>

በቸነፈሩ ሽፋን ሕዝብን ጸጥ ማሰኘት አይቻልም! (ከይኄይስ እውነቱ)

በቸነፈሩ ሽፋን ሕዝብን ጸጥ ማሰኘት አይቻልም!

ከይኄይስ እውነቱ

ርትዕት ተዋሕዶ ሃይማኖት መጽሐፍን መሠረት አድርጋ እንዲህ ትላለች፡፡ ‹‹ኢይኀድጋ እግዚአብሔር ለብሔር ዘእንበለ አሐዱ ኄር፡፡›› እግዚአብሔር አገርን ያለአንድ ቸር/በጎ ሰው አይተዋትም፡፡ ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር መቼም ቢሆን ሰዎች አሉት፡፡ በመንፈሳዊውም ሆነ በሥጋዊ ሕይወት አብነት/ምሳሌ የሚሆኑን፡፡ 

ወደ ርእሰ ጉዳዬ ከመግባቴ በፊት የጊዜያት ባለቤት የዘመናት ጌታ ጋሼ መሥፍንን በሕይወት አቈይቶ ለ90 ዓመታቸው የልደት በዓል ስላደረሳቸው የተሰማኝን ደስታ ለልዑል እግዚአብሔር በምስጋና እገልጻለሁ፡፡ የኚህን ታላቅ ኢትዮጵያዊ የፈሪሃ እግዚአብሔር መንፈስ፣ ሕዝባዊ መምህርነትና ምሁርነት፣ ሰብአዊነት፣ ለጭቈና እና ጨቋኝ አልበገርም ባይነት፣ ለሕግ የበላይነትና ለፍትሕ ተቈርቋሪነት፣ ለዕውቀት መጠማትና ለእውነት ማደር፣ ጠያቂ/መርማሪ አእምሮ፣ከቁም ነገር የዋለ ሕይወት፣ ለኢትዮጵያና ሕዝቧ የሚመኙላት መንግሥተ ሕዝብ ÷ ዕድገትና ልማት፣ ትንሹን ትልቁን ለማንበብና ለማዳመጥ ያላቸው ትዕግሥት፣ ባጠቃላይ የመንፈስ ጥንካሬ አምላከ ኢትዮጵያ በትውልዱ ላይ እጥፍ ድርብ አድርጎ እንዲያሳድር ጸሎቴና ምኞቴ ነው፡፡ በዚህ ዓለም ያለ ሰው እንከን የለሽ ባይሆንም ኢትዮጵያ በጋሼ መሥፍንና እሳቸውን በመሰሉ ዋኖቻችን በኩል ሥጋ ለብሳ ትታየኛለች፡፡ ከተትረፈረፈው ጸጋው አድሎ አሁንም ጤንነት ያለበት ረጅም ዕድሜ ይስጥልን፡፡ 

አሁን ወደ መልእክቴ ልግባ፡፡ ኢትዮጵያ የገጠማት አገዛዝ በአሁኑ ጊዜ የሁሉ ሥጋት ከሆነው ቸነፈር የከፋ መሆኑን በቅርቡ ባቀረብኩት አስተያየት ለማሳየት ሞክሬአለሁ፡፡

https://www.ethioreference.com/archives/22073፡፡

ወያኔ ሕወሓት ወይም ፍጡሩ ኢሕአዴግ (ብልጽግና) የሚባለው አገዛዝ የእሪያና የከልብ ባህርያት የተዋሐዱት ነው፡፡ ታጥቦ ጭቃና ወደ ትፋቱ የሚመለስ፡፡ ዕንቊ ታሪካችንን፣ ዕንቊ ሃይማኖታችንን፣ ዕንቊ ባህላችንን፣ ዕንቊ ቅርሳችንን፣ ዕንቊ ትውፊታችንን፣ ዕንቊ እሤቶቻችንን፣ ዕንቊ ሀገር በቀል ዕውቀትና ሀብታችንን በእሪያ ፊት ማኖር የለብንም፡፡ ማቆሸሽ ብቻ ሳይሆን ያጠፋብናል፡፡ በማጥፋትም ሳይወሰን ለባዕዳን አሳልፎ ከመስጠት ወደኋላ አይልም፡፡ ለሦስት ዐሥርታት በዚህ ጥፋት የተጠመደ አገዛዝ መሆኑን አሳይቶናል፡፡ ወደ ትፋቱ የሚመለስ መሆኑንም በኦነጋዊው ኦሕዴድ በኩል ከበቂ በላይ አሳይቶናል፡፡ ከመምህሩ ደቀመዝሙሩ እንዲሉ የ27 ዓመታቱን ጥፋት አዲሶቹ ተረኞች አል’ቀው (ጠብቆ የሚነበብ) አግዝፈው በሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ‹ክብረ ወሰኑን› ሰብረዋል፡፡ ወደ ትፋት ዘረኝነት፣ ወደ ትፋት ንቅዘት/ሙስና፣ ወደ ትፋት ሰብአዊ መብቶች ጥሰት፣ ወደ ትፋት ግድያ፣ ወደ ትፋት እስር፣ ወደ ትፋት ማፈናቀል፣ ወደ ትፋት ሰላማዊ ሕዝብን ማሸበር፣ ወደ ትፋት ማንአለብኝነት፣ ወደ ትፋት መሬት ወረራ፣ ወደ ትፋት ሥርዓተ አልበኝነት፣ ወደ ትፋት ባንዳነት ወዘተ. ተመልሰዋል፡፡ ወያኔ/ሕወሓት ወይም ኢሕአዴግ ከሚባል ፍጡሩ እንዲሁም ኦነግ ጋር በየትኛውም መልኩ በኃላፊነት ደረጃ ግንኙነት ያላቸው ቡድኖችና ግለሰቦች እውነተኛ ንስሓ ገብተው በእውነተኛ የዕርቅና ይቅርታ ሥርዓት ውስጥ ማለፍ የሚገባቸው የበደሉትን ክሰው የቀሙትን መልሰው፤ ገሚሶቹም በፍርድ ተጠይቀው፣ ቅጣታቸውን አገልግለው፣  ፍትሕ እስኪገኝ ድረስ በኢትዮጵያ ውስጥ በየትኛውም ደረጃ ያለ ሕዝባዊ እና ፖለቲካዊ የአስተዳደር ሥራ ውስጥ እንዳይሳተፉ እገዳ ማድረግ ተገቢ ነው የሚል ጽኑ እምነት አለኝ፡፡ 

አሁን ደግሞ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ያግዛል በሚል በሕዝብ ግፊት የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ ለተልካሻ ፖለቲካ ዓላማቸው ሲጠቀሙበት እያስተዋልን ነው፡፡ ወደ ቀደመ ግብራቸው/ትፋታቸው ሲመለሱ እያየን ነው፡፡ አገዛዙ የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅን በጉልበት የያዘውን ሥልጣን ማስቀጠያ፣ ይቀናቀኑኛል የሚላቸውን ማሳደጃ፣ ሕዝብን ማስለቀሻ፣ ታሪክን የማጥፋትና የሕዝብን አትኩሮት የሚያናጥቡ ድርጊቶች መፈጸሚያ፣ እንደ ተናካሽ ውሻ በሚያሠማራቸው የሕዝብ ያልሆኑ የጸጥታ ኃይሎች ሕዝብን ለማሸበርና ለማስፈራራት እና ለሰብአዊ መብት ረገጣ ነፃ ፈቃድ አድርጎ እየተጠቀመበት ይገኛል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ወራዳና አሳፋሪ ተግባራት እየፈጸሙ ጊዜው ስለወረርሽኙ ብቻ የምናስብበት ነው በሚል የሕዝብን ድምጽና አስተያየት ጸጥ ለማድረግ ሲሯሯጡ ይታያሉ፡፡ ቸነፈሩ የቅድሚያ ጉዳያችን እንደሆነ ብናውቅም ጊዜያዊ ነው፡፡ ያልፋል፡፡ ሕዝብም የሚጠበቅበትን አገዛዙም ሕዝብን መተናኰሉን አቁሞ የድርሻውን ከተወጣ ያልፋል፡፡ ሆኖም 24 ሰዓት ስለ ወረርሽኙ ስናስብ ስናወራ አንገኝም፡፡ 

አገዛዙን ከሥር ከሥሩ እየተከታተልን የሚፈጽማቸውን ዘለቄታዊ ጥፋቶች እናጋልጣለን፣ እናወግዛለን፣ እንዲያቆምም እንጮኻለን፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አገዛዙ የሚፈጽማቸው የአገርና የሕዝብን ብሔራዊ ጥቅሞች የሚጎዱ ድርጊቶች ወይም በቸልታ/በአስደንጋጭ ዝምታ የሚታለፉ ጉዳዮችን (የልጃገረዶቹን/ተማሪዎቹን እስከ የሌለው ዕገታ) ማንሳት የዕለት ተዕለት ጉዳያችን እንጂ ወረርሽኙ እስኪያልፍ ብለን ቀጠሮ የምንሰጠው ጉዳይ አይደለም፡፡ የማይጠገን ጉዳት ከደረሰ በኋላ ከንቱ ጩኸት መጮኽ አንፈልግም፡፡ ሰብል በአንበጣ ተመትቶ የረሃብ ወሬ አለ፤ የተለያዩ ደዌያት መግባታቸው በደበቡ ክፍለ ሀገር ይሰማል፡፡ አገዛዙ ነውሩን በወረርሽኙ ለመሸፈን ከሚሞክር እነዚህን አደጋዎች ለመቋቋም ምን እያደረገ ነው? 

ስለሆነም ወገኔ በማስረጃ የምታነጥረውና የምትደግፈው መረጃና ሐቅ ከያዝክ ወደ ኋላ እንዳትል፡፡ እንደ ፍልፈል አገር የሚቦረቡረውን አገዛዝ በዓይነ ቊራኛ ተከታተል፡፡ ይህ ጥሪ ሕዝባዊ ወገንተኝነት ላላችሁና የኢትዮጵያ ህልውና የሚያሳስባችሁ መደበኛም ሆነ ማኅበራዊ ብዙኀን መገናኛዎችን ይመለከታል፡፡ 

ዛሬ ኢትዮጵያና ሕዝቧ ራሳቸውን ኢሕአዴግ ከሚባል የአገዛዝ ‹ቫይረስ› ለመከላከል ደግመው ደጋግመው ነፃነት÷ እኩልነት፣ አብሮነት፣ የሕግ የበላይነት፣ ማኅበራዊ ፍትሕ በሚባል ‹ሳሙና› ምድሪቱን ማጠብ/ማፅዳት ይኖርባቸዋል፡፡ ይህንን ሠላሳ ዓመታት ያስቈጠረ አገራዊ እድፍ ሙልጭ አድርገን አጥበን ማስወገድ ያለብን፡፡ ሕዝባችን ማኅበራዊ ርቀትም መጠበቅ ያለበት ከወረርሽኙ ከከፋው ከዚህ ‹ቫይረስ› ነው፡፡ ለዘላለሙም ቀሳ መውጣት ያለበት አገራዊ ሕማም የሆነብን  የኢትዮጵያ ሕዝብ እርስ በርሱ እንዳይገናኝና አብሮነቱ እንዲጠፋ የእሾህ አጥር አጥሮ ‹ክልል› በተባለ ማግለያ ውስጥ ለ30 ዓመታት እንዲኖር ያደረገው አገዛዝ ነው፡፡ ለብቻው ተገልሎ/ተከልሎ መቀመጥ ያለበት በጽኑ ደዌ የተያዘው አገዛዙ እንጂ ሕዝብ ሊሆን አይገባም፡፡

Filed in: Amharic