>

በሊባኖስ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የከፋ ችግር ውስጥ ናቸው ...!!! (ኢትዮ ኤፍ ኤም)

በሊባኖስ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የከፋ ችግር ውስጥ ናቸው …!!!

ኢትዮ ኤፍ ኤም
በሊባኖስ መዲና ቤሩት ከተማ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ላለፉት ሰባት ወራት ካለ ስራ መቀመጣቸውንና ከባድ ችግር ውስጥ መግባታቸውን ነው የተናገሩት፡፡
እነሱ እንደሚሉት በሃገሪቷ ስራ የጠፋው የሃገሪቷ ዜጎችም ሰራተኞቻቸውን ማሰናበት የጀመሩት ከሰባት ወራት በፊት ባጋጠማቸው የኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ነው፡፡
በወቅቱም በሁኔታው ተስፋ ቆርጠው ወደ ሃገራቸው ለመመለስ በኢትዮጵያ ቆንስላ በኩል የተጠየቁትን 550 ዶላር ከፍለው የተወሰኑት ሃገራቸው መግባታቸውን አጫውተውናል፡፡ ቀሪዎቹ ደግሞ ተራቸውን እየጠበቁ ባለበት ሁኔታ ኮሮና ቫይረስ በመከሰቱ ወደ ኢትዮጲያ የመመለሻቸው ነገር እየራቀባቸው መምጣቱን ይናገራሉ፡፡
ስደተኞቹ ባጋጠማቸው የገንዘብ ችግር ምክንያት በርካቶች ከተከራዩበት ቤት እንዲወጡ እየተደረጉ መሆኑንና በዚህም ራሳቸውን የሚያጠፉ፤ እንዲሁም ለአእምሮ ህመም የሚዳረጉ ዜጎቻችን ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ነግረውናል፡፡
በሊባኖስ የሚኖሩ እንዚህ ኢትዮጵያውያን እንደነገሩን ከ80 በላይ ልጆች አእምሮ በሽተኛ ሆነው ቆንስላው ውስጥ አሉ ወደ 100 የሚጠጉ ልጆች ደግሞ ህይወታቸው አልፎ አስከሬናቸው ማድረቂያ ውስጥ እንዳለም እናውቃለን ብለውናል፡፡ ስለሆነም መንግስት የሚችለውን አድርጎ ወደ ሃገራችን ያስገባን ሲሉ ነው ድምጻቸውን ያሰሙት፡፡
በውጪ ጉዳይ ሚኒስትር የቆንስላ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ዬሃንስ ሾዴ ከስደተኞቹ የተነሳው አቤቱታ ትክክል መሆኑን በማመን፤ ይህ በሊባኖስ ብቻ ሳይሆን በሁሉም መካከለኛው ምስራቅና ሌሎችም በርካታ ሃገራት ያሉ ዜቻችን ጥያቄ ነው ብለውናል፡፡
ሆኖም ሃገራት በኮሮና ወረርሽኝ ስጋት ምክንያት አለም አቀፍ በረራዎችን በማገዳቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአየር ክልላቸውን ጥሶ መግባት አይችልም ይላሉ፡፡
በመሆኑም ሁኔታዎች ወደ ቦታዎች እስከሚመለሱ ድረስ በሁሉም አቅጣጫ ያሉ ኢትዮጵያዊያን ራሳቸውን እየጠበቁ በትእግስት ይህን ጊዜ እንዲያሳልፉት ጥሪ አቅርበዋል፡፡
Filed in: Amharic