>

የሃገር ቱምቢው  አይረሴ ትዝታዎች!!! [ቢቢ ሽጉጤ]

የሃገር ቱምቢው  አይረሴ ትዝታዎች!!!

ቢቢ ሽጉጤ 
*   ባለ ማህተቡን የጨንቻ ልጅ እንዲህ አስታወስኩት!!!
 
  “……..በ1984 ዓ ም በሽግግሩ ወቅት የሽግግሩ ም/ቤት አባል እያለሁ በት/ት ጉዳይ  ” የአንደኛ ደረጃ ት/ት ፖሊሲ ጥናት ተጠናቋል ” ብሎ የወቅቱ ት/ት ሚንስትር የነበረው ኦነጉ ኢብሳ ጉተማ አንዲት ጥቂት ገፅ የያዘች ከሲታ ዶሴ ለም/ቤቱ አባላት አደለን።
 አፋር እና ቤኒሻንጉል በአረብኛ ፣የተቀሩት ብሄረሰቦች በየቋንቋቸው ይማሩ፣ሌላም ሌላም ተባለ። እኔ ጥያቄ ጠየቅሁ ‘ት/ት ሃገር የምትገነባበት ነው፣ትውልድ የሚቀረፅበት ነው፣ቋሚ ነገር ነው እንጂ ፤ት/ት ሚንስትር ልክ እንደ ሁለተኛ ክፍል የቤት ስራ ማታ ጫርጫር አድርጎ ጠዋት የሚያቀርበው አይደለም። የታሉ ያጠኑት ኤክስፐርቶች ጥያቄ እንድንጠይቃቸው? አልኩኝ።  መለስ ዜናዊ ” ይሄ የፖለቲካ ጥያቄ ነው ‘” ብሎ ተቆጣ ። በእኔ ተቃውሞ፡ በአብላጫ  ድምፅ ፖሊሲው ፀደቀ።….”
” ……የጦር ሰራዊቱን በመበተን ጉዳይ ውይይት ተካሄደ  ‘የደርግ የሚባል ሰራዊት የለም ፡ የኢትዮጵያ ሰራዊት ነው፤ ከሃምሳ አመት በላይ ፈጅቶ የተገነባ የሃገሪቷ ተቋም ነው’  ብዬ ተከራከርኩ ፤ በሻይ ሰአት ላይም “የሰራዊቱ አፍራሽ ኮሚቴ ሰብሳቢ” ወደሆነው የኦነጉ ሌንጮ ለታ ጋ  ሄጄ  ‘ ኧረ ተው ! በትናችሁ የጎዳና ተዳዳሪ የምታደርጉት የኦሮሞ ልጆችንም ጭምር ነው ‘ ብዬ ለመንኩት።  አይሆንም ብለው ሰራዊቱን በትነውት ቀረ።……”
“…… እንደተለመደው አንድ ቀን ስብሰባ ላይ ከሰብሳቢው መለስ ዜናዊ ጋር በጣም ተከራክረን ፣ተጨቃጭቀን፤ ለሻይ እረፍት ወጣን። ወጭላይ በሗላ “የህገ-መንግስት አርቃቂ ኮሚቴ ሰብሳቢ ” የሆነው ክፍሌ ወዳጆ ፡ከሰዎች ጋር ቆሞ ሲያማኝ ደረስኩ ፤ ማማቱ ሳያንስ እኔን ሲያየኝ ወደእኔ ዞሮ በቁጣ “ይህንን ልጅ(መለስን) ለምን ታናድደዋለህ?” ብሎ ጮኸብኝ ፤ እኔም ቡጢ ጨብጬ ስዘጋጅ ሰዎች ይዘውኝ ገላገሉኝ………'”
“…..ም/ቤት ውስጥ ሁልጊዜ ስጨቃጨቅ እና ስከራከር ያየኝ አንድ የሚያውቀኝ የቢቢሲ ጋዜጠኛ ፡ አንድ ቀን በሻይ ሰአት ” ና ቡና እንጠጣ”  ብሎ ወስዶኝ ” poor assefa I pity u ” (ምስኪኑ አሰፋ ታሳዝነኛለህ) አለኝ። ምን ሆኜ አሳዘንኩህ? አልኩት፤ “ስለ ተሰነዩ ስብሰባ ታውቃለህ?” ብሎ ጠየቀኝ፤ አላውቅም። መለስኩ
 ” መንግስቱ ከሃገር ወጥቶ ፣ለንደን ለስብሰባ ከመሄዳቸው በፊት ፤ ሻቢያ፣ህወሃት እና ኦነግ  ኤርትራ ተሰነይ ውስጥ ተሰብስበው ፤ ከደርግ በሗላ ኢትዮጵያን እንዴት እንደሚመሩ ፣ስልጣን እዴት እደሚከፋፈሉ፣ምን አይነት መዋቅር እንደሚዘረጉ ፅፈው ፣ተፈራርመው ነው ወደ ለንደን የሄዱት፤ አሁን እየተገበሩ ያሉት እሱን ነው፤ አንተ ዝም ብለህ ነው የምትጮኸው” ብሎ ነገረኝ፤ አመመኝ፣አ በ ድ ኩ፣ ተናደድኩ………..”
  አሰፋ ጫቦ “ከትዝታ ፈለግ” እና ከቃለመጠይቆቹ
  እንደ አሰፋ አይነት ሰዎች የሃገር “ቱምቢ” ይመስሉኛል። ቱምቢ ባለሞያዎች ቤት ሲሰሩ ቤቱ እንዳይዘም፣ ወደ አንድ በኩል እንዳይጣመም ፣ እንዳይወላገድ ፤ በእርሷ እያዩ “ውኃልኩን ” የሚጠብቁባት መሳሪያ ነች።
  ‘ሃገር ‘ የምትባል የጋራ ቤትም ስትገነባ ፤ህሊናቸውን በሆዳቸው ያለወጡ፣ የነገው ትውልድ እጣ ፈንታ እንዳይበላሽ ቱምቢ ሆነው የሚያገለግሉ ባለ መህተብ ሰዎች ያስፈልጋሉ።
  ‘ኢትዮጵያ’ የምትባለው የጋራ ቤታችን ፡ እንደዚህ እንዳትዘም በሽግግሩ ወቅት ቱምቢ ሆነው ፡ መለስ ዜናዊን እና እንደ ክፍሌ ዎዳጆ ያሉ ስናድራዊያንን ከሞገቱ ጥቂት ሰዎች አንዱ ነው።
 ገፍትረው የብሄር ስልቻ ውስጥ ሊጨምሩት ቢታገሉም  ” ጥሩ ጋሞ፡ ኩሩ ኢትዮጵያዊ ነኝ፤ ጋሞነቴ እና ኢትዮጵያዊነቴ ተጣልተውብኝ ላስታርቃቸው ተቀምጨ አላውቅም”  በሚል መልሱ የዘረኞችን አፍ ያሲዝ ነበረ።
  በስልሳዎቹ መጀመሪያ ላይ የአ.አ.ዩ ተማሪ እያለ አሜሪካ ውስጥ በተካሄደው International moot court ከአለም ከታወቁ ዩኒቨርሲቲ የተወከሉ የህግ ተማሪዎች ውድድር ኢትዮጵያን ወክሎ ሁለቴ ተወዳድሯል። በመጀመሪያው አመት አንደኛ ከወጡት ሦስት ልጆች አንዱ ነው ። በሁለተኛ አመትም ሦስተኛ ከወጡት ሦስት ልጆች አንዱ ነው።
  ደርግ ስልጣን እንደያዘ ለጭቁኖች ለመታገል ኢጭአትን (የኢትዮጵያ ጭቁኖች አብዮታዊ ትብብር) አቋቁመው የነበረ ቢሆንም ደርግ ይዞት ከ1971_81 ለአስር አመት ማዕከላዊ እስር ቤት አስገባው።
  ኢህአዲግ እንደገባ በሽግግሩ ም/ቤት የኦሞቲክ ፓርቲን ወክሎ መግቢያዬ ላይ በጠቀስኩት መልኩ ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር እየታገለ እያለ አውሮፓ እና አሜሪካ ያሉ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ ጋብዘውት ልክ ከሃገር እንደወጣ በመለስ ዜናዊ የሚመራው መንግስት  “አሰፋ ጫቦ በቀይ ሽብር ወንጀል የሚፈለግ ከፍተኛ ወንጀለኛ ነው ” የሚል ሰፊ ዘገባ በጋዜጣ አስነበበ። በሗላ እንደወጣው ሚስጥር ከሆነ ፡ ፅሁፉን መለስ ዜናዊ አርቅቆት ፣በረከት ስምኦን ነው በትዕዛዝ ወደማተሚያ ቤት የላከው። አሰፋ ግን በደርግ 17 ዓመት የስልጣን ጊዜ ውስጥ ፤ 10 ዓመት 6 ወር ከ6 ቀን በማዕከላዊ እስር ላይ ነበረ።
  ከዚያም በሌለበት ክስ መስርተው የአስራ ስድስት አመት እስር አስፈረዱበት ። በውጭ ሃገር ሆኖ ዜናውን የሰማው አሰፋም ወደ ሃገሩ ሳይመለስ በወጣበት ቀረ።
 የጨንቻው ጋሽ አሴ ከሃገሩ ወጥቶ ኢትዮጵያን፣ የጋራ ቤታችንን፣ ትልቋ ቤታችንን ፣ጨንቻን እንዳለ፤  ሳይመለስ ህይወቱ ካለፈች ባለፈው ሳምንት ሦስት አመት ሞላው።
  ባለ ማህተቡን የጨንቻ ልጅ እንዲህ አስታወስኩት።
  ስለ ጋሽ አሰፋ ስብዕና ለማወቅ “የትዝታ ፈለግ” የተሰኘውን መፅሃፉን ማንበብ በቂ ይመስለኛል።
  “ጨንቻ ጥሩ ሃገር ነው ። ያልተፃፈ አያነብም!”
   አሰፋ ጫቦ
የግርጌ ማስታወሻ 
  አጋፋሪ ! ዛሬም ህገ-መንግስቱን እና የቋንቋ ፌደራሊዝሙን አንቀበልም የምንልበት አንዱ ምክንያት፡ ተሰነይ ውስጥ ተዶልቶ ፡ ኦነግ በሚባል አህያ ላይ ተጭኖ ፣ ህወሃት የሚባል ጌታው እየሳበው ፣ ሻዕብያ ‘ ቼ’ እያለ ነድቶት አዲስአበባ ገብቶ ተግባራዊ የሆነ የሴራ ኮተት ስለሆነ ነው።
Filed in: Amharic