>

የሱዳን ህገወጥ ወረራና የጎንደር ትዝታ የመጨረሻ ክፍል (ብርሀኑ ተክለያሬድ)

የሱዳን ህገወጥ ወረራና የጎንደር ትዝታ

 
የመጨረሻ ክፍል
ብርሀኑ ተክለያሬድ
አዘዞ ስንደርስ በፖሊስ ተያዝን ያሁኑ እስር ማባበል አልነበረውም በቁጣና በጉልበት ነው ከነመኪናችን ወደ ፖሊስ ጣቢያ ገባን ስልካችንን ተቀማን ሴቶቹ ለብቻቸው እንዲቀመጡ ተደረገ “መሬት ቁጭ በሉ መነጋገር አይቻልም” ተባለ።
ጥቂት ጊዜ ተቀመጥን፤ውጪ አባሎቻችን ሞይታዩናል፤እምላእሉ፣አፈወርቅ፣ስለሺ ወዘተ ጥቂት ከተቀመጥን በኋላ ሃላፊ መጥቶ ያናግረን ብለን ጠየቅን። ያዘዙን ሀላፊዎች ይመጣሉ ጠብቁ ተባልን። በዐይን ተግባባን ይቺ የለመድናት ዘዴ ናት እስከ ምሽቱ 12 ሰአት አስረው የቅስቀሳ ሰአቱ ካበቃ በኋላ ሊፈቱን መሆኑ ገባን። ጌታነህ ተነስቶ “ልብ አርጉ አሁን ካልፈታችሁን ማታ ውጡ ብትሉን አንወጣም” አለ፤አልመለሱልንም፤መሬት ቁጭ እንዳልን መሸ እንደፈራነውም 12:30 ሲሆን ተለቃችኋል ውጡ ተባልን።”ቅድም ተናግረናል አንወጣም” አልን ፖሊሶቹ ተያዩ ‘ደሞ ተፈታችኋል ሲባል እምቢ ይባላል?’ አሉ በእምቢታችን ፀናን።
ፖሊሶቹ ወይንሸትንና እየሩስን እየገፈተሩ ለማስወጣት ሞከሩ።ይኼኔ ጣቢያው በመዝሙርና በጩኸት ተደባለቀ፤ተከብረሽ የኖርሽው….. በጭብጨባ ተጀመረ፤መፈክር ማሰማት ጀመርን፤የአካባቢው ሰው ግልብጥ ብሎ ወደ ጣቢያው መጣ።የጣቢያው አዛዥ ተጨነቀ፤ዱላ የያዙ ፖሊሶች መጥተው ሌሎች እስረኞችን እየደበደቡ ወደ ክፍል አስገቡ፤ግቢው ውስጥ ብቻችንን ቀረን፤መዝሙሩና መፈክሩ ቀጥሏል፤አዛዡ ከአካባቢው ሰዎች 3 ሽማግሌዎች አስከትሎ መጣ፤ “በስህተት አስረናቸው ነበር አሁን ውጡ ብለናቸዋል አንወጣም አሉ ከሰሟችሁ ንገሯቸው” አለ። ሽማግሌዎቹ ለምን እንደማንወጣ ጠየቁን የታሰርነው ሆን ተብሎ የቅስቀሳ ሰአታችንን ለማሳለፍ እንደሆነ፣ እንድንታሰር ያዘዘው አካል መጥቶ ካላናገረን እንደማንወጣ ነግረናቸው ተስማምተው ሄዱ።
እየመሸ ሲሄድ ፖሊሶች እየመጡ ያናግሩን ነበር”የእስር ክፍሉ መጥፎ ነው እናንተ ለኛ ብላችሁ ነው ከአዲስ አበባ የመጣችሁት እዚህ ቆሻሻ ክፍል ከምታድሩ እባካችሁ ተስማሙና ውጡ” ማለት ጀመሩ ወይ ፍንክች አልን። እስር ቤቱ መብራት የለውም ፖሊሶቹ በራሳቸው ገንዘብ ሻማ ገዝተው ሴቶቹ ወደ አንዲት ክፍል ወንዶቹ ደግሞ ከሌሎች እስረኞች ጋር ተቀላቀልን። እንቅልፍ የለም እስረኛው በየተራ ሲዘፍን ስንጫወት ብሎም  ውጪ የቀሩ ጓዶች ጠዋት ሰልፉን እንዴት ያደርጉታል? ምን ይገጥማቸው ይሆን እያልን ስንወያይ አመሸን።ዮናታን ከመሀላችን ኮከብ ዘፋኝ ሆኖ ነበር። በጠዋት ትፈለጋላችሁ ተብለን ስንወጣ እምላእሉና ይድነቃቸው በር ላይ ቆመው ነበር፤
“እቃችሁን ይዛችሁ ውጡ” አሉን።
‘የለም ሃላፊዎች ካላናገሩን አንወጣም’ አልን
“ይልቃል ልኮን ነው የመጣነው በስብሰባ ወስነናል ፍላጎት ሳይሆን ትእዛዝ ነው” አሉን
ምንም ማድረግ አይቻልም ገብተን ልብሳችንን መሰብሰብ ጀመርን ፖሊሶቹ ተደሰቱ፤ መኪና ውስጥ ገብተን ጉዞ ወደ መስቀል አደባባይ ሆነ።
መስቀል አደባባይ ስንደርስ ያልታሰሩት ጓዶቻችን መፈክር ይዘው ወደ መስቀል አደባባይ እየተሻገሩ ነበር።አደባባዩን ፖሊስ አጥሮታል፤ትራፊኮች እንድንቆም አዘዙን ሹፌሩን ‘ጥሰህ ግባ’ አልነው። ጥሶ ወደ አደባባዩ ገባ።ብዙ ህዝብ ተከትሎን ወደ አደባባዩ ሲገባ ፖሊስ አደባባዩን ለቆ ሄደ መፈክሩ ቀለጠ፤ባነሮች ተዘረጉ፤ተዘጋጅተው ይጠብቁ የነበሩ የአማራ ቴሌቪዥን ጋዜጠኞች ካሜራዎቻቸውን ተከሉ። ሜጋፎኑን እየተቀባበልን መፈክር ማሰማቱን ተያያዝነው። አግባው የቦታ ስሞችን እየዘረዘረ “የኢትዮጵያ ናቸው!!!” እያለ መፈክሩን ይመራል። በኋላ ሌላ ጓድ ወኔ የያዘው ጓድ “አስመራ የኢትዮጵያ ነው!!!” አለ ህዝቡ ተቀበለው።እኔና ዮኒ ተያየን ሳናስፎግር ሜጋፎኑን ተቀበልነው። ዮኒ ያለፈውን አይነት ዲስኩር ደገመው “የጎንደር ህዝብ ሆይ ሰው አፈር ነው፤አፈር ደሞ መሬት ነው፤መሬት ደሞ ወያኔ ለሱዳን የሸጠው ነው፤መሬታችን ተሽጦ አይቀርም እናስመልሳለን” አለ። በመጨረሻም ኢ/ር ይልቃል ግሩም የሆነ የመዝጊያ ንግግር አድርጎ ህዝቡን አመስግነን ሰልፉ ተጠናቀቀ።
ይህ ከሰማያዊ ትግል ጉዞ 1ዱ የሆነው  የ1 ሳምንት የጎንደር ትዝታችን ነው።ስንመለስ በየመንገዱ ያደረግነውና የሆነብን ተረት ይመስላል። ሌሎቹን በየቦታው የገጠሙንን ገጠመኞች ብናወራቸውማ ነግቶ ይመሻል። እንደአስፈላጊነቱ ወደፊት እንቀጥላቸዋለን። የጎንደሩ ሰልፍ ፓርቲው ለሀገር ድንበር መከበር ካበረከተው አስተዋፅኦ ባሻገር ግለሰባዊ ድልም ነበረበት ምንድነው?ከዚህ ውጪ ወደ አዲስ ስንመለስስ ሰላሌ ላይ ምን ተከሰተ? ሁለቱን ገጠመኞች ወዳጄ ጌታቸው ሽፈራው እንዲቀጥላቸው አስረክቤ አበቃሁ!!!
Filed in: Amharic