>
5:16 pm - Sunday May 23, 2269

የጋዜጠኞች ፈተና በኢትዮጵያ [ደረጀ መላኩ]

በወርሃ ነሐሴ መጀመሪያ ቀናት በአንዱ አመሻሽ ላይ ከባልንጀራዬ ጋር በሰሜን ሆቴል ትይዩ ወደ አዲሱ ገበያ አቅጣጫ በማቅናት ላይ ሳለኹ ሚጢጢ የግሩንዲ ሬዲዮኔን በመክፈት የጀርመን ድምፅ የሚያስተላልፈውን የአማርኛ ዝግጅት ማዳመት ጀመርኩ፡፡ የእለቱ ፕሮግራም አዘጋጅ አቶ ተክሌ የኋላ ነበር፡፡ በማራኪ አቀራረቡ የሚታወቀው ጋሼ ተክሌ የእለቱን ዜና መፅሄት ርእሶች ሶያስተዋውቅ ጆሮዬን ቀስሬ ማድመጤን ተያያዝኩት፡፡ የዓለም ዜና በአየር ላይ ከናኘ በኋላ በእለቱ ከቀረቡት የዜና መፅሔት ርእሶች አንዱ የሆነው በኢትዮጵያውያን ጋዜጣና መጽሄት አሣታሚዎች ላይ የወረደውን የክስ ውርጅብኝ የሚያወሳ ነበር፡፡

ነፃ መንፈስ ባላቸው ጋዜጠኞች እና የድምፅ አልባዎች ድምፅ (the voice of the voiceless) ሊሆኑ የሚችሉ ጋዜጦችን የሚያሣትሙ ባለወረቀቶችን በማሸማቀቅና ውጥረት ውስጥ በመክተት የሚታወቀው ይህ የለየለት አምባገነን ሥርአት ፍትህ ሚኒስቴር በተሰኘው ተቋሙ አማካኝነት በፋክት፣ ሎሚ፣ እንቁ፣ ጃኖ እና አዲስ ጉዳይ መፅሄቶች እንዲሁም አፍሮ ታይምስ ጋዜጣ ላይ የክስ ሰበዙን እንደሚመዝ ለኢትዮጵያውያን ኹሉ አርድቷል፡፡ በእውነቱ ዜናው የሰውን ህሊና ያደማል፡፡

በዚች አገር ላይ የኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙኸን ያለምንም ጣልቃ ገብነት መቼ ነው ገቢራዊ የሚሆነው በምንልበት በዚህ ጨለማ ዘመን በጣት በሚቆጠሩት የህትመት ውጤቶችን ዓይናችሁ ላፈር እየተባለ መሞዘቁ ምን ይሉት ፈሊጥ ነው!? ይህቺ ሀገር የማን ናት? ከዘጠና ሚሊዮን በላይ የሚሆነውን ይህን ህዝብ የማንበብ ፍላጎት ለመንፈግ መነሣት ምን ይባላል? ኢትዮጵያን የእውነተኛ ጋዜጠኞች ምድረ በዳ ማድረጉ ለማን ይበጃል? እነዚህ ሰዎች ምንድን ነው የሚፈልጉት? በዚች ሀገር ላይ መንፈስ ድርቀት እንዲሠፍን ይፈልጋሉ፡፡ ይህ ህዝብ ድንገት ገንፍሎ ከተነሣ ማጠፊያው እንዳይጥረን እሰጋለኹ፡፡ አንድ ሰው ለመኖር ተመጣጣኝ ምግብ እንደሚያስፈልገው ሁሉ ለመንፈሱም ሚዛናዊ ዜና የሚያስፈልገው ይመስለኛል፡፡ ወደ ህሊናችሁ ተመለሱ፡፡ ለዚች ሀገር እና ለእናንተም ቢሆን የሚበጀው ነፃው ፕሬስና ነፃ መንፈስ ነው፡፡ በጉልበትም ሆነ በገንዘብ ኃይል፡፡

ነፃ ጋዜጠኖችንና መፅሄቶችን ከአራት ኪሎም ሆነ ከሌሎች ሥፍራዎች ልታጠፏቸው ትችሉ ይሆናል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና እውነትን እና ነፃ መንፈስን ከኢትዮጵያውያን አዕምሮና ልብ ውስጥ ለማጥፋት አይቻላችኹም፡፡ በተቃራኒው የነፃው ፕሬስ ህልውና ማክተም የስልጣን ዘመናችሁን ከማሳጠሩ ባሻገር ፍፃሜያችሁን መራር እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ ነፃ ፕሬስ ነፃ መንፈስ ከሌሉ በዚህች ሀገር ላይ የታሠበው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሊሠርፅ አይቻለውም፡፡ ቂም በቀልም ቤቱን ይሠራል፡፡

በኢትዮጵያ የነፃው ፕሬስ ህልውና ሞቶ እንዳይቀበር ስጋታቸውን ካሰሙት ውስጥ የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት (United Nations Human Rights council)፤ የኢትዮጵያ መንግስት በቅርቡ በግል የፕሬስ አሳታዊሚዎች ላይ ለመሠረተው ክስ ዝርዝር ማብራሪያ እንዲሠጠው መጠየቁን ከዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች ተሰምቷል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ ዝርዝር መረጃ እንዲሠጠው የጠየቀው የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ እንዳለው በክሱ ዙሪያ ትክክለኛ ምርመራ ለማድረግና አቋም ለመያዝ እንደሚያግዘው ገልፆ በክስ ሂደቱ ላይም የኢትዮጵያ መንግስት የገባውን የዓለም አቀፍ ስምምነቶች መነሻ በማድረግ ክሱ እንደሚከታተል ገልፀዋል፡፡

በተያያዘም ከሰሞኑ መንግስት በግል ፕሬሱ አሳታሚዎች ላይ ክስ መመስረቱ ከመጪው ምርጫ ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ ታዋቂው የእንግሊዝ መጽሔት ዘኢኮኖሚስትና ሪፖርተር ዊዛአውት ቦርደርስ የተባለው የጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪ ተቋም ግምቶቻቸውን ማስቀመጣቸውን ተሰምቷል፡፡ ከዚህ ባሻገር ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት አስጠባቂ ድርጅቶችና የኢትዮጵያን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተሉ ወገኖች በነፃው ፕሬስ ላይ የተመዘዘው ሠይፍ ወደ ሰገባው እንዲመለስ አበክረው ጠይቀዋል፡፡

በሌላ በኩል ሎሚ መጽሄት ቅፅ 3 ቁጥር 119 ነሐሴ 10 እትም በነፃው ፕሬስ ላይ ላይ ያነጣጠረው አፈና መንግስትንም፣ ሕዝብንም፣ ሀገሪቱንም እንዳማይጠቅም እንሚከተለው መክራ ነበር፡፡ ‹‹…ሰዎች የተለያየ ሀሳብ አላቸው፡፡ የተለያየ ሀሳባቸው መከበር፣ መደመጥ፣ መገለፅ አለበት፡፡›› በሌላ በኩል ‹‹ሀሳቦች ካልተገለፁ እና ካልተገበያዩ በስተቀር የሰዎችን አስተሳሰብ መግራትም ሆነ ማጎልበት አይቻልም፡፡ በተለይ በዚች ሀገር ዴሞክራሲያዊ መቀጠል ካለበት አገራዊ መግባባት መጎልበት አለበት፡፡ አገራዊ መግባባት በምንድን ነው የሚጎለብተው ከተባለ አገሪቱን ለመገንባት በሚያስፈልጉ መሰረታዊ እሳቤዎች ውስጥ የሀሣብ ግብይቱ እየጎለበተ ሲሄድ ነው፡፡ ብዙ ውይይት ብዙ ክርክር ብዙ ፅሁፍ ብዙ የተመቻቸነ እድል ሲኖር ነው፡፡ በዚህም መንፈስ ከወሰድነው ሚዲያዎችም የሃሳብ መገበያያ መድረኮች በመሆናቸው ይበልጥ መጎልበት አለባቸው፡፡ ሚዲያ እንዲኖርም ወይም እንዳይኖር በማድረግ አይደለም የምንጠቀመው›› ብሎ ነበር ሬድዋን ሁሴን በዘመን መፅሄት የሰኔ 6, 2006 ዓ.ም እትም ላይ፡፡ ጥሩ አሽሞንሙነውታል፡፡

ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ እንዲሉ አገዛዙ ጊሎቲኑን በመምዘዝ በነፃው ፕሬስ አጓገት ላይ ለማሣረፍ እየተቅበዘበዘ በሚገኝበት አስፈሪ ግዜ ላይ እንገኛለን፡፡ በእውነቱ ለመናገር አኹን በህትመት ላይ የሚገኙት የነፃው ፕሬስ ትሩፋቶች ትኹትና ወደ ልሥላሴነት (Liberal) የሚጠጉ ናቸው፡፡ እርግጥ ነው አካፋውን አካፋ ለማለት የማይሰንፉ ናቸው፡፡ ሆኖም ግን ጫፍ የያዘ ዘገባም ሆነ ትችት ለማቅረብ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ስነ ምድር አይፈቅድላቸውም፡፡ በአጭሩ የዜና ዘገባቸውም ሆነ የሚያቀርቡት ትችት ሚዛናዊ ነበር ማት ይቻላል፡፡

ዛዲያ ለመንድን ነው አገዛዙን እንቅልፍ የነሱት? እንደሚመስለኝ ህዝቡ እነርሱን ፕሮፓጋንዳ ከመጋት በቀር ከነፃው ፕሬስ መንደርም ሆነ ከሌሎች ነፃ ሬዲዮም ሆነ የቴሌቢዥን ጣቢያዎች የሚተላለፉ ቁምነገሮችን ማንበብም ሆነ ማዳመጥ እንዳይችል ለማድረግ ቆርጠው ተነስተዋል፡፡ ግን ግን ምን ያህል ታላቁን የኢትዮጵያን ህዝብ ቢንቁት ነው ከጋዜጣ አቅም እጁ እንዳይገባ መሰናክል ያበዙት? ሞኝ የእለቱን ብልህ የዓመቱን እንዲሉ ለጊዜው የነፃውን ፕሬስ ቤተሰቦች ሀዘን ላይ የጣሉ ቢመስላቸውም ውሎ አድሮ ነፃ መንፈስና ሃሳብ ማሸነፉ አይቀሬ ነው፡፡

ሁላችንም እንደምናውቀው ዘመኑ የመረጃ ዘመን በመሆኑ በብዙ ሺህ ማይል እርቀት የተፈፀመ ኹነት በደቂቃዎች ፍጥነት እኛ ጋር ይደርሳል፡፡ ስለሆነም የህዝቡን የማወቅ መብት ማንኛውም ምድራዊ ኃይል መከልከል አይቻለውም፡፡ የሚያዋጣው ቁጭ ብሎ መነጋገሩ ነው፡፡

የነፃው ፕሬስ ጋዜጠኞችና አሣታሚዎቻቸው ውጣ ውረድ
ባለፉት 23 ዓመታት ወደ ነፃው ፕሬስ ዓለም የገቡት ጋዜጠኞችና የጋዜጣው (መፅሄቱ) ባለቤቶች ወይም አሣታሚዎች ቁጥር ሲፈተሽ በጣሙን አስደንጋጭ ነው፡፡ አብዛኛው ባለ ሀብት ማለት ይቻላል ንዋዩን ማፍሠስ የሚፈልገው ትርፍ በሚዛቅበት የንግድ ዓይነት ላይ ነው፡፡ እርግጥ ነው አገዛዙ በፈጠረው ጫና ምክንያት አንዳንድ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎችን ለማቋቋም ሞክረው ሳይሆንላቸው ቀርቷል፡፡ ለምሣሌ ያህል ታዋቂው የህግ ተጠባቢ የነበሩት ጋሼ አበበ ወርቄ እና ጓደኞቻቸው የሬዲዮ ጣቢያ ለማቋቋም ፍቃድ ጠይቀው መሰናክሉ ስለበዛባቸው የሚወዷትን ሀገር ጥለው ተሠደዋል፡፡ በተረፈ ገንዘብ አለን የሚሉ ኢትዮጵያውያን የነፃውን ፕሬስ መንደር ለመቀላቀል የሞከሩ አይመስለኝም፡፡

ወደ ጋዜጠኞች ስንመጣም አንገትን የሚያስደፋ ነገር እናስተውላለን፡፡ የነፃው ፕሬስ ሻማ ከተለኮሰ ጀምሮ በርካታ አንጋፋና ወጣት ጋዜጠኞች ለዚች ሀገር ሲሉ ቢታሠሩም፣ ቢሠደዱም፣ አንዳደንዶች ደግሞ ውድ ህይወታቸውን ቤዛ አድርገው ቢያልፉም ሌሎች ሙያ አጋሮቻቸው የአገዛዙ አፈ ቀላጤ በመሆን ወርቃማ ጊዜአቸውን አጥፍተዋል፡፡ አንድ ቀን ግን የታሪክና የህሊና ተጠያቂ መሆናቸው አይቀሬ ይመስለኛል፡፡
ለማንኛውም የነፃው ፕሬስ አርበኞችን ላስቃኞችሁ፡፡ የነፃው ፕሬስ መከራ ሲታወስ የአጥቢያ ጋዜጠኛ መፅሄት አዘጋጅ ተጋድሎ የሚዘነጋ አይመስለኝም፡፡ “በአጥቢያ ኮከብ የህትመትና የማስታወቂያ ሥራ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር (አክፓክ)›› 1984 ዓ.ም ጀምሮ ትታም በነበረችው ጋዜጣ ባልታወቀ ምክንያት ቢሮዋ ነዶ በመቶ ሺህ ብር የሚቆጠር ንብረቷ ወድሟል፡፡ አንጋፋ ጋዜጠኞች ጋሼ ጎሹ ሞገስ፣ ሙሉጌታ ሉሌ፣ አረጋ ወ/ቂርቆስ፣ አንተነህ መርእድ፣ ታዬ በላቸው፣ ቅዱስ ሀብት በላቸው፣ ትእግስት አጥናፉ፣ አለማየኹ በየግዜው የእስርን ገፈት ቀምሰዋል፡፡ ጋዜጠኛ ብዙአየሁ ወንድሙና ጋሼ አንዳርጌ መስፍን መከራን ተቀብለዋል፡፡ ዝነኛው የኢትዮጲስ ጋዜጠኛ ጋሼ ተፈራ አስመራ፣ መፅሀፈ ሢራክ፣ ክበበው ገበየኹ ሀገሬ በሀገሬ እንዳሉ ክልትው ብለው ቀርተዋል፡፡
ጋዜጠኛ ከፍያለው ማሞ፣ ክፍሌ ሙላት፣ ሢሳይ አጌና፣ ቅዱስ ሀብት በላቸው፣ ደረጀ ሀገብተወልድ፣ በፍቃዱ ሞረዳ፣ ሠርክአለም ፋሲል፣ ታምራት ነገራ፣ መስፍን ነጋሽ ነቢዩ፣ ግሩም ተክለ ሀይማኖት፣ የአዲስ ጉዳይ መፅሔት አሣታሚ አቶ እንዳልካቸው ተስፋዬ፣ ምክትል ዋና አዘጋጁ ኢብራሒም ሻፊ፣ ከፍተኛ አዘጋጁ እንዳለ ተሸ እና በመፅሔቷ ላይ በአምደኝነት የሚሰራው ሀብታሙ ስዩም ስደት እጣ ፈንታቸው እንዲሆን በአስገዳጅነት ወስነዋል፡፡ ይቺ ምስኪን ሀገር በሌለ ጥሪት ያስተማረቻቸው አንጋፋና ወጣት ጋዜጠኞች የባእድ ሢሳይ የመሆናቸው ጉዳይ ሲታሰብ ህሊናን ያደማል፡፡ ይሄም ብቻ አይደለም ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲሠፍን የሚደረገው ሠላማዊ ትግል ተጠናክሮ ካልቀጠለ ኢትዮጵያ የእውነተኛ ጋዜጠኞች ምድረ በዳ ሆና መቀጠሏ አይቀሬ ነው፡፡

እስቲ አኹን ደግሞ ወደ ሥመ ገናናው ጋዜጠኛና የብእር ሰው እስክንድር ነጋ ልውሠዳችኹ፡፡ በእውነቱ ለመናገር የዚህን ሰው መንፈሣዊ ጥንካሬና የህሊና ሠውነት ለመግለፅ ቃላቶች ያጥሩኛል፡፡ ለዚህ ምዝብር ህዝብ ሲል ከዘጠኝ ግዜያት በላይ ወደ ወህኒ አምባ የተወረወረው አኹንም በእስር ላይ የሚገኘው እስክንድር ነጋ የዚህ ትውልድ ማርቲን ሉተር ኪንግ ነው፡፡ እስክንድር ለአሣሪዎቹ ሣይቀር የሚደማ ልብ ያለው ቅን እና ምንግዜም ታሪክ የማይረሣው ትንታግ ጋዜጠኛ ነው፡፡ ደፋሯ ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙም ሆነች ልበ ሙሉው ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ፣ የሱፍ ጌታቸው የኢትዮጵያ ነፃ ፕሬስ መከራ ሲዘከር ሥማቸው መነሳቱ አይቀሬ ነው፡፡
ተስፋ አለም ወልደየስ፣ ዞን ዘጠኝ በሚል ሥያሜ የታወቁት ጦማሪያን በዚህ ለጋ እድሜያቸው መከራን እየተቀበሉ የሚገኙት ለእናት ኢትዮጵያ ብልፅግና ሲሉ ነው፡፡ አልታደልንም እንጂ እንደ ናትናኤል የመሠሉ ባለ ብሩህ አእምሮ ወጣቶች ውሏቸው መሆን የሚገባው በምርምር ተቋም አሊያም ሀገርን በሚጠቅም ሙያ ላይ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ምሣቸው ሥደት ወይም በእግረ ሙቅ መታሠር ሆኗል፡፡ አይ አንቺ አገር!

አፈሩን ገለባ ያድርግለትና የምድር ጦር ኦርኬስትራ ባልደረባ የነበረው ጋሼ ታምራት ሞላ በዛ ዘመን አይሽሬ ጥዑም ድምፅ አንቺ ሀገር የሥደተኞች መጠለያ ትሆኛለች ብሎን ነበር፡፡ በሣንቲሙ ግልባጭ የኢትዮጵያን ድንግል መሬት ለመቀራመት እና ሀገሪቱን መፈንጫ ለማድረግ ከዓለም አካባቢ የተሠባሠቡ ቱጃሮች እንደ ጉንዳን እየወረሩን ነው፡፡ ቀን የጎደለባቸው ኢትዮጵያን ደግሞ እግራቸው ወደ መራቸው አቅጣጫ እየነጎዱ ነው፡፡ በእውነቱ ያማል፡፡

በፈርኦናውያን ዘመን ሰባት ዓመት የቆየ ረሃብ በግብፅ ገብቶ ነበር፡፡ መፅሀፍ ቅዱስ እንደሚነግረን ግብፅ በዚያ በረሃቡ ዘመን እንኳን ልትራብ የጎረቤት አገር ሰዎች እህላቸው የሚሸምቱት ከእዚያ ነበር፡፡ ይኸም የሆነበት ምክንያት ዮሴፍ የሚባል ብልህ ሰው ቀደም ብሎ አዝመራው በሰመረበት ዘመን ለክፉ ቀን የሚሆን እህል እንዲካተት ለንጉሡ ስለነገረውና ንጉሡም የዮሴፍን ምክር ስለተቀበለው ነው፡፡ ይኽንን የመሠለ አገር የሚጠቅም ሕዝብን ከእልቂት የሚያድን ምክር ስለሰጠው ምክሩን ራሱ ከሥራ ላይ እንዲያውለው ዮሴፍን ከእስር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ሾመው፡፡ ታሪኩ የሚነግረን የዮሴፍን ብልህነትና ንጉሡ ኃላፊነቱን በሚገባ ማወቁን ነው፤ የሕዝቡ መሪ ሕዝቡን ከችግር ከማዳን ሌላ ዋና ጉዳይ የለውም፡፡ ፈርኦን ይህ ከባድ ኃላፊነት ስለተሰማው እስከዚያን ቀን ድርስ አልባሌ ለነበረ (ያውም ለውጪ አገር) ሰው የጣቱን ቀለበት አውልቆ ሰጠው፤ ቀለበቱ ጌጥ አይደለም የንጉሡ ማህተም የቀረፀበት ሥልጣንን በእጅ ማድረጊያ ነው፡፡

የአገራችን መሪዎች ስብእና ስንመለከት ከመላ አዋቂዎች የሚሰጣቸውን ምክር ባለመቀበል ሃገራቸውን ለውድቀት እራሣቸውንም ለውርደት እንዳረጉ ስልጣናቸው መልቀቅ ግድ ሆኖባቸዋል፡፡ የቅርብ ግዜ ታሪካችን እንኳን በአንክሮ ብንመለከት የአፄውና የደርጉ ውድቀት ተመሣሣይነት አላቸው፡፡

የዚች አስተያየት መነሻ ሃሳብ ስለ ፈላጭ ቆራጭ መንግስታት አወዳደቅ ምክነያት መጎስጎስ ሳይሆን የኢትዮጵያ ነፃ ፕሬስ ጋዜጠኞች ባለፉት ሃያ ሶስት ዓመታት ለሀገር ጠቃሚ የሆኑ ነገሮችን እንደሠሩ አንባቢን ለማስታወስ ነው፡፡ ለምሣሌ ያህል የጎሣ ፖለቲካ ለዚች አገር ምንም እንደማይፈቅድ በግንባር ቀደምትነት የመከሩት እነዚህ የህሊና ሰዎች ናቸው፡፡ ጋዜጠኞች በተለያዩ የሀገሪቱ ማዕዘናት ግጭቶች ከመከሰታቸው በፊት የዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች መከበር አለባቸው ብለው ጮኸዋል፤ ፅፈዋል፡፡ ሆኖም ግን ለዚህ የተሰጣቸው ምላሽ ጦርነት ናፋቂዎች፤ አሉባልታኞች፤ ሽበርተኞች አብዮት ናፋቂዎችና የመሳሰሉት ነበሩ፡፡ በተቃራኒው የተናገሩት ነገር እውነት ሆኖ ታይቷል፡፡ እየተገባደደ ባለው 2006 ዓ.ም እንኳ በኢትዮጵያ ምን ያህል ግጭቶች ተከሰቱ? ስንት ንፁሃን ዜጎች ወልደው ከከበዱበት ቀዬ በግፍ ተፈናቀሉ? ህሊና ያላችሁን ጠይቁ፡፡

የኢትዮጵያ ነፃ ፕሬስ ጋዜጠኞች ትግላቸው ከድንቁርና፤ ከበሽታ፤ ከጎሰኝነት ከአድርባይነት ወዘተ ብቻ አልነበረም፡፡ ጓደኞቻቸው ዘብጥያ ሲወርዱ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ጮኸዋል፡፡ እኒህ ጋዜጠኞች በዓይን የማይታይ ረቂቅ መሳሪያ (የመንፈስ ጥንካሬ) አላቸው፡፡ ለዚህም ነው፤ የራሳቸውን አንባቢ ለመፍጠር የቻሉት፡፡ የአገሪቱ ህዝብ ቀረጥ የሚከፈልባቸው የኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙኃን ባለፉት 23 አመታት በብዙ መልኩ የነፃውን ፕሬስ ለማዳከም ያልበጠሱት ቅጠል ያልቆፈሩት ጉድጓድ የለም፡፡ ከዚህም እልፍ በማለት የስም ነፃ ፕሬስ በግብር ግን የአገዛዙ የፕሮፓጋንዳ ደጋፊዎች የሆኑ አንዳንድ ጋዜጠኞች (መፅሔቶችም) ብቅ ብለው ነበር፡፡ ሆኖም ግን አንባቢው ፊት ስለነሳቸው እራሳቸውን ከነፃው ፕሬስ መንደር ገሸሽ አድርገዋል፡፡ እነኚህ ሁሉ አንድ ቀን እውነትን ይቅርታ እንደሚጠይቁ ተስፋ አድርጋለሁ፡፡
እውቁ የክቡር ዘበኛ አቀንቃን የነበረው ጋሼ ጥላሁን ገሰሰ ዘመን አይሽሬ በሆነው ጥኡም ድምፁ
ውሸት ለመናገር አትሻም ምላሴ፤
ለእውነት እሞታለሁ አልሳሳም ለነብሴ፡፡

በማለት እንዳዜመው ሁሉ የኢትዮጵያ ነፃው ፕሬስ አርበኞች ለእውነት ሲሉ በእውነት ኑረው፤ በእውነት ምክንያት ለመታሰር፤ ለመሰደድ ወይም ውድ ህይወታቸውን ቤዛ አድርገው ለማለፍ የተዘጋጁ በመሆናቸው አገዛዙ የፕሮፓንዳ አታሺዎች (ቃፊሮች) ትችት ወይም ማስፈራሪዎች ምክንያት የተነሳ ልባቸው አልደነገጠም፤ ጉልበታቸው አልራደም፡፡ እውነት ሰባኪዎች በመሆናቸው የነፃው ፕሬስ ቤተሰቦች ቁጥር አሻቀበ እንጂ አልቀነሰም፡፡

ታላቁ የፈረንሳይ ንጉስ ናፖሊዎን ከአንድ ብርጌድ ጦር ይልቅ የአንድ ጋዜጠኛ ብዕር ያስፈራኛል፤ እንዳለው የኢህአዴግ አገዛዝም የኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙኃንን እና ህትመት መሳሪዎችን በመዳፉ ይዞ እንዲሁም የሀገሪቱን አንጡራ ሀብት እንደፈለገው እየተጠቀመ፤ ብረት አንግቶ፣ ከ20 ሺ ወይም ከሰላሳ ሺህ በላይ ኮፒ ማሳተም የማይችሉ ነፃ መንፈስ ያላቸው ጋዜጠኞች እንቅልፍ ይነሱታል፡፡ ለዚህም ነው እነኚህ ልበ ሙሉ ጋዜጠኞች ላይ ጊሎቲኑን እየመዘዘ የሚያሳርፈው፡፡ በምን ያህል ጥልቀት ነው የህዝቡን ስነ ልቦና የመዘኑት? የታደሉት በራቸው ድረስ ቁጥር ስፍር የሌላቸውን ጋዜጦች (መፅሄቶች) እየመጣላቸው በሚያነቡበት አለም፤ የኢትዮጵያ ህዝብ በገንዘቡ ጋዜጦችን ገዝቶ እንዳነብ ይኼ ሁሉ ትብታብ ለምን አስፈለገ? ከዚህ በላይ ብሔራዊ ውርደት ያለ አይመስለኝም፡፡
የነፃ ፕሬስ ጉዳይ የእውነተኞች ሰላማዊ ታጋዮች ወይም የጋዜጠኞች ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ ጉዳዩ የኢትዮጵየ ህዝብ ጉዳይ ነው፡፡ የሰውነት ጉዳይም ነው፡፡ ስለሆነም በፋክት፣ ሎሚ፣ አፍሮ ታይምስ፣ አዲስ ጉዳይ፣ ጃኖ የህትመት ባለቤቶች ላይ የተመዘዘው ሰይፍ ወደ ጊሎቲኑ እንዲመለስ በሰለጠነ መንገድ መጠየቅ ይገባናል፡፡
የኢትዮጵያን ትንሳኤ ለማየት ያብቃን!

አቶ ደረጄ መላኩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ናቸው፡፡ ኣስተያየት ካለዎት  Tilahungesses@gmail.com ይላኩላቸው

ምንጭ: ነገረ ኢትዮጵያ

Filed in: Amharic