>

የምስጢር ቋቱ ኮሎኔል ተስፋዬ ወ/ሥላሴና የኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት!!! (ዳንኤል እንግዳ - ክፍል -2)

የምስጢር ቋቱ ኮሎኔል ተስፋዬ ወ/ሥላሴና የኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት!!!

ዳንኤል እንግዳ
ፍል -2-
 
➢ስለዚህም፣ የኮሎኔሉ አጠቃላይ ውጤት ሃምሳ ከመቶ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ችግሩ፣ በወቅቱ ከነበረው ከፍተኛ ውጥረት አንፃር  የ5ዐ ከመቶ ውጤት ሽንፈት መሆኑ ነበር፡፡
 
ይሄ ማለት ግን፣ ለስርዓቱ ውድቀት ተስፋዬ ብቸኛና ዋነኛ ተጠያቂ ነበሩ ማለት አይደለም፡፡ ተጠያቂዎቹ ብዙዎች ናቸው፤ የሚጀምረውም ከአናቱ ከእራሳቸው ከኮሎኔል መንግሥቱ ነው፡፡ ቁምነገሩ፣ በዋናነት ከሚፈረጁት መካከል አንዱ ኮሎኔል ተስፋዬ መሆናቸው ነው፡፡ ከደርግ ስልጣን ባሻገር ሃገርን የመጠበቅ ኃላፊነት ነበረባቸው፡፡ ኃላፊነታቸውን አልተወጡም፡፡ ውጤቱ ኤርትራን አስከፍሏል፡፡
 
ኮሎኔሉ ከስርአቱ ለውጥ በኃላም ለተወሰነ ጊዜ ከአዲሱ አለቆቻቸው ጋር ቆይታ ነበራቸው ለምን?   እንዴትአሊያም ለምን ያህል ጊዜ ለሚሉት በቂ የሆነ መረጃ የለም መጨረሻቸው ግን በዘር ማጥፋት ወንጀል ተከሰው ወህኒ ቤት ከነበሩት የቀድሞ የስራባልደረቦቻቸው ጋር ሆኖ ነበር።  
 
ሃያ ዓመታትን በእስር አሳልፈዋል ግንቦት 27 ቀን 2ዐዐ3 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት እስከተለዪባት ሰአት፡፡ እሳቸውም ሆነ የተቀሩት የእስር ቆይታቸው ከመደበኛ እስረኛ የተለየ እንደነበር ይነገራል ፡፡ የደርግ ባለሥልጣናት ከብዙሃኑ እስረኛ ጋር አልተቀላቀሉም፡፡ ለብቻቸው ተከልለው ነው የኖሩት፡፡ እስር ቤታቸው ንፁህ ነው፡፡ ጥበቱም የሚጋነን ሆኖ አያውቅም፡፡ ዓመታት በገፉ ቁጥር፣ ብዙ እስረኞች ወይ በሞት፣ ወይ በፍቺ፣ እየተቀናነሱ መጥተው ነበር፡፡ 
 
ቴሌቪዥንና ቤተመጻሕፍት አላቸው፡፡ የመዝናኛ እና የስፖርት ጊዜም አመቻችተዋል፤ ቢንጎ የዘወትር ጊዜ ማሳለፊያ ነው፡፡ ከመቼ ጀምሮ እንደነበረ ባይታወቅም  አረብ ሳትም ነበራቸው፡፡ የሚከታተሉትን ጣቢያ የሚወስንላቸው ግን ወህኒ ቤቱ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ፣ ቤተሰቦቻቸውን ቶሎ ቶሎ ያገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያ ደረጃ፣ አያያዛቸው የሚያስከፋ አይደለም፡፡ ብዙሃን በኢሕአዴግ ገሃነማዊ እስር ቤቶች ያዩትን መከራ እነሱ አላዩም፡፡ ከዚህ አኳያ፣ እድለኞች ናቸው ማለት ይቻላል፡፡
 
በአንድ ወቅት፣ ተስፋዬ ወልደሥላሴ፣ ፍቅረሥላሴ ወግደረስ፣ ለገሠ አስፋውና ስለሺ መንገሻ አንድ ክፍል ውስጥ እንደነበሩ ተነግሯል ፡፡ የተረጋገጠ ግን አይደለም፡፡ እነዚህ የደርግ አባላት ተስፋዬን አኩርፈዋቸው እንደነበረም በወቅቱ ሰምተናል፡፡ እንደገና ግን፣ የተረጋገጠ አይደለም፤ ወሬ ነው፡፡ እውነት ቢሆን ግን አልገረምም፡፡ ኢሕአዴግ አዲስ አበባን ለመያዝ በተቃረበበት ጊዜ፣ ባለሥልጣናት እንዳይጠፉ ኬላ እንዲዘጋ ተስፋዬ ትዕዛዝ ሰጥተው ነበርና፡፡ በትዕዛዛቸው መሰረት፣ አዲስ አበባ የነበሩት የደርግ ባሥልጣናት በኢሕአዴግ እጅ ወድቀዋል፡፡ (የተረፉት 4 ብቻ ነበሩ፡፡ እነሱም በወቅቱ ጣሊያን ኢምባሲ ገብተዋል፡፡) እስር ቤት ሲገናኙ፣ ትዕዛዙ መንግሥቱን የተኩት የጄኔራል ተስፋዬ ገብረኪዳን እንጂ የእሳቸው እንዳልነበር ተናግረዋል፡፡ ምን ያህል እንደታመኑ አላውቅም፡፡
 
ከኮሎኔል ተስፋዬ በፊት፣ ተካ ቱሉ እዚያው እስር ቤት አርፈዋል፡፡ ከደርግ አባላት መካከል፣ ካሣዬ አራጋውና ካሣሁን ታፈሰም የመጨረሻ እስትንፋሳቸው የወጣችው በእስር ላይ ሆነው ነበር፡፡ ሌሎችም ተጨማሪ የደርግ አባላትም እዚያው እንደሞቱም እገምታለሁ፡፡ በነፍስ የነበሩትም አርጅተው ነበር፡፡ 
የእድሜያቸውን 1/3ኛ በእስር አሳልፈዋል፡፡ ቅስማቸው ያልተሰበረው ጥቂቶች ናቸው፡፡ ሁሉም የፀፀት ስሜት ይታይባቸው ነበር፡፡ ጥፋታቸው የማይረሳ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የሚታዘንላቸው እንጂ የሚጠሉ ሰዎች መሆናቸውም  አብቅቶ ነበር፡፡ ከሞቱት በላይ ከሚኖሩት በታች ሆነው ከሃያ ዓመት በላይ አሳልፈው ነበር፡፡
Filed in: Amharic