>

ከ27 ዓመታት በላይ የተያዘው ሪከርድ ሰሞኑን ተሰበረ! (ዳግማዊ ጉዱ ካሣ)

ከ27 ዓመታት በላይ የተያዘው ሪከርድ ሰሞኑን ተሰበረ!

 

 

ዳግማዊ ጉዱ ካሣ

 

 

 

“በስንቱ ተንጨርጭሬ እዘልቀዋለሁ?” ከሚል የመጻፍ ፍላጎቴን አፍኜ ብጋደምም ይሄውና ከራማዬ በሌሊቱ ጎልቶኛል፡፡ ኧረ እናንተዬ ለደግ ያድርግልህ በሉኝ እንጂ አንዳች ነገር ሸቶኝ ጉሮሮየን በከረከረኝና ባስነጠሰኝ ቁጥር ያ ወስላታ ኮሮና የተጠጋኝ እየመሰለኝ እንደዐረብ ጀማላ ሻይ አበዛሁና ጉሮሮየ ተልጦ ሊያልቅ ነው፡፡ ዱሮ መኖርህን ለማሳወቅ  “እእእህህህ…” ብለህ ጉሮሮህን እንደመጥረግ በማስመሰል የምታወጣው ድምጽ ዛሬ 8335ን አስጠርቶ ለኮሮና አምቡላንስ ሊዳርግህ ይችላል – ቀልድ ዱሮ ቀረ ወዳጄ፡፡ መሳል ማስነጠስ አሁን እንደጉድ ይፈራል፡፡ “እንጥሸው!” ከማለትህ አጠገብህ ያለ ሰው ሁሉ ይበረግጋል፤ ያኔ ትደነግጣለህ፡፡ ለወትሮው በተለያዬ በሽታ ሰው ይሞት ነበር፡፡ ዛሬ ግን ጉንፋን ሳይቀር ሁሉም ነባር በሽታ ለኮሮና እጁን ሰጥቶና በድንጋጤ ተኮራምቶ የሚሞትም ሆነ የሚታመም ሰው እምብዝም አይታይም፡፡ እውነቴን እኮ ነው – ሞትና ሌላው በሽታም ደነገጠ! ደጋግሞ መታጠብን በተመለከተም እንዲህ ተቀልዶላችኋል፡- አንዱ ምን አለ አሉ – ከFB መንደር የተቃረመ ነው መቼም – “እጄን አብዝቼ ከመፈተጌ የተነሣ የ8ኛ ክፍልን አጤሬራ መዳፌ ላይ አገኘሁት!” ሌላው ምን ቢለው ጥሩ ነው – “ሰውነትህን በደምብ ሞዥቀውና ዩኒፎርምህን ታገኘዋለህ!” – መግቢያ የሌለው ነገር ደስ አይልም ብዬ ነው፡፡ ወደመነሻየ ገባሁ፡- 

ሜ/ጄ ተ/ብርሃን የተባለ የቀድሞ የኢንሣ መሪ ሰሞኑን ከአንዲት ልጅ ጋር ባማርኛ ባደረገው ቃለ ምልልስ “አማርኛ ለመማር ያጠፋሁት ጊዜ ይቆጨኛል” ማለቱ በማኅበራዊ ሚዲያ በስፋት ሲዘገብ ሰማሁ፡፡ ይህ ሥነ ልቦናዊ በሽታ በዓይነቱ የመጀመሪያ ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ ከድንቁርናና ገደብ ካጣ ጥላቻ ሊመነጭ የሚችለው የዚህ ዓይነት ንግግር የበሰበሰ ሰው በርግጥም ዝናብ የማይፈራ መሆኑንና የዕውቀትን ጠቀሜታ የማያውቅ እንደተወለደ ሟች መኖሩን የሚጠቁም ነው፡፡ በጣም ነው የደነቀኝ፡፡

      ብዙ ወያኔዎች ስለአማራና አማርኛ ብዙ የጥጋብ ንግግሮችን በልበ ድፍንነት አሰምተውናል፡፡ የዚህኛው ለየት የሚለው ጊዜ መምረጥ አለመቻሉ ነው፡፡ አንድ ሰው ካላበደ በስተቀር አንድን ቋንቋ – ያ ቋንቋ የዝንጀሮም ይሁን የጦጣ – በመልመዱ ምክንያት ሊቆጭ የሚችልበት አንድም አሣማኝ ምክንያት የለም – የአእምሮ ህመም ከሌለበት በቀር፡፡ እኔ ለምሣሌ ትግርኛን ጨምሮ ወደ አምስት የሚጠጉ ቋንቋዎችን በተለያዬ ደረጃ መናገርም ሆነ መጻፍ እሞክራለሁ – አንዳንዶቹን ለብዙ ጊዜ ካለመጠቀሜ የተነሣ ሰነፍኩባቸው እንጂ፡፡ በዚህም ታዲያ እደሰታለሁ፣ እኮራለሁም እንጂ ለአብነት አማራን በገባበት ገብተው እያሳደዱ የጨረሱትና ያስጨረሱት እነመለስና ስብሃት ነጋ በአፍ መፍቻነት ተናገሩት ብዬ ትግርኛን አልጠላም – በጭራሽ፡፡ ኸምዚ እንተገበርኩ ድማ ከም ሰብ እንተዘይኮነስ ከምፀላዔ ሠናይ ምቁፃር ይግብኣኒ፡፡ ይሄ ኢንሣ የሚባል መ/ቤት ግን መፈተሸ አለበት! ከዚያ የሚወጡ ሰዎች ኮምፒውተሩ አንጎላቸውን ወደ ግዑዝነት እየለወጠው ሳይሆን አይቀርም ተበለሻሽተው ነው የሚወጡት፡፡ አቢይን ተመልከቱ – ሰው ሲሉት አፈር፣ አፈር ሲሉት ገለባ ይሆናል፡፡ ያ የአቢይ ተላላኪ የአማራው ክልል ፕሬዝደንት ተብዬም እዚያው ነበር አሉ፡፡ ብቻ መ/ቤቱ የምትታቀፈውን ዕንቁላል ሁሉ ሙቀት እየነሳች እንደምታበላሽ ዶሮ ብዙ ሰው አግምቷል፡፡

ወያኔ አማራ ላይ ያለው ጥላቻ ተነግሮ አያልቅም፡፡ አሁን ገዢ ተለውጦ ኦነግ/ኦህዲድ ሆኗል፡፡ ስለዚህ ጥላቻው ሰከን ሊል ይገባው ነበር፡፡ እነሱ ግን በካፈርኩ አይመልሰኛቸው ገፍተውበታል፡፡ስለዚህም ነው የበሉበትን ወጪት አሁን በዘመነ ንስሃቸው ሳይቀር በተደጋጋሚ ሊሰባብሩት የሚሞክሩት፡፡  እንጂ ካለፉት ሠላሣ ዓመታት ወዲህ የአራት ኪሎን ቤተ መንግሥት የሚረግጥ የሀገር መሪና ባለሥልጣን ሁሉ አማራን ካልተሰዳበና “በአማራ መቃብር ላይ የኢትዮጵያን ሕዝቮችና ቤርቤረሰቦች ባፍጢማቸው ተክለን ውኃ እናጠጣቸዋለን….” ብሎ ካልተለፋደደ ሥልጣኑ የሚረጋለት አይመስለውም፡፡ ሌላው የሚገርመው ነገር ለሥልጣን የሚመለመለው ሁሉ አማራ-ጠልና በትምህርት ያልገፋ እንደዚሁም ዘረኛና ሆዳም መሆኑ ነው፡፡ አማራን የማይሳደብ የዘመናችን ባለሥልጣን ፈልጎ ማግኘት አይቻልም፤ ሲሳደቡ ደግሞ ቀብረር ብለው ነው፤ ቅንጣት ቅፍፍ አይላቸውም፡፡ መለስ አማራ ሲለምን ማየት እንደሚያስደስተው፣ ሣሞራ በእናት ድርጅቱ ሕወሓት አማካይነት አማራን አርቀው እንደቀበሩ፣ የሕወሓት ማኒፌስቶ አማራና ኦርቶዶክስን ማጥፋት እንደሚገባ፣ ሁሉም የወያኔ ጀሌዎች “አህያው”ንና “ፈሪ”ውን አማራ ማጥፋት ጽድቅ እንደሆነ …. የሚያምኑ መሆናቸውንና ተራና ቀፋፊ ስድባቸውንም ፉከራቸውንም ለምደነው ተቀምጠናል፡፡ የተ/ብርሃን አስቂኝ አባባል ደግሞ አትርሱን ይመስላል፡፡ ይህንን ሰውዬና ፀጋየ አራንሳ የሚባለውን የኦነግ በሽተኛ እነሱው በሚያቀነቅኑት “de-Amharicization” የሚባል አዲስ ኦነጋዊ የህክምና ሥልት የመከነ ጭንቅላታቸው ውስጥ የሚገኘውን አማርኛ በ hypnosis  የሚያወጣላቸው የሥነ አእምሮ ጠቢብ ቢገኝ ለአማሮችም ባለውለታ በሆነ ነበር፡፡ እነሱም ከሥነ ልቦናዊ የቁም ሥቃይ በተገላገሉ፡፡ ጊነስ ቡክ ኦፍ ሪከርድስ ሆይ ወዴት አለህ? ይህን መሰሉ ጉድም ይመዝገብ እንጂ! ቡፉጹም የጤና እኮ አይደለም፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን ኦና ስትሆንና የጴንጤው መንግሥት ግን በርካታ የየጉራንጉሩ “ቸርቾች” አዶከብሬ ሲደለቅባቸው ዝም ማለቱን ስናይ ይቺ ኮሮና መልእክቷ ዘርፈ ብዙ እንደሆነ ይገባናል፡፡ አብዛኛው የአቢይ ሹመኛ ጴንጤና ሙስሊም መሆኑ ግልጽ ነው – በበኩሌ አልቃወምም – ምን ቁርጥ አድርጎኝ! የምቃወመው ዜጎችንና ሃይማኖቶችን እኩል ማየት ያለባቸው ኃላፊዎች ለአንዱ ወይ ለሌላው ሲያዳሉ ነው፡፡ ይህ ኃጢኣትም፣ ወንጀልም፣ ነውርም፣ የአእምሮ ዕድገትን መሰነካከል በግልጥ የሚያሳይ ጮርቃነትም ነው፡፡ ሥልጣንን መከታ በማድረግና በተረኝነት ስሜት በመናወዝ ግፍ የሚሠራ ወገን የሚያወራርደው ሂሳብ ለነገ እያስቀመጠ መሆኑን መረዳት አለበት፡፡ ኦርቶዶክስን እንዴት እንደሚያሳድዱ እየታዘብን ነው፡፡ በአሥርና በሃያ ሜትር ርቀት መቆም አይደለም ከናካቴው ወደ ግቢ እንዳትገባ ቤተ ክርስቲያን ትቆለፍብሃለች፡፡ ነገሩ በሰበቡ መምሬ ተሳቡ ዓይነት ነው፡፡ በሌላ ወገን ሲታይ ደግሞ ገበያ ትርምስ ነው፤ ትራንስፖርት ትርምስ ነው፤ ሐኪም ቤት ትርምስ ነው፤ “በጌታዋ የተማመነች በግ…” እንዲሉ በጴንጤዎቹ ብዙ ‹ቸርቾች› ትርምስ ነው፤ … በኦርቶዶክስ ግን ካህንም ሆንክ ሊቀ ጳጳስ ሲያሰኛቸው በዱላ እየዠለጡ ወስደው ያስሩሃል፡፡ ማንን ፈርተው! ዘመነ ዕንቆቅልሽ፡፡

ፈስ ያለበት ዝላይ አይችልም፡፡ ቂጡ ላይ ቁስል ያለበት ውሻም እንደልቡ አይጮህም፡፡ የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያን አብዛኛዎቹ አገልጋዮች እንደኔው በዓለም ኃጢኣት የጠፉ ለመሆናቸው ዘመኑ ራሱ ምስክር ነው፡፡ ንግግሬ ሀሰት ቢሆን ደይኑ(መከራው) ለራሴ ይሁን! እናም “ልጄን በሰላም ላሳድግበት” የሚል ጳጳስ ባለባት ሀገር ስለ ቤተ ክርስቲያንና ምዕመኗ ደኅንነት የሚጨነቅ የሃይማኖት አባት ይኖራል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ከአነስተኛ ደብር ከፍ ወዳለውና ወደሚበላበት ደብር በተራ ቀዳሽነትም ይሁን በደብር አለቅነት ለመዛወር በመቶ ሽዎች የሚገመት ጉቦ በሚከፈልባት ሀገር፣ የቀብር ቦታ ለማግኘት፣ ከቤ/ክርስቲያን አስተዳደር የሰምበቴና የፉካ ቦታ ለመመራት፣ ክህነት ለመቀበል፣ አለሃይማኖትህ ለመቀበር … ያለሙስና በማይታሰብበት ሀገር ጸሎትና ምህላ ከዛፍ በላይ ባያርግና እግዜሩ ፊቱን ቀርቶ ጀርባውን ቢያዞር ማንም ሊፈርድበት አይገባም … ሌላ ሌላውንና ጉግማንጉጋዊውን ኃጢኣት ትተነው፡፡ መብትን ለማስከበር የእውነትን ዘገር ታጥቆ መፋለምን ይጠይቃል፡፡ በሙስናና በዘረኝነት የተተበተበች ቤተ ክርስቲያን፣ የአንድ ወቅት ወሮበላ ፓትርያርኳ “እስካሁን በአማርኛ በመቀደሴ ይጸጽተኛል” ብሎ ሰውን ጉድ ያሰኘባት የሰው መሳይ በሸንጎዎች መናኸሪያ ተቋም ይህን የሰይጣን ዘመን ታግላ ለመጣል ያላት አቅም ከአጋንንቱ ዓለም እንደተላኩ ከሚገመቱ አንዳንድ ተዓምረኛ “እናቶች”ና “አባቶች” የሚሻል አይደለም – ላመነበት ሰይጣንም እኮ ትልቅ ኃይል አለው፡፡ እስኪ ወንድ የሆነ ጳጳስ ስለ “እህተ ማርያም” የዲያቢሎስ ባለሟልነት ይናገር! በየትኛው ድፍረቱ? ጉዴን ያወጡብኛል ብሎ ይፈራላ! በሁሉም አቅጣጫና በማንኛውም ተቋማዊ ይዞታ ልክ ባልሆኑ ዜጎቿ የፊጥኝ ታስራ ኤሎሄ የምትለዋ ኢትዮጵያ እጅጉን ታሳዝናለች፡፡

“ከወፈሩ ሰው አይፈሩ” ይባላል፡፡ እነአቢይና ታከለ ኡማ ቀንቷቸዋል፡፡ ምዕራፍ ሁለት አማራን አሳደህ በለው ዘመቻ አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡ በዚህ በኮሮና ዘመን ሰውን በየቤቱ ኮድኩደው የልባቸውን እየሠሩ ነው – ቀን ሲሰጥ ደግሞ እንዲህ ነው፤ “ቀን ይካስህ” መባሉስ ለዚህም አይደል? አንደኛ አማራን እቦታው ድረስ ጦር አዝምተው እየተቆጣጠሩት ነው – በደንገጡራቸው በብአዴንም ጭምር፡፡ ሁለተኛ በአዲስ አበባና በዙሪያዋ የሚገኙ አማሮችንና “ትውልደ አማሮችን” ባልተወለደ አንጀት ቤት ንብረታቸውን በሌሊት እያፈረሱና እያቃጠሉ በምትካቸው በጠራራ ፀሐይ ኦሮሞዎችን ከየክፍለ ሀገሩ እያመጡ በማስፈር ላይ ናቸው፡፡ “ቀን የሰጠው ድንጋይ ብረት ይሰብራል” ይባላል – ተረቱም ሊጠፋኝ ነው መሰል እናንተዬ!  አዎ፣ እነአቢይና መንጋው ሌቱ የማይነጋ መስሏቸው ቋታቸውን ዝቀው በማይጨርሱት ጥሬ ኩሳቸው እየሞሉት ነው፡፡ እነዚህ ከንቱዎች ከወያኔ የተረፈችዋን “ትንሽዬ መተት” በመጠቀም ጀምበራቸው  እስክትጠልቅ አቅላቸውን ስተው አማራንና ኢትዮጵያን በማጥፋት ሥራ ላይ ተጠምደዋል፡፡

ብዙ የሚታይና የማይታይ ነገር አለ፡፡ ከብርሃኑ በፊት እጅግ ብዙ ድቅድቅ ጨለማ አለ፡፡ የጨለማው ዘመን እንዲያጥር አባቶች እናቶች በርትታችሁ ጸልዩ፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ተዋት፡፡ ለራሷ ትጸልይ፡፡ ራሷን ነፃ ታውጣ መጀመሪያ፡፡ ራሱ ነፃ ያልሆነ አካል ሌላውን ነፃ ሊያደርግ አይቻለውም፡፡ የመጣብን ዘመን የኖኅና የሎጥ ነው፡፡ አንዲት ጥይት ሳይተኮስብን የዶግ ዐመድ ልንሆን የምንችልበት ዘመን ነው እየመጣብን ያለው – ጉልኅ ምልክቶቹንም እያየን ነው፡፡ ኮሮና እኮ ምንም አይደለም፤ እስካሁንስ ምን አደረገን? ምንም!

ምሁራንና ከሙስና የጸዳን ነን የምትሉ ወገኖች በሞረሽ ተጠራሩ፤ ተሰባሰቡ፤ ተመካከሩ፡፡ አንዳች ነገር ቢከሰት ፈጥናችሁ ለመድረስ ተዘጋጁ፡፡ ቀድማችሁ ካልተዘጋጃችሁ ብዙ ጉዳት ሊደርስ ይችላል፡፡ ሠርገኛ መጣ ዓይነት ክስተት እንዳይፈጠር በኔ ይሁንባችሁ እንደእስካሁኑ በግዴለሽነት በዝምታ አትቀመጡ፡፡ በማይማንና በዘረኞች እጅ የምትገኘው ኢትዮጵያ ከእጅ አምልጣ መጨረሻ ወደሌለው እንጦርጦስ የምታደርገውን ጉዞ የምትጀምረው ድንገት ነው – ዱሮም ልጅ ያቦካው ለራት አይበቃም፡፡ ሀገርን ማስተዳደር የእግር ወይ የእጅ ኳስ ቡድን እንደመመሥረት ቀላል አይደለም፡፡ ቡድን ስትመሠርት የምታውቀውን – ከምታውቀውም በጉብዝናው የምትተማመንበትንና ሽንፈትን የማይጋብዝብህን ልጅ ትመርጣለህ፡፡ አቢይ ግን ጴንጤ የሆነንና በወያኔ የፀጥታና የስለላ መዋቅር የሚያቃቸውን ሮጠው ያልጠገቡ ለርሱ ቅን ታዛዥ የሆኑ ባብዛኛው በዘራቸው ኦሮሞ ኩታራዎችን እየሾመ መሣቂያ መሣለቂያ አድርጎናል፤ በነገራችን ላይ እኔ በሃይማኖትና በዘር አላምንም – ምን ማለቴ መሰለህ – ሁሉም ጴንጤ ቢሆን፣ ሁሉም ኦሮሞ ቢሆን – ሁሉም አጫጭር ወይ ረጃጅም ቢሆን … ሥራውን በብቃት እስካከናወነ ድረስ  ግዴለኝም፡፡ ለምሣሌ የንግድ ባንክን ፕሬዝደንት እንደኔ የሚያደንቀው ኦሮሞ ካለ ይገርመኛል፡፡

እንደአካሄድ ግን – የወያኔን አማርኛ መርሳት የለብኝም – እናም እንደ አካሄድ ሕዝቦቻችንን በልማታዊ ዴሞክራሲ ፉልድረቲ ለማለት ከላይ ከፓርላማ የሚሰጥ አቅጣጫ ወርዶ መሬት ላይ መነጠፍ ማለትም መቀመጥ ይኖርበታል፡፡ … ወደ ቁም ነገሩ ስንመጣ ስንትና ስንት ትልልቅና የተማሩ ዜጎቿ ለስደትና ለብኅትውና ሕይወት ተዳርገው ሳለ ሀገራችን ሰው እንደሌላት እነዚህ ሮጠው ያልጠገቡ ውርጋጦች ፊን ፊን እንዲሉ የተፈቀደላቸው ኃጢኣታችን ገና ተከፍሎ ስላላለቀ (ቢሆን) ነውና እኛም ወደ ቀልባችን ተመልሰን የፈጣሪን መንገድ እንከተል (እንዴ! ይቺ “ፊንፊኔ” የተባለች ነገረኛ የሸገር ስም ከኦሮምኛ ሳይሆን ከአማርኛ እንደመጣች የሚነገረው እውነት ይሆን?) ሀገራችን አሁን በኪነ ጥበቡ – በኢነርሽያ – ወንገር ወንገር ትላለች እንጂ መንግሥት እንዳላት አትቆጠርም፡፡ ካለመንግሥት በመኖር ደግሞ እኛ ኢትዮጵያውያን አንታማም፡፡ በአሁኑ አያያዝ ግን የባሰ ነገር ቢመጣ እነዚህ ውጫጮች እግራቸው በመራቸው ጥለውን እንደሚፈረጥጡ … ቱ! ከምላሤ ፀጉር ይነቀል … ነገረ ሥራቸው ሁሉንም ነገር ደፋፍተው ለመሄድ የቸኮሉ ይመስላሉ፡፡ የሚያወጡት ደምብና ህግም የታሰበበት ሳይሆን የቸኮለ ጅብ ዓይነት ነው፡፡ የነዳጅ ዕጥረትንና የመኪና መንገድን ከመኪና ብዛት ጋር ያለመመጣጠን ችግር በተወሰነ ደረጃ ለመቅረፍ ብለው ያወጁትን የሙሉና ጎደሎ ታርጋ ቁጥር የወረፋ እንቅስቃሴ በኮሮና ያሳብባሉ፡፡ ኮሮና ግዴለም ነገ ጠፋ እንበል፡፡ ከዚያ ይህ የሚበላው ያጣ ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ ወደ አራት ኪሎ ቢተም መንገዱን በምን ሊዘጉት ነው? በቄሮ ድንጋይ ወይንስ በአጣና? የዕርዳታውም፣ የብድሩም፣ የበጀቱም ገንዘብ በባለሥልጣናትና በመሰል መዥገሮች እየተቆረጠመ በውሸት እስታቲስቲክስ “ይህን ያህል ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ተሠራ!” የሚባለው ፌዘኛ ዜና ጉዱ ፈጦ ሊታይ መኪናና ሰው መተላለፊያ አጥቶ አዲስ አበባ በጭንቅንቅ ምክንያት ስትፈነዳ ተጠያቂው ኮሮና ወይንስ የ(ነ)አቢይ “ተጨፈኑ ላሞኛችሁ” የውሪ መንግሥት? …  ስንት ሰዓት ሆነ እንዴ ግን እባክህ? ቧይ!… በቃኝ – ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት! EMAIL: ma74085@gmail.com

Filed in: Amharic