>
10:27 am - Wednesday December 7, 2022

የአንድ ልቦለድ አይታመኔ ገጸ ባህርይ የሚከስት ደራሲ…! (አሰፋ ሀይሉ)

የአንድ ልቦለድ አይታመኔ ገጸ ባህርይ የሚከስት ደራሲ…!

አሰፋ ሀይሉ
ደራሲ አውግቸው ተረፈ (በእውነተኛ ስሙ ኅሩይ ሚናስ)
አ‘አንዲት ጠባብ ክፍል ውስጥ ገባሁ፤ እንደ ሳሎን ጠረጴዛ ከአንድ ወንበር ጋር፣ ቴሌቭዥንና ሣጥን፣ እንደ መኝታ ቤት አልጋ፣ እንዲሁም እንደ ማብሰያ ማንደጃ ይዛለች፤ እንደ ሁሉም ታገለግላለች፤ የቀበሌ ናትና በወር ዘጠኝ ብር ይከፈልባታል::
አንጋፋው ደራሲና ተርጓሚ በብቸኛው የእንጨት ወንበር ላይ ተቀምጦ ጠረጴዛውን ተደግፎ ዛሬም በአርትኦት ሥራው ላይ ተጥዷል፤ ለቤቷ ሞገስና ድምቀት ሆኗታል፤ ቤቷ ለሠውየው ፈጽሞ ባትመጥንም እውቀት፣ ጥበብና ትጋት ሰርክ ይፈስባታል::
ወደ ቤት ስገባ ደራሲው ሊቀበለኝ ከመቀመጫው ሲነሳ ቤቷን የሞላት መሰለኝ::’
አውግቸው፣ [ይኼ የብዕር ስሙ ነው፤ ትክክለኛ ስሙ ኅሩይ ሚናስ ነው] ከጎጃም /ደጀን/ መጥቶ አንድን ዓይነ ስውር ለማኝ እየመራ፣ በልመና ከተገኘው ገቢ ትንሽ ትንሽ እየተካፈለ፣ ከ18 ዓመቱ ጀምሮ ጋዜጣና የጸሎት መጻሕፍት በየጎዳናው እያዞረ፣ መርካቶ ገብቶም መጽሐፍ ይሸጥ የነበረ ሰው ነው::
 ኢሕአዴግ ሲገባ ደግሞ በ‘አብዮታዊ ዲሞክራሲ’ ጋዜጣ እና በአንዳንድ መጽሔቶች ላይ ሥራዎቹ የሚነበቡለት ሰው ሆነ:: ከዚያም በሕመምና በመሳሰሉት ምክንያቶች ሥራውን ለቀቀ:: ቀጥሎም ወደ አሮጌ መጽሐፍ መሸጥ ሥራው ተመለሰ – መንገድ ላይ ዘርግቶ – ፀሐይና ብርድ እየተፈራረቀበት:: ይኼኛውን ዘመን ደርሼበታለሁ፤ ደንበኛዬ ነበር፤ ትውውቃችን የተመሰረተውም እዚሁ ነው – ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ጀርባ – ከጀርባው በር ፊት ለፊት:: አሁን ግን ሥራውን ትቶታል::
 አውግቸው፣ በ1950ዎቹ እህል እየለመነ፣ የለመነውን እየሸጠ መኖር ቀጠለ:: ገንዘቡን ግን ሳይበትን ማጠራቀም ቀጠለ:: ከዚያም ልሳኑ የሚባል አንድ ጓደኛው፣ “ለምን አዲስ አበባ አንሄድም?” ይለዋል:: አውግቸው አልተቸገረም:: ሃሳቡን ወድዶታል:: መሳፈርያም ቢሆን አጠራቅሟል::
ምጣ፣ የአዲስ አበባን ምድር ረገጠ:: ቀጨኔ መድሃኔአለም ት/ቤት ገባ:: በዘመኑ አንድ ድርጅት ነበር -ባህላዊ የሆነውን ትምህርት ለሚከተሉ ተማሪዎች እለታዊ መዋጮ የሚሸፍን፣ በወር ሶስት ብር እየሰጠ:: እናም አውግቸው የዚህ እድል ተቋዳሽ ሆነ::
 ይህች ብር፣ ተጠራቅማ ተጠረቃቅማ 21 ብር ሞላች:: ገንዘቡን በእጄ ብይዘው ይጠፋብኛል ብሎም በምስጋቱ ለጓደኛው ቀላድቀው ለሚባል ለእሱ ነበር የሚሰጠው:: ሃያ አንድ ብር በሞላለት ጊዜ፣ ያንን ብር ፈልጌው ነበር ይለዋል:: ጓደኛው ግን በአውግቸው ጥያቄ ተደናገጠ:: መቼ የሰጠኸኝን አለው:: ካደ:: አውግቸው ተናደደ:: መክዳቱ ብቻ አይደለም ገንዘቡን በእጁ ሳያስገባ፣ ክህደት የፈፀመው ሰው ወደ ደጀን ሊመለስ መሆኑን ሰማ:: ተከትሎት ሄደ::
 ወደገባበት ገባ:: አንድ መሪጌታ ተጠግቶ ትምህርቱን መከታተል ያዘ – ጓደኛው አውግቸው የደረሰበትን በደል ሲናገር የሰሙ ተማሪዎችም ክሰሰው ይሉታል፣ ለየኔታ ተናገር ብለው ይወተውቱታል:: ምክራቸውን ሰማ:: የኔታ ፊት ቀረበ:: የጌታ ተከሣሹን ጠርተው ሲጠይቁት ዓይኔን ግንባር ያድርገው ብሎ ካደ:: ማል አሉት ማለ:: አላየሁም አለ:: ጉዳዩ በዚሁ ተቋጨ::
 ከጥቂት ጊዜያት በኋላ፣ ከሳሽና ተከሣሽ ሌላ ቦታ ተገናኙ:: ተከሣሽ ህሩይ ‹‹እንካ ባለፈው የወሰድኩብህን ብር›› ብሎ ሃያ አንድ ብር ከፊቱ ቆጠረ:: ‹‹ለምን ያኔ ስፈልገው ካድከኝ?›› ብሎ ይጠይቀዋል::
“በሆነ ነገር አናደኸኝ ስለነበር ነው” ይለዋል “እንካ አሁን ብሩን…
“አልፈልገውም፤ ይዘህ ሂድ”
“ያንተኮ ነው”
“ቢሆንም፤ አልሰጠኝም ብለህ ምለካል:: እኔ ደግሞ የተማለበትን አልፈልግም”
ጓደኛው ግራ ገባው “ለምን…”
“አልፈልግም ይዘኸው ሂድ፤ የተማለበት ገንዘብ ወስጄ እንድቀሰፍልህ ትፈልግ ኖሯል፤…” አለው፤ ተለያዩ፤ ጥቂት ጊዜያት ያህል በየዘመድ፣ በየደብሩ ሲንከራተት ቆይቶ ወደ አዲስ አበባ መጣ:: እንደመጣ ያኔ ወማሚያውቁት ቀጨኔ መድኃኔዓለም አቀና:: ግና አልቆየም፤ ደብር ቀየረ፤ ወደ አራት ኪሎ ወረደ፤ ወደ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን አመራ::
 መማር ጀምሮ ነበር – ቅዳሴ:: ግና በትምርቱ አልተጋ አለ:: ያዝ ለቀቅ ማድረግ አበዛ:: በዚህም የተነሣ ከዓመት ቆይታ በኋላ ከትምርት ገበታው ተባረረ:: በረንዳ አዳሪ ሆነ:: ከእሱ ጋር የተባረረ ሌላ ጓደኛም ነበረው፡ አንድ ላይ ሆኑና በረንዳ አዳሪነተውን ገፉበት:: አላፊ አግዳሚውን “ራበን” እያሉ፣ እየተመፀወቱ ቀጠሉ::
 አንድ ቀን ተክለሃይማኖት አካባቢ አንድ ዓይነስውር አገኘ፤ ዓይነስውሩ ለማኝ ናቸው፤ ሰው የላቸውም፤ መንገድ ጠቋሚ፡ በረዳትነት ልቅጠርህ አሉት፤ ቀጠሩት:: እሳቸውን ይዞ በየጉራንጉሩ ይዞራል፤ ይገባል፣ ይወጣል፡ ማታ – በተመጽዋችነት ካገኙት ብር የተወሰነ ድርሻ ይሰጠዋል:: ሁለት ዓመት ሰራ::
 ቆይቶ ደግሞ ሌላ አይነስውር አገኘ:: እኝህ ደግሞ የተወቁ ናቸው:: ድምጻቸው በሬዲዮ የሚሰማ:: አለቃ ነብዩ ነው ስማቸው፡ የምስራች ድምጽ በመባል የሚታወቅ ከአንድ የሬዲዮ ፕሮግራም መንፈሳዊ ትምህርት ያስተምራሉ:: የአውግቸው ሥራ የሚፈልጉትን መጽሐፍ እየገለጠ ማንበብ፣ መጻፍ እና መንገድ መምራት ነው:: በወር አስራ ሁለት ብር ይከፈልሃል ተባለ፡ እሺ አለ በደስታ፡ ሃላፊነቱን ተቀበለ፡ ደግሞም – በኋላ ላይ ተፈጻሚ ባይሆንም-ዘመናዊ ት/ቤት አስገባሃለሁ አሉት::
የባልዛክን ‘ምስኪኗ ከበርቴ’፣ የዳንኤላ ስቲልን ‘ጽኑ ፍቅር’፣ የሃሮልድ ሮቢንስን ‘ባይተዋር’ እና ‘ጩቤው’ የተሰኙትን ሥራዎች የተረጎመልን፤ በተለያዩ የብዕር ስሞቹ ዲክሽነሪ ያዘጋጀልን፣ የሕፃናት ተረቶችን አዛምዶ የተረጐመልን አውግቸው አሁን በማይመጥነው ሁኔታ፣ እንደተረሳና እንደተጣለ እቃ ተዘንግቶ አለ:: ያኔ – ባለቤቱ አራስ በነበረች ጊዜ – አልሸጥ፣ አልጠየቅ እንዳሉት ተወዳጅ ዘመን አይሽሬ መጻሕፍት::
 በእሱ ሰበብ ሥራ የጀመሩ አሉ፤ እኔ ሦስት ሰዎች አውቃለሁ፤ ሁለቱ አሁን ለ ‘ደጅ አዝማችነት’ ማዕረግ እየበቁ ነው፤ አንዱ ዓይናለም መዋ ነው፤ የሥጋ ዘመዱ፣ ከገጠር ሲመጣ ተጠግቶት የኖረና፣ እሱጋ የተማረ:: ታዋቂ ደራስያንና ከያንያን አውግቸው ቤት ሲመጡ ስኳር፣ ሻይ ቅጠል፣ ሲጋራ እና የመሳሰሉት ነገሮች ይላላክላቸው የነበረ:: ሁለተኛው ጃዕፈር ሺፋ ነው፤ አውቶቡስ ተራ መሣለሚያ አካባቢ በሚኖርበት ጊዜ እጅጉን የሚቀራረቡ ጐረቤታሞች ነበሩ፤ የጃዕፈር እናት ናት – የአውግቸውን ቤት አንኳኩታ፣ ‘ልጄን ሙያ አስተምርልኝ፤ አንተ የምትሠራውን ዓይነት ሥራ ሠርቶ እራሱን ይቻልልኝ፤ ሥራ ወዳድ ስለሆነ አንዴ መንገዱን ካሳየኸው አያስቸግርህም’ ብላ እጁን ይዛ በአደራ የሰጠችው:: ሦስተኛው ሰው የበኩር ልጁ ነው – ተሾመ ኅሩይ:: ተሾመ ለሰባት ዓመታት ይህንን ሲሠራ ቆየና፣ ቦታው አልመች ብሎት ሥራውን ቀየረ:: የሞባይል አክሰሰሪዎች መሸጫ አደረገ መተዳደሪያውን::
 አውግቸው ተረጋግቶ ሥራውን እንዳይሠራ ያደረገው የደረሰበት የአእምሮ ሕመም ነው፤ የበሽታው ምንጭ ምን እንደሆነ ብዙ ጊዜ ግራ ይገባዋል፤ እናም እንዲህ ይላል::
 ‘እኔ እንደሚመስለኝ ከ1972 እስከ 1974 ዓ.ም ድረስ በቀን በቀን ጫት እየቃምኩ ከጠዋት አንስቶ እስከማታ የፔንጉን ሞደርን ክላሲክስ መጽሐፎችን ከማንበቤ እና በዚህ ወቅት ሳላቋርጥ እበሳጭና እንቅልፍ አጣ ስለነበርኩ ይሆናል እላለሁ:: እንቅልፍ ማጣት፣ ብዙ ማንበብና የገንዘብ እጦት ለእብደት ዳርጐኝ ይሆናል ብዬ አስባለሁ::
 ምናልባትም በእነዚህ ሦስት ዓመታት ባዶ ቤት ውስጥ ብቻዬን ያለ አንድ አነጋጋሪ በመኖሬ ሊሆንም ይችላል:: ወይም የወደፊት እጣ ፈንታዬን በማሰብ አንዱንም ሳልይዘው ባዶ ሜዳ ላይ መና መቅረቴን እያሰላሰልኩ ብዙ ጊዜ በመቆዘሜ ሊሆን ይችላል::”
 በአንድ ወቅት የትኛው ሚስቱ እንደሆነች አላውቅም እንጂ አራስ በነበረች ጊዜ የሚከተለውን ህይወት እንዳሳለፈ አጫውቶኛል:: በሸገር ኤፍ.ኤም 102.1 የጨዋታ ፕሮግራም ላይ ተጋብዞ ለመዓዛ ብሩ ሲነግራትም አድምጠናል፤ በደርግ ዘመን ነው፤ መጻሕፍት በመሸጥ በሚተዳደርበት ጊዜ አንድ ቀን እንዲህ ኖረ:: ያ ቀን ደግሞ ምንም መጽሐፍ ሳይሸጥ ጀንበር ስለጠለቀችበት ልቡ ውስጥ ሃዘን አጥልቶ ነበር::
 የሚይዛቸው መጻሕፍት እሱ ሊያነባቸው የሚፈልጋቸው ዓይነቶች – የጀርመን፣ የእንግሊዝ፣ የአሜሪካ እና የራሽያ ዘመን አይሽሬ ልቦለዶች ናቸው እንጂ ሕዝብ ተሻምቶ የሚገዛቸው አልነበሩም::
ግራ ገባው፤ በሚጠሩለት ዋጋ (በኪሣራም ቢሆን) ለመሸጥ ዝግጁ ቢሆንም፣ እንዳለመታደል ሆኖ ጠያቂ አጣ:: ከነጋ እህል በአፉ አልዞረም:: ያሳሰበው ግን የእሱ መራብ አይደለም፤ ‘ተፈተንኩ’ አለ፤ ‘ለአራስ ባለቤቴ ምን ይዤ ልግባ? ምን ይዤ?’
 መጽሐፎቹን አግባብቶ ለመሸጥ ያደረገው ሙከራ ከንቱ ሆነበት፤ ደግሞ ከመምሸት አልፎ ጨለመ፤ ዞር ብሎ የሚያየው አጣ፤ ጨነቀው፤ በመጨረሻም አንድ የመፍትሔ ሃሳብ መጣለት:: አንድ ጠጅ ቤት ገባ፤ ገብቶም ለአስተናጋጁ የሆነውን አስተዛዝኖ ነገረው:: አስተናጋጁ አውግቸውን ሰምቶ ሲጨርስ ወደ ጓዳ ዘልቆ በፌስታል የሆነ ነገር ይዞ መጣ:: አውግቸው – ደራሲና ተርጓሚው – አሮጌ መጻሕፍት ሻጩ አውግቸው – የያዘውን ይዞ፤ ወደ አራስ ባለቤቱ ገሰገሰ::
 ባለቤቱ ተኝታ ነበር፤ እስክትነቃ ጠበቀ፤ ነቃች፤ ፌስታሉን ሰጣት፤ ርቧታል፤ ለመብላት ተቻኩላ ነበር፤ ፌስታሉን ከፈተችው፤ በውስጡ ያለውን ነገር ስታይ ግን ደነገጠች – “ምንድነው ይኼ?” አለችው፤ ነገራት፤ ቀኑን ሙሉ አንድም መጽሐፍ እንዳልተሸጠለትና፣ ፆሟን እንዳታድር ብሎ፣ ጠጅ ቤት ገብቶ ከተመጋቢ የተረፈ እህል ለምኖላት እንደመጣ …
“ትርፍራፊማ አልበላም” አለችና ባዶ ሆዷን ጥቅልል ብላ ተኛች፤ እሱም አልበላልህ አለው፤ ፍላጐቷን ማሟላት ባለመቻሉ ሃዘን ገባውና ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ::
 ጽፈነው የማያልቅብን፣ አውግተነው የሚተርፍብን ዓይነት ሰው ነው – አውግቸው ተረፈ::
 አውግቸው አሁን ደህና ነው፤ ደህና ነው ማለቴ ከምንም ዓይነት በሽታ ሙሉ በሙሉ ጸድቷል ማለቴ አይደለም፤ ከአዕምሮ ህመም ከዳነ አስራ ስምንት ዓመታት አልፎታል፤ መድሃኒቱን አጥብቆ እየተከታተለ ነውና ከአዕምሮ መታወክ ነፃ ወጥቷል፤ እንደ በፊቱ እንግዳ የሆነ ነገር በመናገር ወይም በማድረግ፣ ዙሪያው ያሉትን ሰዎች አያስደነግጥም፤ አሁን ደህና ነው፤ እራስን ስለማጥፋት አያስብም፤ በዕጣ የደረሰውን ባለ አንድ መኝታ ክፍል ኮንደሚኒየም ቤት መንግሥት መልሶ እንዲወስድበትና በምትኩ ጠበብ ያለ ክፍል እንዲሰጠው ያደረበት ምኞት አሁን ትቶታል፤ ዕድሜ ለሸገር ኤፍ ኤም 102.1 ፕሮግራም አዘጋጅ፣ እድሜ ለመዓዛ ብሩ፣ ሕይወቱን የሚናገር ፕሮግራም በ ‘ጨዋታ’ ዝግጅት ክፍሏ ካስተላለፈች በኋላ ጋዜጠኛው ሳምሶን ማሞ ብር ሃያ ሺህ ብር፣ ድምጻዊው ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) ብር አስራ አምስት ሺህ ብር፣ አበርክተውለት ዕዳውን ቀንሰው አውግቸው ተረፈን ባለ ቤት አድርገውታል፡፡
አሁን ደህና ነው፤ በእርግጥ ያለምክንያት የመፍራት፣ አለቅጥ የመደንገጥ መንፈስ ከሁለንተናው ቢርቅም፣ ጤንነቱ ግን የተረጋጋ አይደለም፤ በአንድ ወቅት የእንቅልፍ መድኃኒት ተብሎ በሃኪም የተሰጠው መድኃኒት የሌላ ህመም ክኒን ሆነና እግርና ወገቡን ለሚያሸማቅቅ በሽታ ዳረገው፤ በዚህ የተነሣ በእግሩ ርቆ መጓዝ አይሆንለትም፤ አንገቱን የሚያዞረው ተጠንቅቆ ነው፤ አንገቱን ማዘዝ አይችልም፤ አሁን ከባለቤቱ ጋር ነው ያለው፤ እንዲህ ይተርክልናል የቀደመ ሕይወቱን::
 “መጀመሪያ ከባሴ ሃብቴ ጋር ነበር የምኖረው፤ ሁለታችን አንድ ቤት ውስጥ በምንኖርበት ጊዜ በማንበብ፣ በመድረስና በመተርጎም ነበር ጊዜያችንን የምናጠፋው፤ በዚህ ዘመን ነው – የዩኒቨርስቲ ትምህርቴን ያቋረጥኩት፤ ትምህርቴን ያቋረጥኩት በ1970 ዓ.ም አብረውኝ ይማሩ የነበሩ የኢሕአፓ አባላት “እኛ እየታገልን አንተ እንዴት አንተ ትምህርትህን ትማራለህ?” ብለውኝ ነው::
 እኔም፣ “ትግሉ ተመትቷል፤ መዋቅሩ ሁሉ ፈርሷል፤ ኢሕአፓ የሚለው ስም ሁሉ በ1969 ዓ.ም ከስሟል፤ ከማን ጋር ነው የምታገለው?” ስላቸው፤ “እምቢ ካልክ እርምጃ እንወስድብሃለን” ብለው አስፈራሩኝ፤ እኔም ፈራኋቸውና ትምህርቴን ትቼ፣ ከእነሱ ጋር ወግኜ፣ የቅስቀሳና የተቃውሞ ጽሑፍ እበትን ጀመር፤ ባሴም ኢህአፓ ነበር፤ ጓደኞቹ ሲታሰሩ፣ አንዳንዶቹ ሲገደሉና ሲሰደዱ፤ እሱ እኔ ዘንድ ተደበቀ:: ከጎፋ ሰፈር ተነስቶ አውቶቡስ ተራ መሣለሚያ መጣ፤ ከዚያ በኋላ ለተወሰኑ ጊዜያት አብረን እየጻፍን፣ እየተወያየን ቀጠልን::
 “በ1970ዎቹ መጀመሪያ ከአቶ ስብሃት ገብረእግዚአብሔር ጋር ተዋወቅን፤ እሱ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ ሥራዬ ‘የካቲት’ መጽሔት ላይ እንዲነበብልኝ ሰጥቶና ልብን የሚያሞቅ አስተያየት ጽፎ ከአንባብያን ጋር ያስተዋወቀኝ፤ ያኔም መጽሐፍ ሻጭ ነበርኩ፤ ‘ወይ አዲስ አበባ’ ግን ዝነኛ አደረገችኝ፤ እራሴን ነው የጻፍኩባት፤ ከጎጃም መጥቼ አዲስ አበባ እስክገባ ስላጋጠሙኝ ፈተናዎች:: ለሁለት ሦስት ዓመት ያህል መጽሐፍ መሸጥ ከቀጠልኩ በኋላ፣ የመጽሐፍ ሽያጭ ሥራ እንደበፊቱ ባለመሆኑ ትካዝና ሃዘን አበዛ ጀመር::
 “ከዚያም ከጋሽ ዳኛቸው ወርቁ ጋር ተዋውቄ ለሥራዬ ጥሩ ግምት ነበራቸውና ኩራዝ አሣታሚ ድርጅት እንድቀጠር አደረጉኝ፤ ያኔ ‘ማሞ ቢጩ’ንና ‘እያስመዘገብኩ ነው’ የተሰኙ ድርሰቶቼ ‘ጉዞው’ በተሰኘ የአጫጭር ልቦለዶች መድበል ውስጥ ተካትተው ታተሙ:: ኩራዝ ውስጥ በአርታኢነት ቀጠልኩ፤ ለሰባት ለስምንት ዓመታት ያህል:: ከዚያ የአዕምሮ በሽታዬ ተነሣና ከሥራ ወጣሁ፤ መጽሐፍ ነጋዴ ጓደኞቼ እነ ክብሩ ክፍሌ አማኑኤል ሆስፒታል ይወስዱኛል፤ እኔ ግን አስቸገርኳቸው፤ ለአስተማሪዎቼም፣ ለአካሚዎቼም የሚመች ባህርይ አልነበረኝም፤ አልታከምም፤ መድኀኒትም አልወስድም ብዬ ከሆስፒታል ወጣሁ::
 “በእብደት ዘመኔ የሆነች የምታናግረኝ መንፈስ ነበረች፤ ለመንፈሷ ነበር የምታዘዘው፤ እኔ ምንም አላውቅም፤ ያለችኝን ሁሉ ከመተግበር ውጪ አልታዘዝም ማለት አልችልም፤ መንፈሷ ‘ማርያም ነኝ’ ብላ እራሷን አስተዋውቃኛለች፤ ይህቺ ማርያም ነኝ የምትለኝ መንፈስ ናት፤ በየመንገዱ እንድሰግድ፣ ጩቤ ይዤ እንድዞር፣ ከጓድ መንግሥቱ ኃይለማርያም ጋር ፍልሚያ የመግጠም ወኔ እንዲያድርብኝ ያደረገችው::
 “ጩቤ ይዤ እዞር የነበረው ያቺ ያደረችብኝ መንፈስ ‘ሰይጣን ሲመጣብህ በዚህ ትቋቋመዋለህ’ ስላለችኝ ነው፤ ቤተመንግሥት ሄጄ ጠባቂዎቹ ፊት ቀርቤ ካልገባሁ ብዬ አስቸገርኳቸው፤ ምን እንደምፈልግ አጥብቀው ጠየቁኝ፤ አለባበሴም፣ አነጋገሬም የጨዋ ስለነበር የውስጥ ስሜቴን መታወክ አላወቁም::
 “ጓድ መንግሥቱ ኃይለማርያምን እፈልጋቸዋለሁ” አልኩ፤ ግራ ገባቸው::
“ምን ሊያደርጉልህ?”
 “ምንም እንዲያደርጉልኝ አልፈልግም፤ በሽጉጥ ፍልሚያ ልግጠማቸውና ማን እንደሚያሸንፍ ይለይልን” አልኩ፤ ሥራዬ ምን እንደሆነና የት እንደምሠራ ጠየቁኝ፤ ደራሲነቴንና የኩራዝ አሣታሚ ድርጅት ተቀጣሪ መሆኔን አስታወቅኋቸው፤ ወደ ቢሮዬ ደወሉ፤ የቢሮዬ ሰዎች ናቸው – አልፎ አልፎ የምትነሳብኝ የአዕምሮ ህመም እንዳለችብኝ የተናገሩት፤ ከዚያም ከአንድ ወታደር አጃቢ ጋር ወደ ክቡር ዘበኛ ላኩኝና ለግማሽ ቀን አሰሩኝ::
 “በደርግ ጊዜ በባህር ዳር በኩል ወደ ሱዳን ለመሰደድ በእግር ጉዞ ጀምሬ ነበር፤ ሽፍቶች ይደበድቡሃል፤ አውሬም ይበላሃል ብለው ነው ከመንገድ ሰዎች የመለሱኝ፤ እኔ ግን መንፈሷ አዛኝ ስለነበር ልሄድ ቆርጬ ነበር፤ ያኔ ‘ወይ አዲስ አበባ’ የምትል መጽሐፌ ታትማለች፤ በዓለም የታወቁ አጫጭር ልቦለድ ደራስያን የጻፏቸውን ሥራዎች ተርጉሜ ‘ያንገት ጌጡ’ በሚል ርዕስ ታትማለች፤ ኪሴ ባዶ አልነበረም፤ ግና የያዝኩት ከአንድ ሺህ ብር በላይ ነበርና አለቀ፤ አለቀብኝና የያዝኩትን ጋቢ ሸጥኩ::
 “ከዚያም ደብረማርቆስ ፖሊስ ጣቢያ ሄጄ፣ ‘የድርጅቴን ገንዘብ ሰርቄ ጠፍቻለሁ፤ አሁን እጄን በፈቃዴ ለመስጠት ነው የመጣሁት፤’ አልኩ፤ ስለራበኝ ነው እንዲህ ያልኩት፤ አስረው እንዲቀልቡኝ፤ ለካስ እነሱም ምግብ የላቸውም፤ ሱሪዬን አውልቄ አስራ አምስት ብር ገደማ ሸጥኩት፤ ፖሊሶቹ ደግሞ አዲስ አበባ ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ቢሮ ደውለው ‘የድርጅታችሁን ገንዘብ የዘረፈው እዚህ ነው’ አሏቸው፤ የሚደሰቱ መስሏቸው:: እነዚያ ግን ‘እሱ ማነው? የምን ስርቆት ነው?’ ሲሉ ቆይተው ‘አቶ ኅሩይ ሚናስ ነው’ ሲሏቸው ጊዜ ‘እሱ ነው? እሱኮ ችግር አለበት’ ብለው አስፈቱኝ፤ የፖሊስ አዛዡ ያውቀኝ ስለነበር ልብስ አልብሶኝ በቢሮው መኪና ወደ አዲስ አበባ ሸኘኝ::
“ይህንን ሁሉ ባላካትትበትም ‘እብዱ’ የምትለው መጽሐፌ (በእብደት ዘመኔ) ስላጋጠሙኝ ነገሮች ትናገራለች፤ አንድ ያልተለመደ ነገር አደርግና በውስጤ ያደረችው መንፈስ ተለይታኝ ስትወጣ በማስታወሻዬ አሰፍረው ነበር፤ ለጓደኞቼ ሳነብላቸው ሳይወዱት ይቀራሉ፤ ካልወደዱት አስቀያሚ ቢሆን ነው እልና ቀድጄ እጥለዋለሁ፤ በኋላ ግን እንደ አዲስ ጻፍኩት:: ብዙ አንባብያን ለምን ጻፍከው? ለምን እራስህን እንዲያ ባለ መልክ ትገልጣለህ? ይሉኛል፤ እኔም ለሌሎች ትምህርት ይሆናል ብዬ፤ ማኅበረሰቡ እብዶችን እንዴት ማገዝ እንዳለበት ያስተምራል ብዬ፣ እላቸዋለሁ፤ እብድ ማለት እኮ ሰይጣን የያዘውና ጋኔን የሰረጸበት ማለት አይደለም፤ እኛ ሀገር እብድ ሲረብሽ፣ አካባቢውን ሲያናውጥ በራሱ ፈቃድ የሚያደርገው ይመስል በአለንጋ ይገርፉታል፤ ቤት ይቆልፉበታል፤ ይዘባበቱበታል፤ ብዙ ያልተገባ ነገር ይፈጽሙበታል፤ ግን ሆስፒታል ሄደው ታክመው እንደሚድኑ እኔ ማሳያ ነኝ::” እያለ ስለ እራሱ ይተርካል::
 እንደ እኔ እንደ እኔ ጋሽ ስብሃት እና ጋሽ አውግቸው ከጻፏቸው ድርሰቶች እኩል ባሕሪያቸው ለአንድ ትልቅ ድርሰት መነሻ የሚሆኑ ሰዎች ናቸው:: ሁለቱም የሚጋሯቸው ባሕርያት አሏቸው፤ ማኅበረሰቡ ተስማምቶ ከሠራው እስር ቤት ለማምለጥ ብዙ ታግለዋል – ተላልጠዋልም:: ወይም የእስር ቤቱን ሕይወት ረስተው እየኖሩበት የሌለ ያህል ቆጥረው ኑሯቸውን ቀጥለዋል:: ስለሌላው ብቻ ሣይሆን ስለራሳቸው በግልጽነትና በነጻነት ተርከውልናል – በሹክሹክታና በአግቦ መናገር በተለመደበት ሀገር::
ስለ አውግቸው ተረፈ
(ሥዩም ተፈራ፣ በኅልፈቱ ማግስት ሰኔ 11/2011 ዓ.ም.)
“ጉድፉን ሳይነቅስ ላደባባይ፣ በጉልምስና ዓመታቶቹ በፊደል ራሱን እየቀረጸ፣ እንዲነበብ አድርጎ በምቹ ከመንደር ይዟት የወጣትን ነፍሱን፣ ማንነቱን ሳያስነካ መጻሕፍት ዓለሙን ያበጃጀ፣ ከእምነቱ ጋር እያቦካ ሲንቦጨራቅ ሲያንቦጫርቅ ያልራሰ፣ ከተሜን በገጠርነት የለካ ያላነበበውን ገጽ ዛሬም ሊያነብ፣ ሞት እንዲህም እንደሚቻል የሆነውን ከእብደትም ጨልፏል፣ ከሄደበትም አንዳች ይላል እርግጥ በፊደል ከቀረጻቸው ማንነቱ ይልቅ፣ በኑሮው ብዙውን ብሎናል::”
ደራሲ አውግቸው ተረፈ (ኅሩይ ሚናስ) በተወለደ በ68 ዓመቱ ሰኔ 10/2011 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ፡፡
(‹ማስታወሻ፡– ይህ መጣጥፍ እንዳለጌታ ከበደ ከጻፈው ‹ማዕቀብ› ከተሰኘው መጽሐፉ የተወሰደ ሲሆን፣መጽሐፉ በ2006 ዓ.ም የታተመ ነው::›
የጽሑፉ ምንጭ፣ በታዛ መጽሔት፣ ህዳር 8፣ 2012 ዓ.ም. የኦንላይን ፖስት ላይ የተገኘ፡፡)
የደራሲውን ነፍስ ይማር፡፡
የከበረ ምስጋና ለእንዳለጌታ ከበደ፡፡
መልካም ጊዜ፡፡
Filed in: Amharic