>

እኔ እነ እስክንድርን ብሆን...!?! (ግርማ ካሳ)

እኔ እነ እስክንድርን ብሆን…!?!

 

 

ግርማ ካሳ
ባልደራስ በአዲስ አበባ እየፈናቀሉ ስላሉ ወገኖች እያደረገ ያለው ጥረት እጅግ በጣም የሚደነቅ ብቻ ሳይሆን የሚመሰገን ነው። ለባልደራስ በዚህ አጋጣሚ እጅግ በጣም ትልቅ አክብሮቴን እገልጻለሁ።
  እንደ ኢዜማም ያሉ ለሕዝብ ቆመናል የሚሉ ሕዝብ በዚህ መልኩ በብልጽግና ሃላፊዎች ግፍና በደል ሲፈጸምበት ዝም ባይሉ ጥሩ ነበር። ከገዢው ፓርቲ ጋር የተለጠፉ ናቸው የሚባሉት ብዙ ጊዜ እንዲህ አይነት አንገባጋቢ ሕዝባዊ ግዳዮችን ጉዳያቸው አድርገው ስለማያዩ ነው። በዚህ ረገድ እነ ኢዜማ ማሻሻያዎች ካደረጉ ምን አልባት ዜጎች ለኛም የቆሙ ናቸው ሊላቸው ይችላል።
ባልደራስ በመስቀል አደባባይ ጉዳይም ተቃውሞ አሰምቷል። ከአክብሮት ጋር እነ እስክንደር  ይሄንን ግንባታ የተቃወሙበትን መንገድ ትክክል ነው የሚል እምነት የለኝም። በግሌ በመስቀል አደባባይ የግንባታ ስራዎች ቢደረጉ ችግር የለኝም። በተለይም አፈርማ የሆነው ቢቀየር፣ አደባባዩን የበለጠ ማሳመር ይቻላል።
እነ ኢንጂነር ታከለ መስቀል አደባባይን ልናሳምር ነው በሚል  ቁፋሮ ጀመረዋል። እንደውም እንዴት አድርገው አደባባዩን እንደሚያሳምሩትን የዲዛይን ሞዴሎችም አሳይተዉናል። በርግጥም ዋዉ የሚያሰኝ ነው። በመርህ ደረጃ ግንባታ የሚደገፍ ነው።
ሆኖም ግን አንድ በጣም መነሳት ያለበት ጉዳይ አለ።  እኔ እነ እስክንደርን ብሆን  ግንባታው ለምን ተደረገ የሚል ተቃውሞ ሳይሆን የማነሳው “በአሁኑ ወቅት ግንባታዉን ማድረግ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባ ነበር ወይ ?” የሚለውን ነበር።
አንደኛ – አዲስ አበባ መስተዳደር ለነዋሪዎች መሰጠት ያለበትን መሰረታዊ አገልግሎቶች ማሟላት አልቻለም። መብራት የለም። ዉሃ የለም። በየቦታው ቁሻሻ አይሰበሰብም።ከተማዋ ትሸታለች።  የትራንፖርት ችግር አለ። የጎዳና ተዳዳሪዎች ብዙ ናቸው። በየቦታው ማስቲሽ የሚያጨሱ። ያ ሁሉ ችግር እያለ፣ የግድ አሁን መደረግ የሌለበትን ቁፋሮ በመስቀል አደባባይ ማድረግ ትልቅ ስህተት ነው።
ሁለተኛ –  ድሃ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን እያፈናቀሉ፣ በየሜዳው  ላይ እየወረወሩ  አዲስ አበባን ልንገነባ ነው ይሉናል። ጉረኞች !!!! አስመሳዮች !!!! አዲስ አበባ ማለት ፎቁና ሰገነቱ አይደለም። አዲስ አበባ ማለት ሕዝቡ ማለት ነው።
ሶስተኛ – መስተዳደሩ መቆፍር እንጂ ቆፍሮ መጨረስ አያውቅም። የጀመራቸው ያላለቁ ብዙ ግንባታዎች አሉ።፡ቁፋሮ ከሚያበዙ መጀመሪያ ቆፍረው የተዉትን ቢጨርሱና ከተማዋን ከአቧራና ጭቃ ቢያላቅቁ ጥሩ ነበር። ከአንድ በፊት በሚኒባስ ከስታዲየም ወደ ቃሊቲ እሄዳለሁ። ጎተራ ጋር ስንደር መንገድ መቆፍ ተጀምሯል። ምን አለፋችሁ ስንት ኪሎሜትር ቁፋሮ ነበር። በጣም ተማርሬ ሳጎረመረም፣ አንድ ጎኔ የነበረ ሰው መንገዱ ሶስት አመቱ አለኝ። ምን አለፋችሁ ከአንድ ሰ’ዓት በላይ ፈጀብን። የግንቦት ጸሃይ ተጨምሮበት አስቡት። አሁን ያ መንገድ አልቆ ይሁን አይሁን አላውቅም። ግን ተመሳሳይ ግንባታዎች አሉ ቁጭ ያሉ።
በርግጥም ለአዲስ አበባ ሕዝብ ጥቅም የቆመ መስተዳደር፡
1.  ነዋሪዎችን አያጎሳቁልም። እንደ ወንበዴ ቤት እየፈረሰ አረጋዉያንንና ሕጻናትን አይበትንም።
2.   በከተማዋ ያለው የዉሃና የመብራት ችግር በቶሎ እንዲቀረፍ ቀንና ሌሌት ይሰራል።ትልቁ አጀንዳው አድርጎ።
3.  በከተማ በየቦታው የሕዝብ መጸዳጃ  ቤቶችን ይሰራል። ቁሻሻ ማጠራቀሚያዎችን በየቦታው ያስቀምጣል። በየጊዜው መጻዳጃ ቤቶችን የሚያጸዱ፣ ቁሻሻዎን የሚሰበሰቡ በቂ ሰራተኞችን ያሰማራል።
4.  በከተማዋ ያለውን የትራስፖርት ችግር ለመቅረፍ ርብርብ ያደርጋል።
5. በየ ከተማ መስተዳደር ሕዝብ እንዳይጉላል፣ አስፈላጊዉን አገለግሎት በበቂ ሁኔታ እንዲያገኝ ያደርጋል:
6. የተጀመሩትን ግብታዎች በቶሎና ያጠናቅቃል።
አሁን ያለው የኢንጂነር ታከለ ኡማ የአዲስ አበባ ያልተመረጠ መስተዳደር እነዚህን እያደረገ አይደለም። የራስን ተክለ ሰዉነት ለመገንባት የፎቶ ፖለቲካ ነው እየተደረገ ያለው።
Filed in: Amharic