>
5:13 pm - Tuesday April 19, 5504

የኮረና ቫይረስ የተፈራረቀበት አሳዛኝ ቤተሰብ! (ወሰን ሰገድ ገ/ኪዳን)

የኮረና ቫይረስ የተፈራረቀበት አሳዛኝ ቤተሰብ!

ወሰን ሰገድ ገ/ኪዳን
የምታስታምማቸው እሷ ነበረች። ለጋ ወጣት ናት። የ17 ዓመት ለጋ ወጣት። ፊቷ ለምለም፤ ንግግሯ የሚጥም። የቪኦኤዋ ጋዜጠኛ ፂዮን ግርማ በወርሃ ሚያዝያ አጋማሽ (April 23) እናቷ ወ/ሮ ሰብለወንጌል በኮቪድ በተያዘች ወቅት ያሳለፈችውን ጊዜ  በተመለከተ ቃለመጠይቅ ስታደርግላት ነበር በቪዲዮ ያየኋት፦ ሐናን ሙስጠፋን።
.
ዛሬ፦
ግንቦት 2/2012 ምሽት ፂዮን ግርማ “የእናቶችን ቀን” ሰበብ አድርጋ ሶስት እናቶችን አነጋገረች። ሶስቱም  የኮቪድ ተጠቂ የነበሩና ያገገሙ ናቸው። በአሜሪካ ሳውዝ ዳኮታ ነዋሪ ናቸው።  ወ/ሮ ሰብለወንጌል፤ ወ/ሮ መርከብ ደምሴ፣ ወ/ሮ መድኃኒት ተክሉ ይባላሉ። ሁለቱ በሳውዝ ዳኮታ ሲፎልስ ከተማ በሚገኘው የስሚዝፊልድ ሥጋ ማቀነባበሪያ ይሰሩ ነበር። ወ/ሮ መድኃኒት ግን ሥራ አይሰሩም ነበር። ሥጋ ማቀነባበሪያው ውስጥ ይሰሩ ከነበሩት ባለቤታቸው ነው ቫይረሱ የተላለፈባቸው።
.
ሶስቱም ሴቶች በአሁኑ ወቅት ተሽሏቸዋል። በደንብ እያገገሙ ነው። ዛሬ ምሽት ለሕክምና ተለይተው የነበረበት 14 ቀናት እንዴት እንዳሳለፉት ነበር የተናገሩት። በዚህ መሃል ወ/ሮ መድኃኒት የተናገሩትን በሰማሁ ጊዜ አዘንኩ። እናም ተክዤ ቀረሁ።  በትካዜዬ ውስጥ ሆኜ የሀናንን ውብ መልክ ለማስታወስ እየሞከርኩ የተናገሩትን ቃል ማመንዠክ ጀመርኩ።
.
“እኔ” አሉ ወ/ሮ ሰብለወንጌል።
“…እኔ 14 ቀን ቆይቼ ነበር የወጣሁት። የማስተላለፍ አቅምሽ ተዳክሟል። ስለዚህ ከልጅሽ ጋር መገናኘት ትችያለሽ ብለውኝ ነበር የወጣሁት። በምን አጋጣሚ እንደተከሰተ አላውቅም አሁን ደግሞ እሷ (ልጄ) ፖዘቲቭ ተብላለች” አሉ።
.
ሐናን ሙስጠፋ ….
የ17 ዓመት ለጋ ወጣት ነች። ለወ/ሮ ሰብለወንጌል ብቸኛ ልጅ ነች። ብቻቸውን ነው ያሳደጓት፦ ያለ አባት።  ሐናን ተማሪ ነች። በትርፍ ሰዓቷና ቅዳሜ እና እሁድ ትሰራ ነበር። እናቷ መታመማቸውን በሰማች ጊዜ ደንገጠች። ያን ቀን የሆነችውን እንዲህ ብላ ነበር የገለፀችው፦
.
 “….ጭንቅላቴ መስራት አቆመ። ወደ ኮምፒውተሬ መሄድ አልቻልኩም።….ክፍሌ ውስጥ የማርያም ስዕል ነበረ። ወደዛ (ወደማርያም) ዞር አልኩና አለቀስኩ።….”
.
ሐናን ይህንን ያለችው በሚያዝያ አጋማሽ (April 23) እናቷ መዳናቸውን በተመለከተ ለቪኦኤ በሰጠችው ቃለምልልስ ነበረ። እናቷ ወ/ሮ ሰብለወርቅም የልጃቸውን እንክብካቤ አወድሰው ጥንካሬዋን መስክረውላት ነበር።
.
ዛሬ ደግሞ ወይዘሮ ሰብለወንጌል እንዲህ አሉ ልብን በሚሰረስር ድምፀት፦
.
“…ልጄን ራሷን ብዳብሳት፤ አይዞሽ ብላት ባፅናናት ደስ ይለኝ። ግን ይኼን ማድረግ አልችልም፤ …. ያኔ የእናቴን ሕመም ለእኔ ያድርገው የምትለው እሷ ነበረች። አሁን ደግሞ እኔ፣ የእሷን ሕመም ለእኔ ያድርገው እያልኩ ነው… “.
.
ያሳዝናል።
ሐናን ሙስጠፋ አሁን ራሷን ለይታ በክፍሏ ውስጥ ነው ያላቸው። እናት ደግሞ በተራቸው እያስታመሟት! እንዲህ ዓይነቱ ክስተት ያሳዝናል። ክስተቱ ደግሞ ሲደጋገም የበለጠ ያስከፋል።
.
እግዚአብሔር ይማርሽ ሐናን!!!!
ምንጭ:- የቪኦኤ
Filed in: Amharic