>
5:18 pm - Friday June 15, 1900

ዘር አይ ድረስ - ገሞራው!!! (ዙኪ ሸዋ)

ዘር አይ ድረስ – ገሞራው!!!


ዙኪ ሸዋ
ኢትዮጵያ ሃገራችን በግርማዊ ጃንሆይ ዘመነ አጼ ዮሓንስ 4ኛ ስትስተዳደር ፡ ቅኝ ገዢዎች እንዲሁም ደርቡሾች( ግብጾች ) የአባይ ወንዝ መነሻ የሚያጠቃልል ካርታ ለመመሥረት ቋምጠው ተደጋጋሚ ጥቃት ቢያደርሱም በፍጹም አልተሳካላቸውም ነበር። በኤርትራ አካባቢ ያለውን መላ ክልል እንዲያስተዳደሩ የተሾሙት ራስ አሉላ አባ ነጋ ተደጋጋሚ የደርቡሾችን ( የግብጾችን ) ጥቃት በተለይም በጉራዕና በጉንዳጉዲ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ 1875 እስከ 1876 የግብጹን የጦር መሪ ( ፓሻ) ማርከውና ገድለው ለመታሰቢያ የፓሻውን ዩኒፎርም ለበሰው ፎቶግራፍም ተነስተዋል።
በከረንና ኩልፊት እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1885 የግብጽ ማህዲስቶች ወይም ደርቡሾችን ድል አድርገዋል። ከማሕዲስቶች ጋር ጦርነት ገጥመው በማካሄድ ላይ እያሉ ጣሊያኖች ምፅዋን ተቆጣጥረው ስለነበር፡ ጦርነቱን በድል አጠናቀው ሳለ ፊታቸውን ወደ ምፅዋ ባዞሩ ዘመን፡እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1887 ዓም ጣሊያኖች ጭራሽ መላውን ኤርትራ ለመያዝ ከምጽዋ ተነስተው ሲገስግሱ ራስ አሉላ ዶጋሊ ላይ የጣሊያን ጦር ሲደርስ ድንገተኛ ማጥቃት ሰንዝረው ከ500 በላይ ጣሊያኖችን በመማረክና በመግደል የድሉ ባለቤት እንደነበሩ፡ የኢትዮጵያ ታሪክ መዛግብት ላይ በተደጋጋሚ ተጽፏል።
በኋላም ደርቡሾች መተማ ላይ ኃይለኛ ጦርነት በከፈቱበት ወቅት እራሳቸው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት አጼ ዮሕንስ ዘምተው በጦርነቱ ላይ ተሰውተዋል። አጼ ዮሓንስ ከአረፉ በኋላ፡ የኢትዮጵያ ጦር ኃይል የመሪው መሞት በድንጋጤ በመዳከሙ፡ የጣሊያን ጦር መላውን ኤርትራ በመቆጣጠር የጣሊያን መንግሥት ቅኝ መሬት አደረገው። ጣሊያኖች በእምዬ ምኒልክ በ1896 ዓም አድዋ ላይ በተሸነፉ በ40ኛው ዓመት እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1928 ዓም መላውን ኢትዮጵያ ወረሩ ፡ ከዚያም በዘረፋ የራሳቸው ታሪክ ያልሆኑትን የሃውልት ሌብነት ሲያደርጉ ከአክሱም አንድ ሃውልትና፡ ለገሃር የነበረውን የይሁዳ አንበሳ ሃውልት ነቅለው ጣሊያን ዋና ከተማ ” ሮማ ” ላይ ተከሉት።
ከዕለታት በአንዱ የጣሊያን አመታዊ በዓላቸው ቀን ፡ ጀግናው ዘርዓይ ደረስን ከአሥመራ በጣሊያን ቋንቋ አስተርጓሚነት ወስደውት እዚያው ስለነበር፡ የሃገሩን የአርበኝነት ዩኒፎርም እስከነ ሙሉ ትጥቁ ጎራዴውን ጨምሮ ለብሶ በዓሉ ቦታ ላይ እንዲገኝ አደረጉ። ከዚያም የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማን መሬት ላይ አንጥፈው እየረገጡና ምራቃቸውን እየተፉ ሲረማመዱበት ጀግናው ወጣቱ ዘርዓይ ደረስ መታገስ አልቻለም፤ አጠገቡ ካሉት በመጀመር የጣሊያን ወታደሮች አንገት መቀንጠስ ጀመረ፤ ጣሊያኖች እግሬ አውጪኝ ሽሽት ጀመሩ፡ ዘርዓይ ደረስን የሚያስቆመው የሰው ክንድ እንዳልሆነ አወቁ፡ ወዲያው ተኩሰው እግሩን አቆሰሉት።
ወደ እስር ቤት አስገብተውት ቢሆንም ጀግንነቱ በመላው ጣሊያን ሃገር ገነነ። ሆስፒታል አስገብተው በሕክምና ሂደት ላይ ሳለ፡ ኢትዮጵያ ሃገራችን ድል እንደተቀዳጀች፡ ሙሶሊኒ በገዛ ሕዝቡ ተገድሎ አዲስ የጣሊያን መንግሥት ስለተመሠረተ፡ ግርማዊ ጃንሆይ አጼ ኃይለሥላሤ፡ በምርኮና በግዞት ጣሊያን የወሰዳቸውን አርበኞች ሲያስመልሱ፡ ጣሊያኖች ሆን ብለው ይህንን ወጣት ጀግና ገድለው ታሞ ሞተ በማለት ሕይወቱን ቀጥፈውት እንደነበር የኢትዮጵያ ታሪክ ጻሕፍትና የአንደኛ ደረጃ ት/ቤት መምሕራኖች በተደጋጋሚ በመዘከር የዘርዓይ ደርስን ትሩፋት ነግረውናል፤ አስተምረውናል። የጀግንነት ስሙ ለዘለአለም ሲታወስ ይኖራል፡፤
Filed in: Amharic