብ አልፎ ዜጎች በሕጋዊ ሥርዓቱ ላይ እምነት እንዲያጡ ያደርጋል።
እግረ መንገዴን የዋስትና መብት ተነፍጋ በግፍ በእስር ቤት እየተሰቃየች ያለችው የሕግ ባለሙያ ኤልሳቤት በአፋጣኝ እንድትፈታ እየጠየኩ ልሰናበታችሁ።
ቸር እንሰንብት!