>
11:07 am - Tuesday October 4, 2022

የሜይ ዴይ ትዝታ - በሶሻሊስቷ ኢትዮጵያ ዘመን! (አሰፋ ሀይሉ)

የሜይ ዴይ ትዝታ – በሶሻሊስቷ ኢትዮጵያ ዘመን!

አሰፋ ሀይሉ
ሜይ ዴይ – በጎርጎሮሳውያኑ የዘመን አቆጣጠር በየዓመቱ የግንቦት ወር የመጀመሪያዋ ዕለት የሚከበረው ዓለማቀፉ የላብአደሮች ቀን – በሶሻሊስቷ ኢትዮጵያ ዘመን – ከመስከረም 2 የአብዮት በዓል ቀጥሎ – እጅግ በታላቅ ድምቀት የሚከበር ብሔራዊ በዓል ነበር፡፡
ገና የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ እያለን – የሰውን ልጅ ሁሉ እኩልነት የሚሰብከውን የሶሻሊዝም ርዕዮተዓለም ከልባቸው የተቀበሉ – ከመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ ለማስተማር ልምምድ በየትምህርት ቤቱ የሚመደቡ ትኩስ ወጣት መምህራን ነበሩን፡፡ እና ከሜይ ዴይ ቀደም ብሎ – በሁለተኛው ሰሚስተር – በዓመቱ መጨረሻ አካባቢ ነው ወደየትምህርት ቤቱ የሚመጡልን፡፡ በመደበኛ አስተማሪዎቹ የተለመዱ ፊቶች የተሰላቸን ተማሪዎች ሁሉ – እነዚያን ገና ማስተማርና ማስረዳት ያልሰለቻቸውን ትኩስ ወጣቶች በጉጉት ነበር የምንጠብቃቸው፡፡ ገና አልሰለቻቸውምና ልጆችን፣ ተማሪዎችን በፍቅር ነው የሚቀርቡት፡፡ በፍቅር ነው የሚያተምሩት፡፡ በፍቅር ነው የሚሰብኩት፡፡ የምን ስብከት?
የሶሻሊዝም፣ የኮሙኒዝም ስብከት ነዋ፡፡ እነዚያ ወጣቶች እንዴት ምንም ለማይገባን የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች ስለ ኮሙኒዝምና ማርክሲዝም ይሰብኩናል? ጤና የላቸው ይሆን? ብዬ አስብና እስቃለሁ፡፡ ወንድሜ – በሶሻሊስቱ ዘመን እኮ – ወያኔ-ኢህአዴግ በ83 ላይ አዲሳባ ገብቶ እስከቀረልን ጊዜ ድረስ – ‹‹ፖለቲካ›› የሚባል አንድ ራሱን የቻለ የትምህርት ዓይነት እኮ ይሰጠን ነበረ፡፡ የመማሪያ መጽሐፍ ሁሉ ነበረው፡፡ ብዙም ባይገባንም ‹‹የምርት ኃይሎችና የምርት ግንኙነቶች… ወዘተ..›› እያልን እንቦጠረቅ ነበረ በፖለቲካ ትምህርት ክፍለ ጊዜያችን፡፡
እና እነዚያ አዳዲስ ወጣት መምህራንም በተለይ ፖለቲካን ይወዷት ነበረ፡፡ ይወዷት ነበረ ብቻ ሳይሆን – እንድንወዳት አድርገው በልጅነት አዕምሯችን ውስጥ እንዴት አድርገው መቅረፅ እንደሚችሉ ጠንቅቀው የተረዱ ነበሩ፡፡ ብዙዎቻችን ያን የፖለቲካ ትምህርት ይኸው እስከዛሬ እናስታውሰዋለንና – ተሳክቶላቸዋል ማለትም አይደል?
እና ከእነዚያ ወጣት ሠልጣኝ መምህራን አንዱ የክፍል መምህራችን ሆኖ በተመደበልን በ1979 ዓመተ ምህረት ላይ ለሜይ ዴይ በዓል የምትሆን አንዲት ገራሚ ሶሻሊስታዊ መዝሙር አስጠንቶን ነበረ፡፡ ትዝ ይለኛል ያቺን መዝሙር ሸምድደን፣ ከትምህርት ሚኒስቴር መጥቶ ለየትምህርት ቤቶች የታደለውን አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ በክንድ ውስጥ የሚጠለቁ ገንባሌ የመሰሉ ጨርቆች ተላብሰን፣ በየመንገዱ ወዛደሮችን ተከትለን ላንቃችን እስኪሰነጠቅ በጩኸት የዘመርነው! ወይኔ! ለካ ኃይለኛ ኮሙኒስት ሆነን ነበር ገና በጊዜ! ያቺን የ1979 ለሜይ ዴይ ዕለት የዘመርናትን መዝሙር እስካሁን አስታውሳታለሁ፡፡ አንጀትን በሚበላ ዜማ የታጀበች እንዲህ የምትል ነበረች፡-
‹‹ግንባር ቀደሙ ወዛደር ያሸንፋል፣
ኮምኒዝም በምድራችን ያነግሣል!
የካፒታሊዝም መምጣት ህልውናውን የፈተነው፣
ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ንብረቱን ያራቆተው፣
ንብረት አልባነቱ የደሞዝ-ባሪያ ያደረገው፣
ወዛደርነቱ – ለዓለማቀፋዊ – ክብር የዳረገው፣
ግንባር-ቀደም መሪ ወዛደር እሱ ነው!››
ደግሞ ያቺ በደማቅ የሠልጣኝ መምህራን መዝሙር የታጀበችው የወዛደሮች መዝሙር ዓመቱን ሙሉ በሙዚቃ ክፍለጊዜ ሳይቀር እየዘመርናት ወደቀጣዩ ዓመት አደረሰችንና ደግሞ የ1980 ዓመተ ምህረት ቀጣይ ወዛደራዊ መዝሙር በቀጣዮቹ መምህራን አማካይነት መጣችልን፡፡
(በነገራችን ላይ ያኔ በተለይ እትዬ ሸዋዬ የምንላት የሙዚቃ መምህርት – እነዚያን መዝሙች ስንዘምር በጣም ትቁነጠነጥ ነበር – በምቾት ማጣት፡፡ እና በመጨረሻ በአንድ በመረራት ዕለት ‹‹ሁለተኛ ይሄንን መዝሙር ከአፋችሁ እንዳልሰማው!›› ብላ ገላገለችን፡፡ እስቲ ስለ ወፍ ዘምሩ፡፡ ስለ አበባ፡፡ ስለ ፍቅር፡፡ እስቲ አዲስ የወጣ ዘፈን የሚዘፍንልን ማነው? ትላለች፡፡ ወይ ያለምወዝ፣ ወይ ወንድዬ ወይ እማዋይሽ ከመካከላችን ይነሱና በየተራ ያስነኩታል – ያኔ አዳዲስ የወጡትን የንዋይ ደበበን ‹‹ማዕበል ነው ፍቅሯ››ን፣ የአረጋኸኝ ወራሽን ‹‹ከወገብሽ ነቀል፣ ከአንገትሽ ሰበር፣ እስኪ ዘለል ዘለል››ን፣ የሃመልማል አባተን ‹‹የታለ ልጁ የታለ››ን፣ ወዘተ ወዘተ፡፡ እና በፈገግታና በደስታ ትሞላለች መምህርታችን፡፡ እኛም በተለይ በወንድዬ ዳንስ በሳቅ እንንተከተካለን፡፡
የምን ሶሻሊዝም?! የምን ኮሙኒዝም?! ሃይለኛ እዚያው በዚያው ኢምፕሮቫይዝ ተደርጎ የተፈጠረ ድራማና መዝናኛ ሙዚቃ እያለልህ!? ያቺን ፀረ-ኮመኒስት መምህርት ግን በራሷ ክፍለጊዜ ለምን ያን አዘፈንሽ ብሎ የሚጠይቃት ማንም ተቆጪ አካል አልነበረም – ሁሉም ሰልችቶት ነበር ማለት ነው ሶሻሊዝም? ከትኩሶቹ ወጣት መምህሮቻችንና – ከእኛ ከትኩሶቹ ህጻናት በስተቀር? ምን አውቄ!)
እና በ1980 ዓመተ ምህረት ላይ ደግሞ ሌላኛዋ ለሜይ ዴይ በዓል የምንዘምራት ኮሙኒስታዊ መዝሙር ተሰጠችንና – እንደለመድነው በልጅ ብሩኅ አዕምሯችን ሽምድድ አድርገናት – ኃይለኛ ኮሙኒስቶችን በሚያስንቅ ሞራልና ወኔ ተሞልተን እንደ ጉድ ዘመርናት ይቺኛዋን ደግሞ! አይ ጊዜ! አይ ወኔ! አይ ልጅነት! የዚህችኛዋንም ዜማ ከነስንኞቿ እስካሁንም አልዘነጋኋትም፡፡ የሚገርመው ግን የመምህራኑን ስም ብዬ ብዬ ማስታወስ አልሆንልህ አለኝ፡፡ ለማንኛውም ያቺ የልጅነት ለወዛደሮች የዘመርናት አዲስ ዜማ እንዲህ ትል ነበረ፡-
‹‹ለትግሉ ሂደት ለዓላማው፣
መሠረቱ ዳያሌቲክስ ሁለመናው፣
ርዕዮት ዓላማው መራመጃው፣
ግዙፍ ሞተሩ መንቀሳቀሻው፣
ማርክሲዝም ሌኒኒዝም ነው፣
ማርክሲዝም ሌኒኒዝም ነው!
የወዛደሩ መደብ አሸናፊ ነው!
የሠርቷደሩ መደብ አሸናፊ ነው!››
እንግዲህ እነዚህ ሁሉ በየዓመቱ አዲስ አዲስ ሆነው የሚመጡና በፍቅር በሞራል በጋራ የሚቀነቀኑ ልዩ መዝሙሮቻችን ነበሩ፡፡ ‹‹ኢንተርናሲዮናል የሰው ዘር ይሆናል›› የምትለዋንማ መዝሙር በያመቱ እንባችን እየመጣ ሁሉ ነበረ የምንዘምራት፡፡ ያኔ በልጅነት ዕድሜዬ ‹‹ተነሱ እናንት የርሃብ እስረኞች፣ ተነሱ የምድር ጎስቋሎች›› እያልኩ ኢንተርናሲዮናልን ስዘምራት – ከምር ታሳዝነኛለች፡፡
ልክ በልጆች ሁሉ ዘንድ ተወዳጅ የነበረችዋንና አንጀታችንን እየበላችን በሚገርም የማስተዛዘን ስሜት የምንዘምራትን ‹‹ኧረ አምሳለ፣ ኧረ አምሳለ፣ አለሽ ወይ? አለሽ ወይ? – አለሁ በመከራ እንባዬን ሳዘራ፣ ለምን ታዘሪያለች ምስኪን ደሃ ሆነሽ? – ምስኪን ደሃ ሆነሽ ምን በልተሸ ታድሪያለሽ? – ባገኝም በልቼ ባጣም ተደፍቼ… ኧረ አምሳለ… ኧረ አምሳለ… አለሽ ወይ… አለሽ ወይ…?›› አቤት አቤት አንጀታችንን ስትበላው አምሳለ! ኢንተርናሲዮናልንም መዝሙር እንደ ‹‹ኧረ አምሳለ›› መዝሙር ነበረ የምናያት፡፡
እንዲህ እንዲህ ነበር በኮምኒስቷ ኢትዮጵያ – ለጭቁኑ ወዛደርና ለጭቁኑ ሕዝብ የመደብ አጋርነትና ተቆርቋሪነት በልባችን እንድናሳድር – ገና በለጋ ዕድሜ የምንሰበከው – ወይም ‹‹ኢንዶክትሪኔት›› የምንደረገው!! ዋ ኮሙኒስቱ እኔ! ዋ ልጅነቴ! ዋ ሜይ ዴይ! ዋ ወዛደር ! ዋ…!!
ልጅነት ጥሩ ነው፡፡ ልጅነት ብዙ ጅልነትም አያጣውም፡፡ ግን የሚገርመው አሁንም አምናለሁ፡፡ በወዛደሩ ጭቁን ህዝብ የኑሮ ትግል፡፡ አምናለሁ በዚህች ዓለማችን የሚለፉ፣ ላባቸውን የሚያንቆረቁሩ የላባቸውን ፍሬ በትክክል እያገኙ እንዳልሆነ፡፡ አምናለሁ ታላቁን የህይወት ቀንበር የተሸከሙት በንፁህ ላባቸው ታትረው ደክመው የሚኖሩት ምስኪን ላብ-አደሮች እንደሆኑ፡፡ አሁንም አምናለሁ በኅብረት፡፡ አምናለሁ በሜይ ዴይ፡፡ አምናለሁ በሜይ ዴይ ውብ ትዝታዎች፡፡
የአሁኑን አላውቅም፡፡ ያኔ ግን ሜይ ዴይ የሚከበረው በኢትዮጵያችን ሠማይ ሥር ለፍተው ደክመው በላባቸው ፍሬ በሃቅ ለሚኖሩ ንፁህ ኢትዮጵያውያን ክብር ነበር፡፡ ሜይ ዴይ በንፁህ ላባቸው የማያድሩ ሌቦችን፣ ቀማኞችን፣ ሙሰኞችን፣ ዘራፊዎችን፣ ሳይዘሩ ሳያጭዱ የሚኖሩ የባለጊዜ አደግዳጊዎችን አይመለከትም ነበር፡፡ ሜይ ዴይ የተሰጠቻቸውን ውሱን ኑሮ ለማቅናት ላባቸውን ለሚያንቆረቁሩ የጭቁኑ ሕዝብ ልጆች መታሰቢያ ትሆን ዘንድ የተሰጠች – ጥረህ-ግረህ በወዝህ እደር የተባለው የአዳም ዘር ሁሉ በወዙ የሚያከብራት – ቅድስት በዓል ነበረች፡፡
ሜይ ዴይ በየሙያ መስኩ ተሰማርተው ይህችን የጎበጠች ዓለም ለማቃናት ቀን ከሌት ለሚታትሩ፣ ጉልበታቸውን ለሚያንጠፈጥፉ፣ በዓለም ዙሪያ ላሉ ወዝ-አደሮች (ወይም ላብ-አደሮች) ዕውቅናና ክብር የተሰጠባት ‹‹ሰውን ሰው ያደረገው ሥራ ነው›› የሚል ዓለማቀፍ ዜማ የሚቀነቀንባት – ‹‹የማይሠሩ እጆች አይብሉ›› የሚል መፈክር የሚንቦገቦግባት ሥራና ሠራተኛ በታላቅ ክብር የሚወደስባት የተከበረች ዕለት ነበረች፡፡
ሜይ ዴይ ሠራተኞች ሰብዓዊ ፍጡራን እንጂ ሰብዓዊ ፍላጎታቸውን የተቀሙ አገልጋይ ባሮች አይደሉም በማለት የሠራተኞችን መብት ለማስከበር ከአረመኔ ፈርጣማ ባለሃብቶች ጋር ሲተናነቁ ለከባድ መከራና መስዋዕትነት ለተዳረጉ የሠራተኞች መብት አራማጆችና ተወካዮች ክብርና ዕውቅና የሚሰጥባት – የአርምሞ በዓልም ነበረች፡፡
ለእነዚህ ሁሉ ሲባል ነበረ፣ ሜይ ዴይ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ ከተሞች ሁሉ ደምቃ ትከበር የነበረችው፡፡ በሶሻሊስቷ ኢትዮጵያ ዘመን፡፡
የሜይ ዴይ ዕለት ልዩ ድምቀት የሚቸራት ዕለታችን ነበረች፡፡ ቀያይ የሶቭየት ባንዲራዎች ከኢትዮጵያ አረንጓዴ፣ ቢጫ ቀይ ባንዲራ ጋር የሚውለበለቡባት፣ የየፋብሪካው ወዛደሮችና የገበሬ ማህበራት ሰማያዊ ቱታቸውን ለብሰው ልዩ ትርዒታቸውን የሚያሳዩባት፣ ከተለያዩ መሥሪያ ቤቶች የተውጣጡ ሠራተኞችና መምህራን በሠልፍ አደባባይ ወጥተው ‹‹ዓለማቀፉ ወዛደራዊ ወንድማማችነት ይለምልም!›› እያሉ፣ ግራ እጆቻቸውን በኃይለ ቃል ከፍ እያደረጉ፣ ጮክ ያለ የኅብረት መፈክራቸውን የሚያሰሙባት – ከቀኖች መሐል በወዝ የደመቀች ወዛም የወዝ-አደሮች ዕለት ነበረች፡፡
እስከማውቀው – በኢትዮጵያችን – ሜይ ዴይን – ዓለማቀፉን የሠራተኞች ቀን – ከሥራ ነጻ ሆኖ በመላው ኢትዮጵያ ዝግ ሆኖ የሚከበር ብሔራዊ በዓል እንዲሆን ያደረገው – የሶሻሊስቷ ኢትዮጵያ ወታደራዊ መንግሥት ነበረ፡፡ ሜይ ዴይ! ዓለማቀፉ የላብአደሮች ቀን! በዚያ ዘመን ለኖርን ዓመት ጠብቃ በመጣች ቁጥር የቆየ ትዝታዋን የምትለኩስብን የሶሻሊስት ዘመኗ ሜይ ዴይ ይህች ነበረች፡፡
በንፁህ ላባችሁ – ጥራችሁ ግራችሁ በወዛችሁ ለምታድሩ – ንፁሃን ያገሬ ኢትዮጵያ ሰዎች ሁሉ፡-
እንኳን ለሜይ ዴይ – ለዓለማቀፉ የወዛደሮች ቀን – በሠላም አደረሳችሁ!
የለፋችሁበት፣ የነካችሁት ሁሉ የተባረከ ይሁን!
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!
Filed in: Amharic