>
5:13 pm - Monday April 18, 6039

"ወታደርተኝነት" የተጠናወተው ዲስኩር!!! (ኤርሚያስ ለገሰ ዋቅጅራ)

“ወታደርተኝነት” የተጠናወተው ዲስኩር!!!

ኤርሚያስ ለገሰ ዋቅጅራ
ከእንቅልፌ ስነቃ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ማስፈራሪያ ሰማሁት። እውነት ለመናገር ጠሚሩ የቀራቸው ወታደራዊ ዩኒፎርም መልበስ እንጂ ዲስኩራቸው “ወታደርተኝነት” የተጠናወተው ነበር።
የድሮው ኢህአዴግ “የወጣቱን ደም ለማፍሰስ የሚሯሯጡ” የምትል ቃል የዘወትር ማስፈራሪያው ነበረች። የዛሬው ኢህአዴግ (ብልጥግና) ወጣቶችን ወደ እናቶችና ህፃናት ለማስጨረስ በሚል ቀይሮታል።
ለማንኛውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለስልጣናቸው ቀናኢ እንደሆነ በተደጋጋሚ ተገልጧል። በሌላም በኩል የቻይና ወረርሽኝ ቫይረስም የሕዝበኛ መሪዎችን ጭንብል በመግለጥ ወደ ለየለት አምባገነንነት እንደሚወስዳቸው ግንዛቤ ተይዞ ነበር።  ዛሬ የቀድሞ ኮረኔልነታቸውን በአደባባይ የገለጡት ጠቅላይ ሚኒስትር በእናቶች እና ህፃናት ሰበብ የሃሳብ ነፃነትን በመደፍጠጥ የአምባገነንነት ጉዞውን ተያይዘውታል።
በነገራችን ላይ የፓለቲካ ፓርቲዎች ተሰባስበው የሚመሰርቱት የሽግግር መንግስት ” የብጥብጥና ሁከት” አልፎ ሄዶም አገር የማፍረስ ፕሮጀክት ላላቸው ኃይሎች ምቹ አጋጣሚ የሚፈጥር መሆኑን እኔም አምንበታለሁ። ነገር ግን ይህ ሃሳብ መገለጥ የለበትም በሚል በማስፈራሪያ እና የህገ-መንግስቱ ጠበቃ ሆኖ ለመታየት መሞከር ግን ” ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ!” ነውና ቢቀር ይሻላል። የአራዳ ልጆች ” አይነፋም!” እንደሚሉት።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር! አንድ ነገር ልምከሮት። ያልተገለጠ ሃሳብ አይታወቅም። ካልታወቀ ደግሞ ሰዎች ምን እንደሚያስቡ ማወቅ አይቻልም። እናም በሃሳብ ነፃነት ላይ እውቀቶን ትንሽ ሰፋ ያድርጉት። መጥፎ የሚሆነው አጥፊ ሐሳብ ወደ ድርጊት ተቀይሮ ጉዳት ሲያደርስ ነው። ይሄም ቢሆን ቅድሚያ የሚሰጠው ሃሳብን በሃሳብ ለማሸነፍ መሞከር ነው።
ለነገሩ እኩይ ሃሳብ ወደ ድርጊት ተቀይሮ 86 ንጹሃን ኢትዮጵያውያን (እናቶች እና ህፃናት) ሲጨፈጭፍ፤ አስጨፍጫፊውን ሐረር ተገኝተው ያሞካሹትና ወንድምዎ መሆኑን የገለጹት እኮ እርሶ ኖት። ይህ ድርጊቶ ስልጣኖትን ለጊዜውም ቢሆን የተከላከለ ቢሆንም በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ የማይጠፋ ጥቁር አሻራ አሳርፏል። ይባስ ብሎ ሰሞኑን የእርሶ የበላይ ሹም የሆኑት አለሙ ስሜ “ተከበብኩ ብሎ ሰው ያስጨፈጨፈ” ብለው ሲናገሩ ህዝቡ እንዴት እንደታዘባቸውና እንደናቃቸው አይተዋል። ዛሬም የነዛ 86 ኢትዮጲያውያን ፣ ህፃናት እና እናቶች ደም ይጮሃል። የፍትሕ ያለህ ይላል። አቶ አለሙ ስሜ እንዳሉት ያስጨፈጨፈው ማን እንደሆነ ድርጅታዊና መንግስታዊ ብይን ካላችሁ ለፍርድ አቅርቡና የንጽሃንን ደም እና እንባ አብሱ። እኛም ከእርምጃችሁ ተነስተን አክብሮታችንን እንስጣችሁ።
Filed in: Amharic