>

ፖለቲካ ስትጀምሩ ጥሩን!!! (አገኘሁ አሰግድ)

ፖለቲካ ስትጀምሩ ጥሩን!!!

አገኘሁ አሰግድ
ስለ ፒኮክ አውርታችሁ ጨረሳችሁ?  
እንደኔ እንደኔ ግን ምስራቅ አፍሪካ ላይ ትልቅ አደጋ ስለደቀነው አንበጣ ብታወሩ ያዋጣ ነበር። 
እውነት፤
-ባልደራስ ጣዖስ ላይ ፊርማ ከሚያሰባስብ፣
-ጃዋር በፌስቡኩ ፒፒን እየነቀፈ ላይክ ከሚሰበስብ፣
-አብን፣ በሉት ኦነግ፣ ወይም ኦፌኮ ቁጭ ብሎ ስለ ሽግግር መንግስት ከሚያስብ ይሄን የአንበጣ ጉዳይ አጀንዳ አድርጎ ቢስብ… ትልቅ አክብሮት ነበረኝ!
ፖከቲካ የሚበላሸው የአጀንዳ ብልት በማያውቅ ፖለቲከኛ የተከበበ ሰሞን ነው። ጣዖስ አስፈርሳለሁ ትላለህ። አንበጣ በሶስት ሀገር የ25 ሚሊዮን ሄክታር የእርሻ መሬት እህል አውድሞልሃል።
አንበሳ ነኝ”
አዎ አንበሳ ነህ!  አንበሳ ተኝቶ ነው የሚበላው። አያድንም። ሰነፍ ነው። መተኛት ነው! ሴቷ ናት አድና የምታበላው። ሲበላ ደሞ ቀላል ይበላል!
ድብን ያልከው አንበሳ ነህ እንጂ!
እስቲ ባለፉት ጥቂት ጊዜያት ብቻ ሀገር የተቀበለችውን እርዳታ እና የእርዳታ ቃል መለስ ብለህ ቃኝ… ዝም ብለህ አንበሳ አትሁን፣ ተኝተህ አትብላ! ከየት የመጣ ምግብ ነው ያበሉኝ በል። ጠይቅ፣ ገና ሊበሉህም ሲለሚያስቡ ለዛ ጊዜ ይሆንሃል።
«የአንበጣው ወረርሽኝ በዓመታት ውስጥ ያልታየ ዓይነት ወረርሽን ነው። በአንድ ቀን 150ኪሜ ይሸፍናል ስትባል» … “ግን ጣዖሷስ… አንበሳ ነበር እኮ መሆን ያለበት” ትልልኛለህ።
«35ሺ ያህል ሰዎች የሚመገቡትን ምግብ በአንድ ቀን ሊያወድም ይችላል» ስትባል ግን ጣዖሷስ? …ጦስ።
«በምስራቅ አፍሪካ ኦልረዲ 20 ሚሊዮን ሰዎች የምግብ ዋስትና አጥተዋል» ስትባል ግን እኮ ታሪካችንን፣ ምልክታችንን፣ አንበሳችንን… ደቅ ደቅ ደቅ…
ታሪክህ ምንድነው? ፈትሽ እስቲ? በልቶ ማደር ነው ተባልቶ ማደር?
ተደፍቶ እና ተደፋፍቶ ማደር አልነበረም?
ሲባላ ለነበረ ሕዝብ ከአንበሳ ይልቅ ጣዖስ ሲመጣለት፣ እንደ አንልኮ ቦታ መሳም ቢያቅተው የምን ለቅሶ ነው።
ቤታቸውን ህገ ወጥ ብለው አፈረሱት ይባልና ሄዶ ብሶት ተሰምቶ፣ «ጋሽ ታከለ በምርጫ እንዘርሮታለን» ብሎ ብሽሽቅ የፖለቲካ ፖርቲ ነው የፑበርቲ?
ነብሴ፣ ሀውሲንግ የፍትሕ ጉዳይ መሆኑ ካልተያዘልህ ስልጣን ብትይዝ ምን ልታቀብለን ነው?  ብሶት እየተከተሉ ምርጫ ይድረስ ብቻ መባባልማ እኛም አያቅተንም እኮ። ከፍፍ አድርገው፣ አማራጭ ፖሊሲ አሳይ… እንዲህ እንዲህ በማድረግ መፍታት ይቻላል የሚል መንገድ አመላክትና ለወንበሯ እናብቃህ ነው የኛም ሃሳብ።
ወዶ እኮ አይደለም የፌስቡክ ሞገድ አስነስቶ፣ የቀብር ቦታ መርጦ ፓርቲ ውስጥ ከገባ በኋላ ሰዉ ወደ አክቶቪዝም የሚመለሰው ስለ አሜሪካ ናሽናሊዝም የተፃፈ እየመዘዘ፣ አያችሁ ናችናሊዝም ዓለምአቀፋዊ ክስተት ነው አይሞትም ይልልሃል። ልዩነቱን ካለየ፣ የሞትክ ብለህ እለፍ። ዋይት ናሽናሊዝም ፣ ከብሔር ብሔርተኝነት የሚምታታብህ ከሆነ እንደቃልህ ይብራብህ ጓዴ።
ብሔርተኝነትም እኚህ እኛ ሰፈር ያሉት ትርሃስ፣ አለማየሁ (“አለማዮ” ነው የሚለው ራሱን ሲጠራ፣  ወይኔ አለማዮ ነገር) እና ጥላሁንም ይኖሩታል። እንደውም ካንተ በላይ ባያሾሩት ብለህ!
የነሱን ፖለቲካ ፖለቲካ ካደረክማ ላይ ሰፈር አልነህ እንጂ የኛው ሰፈር ነህ።
ስለ ጄኔቲካሊ ሞዲፋይድ የእህል ዘሮቹ አታወራም? ስግብግብ የውጪ መልቲ ሚሊየነር ካምፓኒዎች ይሄኛው ብሔሩ እንዲህ ነው ብለው ገበሬውን የሚምሩት ይመስልሃል?
አንተ የኛ እና ኬኛ የምትለውን ሕዝብ ገንዘቡን የሚያስተፉ… ከስተመር የሚሉት ሊበሉት ተሰልፈዋል። እ?  እጅ ከምን?
ከኮሮና ወረርሽ በኋላ ደሃውን ሊነካ የሚችልን ኢኮኖሚያዊ አደጋ መቀነሻ አማራጮች ካንተ አልነበረም መስማት የነበረብኝ?  አማራጭ ነው ጩኧት አላልኩም። ድምፅ እንድታሰማ ወረርሽኙንም በብሔር እንከፋፈለው?
“ስልጡን ፖለቲካ ያስፈልገናል”
“ፖለቲካውን በልቼዋለሁ”
” ስለሽግግር መንግስት ካላወራን ሞቼ እገኛለሁ” ፒፒፒፒ…  ሞቼ እገኛለሁ? …አሁን ምን ሆነህ ነው የምትገኘው?
ወላሂ ያ ትውልድ እኮ ከነችግሩ ሺ ጊዜ ይግደለን። መሬት ላራሹ ብሎ ነው፣ የሰራተኞች የመደራጀት መብትን ጠይቆ ነው፣ በኢምፔሪያሊዝም እንዳታስበሉን ብሎ ነው፣ ቢሮክራሲያዊ ከብርቴ፣ አቀባባይ ከበርቴ፣ ጭቁን መደብ ብሎ ነው… ቢያንስ የሚጠይቀውን በቋንቋ ያውቃል።
ወደን እኮ አይደለም የሽግግር መንግስት የምንፈራው። እንኳን ተሰብስባችሁ በተናጠልም ታስፈሩናላችሁ፣ እውነት።
ደሞ ይደክመኛል። ከዚህ ከቆንጆ ግጥም ከፍ ያለ ዋጋ ለሌለው ጣዖሳም ፖለቲካም መዳረቅ ምን ይሰራል?
እንደሕዝብ ላውራ እስቲ። ምን አባቱ፣ ስንቱ የሚወክለው ሕዝብ አይደል እንዴ?  እኔ ዛሬ ብወክለው ምን ይሆናል?
.
.
.
ፖለቲካ ስትጀምሩ ጥሩን!
Filed in: Amharic