>

ከኮሮና ወጣ ያለ አስደንጋጭና አሣዛኝ የተረኝነት ... (ግርማ በላይ)

ከኮሮና ወጣ ያለ አስደንጋጭና አሣዛኝ የተረኝነት …

 

 

ግርማ በላይ

 

 

በታከለ ኡማ አስተዳደር  የተማመኑ የአክራሪ ኦሮሞዎች ጀብድ ይህን ይመስላል፡፡

 

ሥፍራው አዲስ አበባ ውስጥ ለቡ በሚባለው አካባቢ ነው፡፡ በዚያ አካባቢ አብርሃሙ ሥላሤ የሚባል ቤተ ክርስቲያን አለ፡፡ በዚያ ቤተ ክርስቲያን ዙሪያ የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ የነበሩ ነባር ባለይዞታዎች ከአምስትና ስድስት አይበልጡም፡፡ እነሱም ግምት ተሰጥቷቸው ወደ ሌላ ቦታ ሊሄዱ ነበር፡፡ ምክንያቱም የቤተ ክርስቲያኑ ይዞታ እንደተጠበቀ ሆኖ ቀሪው የተለያዩና እጅግ በርካታ ዛፎች ስለነበሩበት ለመናፈሻ ይፈለግ ስለነበረ ነው፤ እንደሚባለው አዲስ አበባ ውስጥ ቁጥር አንድ ሊባል የሚችል መናፈሻ ሊሠራበት የሚችል ሥፍራ ነበር፡፡ አሁን ግን ዕድሜ ለታከለ ኡማ፣ ቄሮዎች ወርረውት ከአራት መቶ በላይ ቤቶች ተሠርተውበታል –  ሥፍራው ሃይ ባጡ ባለጌዜ ቄሮዎች ተቸብችቦ አልቋል፡፡ አካባቢውም ተላጭቶ አንድም የደን ምልክት አይታይበትም፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ የሚያቀናውን መንገድ ሳይቀር በሽሚያ ተቀራምተውት ሰዎች በአጥሮች እየታከኩ ነው ወደ ግቢው የሚገቡት፡፡ ልክ እንደዚህ አካባቢ ሁሉ ሌሎች የአዲስ አበባ ዳርቻ ሠፈሮችም በቄሮዎች ተሸጠው አልቀዋል፡፡

የኦሮሞ ወጣቶች በሌሎች ቦታዎችም እንደሚያደርጉት በዚህም አካባቢ በዘመቻ መልክ ነው የወረሩት፡፡ አማራና ሌላ ዜጎች የሠፈሩባቸውን ቦታዎች በኃይል እያስለቀቁ ኃይሌ ጋርመንትና ለቡ አካባቢን ከሞላ ጎደል ተከፋፍለው ጨርሰውታል፡፡ በዚያ አካባቢ አንድም ባዶ ቦታ እንደሌለ የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ የሚጮኹበትም ቦታ ባለመኖሩ ለራሳቸው ተጨንቀዋል፡፡ 

የዛሬ ሁለት ዓመት የሰው ቤት ተላላኪና የጉልበት ሠራተኛ የነበሩ በትምህርትም በዕድሜም ያልገፉ ለጋ ቄሮዎች አሁን ለአዲስ አበባ አስተዳደር ምሥጋና ይግባውና ባለዲፎርዲ የሕዝብ ማመላለሻ  መኪናና ባለሕንጻ እየሆኑ ነው፡፡ ሀፍረት የሚባል ነገር አያውቁም፡፡ የሚጠበቅባቸው አንድ ነገር ብቻ ነው – እርሱም “መፈለግ” ብቻ ነው – አንድ ሰው ከነዚህ ውርጋጦች ጦስ ነፃ ሊሆን የሚችለው በሱ ላይ አንድም ፍላጎት እንዳይኖራቸው ፈጣሪ ከረዳው ብቻ ነው፡፡ አንድ ነገር ከፈለጉ የማንም ይሁን የማን ሥልጣን ላይ ያለውን የኦሮሞ መንግሥት በመተማመን ይቀሙታል፤ አዲስ አበባ ደግሞ የሁለት መንግሥት ንብረት መሆኗ የታወቀ ነው – የፌዴራሉና የኦሮሞ፤ በአሁኑ ወቅት ግን ይህ ሁለትነት ለይምሰልና ለስም አጠራር እንጂ ሁለቱም አንድ ናቸው – “ያዋጁን በጆሮ” ካላላችሁኝ በአብዛኛውና ወሳኝነት ባለው ሁኔታ በኦሮሞዎች የሚመሩ በስያሜ ሁለት በግብር አንድ ናቸው፡፡ 

የበፊተኞቹ ተረኞች ከነዚህኞቹ ጋር ሲነጻጸሩ በይሉኝታ ሳይበልጡ አይቀሩም፡፡ አሁን ላይ ወደኋላ ዞሬ ሳየው ስማቸውን ቄስ ይጥራውና እነዚያኞቹ እንደምንም ብለውም ቢሆን ለማስመሰል ይሞክራሉ፤ ደግሞም በአንደበትና በብዕር ሊገለጹ የማይችሉ በተለይ አማራው ላይ የፈጸሙትን ግፍና በደል ጨምሮ እጅግ ብዙ የሙስናና የዝርፊያ ተግባራትን ያከናወኑት በ27 ዓመታት ውስጥ ነው፡፡ እነዚህኞቹ ግን ገና በሁለት ዓመታት ውስጥ አዲስ አበባንና ዙሪያዋን ተቆጣጥረዋል፡፡ ከቀበሌና ከወረዳ ጀምረህ እስከከፍተኛና የሚኒስቴር መ/ቤቶች ብትዞር ግፋ ቢል ቢሮ ጠባቂና ዘበኛ እንጂ በረባ የኃላፊነት ቦታ ላይ ከነሱ ውጪ እምብዝም አታገኝም – እኔ በዚህ አፍራለሁ፤ በዚህ ዘመን የዚህ ዓይነት ድውይ አስተሳሰብ ሰለባ ሆኖ በዘረኝነት አዛባ ውስጥ የሚርመጠመጥ ሰው ማግኘት በርግጥም እንደሰው በሀፍረት ያሸማቅቃል – ለዚያ ዓይነቱ በቁሙ የሞተ ሰውም ታዝናለህ፡፡ አሁን ባለችዋ ኢትዮጵያም ሆነ በአዲስ አበባ ሌላ ሰው ምንም መብት የለውም፡፡ ሁሉም ነገር የነሱ ብቻ ይመስላቸዋል መሰለኝ ሰክረዋል፡፡

የድንቁርናቸው ብዛት እንደግሪሣ “ግር” ብለው ነው አንድን ባዶ ቦታ የሚወርሩት – ቦታው የትም ይሁን ግዴላቸውም፡፡ “ግሪን ኤሪያ” ምናምን ብሎ ነገር አይሰሙም፡፡ ባዶ በታ ከሆነች በቡድን ሄዶ ፊጥ ማለትና ገመድ ዘርግቶ፣ አጣና ኮልኩሎ መከፋፈል ብቻ ነው፡፡ ደህነኛ አስተሳሰብ ያላችሁ ኦሮሞዎች ከሌሎቻችን ትሻላላችሁና በሚገባቸው ቋንቋና የአነጋገር ለዛ ይህ ነገር ከሌሎች ጋር እንደማያቀባብርና ለአብሮነታችን ረጂም ጉዞም መርዝ እንደሆነ እባካችሁን አስረዷቸው፡፡ እርግጥ ነው ማግኘት ያነበርራል፤ ባላሰቡትና ባልጠበቁት አዱኛ መጥለቅለቅ ኅሊናን አስቶ በጊዜያዊ ስካር እያነፈለለ በስሜት ፈረስ አምባላይ ሊያስጋልብ ይችላል – እነሕወሓትን ጉድ የሠራቸውም ይሄን መሰሉ ጥጋብ ነው፡፡  እንዳለ የሚቆይ ነገር አለመኖሩን ግን በእግረ መንገድ ንገሯቸው፡፡ በመጨረሻ መጨረሻ ዋና ተጎጂ የሚሆኑት እነሱ ራሳቸው መሆናቸውንም አስገንዝቧቸው፡፡ 

ሌላው አስደናቂ ነገር ደግሞ በህገ ወጥ መንገድ ወርረው ለያዙት ቦታ  ከሚመለከተው የመንግሥት አካል የመሬት ይዞታ የባለቤትነት ካርታ በልዩ ትዕዛዝ ወዲያውኑ የሚሰጣቸው መሆኑ ነው፡፡ ሁኔታዎች በሚገርም ፍጥነት እየተለዋወጡ ነው፡፡ ኮሮና ቫይረስም ከዚህ ሩጫቸው ሊገታቸው አልቻለም – እነዚህ ሰዎች ማሰብ አለመቻላቸውን ብቻ ሳይሆን ማሰብ የሚችል የሰውነት ክፍል እንዳላቸውም መገመት የማንችልበት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ ቢያንስ አሁን ላይ እኮ ትንሽ ሶበር ማለት ነበረባቸው -አይደለም እንዴ? አክራሪ ኦሮሞዎችና ኦህዲድ/ኦነጎች ለኮቪድ 19ኝም ካቅሙ በላይ ሆነውበታል፡፡ ለነዚህ አክራሪዎች መድኃኒታቸው መንግሥቱን ወይም መለስን ዓይነት በጫማ ጥፊ የሚያቀረና ዐረመኔ ሰው ነው፡፡ ሰው በራሱ ላይ ለምን ጨካኝን እንደሚጋብዝ መቼም ቢሆን አይገባኝም፡፡ ይህን የምለው ቀጣዩን አሳምሬ ስለማውቅ ነው፤ የኔ ነው የምትለውን በቅጡ ካልያዝከውና ያንተ ነኝ የሚለውም ብልኃትና ጥበብ ከጎደለው መጪው ዘመን ላንተም ሆነ ጠቅሞ ላይጠቅምህ ያንተ ነኝ ለሚለው ወገንም አይሆንም – ይህን ዐረፍተ ነገር ደግመህ አንብበው፡፡ ግን ደግሞ እውነቴን ነው …

Filed in: Amharic