>

"ቅድስት ቤተክርስቲያን ልትከፈት ግድ ነው!!!" (ቢንያም ጸጋዬ)

“ቅድስት ቤተክርስቲያን ልትከፈት ግድ ነው!!!”

ቢንያም ጸጋዬ
 
* አማናዊት ቤተክርስቲያን ተዘግታ ሥርዓቷ ተጥሶ ምእመናን ስጋ ወደሙ ሊቀበሉ ሲሄዱ በዱላ መደብደባቸው እንባቸውን አፍስሰው መመለሳቸው በጣም ያማል ። መቀነታቸውን ፈተው ያሰሯት ክርስቶስ በደሙ የዋጃት መሰረቷም ጉልላቷም ክርስቶስ ኢየሱስ የሆነላት የጸጋ ግምጃ ቤት ስንዱ እመቤት ባህረ ጥበብ የሰማይ ሥርዓት ምሳሌ መጀመሪያችን ልደታችን መጨረሻችን እረፍታችን የሆነው እምዬ ተዋህዶ ደጆቿ ሊዘጉ አይገባም!
 
*  ምግብ ቤት፣ ሬስቶራንት፣ ሆቴል ተከፍቶ የሥጋ ምግብ  መብላት ከተቻለ ለዘላለም የማያስረበውንና የማያስጠማውን አማናዊ ምግብን መመገብ አትችሉም ማለት አግባብነት የለውም ። ገብያው ደርቶ ሰው በሰው ላይ እየተነባበረ በአውቶብስ ተራ እየታየ ትኩረትን ቤተክርስቲያን ላይ ማድረግ በፍጹም ነውር ነው!
 ርቀት ጠብቆ ትራስፖርት ከተያዘ ርቀት ጠብቆ ማስቀደስ ምኑ ነው በደሉ ? ክርስቲያኑ እንባው የሚታበስበት ጩኸቱ የሚሰማበት ታሪኩ የሚቀየርበትን ቤተክርስቲያን አትገባም ማለት ግራ የሚያጋባ ነው ።ከተማውን የሞሉ ንግድ ቦታ ቡቲክ ሱቆች መግባት እየተቻለ ቅድስት ቤተክርስቲያን በመግባትህ በበሽታ  ትሞታለህ ብሎ ምክንያት ማቅረብ መድኃኒት የሆነውን አምላክን መገዳደር ነው ። ትናት በእለተ ሰኞ የአዲስ አበባ ከተማ አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች በEOTC አባቶቻችን የሰጡት እጅግ ደስ የሚል ለቅድስት ቤተክርስቲያን ያላቸውን ተቆርቋሪነትን የአሳየ ግሩም የሆነ መልእክት ነው ። ዛሬ በኮሮና ሰበብ ቤተክርስቲያን ስትዘጋ ሥርዓት ተጥሷል ። 1፦ ካህን የክርስቶስ ምሳሌ ዲያቆን የአዳም ምሳሌ ምእመናን የሲኦል የነበሩት ነፍሳት ምሳሌ ይካሄድ የነበረው ሥርዓተ ቅዳሴ የምእመን ድርሻ ይበል ሕዝብ የሚለው ቀርቶ አባቶቻችን ያዘጋጁት ሥርዓት ተጥሷል። 2፦ ከአሉት ጸሎት ውስጥ በተለየ መልኩ ሥጋ ወደሙ የሚፈተትበት ልዩ ጸሎት ሥርዓተ ቅዳሴ ብቻ  ነው ። ሥጋ ወደሙ ከተፈተተ ማን ነው የሚቀበለው ? ይህ በራሱ አገር ላይ መከራን ያስከትላል ።
3፦ የእኛ ሃይማኖት ከሌሎቹ ሃይማኖቶች የሚለይ ሥርዓት አላት።  ለምሳሌ፦ ክርስትና በቅድስት ቤተክርስቲያን ብቻ ነው የሚፈጸመው ። ይህ ብቻ አይደለም ወንድ ልጅ በ40 ቀን ሴት ልጅ በ80 ቀን በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ትእዛዝ ጥምቀት ይከናወናል ። ለሞት የሚያደርስ ህመም ካለ ከቀኑ በፊት መጠመቅ አለበት።  ይህን የመሰለ ምስጢር አሁን እንዴት ይፈጸማል ? ሰባቱ ምስጢራተ ቤተክርስቲያን የሚፈጸሙት በቤተክርስቲያን ብቻ ነው ። የቤተክርስቲያን መዘጋት ምስጢራት እንዳይፈጸሙ አድርጓል ይህ ደግሞ ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን መጣስ ነው ። ቅዳሴ በቴሌቪዥን ቢኖር እንኳን እጣኑን ፣መስቀሉን ፣ ጸበሉን ፣ወንጌሉንና መንፈሱ ግን በፍጹም የለም ። ምስጢራቱ ደግሞ ፈጽሞ አይታሰብም ።
 አሜሪካን ጽዳቷ ለጉድ ጥንቃቄዋ ድንቅ ሆኖ ሞትን ስታጭድ እኛ  እስከ ዛሬ 3 ሰዎች ብቻ መሞታቸው ቸርነቱ እንጂ እንደ ሥራችንና እንደ አኗኗራችን ቢሆን በሟች ቁጥር  ሪኮርድን በያዝን ነበር ። በከመ ምህረትከ ብለናል ።  በጥምቀት ወቅት ይህ ሁሉ ታቦታት ሲወጡ ወጣቱ ሲያስተናግድ ህዝቡም ሰላማዊ ስለ ሆነ ሥርዓቱ ሁል ጊዜ ውብ ነው። አሁንም ቢሆን 1ኛ ፦ ርቀትን ጠብቆ በሥርዓት ማስቀደስ እንዲሁም ቆራቢያን ገብተው ይቆርቡ ዘንድ ቤተክርስቲያን ልትከፈት ግድ ይላል። ለማስተናገድ መንግስት አይስጋ ከበቂ በላይ ሰራዊት አለን የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ። ሥለዚህ ቅዱስ ሲኖዶስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር የህዝቡ እንባ እንዲታበስ ነፍሱ እንድትጠግብ  ከጭንቀቱ እንዲረጋጋ  ቤተክርስቲያን እንድትከፈት  ያደርግ ዘንድ  በተሰበረ መንፈስ በፍጹም ትህትና እንጠይቃለን ።
2ተኛ ፦ ማታ ማታ የሚደርሰው ጸሎት የሚፈሰው በተለያየ ቋንቋ ቃለ እግዚአብሔር በማእድ አንድ ሆኖ የማያውቀውን ቤተሰብ እድሜ ለኮሮና በጸሎት አንድ አድርጎናልና ይህ መቀጠል ያለበት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ቤተክርስቲያን ዋጋን በመክፈል ወደ ፊትም እስከ ለሌለው ጊዜ ይህ ሥርዓተ ጸሎትና ቃለ እግዚአብሔር እንዲቀጥል መደረጉ ጠቃሚነቱ ዋጋ አይተመንለትም ።3ተኛ ፦ በቴሌቪዥን የሚተላለፉ ሥርዓተ ቅዳሴ ከፍተኛ ጥንቃቄ ቢደረግ  ሰናይ ነው ። ምክንያቱም በክርስቶስ ስቅለት እለት የፈጣሪዬን ገላ አናሳይም በማለት ፀሐይ ጨለመች ጨረቃም ደም ሆነች ከዋክብትም ረገፉ ለሶስት ሰዓት ጨለማ ነበር እያልን እያስተማርን ሰዎች ሲቆርቡ መታየት ፈጽሞ የለበትም ። በቁርባን ጊዜ ቆራቢያን አፋቸውን በነጠላ ወይንም በመሀረብ የሚሸፍኑት የአምላኬን ሥጋ አላሳይም ብለው እንጂ ጉንፋን ይዟቸው አይደለም ። ከፀሐይና ጨረቃ ተምረው ነው እንጂ ። በእግዚኦታም ሰዓት  መጋረጃ ይዘጋል ። ቤተክርስቲያን አንድ ሥርዓት ነው ያላት።
 አባቶቻችን የሰሩትን በጎ ሥርዓት እኛ ልንጥስ አይገባም። ነብዩ ኤልያስ እኔ ከአባቶቼ አልበልጥም እንደ አለ እኛም አንበልጥምና ። 4ተኛ ፦ ኮረና ከአሳየን ነገር ወደ ፊት ቢቀጥል የምመኘው ውኃ የለም እንጂ ቢኖር እጅ መታጠብ ልማድ ሆኖ ቢቀጥል እመኛለው ። 5ተኛ፦ አለመጨባበጥም ቀድሞም የእኛ ባህል ሥላልነበር በዚሁ ቢጸና ሸጋ ነው ። 6ተኛ ፦ መረዳዳት የቀደመው የእኛነታችን መገለጫችን ነውና በዚሁ መቀጠሉ በእጅጉን ይበረታታል ።7ተኛ ፦ ንስሃ መግባቱ የዮሐንስ መጥምቅ አዋጅ ነውና ለዘመናት አልሰማ ያልነውን  ኮሮና የንስሃ ያለ እንድንል አስብሎናልና ለሥጋዊ ሞት ብቻ ሳይሆን በዋንኛነት ነፍሳችን እንዳትሞትና ሁለተኛ ሞትን ሞተን ወደ ጥልቁ እንዳንጣል ንስሃ የእለት እንዲሆን ቢቀጠል በረከት ነው ።
 8ተኛ ፦የቤተክርስቲያን ፍቅርና ናፍቆት ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ ነው ። ቤተክርስቲያን ሥለ ተዘጋ ሳይሆን ሁል ጊዜ በፍቅር በንስሃ የምንመላለስበት የሰማይ ደጅ ናትና ሁል ጊዜ እንደ አለ ነብዩ ዳንኤል “ሁል ጊዜ” ልንናፍቃት ይገባል ። 9ነኛ፦ ቅድስት ቤተክርስቲያን ክብሯ በዓለም ላይ ተገልጣልና ማንነቷ ጎልብቷልና ሁላችንም ከቅድስት ቤተክርስቲያን ጎን ልንሆን ያስፈልጋል ። 10ኛ ፦ ትናንትና ልጅነትን ዛሬ እግዚአብሔር ይፍታህን ነገ ፍትሃተ ጸሎት የሚሰጡንን ሰማያዊ ስልጣን የተሰጣቸውን ካህናት አባቶቻችንን ዲያቆናት ወን ድሞቻችንን ቀርበን እንመልከታቸው።  በምንችለውም እናግዛቸው።  ምን አልባት እኛ በልተን ሥናድር እነርሱ ትናትና ቅዱስ ሥጋውንና  ክቡር ደሙን ሲመግቡን የነበሩት ዛሬ ተርበው ይሆናልና። ተቸግረው ይሆናልና።  ሰው ናፍቋቸው ይሆናልና። በበጎ ህሊና በጎ ነገር እናስብላቸው ።  ወዳጆቼ ዛሬ ብዙ አገልጋዮች ተፈትነን አንዳንዶች ቀለው የተገኙበት ጊዜ ነው ። ቤተክርስቲያንን በጥቅም እና በመሳሰሉት አሳልፈው ሸጠው አብረው አዘግተው ዛሬ ተቆርቋሪ መስለው የሚጮሁ በአንድ ራስ ሁለት ምላስ የሆኑ አውርቶ አደሮች አሉ ። ቅዱስ ሲኖዶስ ዙሪያውን ሊፈትሽ ይገባል ።ተላላኪዎች  እነ 40/60 ባለ አራት መኝታ ኮንደሚንየሞችን ሊያምኗቸው አይገባም ። ባለ ተስፋዎችም ብትታቀቡ መልካም ነው ። ማንም የፈለገውን ባለ ሥልጣን መውደድ የፈለገውን ፓርቲ መደገፍ ይችላል መብቱም ነው ። ግን ቤተክርስቲያንን መሸጥ ግን አይቻልም ። ባንዳነት ግን አይሰራም ይሁዳነት ግን የሲኦል ሟሟሻ ያደርጋል ። ይህ በዘመናችን የተደረገ ታሪክ ነው ። ነገ ሥለ እኛ ይጻፋል።
ዛሬ ለቅድስት ቤተክርስቲያን ልንቆምላት ያስፈልጋል።  አንዳንዶች በየዋህነት፤ እንዳንዶች በዓላማ ፤ አንዳንዶች በጥቅማ ጥቅም፤ አንዳንዶች በትምክህት፤ አንዳንዶች በፖለቲካ፤ የቤተክርስቲን ክብሯን ልእልናዋን እንዲደፈር እያደረጉ ናቸው ። ሁላችንም ወደ ልባችን በመመለስ ቅድስት ቤተክርስቲያን እንድትከፈት ማድረግ አለብን ። ምስጢራቶቿም እንዳይጓደሉ የበኩላችንን ጥረት እናድርግ ። ደጇ ሲከፈት እኛ እኮ ነን እንዲህ አድርገን ያስከፈትነው ብሎ ለማውራት ከመሮጥ ዛሬ ደጇ እንዲከፈት በምንችለው ሁሉ በኅብረት እንታገል ። ወደ ፊት ገድለ ኮሮና ሲዘከር የማንነታችን ፋይል ፍንትው ብሎ መውጣቱ አይቀርም ። የማይታወቅ የተሰወረ የማይገለጥ የተከደነ ምንም ነገር የለምና ። መንግስትም ቆም ብሎ ቢያስብ መልካም ነው እጅግም የአማረ ነው ። ቅድስት ቤተክርስቲያን  ትከፈት ዘንድ ግድ ይላል ። የእግዚአብሔር ቸርነት የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት የአባቴ የአቡነ ሲኖዳ ተራዳኢነት አይለየን ። አሜን ። ደረጀ ዘወይንዬ ሚያዝያ 20/2012 ዓ.ም አዲስ አበባ ።
Filed in: Amharic