>
8:23 am - Saturday December 10, 2022

በክህደት የተሞላው የበቀለ ገርባ ወለፈንዲ!!! (ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው)

በክህደት የተሞላው የበቀለ ገርባ ወለፈንዲ!!!

ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው
* “ስለ ወያኔ የሚነገሩት ሁሉ ውሸት ናቸው!”
አቶ በቀለ ገርባ
በቀለ ትህነግ እስር ቤት ውስጥ ድብደባም ሆነ በማንነት ጥቃት እንደማያደርግ ሲከራከር ሰማሁት።  አብዛኛው ውሸት ነው ሲል ተከራክሯል። አልተደበደብኩም ማለት መብቱ ነው። ራሱ ነው የሚያውቀው።  ነገር ግን ስለ ህወሓት አረመኔነት የሚወራው አብዛኛው ውሸት ነው ብሏል። የሌሎቹንም ጨምሮ።
 ራሱ ማዕከላዊ እያለ በርካታ ኦሮሞዎች ተጎድተዋል።  ከዮናታን ጋር ከመደብደቢያው ስር ታስረው በስቃይ ጣር እንቅልፍ ሲያጡ “መደብደብ አቁሙ ወይንም እኛን ቀይሩን ብለው ጥያቄ አቅርበዋል።” እነሱ ታስረውበት ከበረው ጥግ የነበሩት ሴቶች መካከል አንዲት “ባልሽ ከኦነግ ጋር ይሰራል” የተባለች ሴት ለአራት ተደፍራ ተብሎ በምርኩዝ የመንበርከክ ያህል ተጎንብሳ ስትሄድ ያውቃል። የተኮላሹ የኦሮሞ ወጣቶችን ያውቃል። ሌላው ቀርቶ ጆሮውን ያሳጡት ወጣት፣ ለ43 ቀን የተደበደበ መምህር፣  እንዲሁም ሲገለብጡት የነበረ ወጣት የኦፌኮ አባላት ናቸው። ወጣቶች አስተኝተው ሲረግጧቸው የሚያድሩት ሽማግሌዎች ይህን ሲሰሙ ምን ይሉ ይሆን? በድብደባ እስር ቤት ውስጥ ሕይወቱ ያለፈው አርማዬ ዋቄ አባትና ባለቤቱ ምን ይሉ ይሆን? ጦር ኃይሎች ወስደው ያኮላሹት፣ ማዕከላዊ መጥቶ ስብሰባ ላይ አኮላሽተውኛል ሲል ተክላይ ጨለማ ቤት ያስገባው የሀረሩ ኢብራሂምን ዘንግቶት ነው?  በልጅነቱ አይኑን ሸፍነው የትም ወስደው ሲፈታ ቤተሰቦቹ የት እንዳሉ እንኳ የማያውቀው ኦሮሞ ምን ይል ይሆን? ሕክምና ተከልክለው ከእስር እንደተፈቱ የሞቱት መምህር ቤተሰቦች ምን ይሉ ይሆን?  አብዛኛውን ዘመናቸውን በእስር ያሳለፉት የአምቦው መምህር ምን ይሉ ይሆን? 97 ላይ ወንድማቸው ተገድሎ፣ በእሱ ምክንያት የተሰቃዩት ሽማግሌ፣ ታስረው የከሰሩት የወለጋ ባለሀብቶች ምን ይሉ ይሆን?
ከማዕከላዊም የባሰው የጦር ኃይሎች የደሕንነት ቢሮ ሲረገጡ ከርመው የሚመጡትን ወጣቶች ያውቃቸዋል። አቅም ቢያጡ ግድግዳዋ ላይ ፍቀው በኦሮምኛ የሚግባቡባትን ያውቃታል። በኦሮሞ  ታሳሪዎች ላይ በሚደረግ ድብደባ ምክንያት የርሃብ አድማ የመራው ራሱ ነው። ለሁለተኛ ጊዜ ድብደባ ሲከፋ ርሃብ አድማ ይደረግ ሲባል “ቀን ቆርጣችሁ ንገሩን፣ ይህን አንታገስም” ያለውኮ ራሱ በቀለ ነው። አቶ ደጀኔ ጣፋ የርሃብ አድማው የግንቦት 7 ነው ብሎ ሲቃወም እንኳ በቀለ ጤነኛ ነበር።
 ደረጀ የሚባል የኦፌኮ አባል ለወራት በካቴና ታስሮና ካቴናው ዝጎ አልፈታ ብሎ ፍርድ ቤት ድረስ አምጥቶ አሳይቷል። በኋላ ካቴናው ተቆርጦ ነው ከእጁ የተላቀቀው።  በማንነታቸው የተገረፉትን አማራ፣ ጉራጌና ሶማሊዎች ብንጠቅስ ግዱ  አይደለም ብዬ ነው ያልዘረዘርኩት።
ሁለት እግሩ የተቆረጠውን ልጅ ታሪክና የሌሎች ኦሮሞ ወጣቶችን ታሪክኮ ቀድሞ የነገረን አቶ በቀለ ነው። አቶ በቀለ ገርባ ማዕከላዊ ምርመራ ውስጥ በትህነግ ዘመን በኦሮሞ ህዝብ ላይ የተፈፀመውን በደል በምሬት ሲናገር አንድ መርማሪ ማልቀሱ ሲነገር ነበር። አቶ በቀለ ራሱ በኦሮሞ ላይ ደረሰ ያለውን  ግጥም አሰናድቶ መዝሙር አዘጋጅተው ነበር። ሌሊት እስረኞች ይዘምሩት ነበር። ወደ ፍርድ ቤት ሲወሰዱ፣ ራሳቸው እነ በቀለ እስር ቤት ውስጥ “አቁሙ” እየተባሉ ዘምረውታል። ኦሮሞ ፖሊሶችም ይዘምሩት ነበር።
የዛሬዎቹ ኦሮሞን በማንነቱ ያጠቃሉ አለ። ከትህነግ አነፃፅሮ። ለምሳሌ የጠቀሰው ሚዲያዎችን ነው። እኛ የምናውቀው ይህ መንግስት እነ አቶ በቀለን ጨምሮ የአፓርታይድ ሕግ ካልተተገበረ፣ የፋሽስት ስርዓት ካልቆመ ብለው ሕዝብ ላይ ነቀርሳ የሚተክሉትን እንኳ ዝም እያለ ሰላማዊ የአማራ ወጣቶችን እንደሚያስር ነው። ሌላ አካል ቢለው የሚያሳስረው እነ በቀለን ምንም አላስደረጋቸውም። እኛ የምናውቀው 86 ሰው ያስገደለ እንኳን አለመጠየቁን ነው። ሌላ ቢሆን ሰበብ በቂው ነበር። በትህነግም ዘመን የምናውቀው በማንነት ሲንቋሸሹ የነበሩ መሆኑን ነው። እስር ቤት ውስጥ ኦሮሞ ወጣቶች ይፈፀምባቸው ከነበረው ውጭ የትህነግ አመራሮች ሕዝብ ሲዘልፉ ነበር።
አማራ ትናንትም ዛሬም በማንነቱ እየተጠቃ መሆኑ ቢገልፅ አይገርመኝም።  እውነትም ይሁን አይሁም ትህነጎቹ በማንነት ተጠቃን ቢሉ የበቀለን ያህል ባላስገረመ።
በቀለኮ በትህነግ ዘመን ኦሮሞ ላይ ይፈፀም የነበረውን በደል ለማስረዳት ነበር እነ አብይ አህመድን፣ ለማ መገርሳን ጨምሮ ምስክርነት የጠራው። ፈርተው አልመጡለትም  እንጅ!
በቀለ ግን 7 ጊዜ ሲታሰር ሰርቆ ነበር? የገራፊዎች፣ የአረመኔዎችን ወንጀል ለመደበቅ ይህን ያህል ርቀት ከሄደ ነገ ስልጣን ቢያገኝ ምን ሊያደርግ ነው? ከስር በፎቶው የሚታየው ሰውንምኮ ይክደዋል?
Filed in: Amharic