>

“ጅል አይሙት እንዲያጫውት....” (እንግዳ ታደሰ)

“ጅል አይሙት እንዲያጫውት….”

 

 

እንግዳ ታደሰ

 

 

የሰሞኑን የአንበሳና፥ የጣዎስ እንካሰላንትያን ጉዳይ በአንክሮ ስከታተለው ነበር የከረምኩት። ወንዱ ጣኦስ ነው እንደ ርችት ከለር የሚቀያይረው የሚለውን ግኝትና አንበሳም ቢሆን ነጥቆ በላተኛ ነው ለምን እሱ ይመረጣል? የሚለው ካድሬያዊ ክርክር ውስጥ መግባት አልፈልግሁም ። ችግሩ የመጣው ከህወሃታዊ አስተምህሮት በመሆኑ ነው።

አንበሳ የአማራ ነው ፣ የአሃዳዊ ምልክትም ነው ተብሎ በተፈበረከው ህወሃታዊ ተረት፣ ኦሮሞውም ፥ ደቡብም አንበሳን የአማራ አድርጎ እንዲያምን በኢህአደጋዊ ቅስቀሳ ስለተበየደ አንበሳ ቢያስቃዠው አይገርምም።

በነገራችን ላይ የትግራይ ህዝብ በአንበሳ ምልክትነት የሚታማ አይደለም ። የህወሃት መጫወቻ ካርድ እንደሆነች ያውቃል። የንጉሰ ነገስት ዮሃንስ ንግስና ውስጥ አንበሳውም ቦታ ነበረውና ነው።

ባለፈው ታህሳስ ወር ጠቅላይ ሚንስቴር አብይ ኦስሎ ብቅ ብለው የኖቤል ሽልማታቸውን በወሰዱበት ጊዜ በማግስቱ፣ የኖርዌይን ፓርላማ ጎብኝተው ሲወጡ እግር ጥሎኝ ፎቶ አንስቻቸው ነበር። ኖርዌይ የምትታወቀው በተለይ በግዙፉ ነጭ ድቧ ቢሆንም ! ፓርላማዋ መግቢያ ላይ ግን የደቀነችው ግዙፉን አንበሳ ነው። የንጉሰ ነገስቱም አርማ ላይ ዘውዱን በግራና በቀኝ የተሸከሙት ሁለት አንበሶች ናቸው ።

ታድያ ይህን አንበሳ ታከው ሲያልፉ ነበር ጠቅላይ ሚንስቴር አብይን በካሜራዬ ያገኘኋቸው ። ጨዋታን ጨዋታ ያነሳዋልና ፣ የዚህ አንበሳ ቀራጭ’ ሰው ታሪክ ስቦኝ ነው ታሪኩን ከአንበሳና ጣኦስ በማዛመድ ላካፍላችሁ የፈለግሁት። Gulbrand Eriksen ይባላል የቀራጩ ስም ። ጉልብራን በፎርጅድ ገንዘብ ሰሪነት ከአንድ ጓደኛው ጋር ተሳትፎ ስለተነቃባቸው በስተመጨረሻ ጓደኛው ለፖሊስ ሊያጋልጠው ሲሞክር በጓደኛው ድርጊት ጉልብራን በመበሳጨት በጩቤ 13 ጊዜ ጨቅጭቆ ጓደኛውን በመግደልና በመጨረሻም የጓደኛውን አንገት በመቁረጥ ጭካኒያዊ ድርጊቱ የተነሳ ሞት ይፈረድበታል ።

ጉልብራን የሞት ፍርዱ እስኪጸናበት ድረስ በከባድ የጉልበት ስራና እስር ላይ ሳለ የሃውልት ስራ ትምህርት በስር ቤቱ ውስጥ ይማራል። በአገኘውም እውቀት ይህን አንበሳ ይቀርጻል። ለፓርላማውም በ1865 ዓም ያበረክታል። በዚህ አንበሳ የተነሳ ከሞት ፍርድ ወደ እስር ማቅለያ ገብቶ ይፈታል። ወደ አሜሪካም ተሰዶ ቺካጎ ውስጥ በ1888 ያርፋል። በህወሃት ትርክት ተወልደው የጎለመሱት የአገራችን ብሄር ብሄረሰቦች አዲስ ትውልዶች ደግሞ የምኒሊክ ድኩላ የተባለውን እንስሳ ገድለው ሲጨርሱ አንበሳንም እንዲሁ ለምን እናያለን እያሉ ነው። ጅል አይሙት እንዲያጫውት አበው እንዲሉ !

Filed in: Amharic