>

ይህ ሕዝብ የዋዛ አይመሰላችሁ …  (ለራስ ያልተፃፈ ደብዳቤ ቁ.3) ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን

ይህ ሕዝብ የዋዛ አይመሰላችሁ

(ለራስ ያልተፃፈ ደብዳቤ ቁ.3)
ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን
ይሕ ሕዝብ
አፄ ቴዎድሮስን ወልዶ የበላ፤ የአፄ ዮሐንስን አንገት ያስቆረጠ፤ በእምዬ ምንሊክ ሐውልት ላይ ቁማር የሚጫወት፤ አባባ ጃንሆይን (ሥዩመ-እግዚአብሔር) አንግሶ ያዋረደ፤ ቆራጡን መሪ ጓድ መንግሥቱ ኃይለማሪያምን አንቆራጦ ያባረረ (በቁሙ አስቀምጦ ቲያትር የሚያሳይ)፤ ታጋይ መለስ ዜናዊን ያስደነገጠ (አስደንግጦ የገደለ የሚሉም አሉ)፤ እንደሠራ አይገድል!
መሪዎቹን የሚፈራ- መሪዎቹን የሚጠላ
መሪዎቹ የሚፈሩት-መሪዎቹ የማይወዱት ፡፡ (No love lost between them)
ሠምና ወርቅ የሆነ ሕዝብ ነው፡፡
ይሕ ሕዝብ፡-
ፍቅሩንም ጥላቻውንም በሆዱ የሚፈጅ ምሥጢረ ሥላሴ የሆነ ሕዝብ ነው፡፡
ይሕ ሕዝብ፡-
አድዋ ላይ ነጭ ተራ ፍጡር መሆኑን ያስመሰከረ፡፡ “ጥቁር ሠው” የሠው ዘር መገኛ ብቻ ሳይሆን ከሌላው ዕኩል መሆኑን ያረጋገጠ ኩሩ ሕዝብ ነበር፡፡
ይሕ ሕዝብ፡
ክፉ ቀንን ያለፈ፤ ከ66 የተረፈ፤ 77 ትንም 97ትንም ያያ… ተአምረኛ ሕዝብ ነው፡፡
ይሕ ሕዝብ፡-
ለኮሪያ የዘመተ፤ ማንዴላን ያሠለጠነ፤ ለአፍሪካ የነፃነትና የባንዲራ እርሾ ያበደረ… ገራሚ ሕዝብ ነበር፡፡
ይሕ ሕዝብ፡
እየሱስ ክርስቶስ ሲጠመቅ ቆሞ የመሠከረ፤ ሞስሊሞች ሲሳደዱ ያስጠጋ፤ በመጽሐፍ ቅዱስ እስከ ቱንት የተጠቀሰ፤ በቅዱስ ቁራን የተወደሰ፤ በእየሩሳሌም ርስት ያለው፤ለነብዩ መሐመድ አዛን ያለ፤ የጠገበ መንፈሳዊ ታሪክ ያለው ሕዝብ ነው፡፡
ይሕ ሕዝብ፡-
የአክሱም ሀውልትን ያቆመ፤ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ያነፀ፤ የጎንደር ቤተ-መንግሥቶችንና የሐረር ግንቦችን የገነባ አሪፍ ሕዝብ ነበር፡፡
ይሕ ሕዝብ፡-
ንጉሡ ጥለውት ጠፍተው (ተሰደው) ለራሡ የጎበዝ አለቃ በመፍጠር ፋሺሽቶችን ተዋግቶ አገሩን ነፃ ያወጣ፤ መንግሥቱም (ኃይለማሪያም)ወደ ዚምባቡዬ ሪፈር በተባለ ጊዜ ራሱን በራሱ ያስተዳደረ ጨዋና ንጉሡ ከሥደት ሲመለሱ አልጋውን ያስረከበ የዋህ ሕዝብ ነበር (አይገርምም?)፡፡
 
ይሕ ሕዝብ፡-
በራሡ ቋንቋ ፍቅሩን አስከመቃብር የጻፈ፤ ሼክስፒርን ፈቶ የመግጠም ፀጋ (ዬ) የተሠጠው ሕዝብም ነው፡፡
ይሕ ሕዝብ፡-
በቅዱስ ያሬድ በኩል ከሠማየ ሠማያት የመልአክትን ዝማሬ ሰምቶ ዜማ የሠራ ዜመኛ ሕዝብ ነው፡፡ (ሞዛርት የለ -ቬቶቨን የት ነበር? ወፍ የለም)
ይሕ ሕዝብ፡-
ጦርነትን በባዶ እጁ እንዳሸነፈ ሁሉ ኦሎምፒክንም በባዶ እግሩ ድል ያደረገ ጉደኛ ሕዝብ ነው፡፡ (ሮም ሁለቴ ጉድ ሆነች እንዳሉት የአውሮፓ ወሬኞች…)
ይሕ ሕዝብ፡-
የዓባይን ልጅ ውሀ ጠማው ተረቱን እያደሰ ሱዳንን አልፎ ግብፅን እስከ ሲናይ በርሀ ውሃ የሚያጠጣ ሳይተርፈው የሚቸር ውሃ የሚያደርግ ሕዝብ ነው፡፡
ይሕ ሕዝብ፡-
ሌላው የአፍሪካ ሕዝብ የቀኝ ግዛት እባጩ ንፍፊት ሳይፈነዳለት አብዮት ያፈነዳና እውነተኛው መንገድ የእኔ ብቻ ነው ብሎ ባላብ አደርና በወዛደር በእናቸንፋለንና በእናሸንፋለን ጎራ ለይቶ አንድ ጥይትና ወጣት እስኪቀር ድረስ የሚጫረስ ግራ የገባው-ግራ -ዘመም ሕዝብ ነበር (ው)፡፡
ይሕ ሕዝብ፡-
ከእናቱ ልጅ ይልቅ በመጽሐፍ ለሚያውቃቸው አብዮተኞች በማድላት ወንድሙን የሚገድል፤ አገር ለመገንጠልና ለማስገገንጠል እስ-በሱ የተጫረሰ ጉደኛ ሕዝብ ነው፡፡ የሆነው ሆኖ…
ይሕ ሕዝብ፡-
መሪዎቹን የሚፈራ- መሪዎቹን የሚጠላ
መሪዎቹ የሚፈሩት-መሪዎቹ የማይወዱት ፡፡
ሠምና ወርቅ የሆነ ሕዝብ ነው፡፡
ፍቅሩንም ጥላቻውንም በሆዱ የሚፈጅ ምሥጢረ ሥላሴ የሆነ ሕዝብ ስለሆነ በቅጡ ግዙት፡፡
Filed in: Amharic