>
2:53 am - Wednesday February 1, 2023

''እስካሁን ኢህአዴግን ከሚያውቁት ሰዎች የተሻለ እና የታቀደ መጽሃፍ የመለስ ቱሩፋቶች ነው''[ሶሊያና ሽመልስ ገ/ማሪያም]

አቶ Tam must listen ብሎ የኤርሚያስ ለገሰን  ኢንተርቪው ካጋራ ጊዜ ጀምሮ ለማንበብ የፈለኩትን የመለስ ቱሩፋቶች አንብቤ ጨርሼ ስገርበው ቆየሁ፡፡
( ከነበፍቄ እና አቤል ትዝታ ጋር- አብርሃም ገብረመድህንን ጆሮዪ ላይ ሰክቼ “አንቐውታን” እየሰማሁ፡፡ እኔና በፍቄ በጋራ በተደጋጋሚ ለረጅም ጊዜ የሰማናቸው ዘፈኖች የአብርሃም “አንቐውታን” እና የጸጋዩ እሸቱ “እስቲ ዶሴው ይውጣ የምከሰስበት”ለ የሚለው ዘፈን ይመስለኛል፡፡) አንቀውታን የማስታውሰው በፍቄ አፍሪካ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ባንጁል ለስብሰባ ሄዶ እስኪመለስ ድረስ አስቸገረ፣ ምእራብ አፍሪካ አገሮችን እያጣጣለ ይጽፍልን ነበር፡፡ እነጋምቢያም ከኢትዮጲያ እኩል አገር ይባላሉ እያለ፣አብረውት ያሉ የውጪ ዜጎችን ማዋራት እስኪደክመው ድረስ በሳምንት ውስጥ አዲስ አበባ ናፈቀችው ሲመጣ ቦሌ ላይ ተገናኘን ፣ ወይኔ አማርኛ ወይኔ አገር ……ከቋንቋ ቋንቋ ከአገር አገር የላቸው ልቤ ተሰቀለ እኮ አዲስ አበባ እስክገባ ድረስ ብሎ አሳቀን …..የአብርሃም ዘፈን ቃል በቃል ያንን የሚል ቃል ነበረው አብረን ደጋግመን ስንሰማው የምእራብ አፍሪካ ጉዞውዎቹን እያነሳን አንስቅ ነበር፣ አሁን ያ ጉዞው የሽብር ወንጀሉ ማስረጃ ነው)

Ye-Meles-Turufawoch-Book-300x300የመለስ ቱሩፋቶችን ሳነብ ዞላ (ዘላለም ክብረት) እያነበበ ሊያሾፍ የሚችልበት ታሪክ ብዛት በፍቄ (ዘ-በፍቃዱ ሃይሉ)እየተናናደደ ሊል የሚችለው፣ አቤል ደውሎ ገጽ እንትን ላይ ያለውን ታሪክ አይተሽዋል? በናታችሁ አንገናኝና እናውራበት የሚለውን እያስታወስኩ ……..አንዳንድ ቦታ ፈገግታ ብዙ ቦታ መገረም ሌላ ቦታ ተሰብስቦ ስለመጽሃፉ የማውራት ጉጉት ተደራርበውብኝ አለቀ፡፡

አዲስ አበባ – መጽሃፉ ራሱን በአዲስ አበባ መገደቡ በጣም ጥሩው ነገሩ ይመስለኛል፡፡ የተገደበው scope በደምብ አደርጎ መረጃ አንዲሰጠን ረድቷል ብዪ አስባለው፡፡ ኤርሚያስ ብዙውን ዘመን የአዲስ አበባ ካድሬ ቢሆንም ከዚያም ውጪ በፓርቲ ቅርበቱ ብቻ የሚያውቃቸው ብዙ ነገሮች ይኖሩታል፡፡እነሱን ብዙም ሳይቀላቅል አዲስ አበባ ላይ መጽሃፉን መገደቡ መረጃውን ተጨባጭ አንዲሆን በማስረጃ አንዲያግዘውም ረድቶታል፡፡ አዲስ አበባ ላይ ጥናት መስራት የሚፈልግ መልካም አስተዳደሩ ላይ ጥናት ለሚያደርግ መጽሃፉም ሆነ ኤርሚያስ ጥሩ ሃብቶች ናቸው ፡፡( ወይ አዲስ አበባ ወይ አራዳ ሆይ ከተማም እንዳንቺ ይጨቆናል ወይ እያሉ ዳታውን ማቀናበርም ይቻላል)፡፡ነጥብ ባለመሳት ከጀርባ ያለውን የህግ እና የፓለቲካ ኢንቴንሽን በመረዳት ረገድ የኤርሚያስ ጥሩ ካድሬ እነደነበር አስመስክሯል፡፡

የምን ተስፋየ ገብረአብ?– የውስጠ ፓርቲ የሃይል ሚዛኑን አስመልክቶ ማወቅ የሚፈልጉ የፓወር ስትራክቸር አና አተረጓጎምን ማወቅ ለሚፈልጉና ለሚስባቸው መነበብ ያለበት ወሳኝ መጽሃፍ ነው፡፡ የኢህአዴግን የስልጣን ተዋረድ ተከትሎ አዋቂ ነን ባዮችን ሳይቀር ሊያነቡት የተቃዋሚ ሰዎችም(የምር ካሉ)ሊጠቀሙበት የሚገባ መረጃ አለው ብየ አስባለው፡፡ በብዙ ነገሮች ቢታጨቅም በፈርጅ በፈርጁ እየከፋፈሉ መተንተን ይቻላል፡፡ እስከዛሬ በተሻለ መልኩ ራሱን የውስጥ ወሬዎች አዋቂ አድርጎ የሚያቀርበው ተስፋዩ አንኳን ሃሳቡን በመቅረጽ ደረጃ ብዙ ልዪነት ባይኖረውም ኢህአዴግንም ሆነ ህወሃትን በማወቅ ረገድ ግን በጣም ሩቅ እነደሆነ የኤርሚያስን መጽሃፍ ያነበበ ይረዳል፡፡ ተስፋየ ከተቆራረጡ ታሪኮች እና እውነትን መሰረት ካደረጉ አሉባልታዎች ውጨ የረባ ነገር አልነገረንም ….አሁን እሱ ራሱ የኤርሚያስን መጽሃፍ እንደሚያነብ አስባለሁ(ብዙ መረጃ ይሆነዋል)። በነገራችን ላይ ከኤርሚያስ መጽሃፍ የተቀረጸበትን መንገድ የወደድኩት የግለሰቦች እና የሰዎች ታሪኮችን ምእራፎቹ የሚያስተላልፉትን መልእክት ደግፈው ስለሚከተሉ ነው ፡፡ አንዳንድ ሃይማኖት ተቋማትን ተከትሎ ያነሳቸው ሃሳቦች በተሻለ እና በሰፌው ሁኔታ ፍሬም መደረግ ይችሉ ነበር ብየ ባስብም (ከሲኖዶሱ ጋር የተሰረገው ስብሰባ ታሪክ ጮክ ብሎ አስቆኛል፣ ሬድዋን መርቅኖ ውሃ የተሞላ ኮንዶም ይዞ ቆሞ ፌቴ ላይ ድቅን ይላል) በአጠቃላይ ግን በይዘትም በጥራትም በስነስርአትም የምን ተስፋየ ገብረአብ ነው አስብሎኛል፡፡

ሬስት ኢን ፒስ አርከበ እቁባይ ! በዚህ መጽሃፍ ከተጋለጡ ታላላቅ ማንነቶች መካከል በአርከበ ደረጃ ያለ አይመስለኝም፡፡ እኔ መቼም አንደ አዲስ አበባ ነዋሪ በጣም ታዋቂ እና ተወዳጅ ከነበሩ ጥቂት የኢህአዴግ ሰዎች አንዱ እንደነበር ነው የማስታውሰው፡፡ በተቃራኒው ይህ መጸሃፍ ከአመጣጡ እስከአካሄዱ በተጨባጭ ማስረጃ የአርከበን ግብአተ-መሬት ፈጽሞኣል፡፡ በፓርቲው እና በህዝብ መካከል ያለውን ልዩነት ለመረዳትም የውስጡን አርከበና የውጪውን አርከበ ልዩነት ማየት ይበቃል ፡፡ (አንዲሁ ስንሸዋወድ መኖራችንን ማወቃችንም አነድ ነገር ነው )ከመለስ ቀጥሎ እነደ አርከበ መጠቅለያውን አሰማምረው የሸጡልን ሰው መቼም የለም፡፡

ኤርሚያስ በምን ይለያል? – እስካሁን የኢህአዴግ ከፍተኛ ባለስልጣናት ከፓርቲው ሲለያዩ በተወሰነ መልኩ መጽሃፍትን ለመጻፍ ሞክረዋል፡፡ አብዛኛዎቹ ራሳቸውን ከመከላከል በመነጨ እንደጻፉ ይሰማኛል፡፡ሌሎች ደሞ የሚረባ ነገር ሳይነግሩን መጽሃፉ ያልቃል፡፡ እስካሁን ኢህአዴግን ከሚያውቁት ሰዎች የተሻለ እና የታቀደ መጽሃፍ የመለስ ቱሩፋቶች ነው ለማለት እደፍራለሁ፡፡መረጃና ስነምግባርን የጠበቀ፡፡ራስን ወደ መከላከል ያላዘነበለ፡፡ ተቃዋሚ ቢኖረን ኖሮ መጽሃፉን እና ሃሳቦቹን በማባዛትና መረጃዎችን በመስጠት ብቻ ብዙ አድቫንቴጅ መውሰድ ይችሉ ነበር፡።( የሰሞኑን የአቶ ገብሩ አስራት መጽሃፍ የተለየ አንደሆነ አላውቅም)

በመጨረሻም – ኤርሚያስ ተግዳሮቶች የሚኖሩበት ይመስለኛል ፡፡ የተለመደ ራሱም ተጠያቂ ነው፣ ተልኮ ነው ምናምን የሚሉ አቅጣጫና ሃሳብ የሚቀይሩ ስዎች ላይ የሚቀርቡ ጉንተላዎች አይጠፉም፡፡ ለዚህም በሰጣቸው ቃለ-መጠይቆች ሁሉ ራሱን ከተጠያቂነት አለማሸሹ ቢረዳም …..ትከሻውን አደንድኖ ጊዜ ወስዶ ወደ አደባባይ እንደወጣ ተወደደም ተጠላም አንዲህ አይነት መጽሃፍትና ሰዎች ፍቃደኛ ሆነው ወደ አደባባይ ሲወጡ የሚያሳድሩት ተጽእኖ ቀላል አይደለም፡፡ ትላንትና ስለመጽሃፉ ስናወጋ አንዱ ወዳጄ ተቃዋሚው የመረጃ ድርቅ ስላለበት ኤርሚያስ መረጃ ላይ የመመርኮዝ እድሉ በጣም ሰፌ ነው፡፡ መረጃውም ሆነ ትንታኔው ትንሽ ስህተት ካለውም በዛው መጠን affect ያደርጋቸዋል አለኝ፡፡ ተቃዋሚዎች የምራቸውን ካሉ መረጃውንም ሆነ ትንታኔውን ለሚገባ የትግል ስትራቴጂ መጠቀም የነሱ የቤት ስራ ነው፤ እሱ ምን ያድርጋቸው አልኩት፡፡ የወዳጄን ስጋት ብረዳም ገና ለገና የተቃውሞው ጎራን ሃላፊነት ለግለሰቦች ማሸከም አግባብ አልመሰለኝም ፡፡
ደጋግሜ በበጎ መልኩ ሳነሳው የተጠያቂነትን ጉዳይ አንስተው ለረጅም ሰአት የሞገቱኝም አሉ፣ እኔ በአጠቃላይ መሰረት ያለው ስትራቴጂ ላይ ያልቆሙ የተቃውሞ መንገዶችን ፊት አልሰጣቸውም ፡፡ብዙ ኤርሚያሶችን የማግኘትን ስትራቴጂ አንደ አንድ ነገር ወስደን ሌላው ቢቀር ተጠያቂነቱ የሩቅ ጉዳይ አድርገነው ፣ አፌን እየከፈትኩ እየሳቅኩና እየተገረምኩ ላነበብኩት መጽሃፍና ለጨመረልኝ የኢትዪጲያን ውስብስብነት መረዳት ስል ቢመሰገን አይበዛበትም፡፡

(በነገራችን ላይ ኤርሚያስን የማውቀው ከህግ ትምህርት ቤት ተመርቀን (2000 አም) ላይ የመንግስትን ፓሊሲ ለመሰልጠን በገለልተኛው የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር የተጠራ ስብሰባ ሚኒልክ ት/ቤት ሁለተኛ ቀን ላይ የመንግስትን ፓሊሲ ለማሰልጠን የመጣ ሰው ሆኖ ነው፡፡ (ያኔ ኢህአዴግ ጽህፈት ቤት የነበረ ይመስለኛል)፡፡ ዩኒቨርሲቲ ምሩቃንን ለማሰልጠን ትክክለኛ ምርጫ ነበር፡፡ ሁለት ውጤታማ ካርዶችን ደጋግሞ ተጫውቷል፡፡ አንደኛው ወጣትነቱን ሲሆን ሁለተኛው በየመሃሉ መነበብ ያለባቸው መጽሃፍት እያለ የመጽሃፍት ስም ይጠራል( who moved my cheese አንዱ ትዝ የሚለኝ ነው ) ወጣትነት እና የተማረ ሰውነት ካርድ እየተጠቀመ በ97 ቂም የያዝን ልጆች ቢያንስ 4 ቀን ሙሉ የሚያወራውን ሰምተነዋል ፡፡)

በመጨረሻም በጣም የገረመኝ ሰዎቹ ምን ያህል በስልጣናቸው መረጋጋት ቢተማመኑ ነው በውስጥ ፓለቲካ ውስጥ እንዲህ ተዘፍቀው የሚኖሩት? የኢህአዴግ የስልጣን መደላደል ምንጭና የውስጥ ፓለቲካውን ሚዛን አስመልክቶ መጠናት የሚገባው ሌላ ትልቅ ገጽ ያለ ያመስለኛል፡፡

አገር ቤት ያላችሁ ወዳጆች ቅሊንጦ ሄዳችሁ ታሪኩን ለዞላ የምታጋሩት ከሆነ( የሬድዋን ኮንዶም የሚል አሪፍ አርቲከል ጽፎ በሳቅ ፈነዳን ነበር) ለበፍቄ በምእራፍ ከፋፍላችሁ ለመንገር ቃል ከገባችሁ ከአሸባሪ መጽሃፍ መቀበልም ካልፈራችሁ መጽሃፉን ለማጋራት ፍቃደኛ ነኝ፡፡ #‎FreeZone9bloggers‬

Filed in: Amharic