>
11:16 am - Sunday December 4, 2022

የመለስ አጓጉል ትሩፋቶች (ክፍል ሁለት) አሰፋ ሃይሉ

የመለስ አጓጉል ትሩፋቶች

(ክፍል ሁለት)
አሰፋ ሃይሉ

6ኛ/ የኢትዮጵያን ብሔሮችና ብሔረሰቦች መብት የጨፈለቀ ጀግና 

ወቅቱ በፈጠረው አጠራር እንጠቀምና በኢትዮጵያ ውስጥ 86 ብሔሮች ይገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያ በተለያዩ ብሔሮች አንደበት የሚነገሩ ከ60 በላይ ቋንቋዎች አሉ፡፡ መለስ ዜናዊ በህገመንግሥት አረጋገጥኩ የሚለው የብሔሮችን እኩልነት ነው፡፡ ሌት ተቀን የሚሰብከውም እያንዳንዱ ብሔር ካስፈለገው ራሱን ከኢትዮጵያ እስከ መገንጠል የሚደርስ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብት ያጎናፀፈች የኢህአዴግ ኢትዮጵያ እንደተፈጠረች ነው፡፡ ይሄ ‹‹የብሔሮች እኩልነት›› ግን በተግባር የሌለና በወያኔ-ኢህአዴግ ዘመን በፍፁም እውን ሊሆን የማይችል የመለስ ዜናዊ የማደናገሪያ የፈጠራ ድርሰት ነው፡፡ ምክንያቱን ኋላ ላይ አስረዳለሁ፡፡
መለስ ዜናዊ በፈጠራት ጠባቧ ኢትዮጵያ ግለሰቦች ሀልዎት ወይም ህልውና የላቸውም፡፡ ግለሰቦች በፖለቲካው ሜዳ አንዳች ቦታ የላቸውም፡፡ ግለሰቦች መብት የላቸውም፡፡ ግለሰቦች እንደ አንድ ሰብዓዊ ፍጡር እውቅና የላቸውም፡፡ የመለስ ዜናዊና ግብረአበሮቹ ጠባብ አመለካከት ከብሔር ቆዳ ውጭ የሆነ ግለሰብ በኢትዮጵያ ምድር ይፈጠራል ብሎ አያምንም፡፡ ይህን የማያምን ጭንቅላት እንዴት አድርጎ ከኢትዮጵያ የብሔር ቆዳ ያልወጣውን ካርል ቦህም ሄንዝ ለመሰለ ግለሰብ ዜግነት እንደሰጠው እጅግ የሚደንቅ ጉዳይ ነው፡፡ እርሱንም ቢሆን የኦሮሞ ካባ ለማልበስ ያልታተሩት የህዝብ ግንኙነት ሥራ የለም፡፡ በመለስ ዜናዊ የፕሮፓጋንዳ ማሽን ጀርመናዊው ካርል በመራቤቴ ዓለም ከተማ ላይ ስላሰራው ታላቅ ሆስፒታልና ስላቋቋማቸው በርካታ የጤና ኬላዎች ማውራት ነውር ተደርጓል፡፡ ከዚያ ይልቅ ካርልና ሌት ተቀን ለመጠበቅ ምሎ ስለቆረበው የኦሮሞ ተወላጅ ታላቅ ትርክት ተፈጥሮለታል፡፡ ይሄኛውም ራሱን የቻለ የወያኔን የጠበበ የብሔር ቆዳ ትርክት በጣጥሶ የወጣ ሰብዓዊ ትንግርት መሆኑ ግን አይካድም፡፡ አንድ ኦሮሞ፣ ወይም አንድ አማራ የተባለ ሰው – በሰብዓዊ ሚዛን ታላቅ ሚዛን ላይ ላስቀመጠው ጀርመናዊ – ታላቅ ሰብዓዊ ክብር እንደሚሰጠው ያሳያልና፡፡ እንዲያም ሆኖ ወያኔ-ኢህአዴግ ኢትዮጵያን ያህል ሰፊ ሀገር እንደ ድግስ ከበሮ በብሔር ቆዳ አስሮ ካመት ዓመት ጠባብነትን እየደለቀ መኖርን የሙጥኝ ብሎ እስካሁን ቆይቷል፡፡
በመለስ ዜናዊ የብሔሮች ኢትዮጵያ የተከበረ የብሔር መብት የለም እንጂ – በሀሳብ ደረጃ ግን የታሰበው ዕቅድ የግለሰቦች ህልውና የተፋቀባትን የብሔሮች ከረጢት የሆነች ኢትዮጵያን መፍጠር ነበር፡፡ እንደ ሃሳቡ ከሆነ – ሕግ የሚያወጡት የየብሔሩ ተወካዮች ናቸው፡፡ ሕግ የሚተረጉሙት የየብሔሩ ተወካዮች ናቸው፡፡ ሀገር የሚያስተዳድሩት የየብሔሩ ተወካዮች ናቸው፡፡ ግለሰቦች ‹‹ብሔር›› በተባለው መቃብር ውስጥ ተከርችሞባቸዋል፡፡ ግለሰብ የሚባል ማንነት በመለስ መዝገበ ቃላት ውስጥ የለም፡፡ በአንድ ወቅት መለስ ዜናዊ ቅንጅትን ወክሎ ሊወያየው ወደ ቤተመንግሥት የገባውን ዶ/ር ብርሃኑ ነጋን ወደ ጆሮው ጠጋ ብሎ ‹‹እሺ እንዴነህ የእዣ ነፃ አውጪ?›› እንዳለው ብርሃኑ ነጋ ‹‹ነፃነት ጎህ ሲቀድ›› በተሰኘውና በወያኔ-ኢህአዴግ እስርቤት ውስጥ እያለ ባሳተመው መጽሀፉ አትቶልን እናገኛለን፡፡ ይህ የሚያሳየው ሰውን በየመጣበት የብሔር ቆዳ አንፃር ካልሆነ በቀር ብርሃኑ ነጋ የተባለን ራሱን ችሎ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ መቆም የሚችል ነፃ ሰብዓዊ ፍጡር የማይቀበለውን በጠባብነት የተደፈነውን የመለስ ዜናዊ አዕምሮ ነው፡፡
ቀደም ብዬ ወደ ጀመርኩት ሃሳብ ልመለስ፡፡ እንዲህም የብሔሮች ከበሮ እየተደለቀ ባለባት የመለስ ዜናዊ ኢትዮጵያ እውነተኛ የብሔሮች መብት ተከብሯል ወይ? እውን አንዱ ብሔር ከሌላው ብሔር እኩል በኢትዮጵያ ሀገሩ ላይ የመወሰን መብት አግኝቷል ወይ? በመለስ ዜናዊ ኢትዮጵያ ሁሉም ብሔሮች ወይም እያንዳንዱ ብሔር እኩል ነበር ወይ? አሁንስ ብሔሮች ሁሉ በሀገራቸው ጉዳይ ላይ በያገባኛል ስሜት ለመወሰን፣ ራሳቸውን በራሳቸው ለማስተዳደር፣ እኩል ናቸው ወይ? ወይስ ጆርጅ ኦርዌል የተባለው እንግሊዛዊ ፀሐፊ “Animal Farm” (የእንስሳት ዕድር) ብሎ በጻፈው ድርሰቱ “All animals are equal. There are some animals more equal than others.” እንዳለው – በመለስ ዜናዊም ኢትዮጵያ – ‹‹ሁሉም ብሔሮች እኩል ናቸው… ነገር ግን አንዳንድ ብሔሮች ከሌላው ብሔር የበለጠ እኩል ናቸው!›› የሚል በህገመንግሥቱ አንቀጾች መካከል የተሸጎጠ ለመለስና ጭፍራዎቹ ብቻ የሚነበብ ታላቅ ህገመንግሥቱን ገዢ መርህ በሥራ ላይ ውሎ ነበረ?
እውን ብሔሮች ሁሉ እኩል ከሆኑ ስለምን እያንዳንዱ ብሔር ራሱን በራሱ የሚያስተዳድርበት የየራሱ አስተዳደራዊ ክልል ተመስርቶለት – ለምን የክልሎች ቁጥር በሀገሪቱ ብሔሮች ቁጥር ልክ እንዲሆን አልተደረገም? ብሔሮች እውን እኩል ከሆኑ – ስለምን የሀረሪ ብሔር ከትግራይ ብሔር ያነሰ ድምፅና ውክልና ይኖረዋል? የትግራይ ብሔር የሚባለውስ በውስጡ ያሉትን የኢሮብ፣ የእንደርታ፣ የተምቤን፣ የወልቃይት፣ ወዘተ ብሔሮችን ባህል፣ እና መብት የደፈጠጠ ብሔርነት አይደለም ወይ? የመለስ ዜናዊ የብሔሮችን እኩልነትና ራስን በራስ የማስተዳደር መብት የሚሰብክ ህገመንግሥት – ስለምን ኢሮቦችን ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩ ብሔሮች አላደረጋቸውም? ስለምን ኢሮብ በትግራይ ብሔር፣ እና በትግራይ ክልል የተጨፈለቀ ብሔር ሊሆን ተፈረደበት? እውን የብሔሮች መብት በመለስ ዜናዊ ኢትዮጵያ ተከብሯል? ለምን ወልቃይት ራሱን ችሎ ራሱን በራሱ የሚያስተዳድር ብሔር አልተደረገም? ለምን ራሱን በራሱ የሚያስተዳድርበት ክልል አልተሰጠውም?
በመለስ ዜናዊ ብሔሮች ሁሉ ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩ እኩል ህገመንግሥታዊ መብት ያላቸው ናቸው ተብሎ በሚሰበክባት ሀገር ስለምን አምስት የደቡብ ኢትዮጵያ ብሔሮች ‹‹ደቡብ ኦሞ›› በሚል ዞን ተጨፍልቀው ተደመጠጡ፡፡ ‹‹ትግራይ›› ለተባለ ብሔር መብት የታገለው መለስ ዜናዊ ስለምን ሀመር የተባለ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብት ያለው ብሔር በኢትዮጵያ መኖሩ ተዘነጋው? ለምን ፀማይ ብሔር ራሱን የሚያስተዳድርበት የራሱ አስተዳደርና የራሱ ክልል አይኖረውም? በና፣ እና ቢራሌስ ለምን ራሳቸውን የሚያስተዳድሩ ክልሎች አልሆኑም? እውን በመለስ ዜናዊዋ የብሔሮች ኢትዮጵያ ሁሉም ብሔሮች እኩል ሆነው ያውቃሉ?
በመለስ ዜናዊ የብሔሮችን እኩልነት እንደረጋገጠች በሚሰበክላት የብሔሮች ኢትዮጵያ – በእርግጥም ሁሉም ብሔሮች እኩል ከሆኑ – ስለምን ‹‹ትግራይ›› የተባለችው ብሔር የራሷ ክልልና መንግሥት፣ የራሷ አስተዳደር ሲኖራት ‹‹ሀዲያ›› የተባለች ብሔር ይህን መብት ተነፈገች? በመለስ ዜናዊ የብሔሮች ኢትዮጵያ ሀዲያ ‹‹ደቡብ›› በተባለው ብሔር ውስጥ መደፍጠጡ ተገቢ ሎጂክ ሆኖ ከታየ – ስለምን ትግራይስ ‹‹ሰሜን›› በተባለ ክልል እንድትደፈጠጥ አልተደረገችም? እውን ብሔሮች ሁሉ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በመለስ ዜናዊዋ የብሄሮች ኢትዮጵያ አግኝተዋል ወይ?
ሀረሪን ክልል ያደረገ የመለስ ዜናዊ መንግሥት ሀመርን ክልል የማያደርግበት ምክንያቱ ምንድን ይሆን? ሀዲያንስ? ሂራብንስ? ላቂን? መካንን? መዠንገርን? ሙርሌንስ? ሙርሲንስ? ማኦንስ? ሜ -ኤ -ንስ? ሜርንስ? ሱሪንስ? ራያንስ? ሰባትቤትንስ? ሱርማንስ? ሲዳማንስ? ሳኦንስ? ስልጤን? ሶክን? ሸኮን? ሺታን? ሺናሻን? ሻንቅላንስ? ቀፊቾንስ? ቃሉን? ቃጫማን? ቅማንትንስ? በርታን? ቡርጂን? ባስኬቶንስ? ባቹማን? ፈላሻን (ቤተ እስራኤልን)? ቤንችን? ቦረናን (ቦረና ኦሮሞን)? ቦዲን? ቲርማን? ኑየርን? ኑያጋቶምን? ኒሞቲክን? አላባን? አራፕን? አርሲ ኦሮሞን? አርቦሬን? አርጎባን? አኝዋክን? አዊን? አዩፕን? አይዳን? አገውን? ኢሮብንስ? ኢሳን? ኢቱን? ኤክሳምታን?  ከሪሞጆን? ከንባታን? ከፊቾን? ከፋን? ኩሎን? ኩናማን? ኪቼፓን? ካራናሌን? ካሮን? ክስታኔን? ክዋማን? ክዌጉን? ኮንሶንስ? ኮንታንስ? ኻሳን? ወላይታን? ወርጂን? ወይጦን? ዛይን? የምን? ዳሰናችን? ዳንይሮን? ዲሜን? ዲዚን? ዳውሮን? ዶርዜን? ዶቦን? ዶሎን? ጅሩን? ገለብንስ? ጉምዝን? ጉራጌን? ጉጂን? ጊሚራንስ? ጊሞጃንን? ጋሞን? ጋዋዳን? ጌዴኦንስ? ጎንጋን? ጎፋን? ጫራን? ጻሚንስ?…
እውን … እነዚህ ሁሉ ብሔሮች በመለስ ዜናዊ ጊዜ እውን በተግባር ተደፈጠጡ ወይስ መብታቸው ተከበረ? እውን የብሔሮች እኩልነትን አረጋገጥኩ የምትለው የመለስ ዜናዊ ጠባቧ ኢትዮጵያ የሀገሪቱ ብሔሮች የእውን እና በሃቅ ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ፣ የየራሳቸውን የአስተዳደር ክልል እንዲመሰርቱ የሚፈቅድላቸው ህገመንግሥትስ ነበረ ወይ? ዋለልኝ በ60ዎቹ ‹‹የብሔሮች እስርቤት›› ብሎ የጠራት ኢትዮጵያ አሁንስ ሌጂትሜሲውን በብሔሮች ስም ባደረገው የመለስ ዜናዊ አስተዳደር ዘመን ከብሔሮች እስርቤትነት ተላቃለች ወይ? እውነት መለስ ዜናዊ በኢትዮጵያችን የብሔሮችን እኩልነት አረጋግጧል? እውን የቦዲ ብሔር ከትግራይ ብሔር እኩል ነበር በመለስ ዜናዊ ‹‹የብሔሮች›› ኢትዮጵያ? እውን ሱርማ ብሔር ከአማራ ብሔር እኩል መብት ነበረው? እውን የባስኬቶ ሕዝብ ከሀረሪ ህዝብ እኩል ራሱን የማስተዳደር መብት ኖሮት ያውቃል? እውን የደንጣ ድባሞ ክችንችላ ሕዝብ በመለስ ዜናዊ የብሔሮችን መብት አረጋገጠ የሚባልለት ህገመንግሥቱት ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብት አግኝቷል? ብሔሮች ሁሉ እኩል ከሆኑ – ለምን ሁሉም ብሔሮች እኩል ውክልና፣ እኩል ድምፅ፣ እኩል መብት ያላቸው የየራሳቸው ክልል አይኖራቸውም? ወይስ በመለስ ዜናዊ የብሔሮች ኢትዮጵያ – ከሌሎች ብሔሮች ይበልጥ እኩል እንዲሆኑ የተደረጉ ጥቂት ከፍ ያሉ እኩሎች ብሔሮች አሉ?
እውነታው ይሄ ነው፡፡ በመለስ ዜናዊ የማደናገሪያ ድርሰት የተፈጠረችው የብሔሮች ኢትዮጵያ – የብሔሮች ህገመንግሥት – የወያኔ-ኢህአዴግ የግለሰቦችን ሰብዓዊ መብት ደቁሶ፣ የብሔሮችን መብት እንዳሻው ደፍጥጦና ረግጦ፣ በቀጥቅጠህ ግዛው ታጣፊ ክላሽ ፖለቲካ የገዛባትና የሚገዛባት የግል መነባንብ ድርሰት ነበረች እንጂ – በእውን የተረጋገጠችና ያለች የብሔሮችን መብት በህገመንግስት ያፀደቀችና ያከበረች የኢህአዴግ ኢትዮጵያ አልነበረችም! አሁንም የለችም! ቀድሞም በመለስ ዜናዊ አዕምሮ የተፀነሰው፣ አሁንም በወራሾቹ የቀጠለው – በብሔሮች ስም የጥቂቶችን አምባገነን አስተዳደር ለማስቀጠል የቆረጠ – እና ለዚህ ዓላማው በፊቱ ያለውን ሁሉ ለመጨርገድ ምሎ የቆረጠ – በአንድ ወቅት ጊዜ የሰጣቸውና ‹‹የመንግሥትነትን ቡራኬ›› የተጎናፀፉ የአምባገነን ሽፍቶች አስተዳደር ብቻ ነው! እውነቱ ይሄ ነው!
የመለስ ዜናዊ የብሔር ብሔረሰቦች መብት የተከበረባት ኢትዮጵያ የምትገኘው – በእውኗ ኢትዮጵያ ሳይሆን – ህገመንግሥት ተብዬውን ጨምሮ – መለስ ዜናዊ በጻፋቸው የወያኔ-ኢህአዴግ የማደናገሪያ ወንጌሎች ላይ ብቻ ነው! መለስ ዜናዊ ፈጠርኳት የሚላት ኢትዮጵያ ካለች – ያቺ ኢትዮጵያ የብሔሮችን ሁሉ መብት ያስከበረችና የተከበረባት ኢትዮጵያ ሳይሆን – ጥቂቶችን ብሔሮች በበላይነት አንግሣ – የሌሎችን ብሔሮች መብት የደፈጠጠች፣ ብዙሃኑን የሀገሪቱን ብሔሮች አንገት አስደፍታና በእንባ አራጭታ – ጥቂቶችን የፌሽታ ውስኪ ያራጨች ኢትዮጵያ ነች! ይኸውም ይኸው ነው!
(…./ ይቀጥላል)
Filed in: Amharic