>

"በኮሮና ቫይረስ ላይ የምናሳየው ቸልተኛነት ዋጋ እያስከፈለን ነው!!! " (የአዳማ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ዳግማዊ በቀለ)

በኮሮና ቫይረስ ላይ የምናሳየው ቸልተኛነት ዋጋ እያስከፈለን ነው!!! “

የአዳማ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ዳግማዊ በቀለ
 
በኮሮና ቫይረስ (COVID-19) ተይዘው ያሳለፉትን ስቃይና ከሞት ጋር ያደረጉትን ግብግብ አጫውተውናል፡፡ እኛም በሚከተለው መልኩ አቀናብረን አቅርበንላችኋል፡፡
ቫይረሱ እንዴት እንደያዛኝ በእርገጠኝነት ለመናገር ባልደፍርም ጥርጣሬ ግን አለኝ፡፡ የካቲት 23/2012 ዓ.ም በስራ ቦታዬ እንደወትሮው ሁሉ ስራዬን እየከወንኩ ባለሁበት ሁኔታ አንድ የውጭ ሃገር ዜጋ መጥቶ እንደነበር እና ከእሱ ጋር በነበረኝ ቆይታ ሊሆን እንደሚችል ነው የምገምተው፡፡ በሰውዬው ላይ ጥርጣሬዬን ያጠናከረልኝ ደግሞ በአዳማ ከተማ ከእኔ በፊት በቫይረሱ የተያዘ ሰው አለመኖሩ ነው፡፡
መጋቢት 9 ቀን ከምሽቱ አንድ ሰዓት አካባቢ በስራ ቦታዬ ላይ ድንገት ብንብን የሚል ሳል አሳለኝ፡፡ ነገር ግን አጠገቤ አየር ማቀዝቀዣ (ቬንትሌተር) ስለነበረ እሱ ሊሆን ይችላል ብዬ ገመትኩና ወዲያው ኮሮና እንዳይሆን እንጅ ብዬ ባለቤቴና ሰራተኞቼ ባሉበት ተናገርኩኝ፡፡ ይህንን እንድል የደፈርኩትም ስለኮሮና ቫይረስ ቀድሜ በቂ ግንዛቤ መያዜ ነው፡፡
በሚቀጥለው ቀንም እያሳለኝ ዋልኩ፡፡ አሁን ጥርጣሬዬ ስላየለብኝ መደረግ ስላለበት ጥንቃቄ ማሰብ ጀመርኩ፡፡ ወደ ሌላ ሰውም እንዳላስተላልፍ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል (Face mask) እና ጓንት (glove) ወዲያውኑ መጠቀም ጀመርኩ፡፡
ቀናቶቹ እየጨመሩ ሲሄዱ የእኔም ምልክቶች እየጨመሩ ሄዱ፡፡ መጀመሪያ የጀመረኝ ብንብን የሚል ሳል እንደቀጠለ ነው፤ ጉሮሮዬ አካባቢ የመብላትና የማሳከክ፤ የመቆረጣጠም አይነት ስሜቶች ስላሉብኝና የሰውነት ሙቀቴም ወደ 38.8 ዲግሪ ሴንት ግሬድ ከፍ ስላለ ራሴን ከሌሎች ሰዎች አገለልኩ፣ የምጠቀማቸውን እቃዎችን እንዲሁም ማደሪያዬንም እንድለይ ተገደድኩ፡፡
በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለሁ ናሙና ሰጥቼ ስለነበር ከአዳማ ጤና ቢሮ ተደወለልኝ እና ውጤቴ እንደደረሰ ተነገረኝ፡፡ ነገር ግን ውጤቱ pending ነው የሚለው ይህ ማለት ቫይረሱ ሊኖርብኝም ላይኖርብኝም እንደሚችል ተገልፆልኝ ያለሁበት ቦታ እንድቆይ ተነገረኝ፡፡ ለሁለተኛ ግዜ ተደውሎ ውጤቱ የኮሮና ቫይረስ (COVID-19) ፖዘቲቭ እንደሆንኩ ተነገረኝ፡፡ ቀድሞውኑም ጠርጣሬ ስለነበረ አልተረበሽኩም፡፡
ከዚህ በኃላ ራሴን አግልዬ ከቆየሁበት እንድወጣና አዲስ አበባ ውስጥ የኮሮና ቫይረስ (COVID-19) ህክምና ማዕከል ወደ ተዘጋጀው ኤካ ኮተቤ ሆስፒታል እንድገባ ተደረኩ፡፡ እዛ ከገባሁ በኃላ ሐኪሞች በተደጋጋሚ ይገባሉ፤ ራሳቸውን ያስተዋውቁኛል፤ ይመክሩኛል ይከታተሉኛል፡፡ ይህ ሁኔታ የበለጠ እንድረጋጋ ረዳኝ፡፡
ሆስፒታል በገባሁ በሦስተኛው ቀን ሙሉ ሌሊት አሞኝ አደርኩ ሃኪሞቹም ሲረዱኝ አደሩ፡፡ ጧት አንድ ዶ/ር ራሱን አስተዋውቆ  የሃኪሞችን ምክር መስማት እንዳለብኝ፤ ብዙ መጨነቅ እንደሌለብኝ ፤ቢያስመልሰኝም ምግብና ፈሳሽ ነገሮችን መውሰድ እንደሚገባኝ አስረድቶኝ ይህንን ሳደርግ የመዳን እድሌ በጣም ሰፊ እንደሚሆን አብራራልኝ፡፡
በዙሪያዬ የነበሩ ጓደኞቼ፤ የስራ ባልደረቦቼ እንዲሁም በተለያየ አጋጣሚ ያገኘዄቸው ሰዎች እዲመረመሩ በተጠየቅኩት መሰርት ሰጥቼ ስለነበር ሁሉም ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸውን ስሰማ ደስተዬ ወደር አልነበረውም፡፡ ይህ እንዲሆን ቀደም ብዬ በታዩኝ ምልክቶች ሳልዘናጋ መጠንቀቅ ስለቻልኩ ነው፡፡
ነገር ግን ሆስፒታል በገባሁ በ7ተኛው ቀን ባለቤቴም እኔ ወደተኛሁበት ሆስፒታል እየመጣች እንደሆነ ስልክ ደውላ ነገረችኝ፡፡ ለምን እንደሆነ ስጠይቃት ቫይረሱ እንደተገኘባት፤ ነገር ግን ምንም አይነት የህመም ስሜት እንደሌለባት ነገረችኝ፡፡
አሁን ቤተሰቤ እየተበተነ እንደሆነ ተሰማኝ፡፡ እኔ እና ባለቤቴ ሆስፒታል፤ ልጆቼ ግማሾቹ አዲስ አበባ ፤ ሌሎቹ አዳማ  ትንሿ ልጄ ደግሞ አክስቷ ጋ ተበታትነናል፡፡
ባለቤቴ ሆስፒታል የገባች እለት እና በማግስቱ ተገናኝተን ነበር፡፡ በሚቀጥለው ቀን ግን አልመጣችም፤ ቀረች፡፡ ምን ነው ምን ሆንሽ ብዬ ስደውልላት ህመሙ እንደባሰባት እና እኔ ጋ መምጣት እንደማትችል ነገረችኝ፡፡ ስለዚህ እኔ እንደምንም ሄጄ ማየት አለብኝ ብዬ ቀስ እያልኩ በኮሪደር እየተራመድኩ ሳለ አንዱን ልጄንም በውኔ ይሁን በህልሜ ሆስፒታል ውስጥ ያየሁት ስለመሰለኝ በጣም ጮኩ፡፡ አሜን ብዬ ተጣራሁም፤ አሜን የልጄ ስም ነው፡፡ ለካ እውነት ነበር ልጄ በሽታው አለብህ ተብሎ ገብቶ ኖሯል፡፡ በዚህ ግዜ የተሰማኝን ስሜት መግለፅ ከበድ ነው፡፡ ብቻ የተደበላላቀ ከባድ የሃዘን ስሜት ተሰማኝ፡፡ የቤተሰቤ ገዳይ እኔ  እንደሆንኩ አሰብኩ፡፡ እንደገና ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ውስጥ ገባሁ፡፡
ቀስበቀስ የምግብ ፍላጎቴ እየተሻሻለ መጣ፣ መንቀሳቀስም ጀመርኩ፡፡ እኔ ሆስፒታል በገባሁ በ16ተኛው ቀን ባለቤቴ ከቫይረሱ ነፃ መሆኗ ተነገራት፡፡ ይህን ግዜ እንደገና ተስፋዬ ለመለመ፡፡ ምክንያቱም ልጆቼ እናታቸውን መልሰው አግኝተዋል ብዬ በጣም ተደሰትኩ፡፡ እሷ በወጣች በማግስቱ እኔ እና ልጄም ነፃ መሆናችን ተነገረን፡፡ ደስታችን ወደር አልነበረውም ፡፡
በእኔ የደረሰ በማንም እንዲደርስ ፈፅሞ አልሻም እኔ ለ14 ቀናት እንቅልፍ በዓይኔ አልዞረም፤ በተመሳሳይ ምግብም አልቀምስም ነበር፡፡ በእያንዳንዷ የህመምና ስቃይ ግዜዬ ስለሞቴ ነበር የማስበው፡፡ ለህዝቤ መናገር የምፈልገው ትልቁ ነገር መታጠብ ነው! መታጠብን ተግብሩ! ከእኔ አይታችሁ እኔን አይታችሁ ተማሩ ለመታጠብ የምንከፍለው ነገር የለም፡፡ ይህ ምክር አይደለም ግዴታም ጭምር ነው፡፡ አስገዳጅ ሁኔታዎች እስካልተፈጠሩ ድረስ ከቤታችሁ አትውጡ፤ መውጣት ግድ ከሆነ ግን ከሌሎች ጋር አትጨባበጡ፤ ሁለት ሜትር ርቀት ጠብቆ መንቀሳቀስ፤ ሰዎች የበዙበት ቦታ ስትሄዱ ከቻላችሁ ማስክ መጠቀም ፤ ማስክ ማግኘት የማይቻል ከሆነ ደግሞ ስካርብ በመጠቀም አፍ እና አፍንጫችንን መሸፈን ግዴታ ነው፡፡
ወላጆች ውጭ ቆይታችሁ ሰትመለሱ እጃችሁንና ፊታችሁን በሳሙና በውሃ በሚገባ ሳትታጠቡ ልጆቻችሁን ከማቀፍ ተቆጠቡ፤ ወደ ቤት ስትመለሱ ጫማችሁን ውጭ አውልቃችሁ በተቀያሪ ጫማ ወደ ውስጥ ግቡ፤ ለብሳችሁ የዋላችሁትን ልብስ ከሌሌች ልብሶች ጋር ሳትቀላቅሉ ለብቻ አስቀምጡ፡፡ አቶ ዳግማዊ አክለውም ይህንን ምክር በተግባር አውሉ ፡፡ እኛ በድሃ አገር ውስጠ የምንኖር ህዝብ ነን፤ የተመከርነው ምክር በቂ ነው  ወደ ተግባር መቀየር ላይ ያሉብንን ችግሮች አርመን ጥንቃቄዎቻችንን እናጠናክር፡፡ የጤና ባለሙያዎች የሚሰጡንን ምክርም እንተግብር!!
በመጨረሻም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ስራቸውን እየሰሩ ላሉ የጤና ባለሙያዎቻችን፤ ለኦሮሚያ ጤና ቢሮ እንዲሁም ታምሜ በነበርኩበት ወቅት ስልክ በመደወል እና መልዕክት በመላክ ከጎኔ ሆናችሁ ላበረታችሁኝ ሁሉ ምስጋናዬ ይድረስልኝ፡፡
እኛም መልዕክታቸውን አድርሰናል፡፡ ግንዛቤ እንደጨበጣችሁበት እምነት አለን፡፡
Filed in: Amharic