>

በደጅ መወለድሽ - በገዛ እጅሽ (ቀሲስ አባይ ነህ ካሴ)

በደጅ መወለድሽ – በገዛ እጅሽ

ቀሲስ አባይ ነህ ካሴ
አንቺን የሚሸከም ቤት በዚህ ዓለም አልተገኘምና ልደትሽ በውጭ ኾነ። ቅዱስ ያዕቆብ የሰማይ ደጅ እንዳለሽ ትዝ ይለናል። ድሮስ ሰማይን የሚችል ምን ቤት በዚህ ዓለም ይኖራል? ከምድር እስከ ሰማይ የተዘረጋሽ መሰላል ይልሻል። እናስ አንቺን ምን ዓይነት ቤት ያስተናግድሻል?
ደግሞ ስትመጪ ብቻሽን አይደለም። የራቀንን እግዚአብሔርን ከአሽከሮቹ መላእክት ጋር ይዘሽ እንጅ። እኮ ለአንችም ቤት አላገኘን ስንኳን ለምሉዕ በኩለሄው። እስከዛሬ የሚመጥንሽን ቤት ልንሠራ አልተቻለንም። ያ ወንጌላዊ ስፍራ አልተገኘላቸውም ያለን ለዚህ ነበር ለካ።
አንች ግን ቅዱስ ዳዊት እንደተናገረው ሰማይና ምድር ለማይችሉት ቤቱ ኾንሽ። ለወለዱሽ ለተራሮች መልሰሽ እናት ኾንሻቸው። ያ ዶኪማስ እንኳን ልጅሽ ተጨምሮ ለአንችም ቤቱ እንዳይበቃ ዐውቆ በአዳራሽ በድንኳን ቢያስቀምጥሽ ከመንበርሽ ሳለሽ ጓዳውን ዐየሽበት። ቤቱን ከባዶነት ወደ መትረፍረፍ ለወጥሽው።
አክስትሽ ቅድስት ኤልሳቤጥም ቤቷ እንዳይበቃሽ ዐውቃ ወደ እኔ ትመጪ ዘንድ እንዴት ይኾናል? ብላ ተርበተበተች። አንቺ ግን ገና በደጅ ሳለሽ በቤት በነበረችው በአክስትሽ ማኅፀን ላለው ጽንስ ታየሽ። በረድኤትሽ ቀርበሽዋልና ጠብ እርግፍ ብሎ ሰገደልሽ። የኾነው ሁሉ የተገለጠላት ቅድስት ኤልሳቤጥ እኛ ሁሉ እንሰማው ዘንድ በታላቅ ድምፅ ዐወጀችሽ። ከቤቷ በላይ ነሽና።
ሰማይ ነሽ ብለን ስንደነቅ ምድር ኾነሽ ያለ ዘር ታበቅያለሽ። ምድር ነሽ ስንል ሰማይ ቤት ደርሰሽ ዙፋን ትዘረጊያለሽ። በሰማይ አንድ ልጅ ብቻ ቢኖር የእርሱም እናቱ ኾንሽ። አብ አንድ ዘር ቢኖረው ሙሽራው አደረገሽ። ያለ እናት ቢወልደው ያለአባት ወለድሺው። ታዲያ ምን ዓይነት ቤት ይችልሽ ኖሯል? እመቤታችን ሆይ በደጅ የተወለድሽው በገዛ እጅሽ ከአቅማችን ስለገዘፍሽ ነው።
እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለአንቺ ማደሪያ የሚበቃ ቤትም ሰውነትም አሁንም ገና አልሠራንም። ግን የጎደለባት ጓዳችንን ባለሽበት ማየትሽ አይቀርምና ውኃ ውኃ የሚለውን ኑሯችንን መዓዛ ወይን አርከፍክፊበት።

እንኳን ለልደታ ማርያም አደረሳችሁ!

Filed in: Amharic