>

የመለስ አጓጉል ቱሩፋቶች! አሰፋ ሃይሉ (ክፍል ሦስት)

የመለስ አጓጉል ቱሩፋቶች!

አሰፋ ሃይሉ
(ክፍል ሦስት)
7ኛ/ እፍረትን ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ያደረገ ጀግና
ብሔራዊ ስሜት፡፡ የሀገር ክብር፡፡ የዜግነት ኩራት፡፡ የታሪክ ምርኩዝ፡፡ የጀግንነት ውርስ፡፡ የባህል ጌጥ፡፡ የሀገር ፍቅር፡፡ ጥንታዊ ጥበብ፡፡ አርበኝነት፡፡ ሀገርህ ያፈራችው ነገር ሁሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ የሀገርህ ጥለቶች ጌጥህ ናቸው፡፡ በመከራ ጊዜ እነርሱን እያሰብክ ቀና የምትልባቸው ቅስምህ ናቸው፡፡ ለአንድ ጤናማ ዜጋ የሀገሩ ፍሬዎች ሁሉ የኩራቱ ምንጮች ናቸው፡፡ የክብሩ ካባዎች ናቸው፡፡ ዜጋን ከዜጋ ጋር የሚያስተሳስሩ፣ በመከራም በደስታም ጊዜ የአነድን ሀገር ህዝብ በአንድ ሀገራዊ ዣንጥላ ሥር እጅ ለእጅ አያይዘው የሚያቆሙ የጠነከሩ የህብረት መሠረቶች ናቸው፡፡ በዓለም ላይ ያሉ መንግሥቶች ሁሉ እነዚህን ብሔራዊ የሀገር ኩራት ስሜቶች በየዜጎቻቸው ላይ ለማስረፅ ታትረው የሚሠሩት – ሀገራዊ ኩራት ለዜጎችና ለሀገር ያለውን ከፍ ያለ ፋይዳ ስለተገነዘቡ ነው፡፡
በቅርቡ ያገኘሁት በ124 የዓለማችን ሀገሮች ላይ የተካሄደ አንድ ጥናት ሀገራዊ ኩራትን (ወይም ‹‹ናሽነል ፕራይድ››) ምንነትና ለምን ለአንድ ሀገር ሕዝብ አስፈላጊ እንደሆነ በቀላሉ እንዲህ በማለት ያስረዳል፡-
“Patriotism or national pride is the feeling
of love, devotion and sense of attachment
to a homeland and alliance with other
citizens who share the same sentiment.
This attachment can be a combination
of many different feelings relating to one’s
own homeland, including ethnic, cultural,
political or historical aspects. National pride
matters because it brings joy and happiness
towards one’s country. A country’s source
of pride is to stand and defend their system.
A country’s pride deals with respect. A
country that takes in pride also takes
respect.”
የሀገር ኩራት ለዜጎች ደስታን ይፈጥራል፡፡ የሀገር ኩራት ዜጎች ሀገራቸውን እንዲጠብቁ ያደርጋል፡፡ በተለይ ብርቱ የሕይወት ትግል ባለባቸው ታዳጊ ሀገራት በዜጎች ልብ ውስጥ ያለ ሀገራዊ ኩራት በመከራ ጊዜ ታላቅ ኃይልና ብርታት ሆኖ ከውድቀት ይታደጋቸዋል፡፡ በሀገራቸው ኩራት የሚሰማቸው ሰዎች ለራሳቸውም፣ ለሀገራቸውም፣ ለወገናቸውም ክብር ይኖራቸዋል፡፡ ሀገራዊ ኩራት መከባበርንም፣ መተባበርንም ያመጣል፡፡ የጋራን ችግር ለመመከት ሁሉንም ወገን በፅናት አጣምሮ ያቆማል – ውስጣዊ የሀገር ኩራት፣ የሀገርና የወገን ክብር ስሜት፣ ብሔራዊ የአርበኝነት ስሜት፡፡ እንግዲህ ይህ በጥናትም በታሪክ ሂደትም የተረጋገጠ ጥቅም ስላለው ነው – የዓለም ሀገሮች ሁሉ ዜጎቻቸው በሀገራቸው ልባዊ ኩራት እንዲሰማቸው የሚያደርጓቸው፡፡
በመለስ ዜናዊዋ ኢትዮጵያስ? መለስ ዜናዊ መልካም አሳቢ አዕምሮ ቢኖረው ኖሮ – ድህነቱ ጉድለት ሆኖበት ያሸማቀቀውን፣ ኑሮው አንገት ያስደፋውን ዜጋ – በተግባር ባይችል በሞራል ጠግኖ – አይዞህ ገንዘብ ነው ያጣኸው፣ ነፃነት አላጣህም፣ ታሪክ አላጣህም፣ የሀገር ክብር አላጣህም፣ አርበኝነት አላጣህም፣ ጀግንነት አላጣህም፣ በላብህ ጥረህ ግረህ ቤተሰብህን ደግፈህ አቅምህ ያፈራውን ኑሮ መምራትን አላጣህም፣ ቀና በል ያገሬ ሰው! አይዞህ ችግርህ ያልፋል ያገሬ ሰው! ተነሳ በኩራት! ታጠቅ በክብር! ተግተህ ሥራ በሞራል! …. – እንዲህ እንዲል እኮ ነበር የሚጠበቀው ከሀገር መሪ፡፡ በመለስ ዜናዊዋ ኢትዮጵያ እኮ ‹‹እፍረት እንደ ብሔራዊ ካባ›› ተቆጥሮ – በሀገር ደረጃ ‹‹እንፈር!›› የሚል ሀገርአቀፍ ዘመቻ እኮ አስጀምሮ የነበረበት ጊዜ ነበር፡፡
መለስ በዚያው የ‹‹እንፈር›› ሀገራዊ ዘመቻው ሰሞን በቴሌቪዥን ቀርቦ ቃል በቃል ያለውን ልድገመው፡-
‹‹ይሄ የተቀዳደደ የውስጥ ልብስ እየለበሱ፣
ከላይ ያለው ሰው፣ የተመቸው ሰው ለመምሰል፣
ነጭ ጋቢ ለብሶ መውጣት፣ እና ለሰው መታየት
ማብቃት አለበት! ኩራት እራት አይሆንም!
እንፈር! ሁላችንም እንደ ሀገር ልናፍር ይገባናል!››
የዓለምን የብዙ ሀገሮች ታሪክ አንብቤያለሁ – በበኩሌ – በሀገሩ በወገኑ እርዛት የሚሳለቅ መሪ – ከመለስ ዜናዊ በስተቀር አይቼም ሰምቼም አላውቅም! እንዴ? ሕዝቡ በላዩ ላይ ልብሱ የነተበው፣ ካኒቴራው በላዩ ላይ የተቀዳደደው እኮ ዘራፊ መንግሥታት ህዝባችንን ምን ፈትለን እናልብሰው ብለው በመጨነቅ ፈንታ በላዩ ላይ እየተፈራረቁ ቤተመንግሥታቸውን በማሞቅ ስለተጠመዱ እኮ ነው! ለደሃው ህዝብ ነው የምታገለው ብለው ተነስተው እርስዎና ጋሻጃግሬዎችዎ ዓይተውት ሰምተውት በማያውቁት የምቾት ስካር ሲዋኙ – ይሄን ህዝብ ከእርዛት ባለማውጣትዎት እኮ እርስዎ እንደ መሪ የህሊና ሰላም ሊያጡ በተገባዎት ነበር እኮ! ሊያፍሩ የሚገባዎት – የጨርቃጨርቅ ኢንደስትሪዎችን የሀገርዎን የወገንዎን ሰው ከማልበስ ይልቅ ለቱርክ ባለሀብቶች ሲቸበችቡ የኖሩት እርስዎ ነዎት እኮ! – የሚል ሰው እንዴት አልተገኘም ግን?
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር – ማፈር የሚገባዎት እኮ እርስዎ ራስዎ ነዎት! – የሚል ሰው እንዴት አልተገኘም በሰዓቱ? – ይህን ተናግሮ መገኘት ማለትማ በመለስ ዜናዊ መንግሥት ምላስ ያስቆርጣል! እጅ ያስቆርጣል! እግር ያስቆርጣል! እና ማፈር የሚገባው ሰው በቤተመንግሥቱ በሺኅ ጠባቂዎች፣ በሺህ መኪኖችና፣ በሺህ የክብር አጀቦች ተከቦ እየተምነሸነሸ – ያላለፈለት ህዝባችን በብሔራዊ ደረጃ – እፈር! እፈር በኑሮህ! እፈር በማንነትህ! እፈር በሀገርህ! እፈር በታሪክህ! እፈር በምትለብሰው ልብስ! ተባለ፡፡
በአንድ ወቅት ስለ አፄ ቴዎድሮስ በአካል ያየውን የታዘበውን በታሪክ ድርሳን ከትቦ ያኖረው ራሳም የተባለ የእንግሊዞች መልዕክተኛ – ከቴዎድሮስ ሞት በኋላ ባሳተመው ጽሑፍ – አንዴ ከአፄ ቴዎድሮስ ጋር በበቅሎ ላይ ተቀምጠን በመንገድ እየተዘዋወርን ሳለ – አንዲት ልብሷ በላይዋ ላይ የተቀዳደደ ጎስቋላ ሴትዮ አጋጠመችን – ቴዎድሮስም ከእኔ ጋር ንግግራቸውን አቋርጠው ከበቅሏቸው ወረዱና ባዘነ ልብ ‹‹አይዞሽ እናቴ! አይዞሽ ቀን ያልፋል!›› ብለዋት ካባቸውን አውልቀው በትከሻዋ ደረቡላት – በማለት ምስክርነቱን ሰጥቶ እናገኛለን፡፡ ይሄንኑ በአማርኛ ለማግኘት የፈለገ የጳውሎስ ኞኞን ‹‹አጤ ቴዎድሮስ›› የተሰኘ መጽሐፍ ቢያነብ እዚያም ላይ ሰፍሯል፡፡ ይሄ እኮ የፈረንጆቹ ደግ የአፈታሪክ ንጉሥ የሮቢንሁድ ታሪክ አይደለም እኮ! ይሄ በእውን የነበረ በዓይን እማኝ ፈረንጆች የተመሰከረለት የኢትዮጵያ ደግ ንጉሥ ታሪክ ነው፡፡
ሌላ ቀርቶ በቅርብ ዘመን እንኳ – የቱንም ያህል ለግል ሰብዕና ግንባታ እንደ ፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ቢጠቀሙበት – ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴም ቢሆኑ – በየሄዱበት የችግረኛ ልጅን እንዳለበሱ፣ ዳቦ እንዳደሉ፣ ብር እየዘገኑ እንዳደሉ፣ ባጠገባቸው ያለፈውን ሁሉ የሆነች የእጃቸውን በረከት እንዳቀመሱት ነው ያለፉት! ኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማርያም – ከራሱና ከኢሠፓአኮ አባሎቹ ጀምሮ – በሀገራችን ተመርቶ በሀገራችን የተሰፋ ካኪ እንልበስ ብሎ – ራሱንም ዜጎቹንም በካኪና አቡጀዲ መዓት ያጥለቀለቀ ሰው ነበር፡፡ ሌላ ነገር አያልብስ – ቢያንስ ያለውን ያልረባውንም ቢሆን ግን ለሀገር ለወገን ሁሉ አልብሶ አዳርሶ ያለፈ መሪ ነበር! በፍፁም እና በምንም ምንክንያት በሀገሩ ገበሬ፣ በሀገሩ ድሃ አኗኗርና ድህነት ያመጣው አለባበስ ላይ ተሳልቆ አያውቅም! በኢትዮጵያ ታሪክ ይህን የመሰለ ከክፉ ህሊናና ከፍ ካለ የሀገርና የወገን ንቀት የሚመነጭ ሀሳብም፣ ንግግርም፣ ተግባርም ያመጣ – ራሱ ማፈር ሲገባው ዜጋውን ስለታረዘ እፈር ብሎ ሀገራዊ የእፍረት ዘመቻ ያወጀ መሪ – እስከማውቀው ድረስ – መለስ ዜናዊ ብቻ ነው!
ያኔ መለስ ዜናዊ ‹‹ሁላችንም እንፈር!›› በሚል መሪ ቃል – የሀገራዊ እፍረትን አስፈላጊነት ባብራራበት ወቅት – እና የእርሱን የእፍረት አዋጅ ተከትሎ – የወያኔ-ኢህአዴግ ካድሬዎችና ባለሥልጣናት ከሚኒስትር ጀምሮ እስከ ፅዳት ሠራተኛ ድረስ – ከከተማ የመንግሥት ሠራተኛ እስከ ገጠር የገበሬዎች ማህበራት አባላት ድረስ – ሰዉን ሁሉ በስብሰባ ጠምዶ – ሁላችሁም እፈሩ፣ እንደ ሀገር እንፈር፣ እንደ ግለሰብ እንፈር፣ እንደ ምናምን.. እንፈር – እየተባለ በሚደሰኮርበት በዚያን ጊዜ – አንደ በረከት የሚባል ቆራጥ የንግድ ባንክ ሠራተኛ የነበረ ወጣት የኮሜርስ ግራጁዌት የነበረ ልጅ – ሥራ አስኪያጁን በእዚያው የእንፈር ስብሰባ ላይ ቃል በቃል፡-
‹‹እኔ በበኩሌ በሆንኩት፣ በምኖረው፣ እና በምሆነው ነገር፣
በሀገሬም ሆነ በኑሮዬ… አፍሬም አላውቅም! መቼውኑም
ቢሆን አላፍርም! እንዲያውም እኮራለሁ!››
ብሎት በስብሰባው ላይ የነበርነውን ሁላችንንም በሳቅ አፍርሶን ነበረ፡፡ ያ ልጅ በወቅቱ ከእኔ በዕድሜ ያነሰ፣ ነገር ግን ከእኔ በላይ ከፍ ያለ ድፍረትና ግንዛቤው የነበረ የልጅ-አዋቂ ነበረ፡፡ ጓደኛዬ በመሆኑ እስካሁንም ያራመደውን አቋም ሳስታውስ ያኮራኛል፡፡ ይህን የመሰሉ ብዙ ወጣቶች አዕምሮ ውስጥ ያለውን ሀገራዊ ኩራት ለመናድ ነበር እንግዲህ – መለስ ሞክሮ ሞክሮ ያልተሳካለት ነገር! (በከፊልማ ሳይሳካለትስ ይቀራል ለመሆኑ!?)
አንዳንዴ እጅግ ግርም ይለኛል! እንዴት የአንድ ሀገር መሪ በራሱ ሀገር፣ እና በታሪኳ፣ እና በጀግኖቿ፣ በነገሥታቷ፣ ጠብቃ ባቆየቻቸው ታላቅ ትውፊቶቿና ታሪካዊ ሀብቶቿ እንዴት ክብርና ኩራት አይሰማውም? እንዴት ሀገርን ጠብቀው ያቆዩት በባዶ እግራቸው በእሾህና ቆንጥሩ ላይ የሚራመዱ፣ እና የረባ ልብስ ያልነበራቸው – ነገር ግን ታላቅ የሀገር እና የትውልድ እና የወገን አደራን የተሸከሙ – ታላላቅ ሰማዕት ሕዝቦች መሆናቸውን የሚገነዘብ አዕምሮ ሳይኖረው የመሪነት ወንበር ላይ ፊጥ ሊል ቻለ? እኔ ግን እጅግ ይገርመኛል! ሲገርመኝ ይኖራል ይኸው እስከዛሬ ድረስ – እንደ መለስ ያለውን – እፍረትን እንደ ብሔራዊ ዳቦ ለዜጎቹ ያደለን፣ እፍረትን እንደ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርጎ የሰቀለ መሪን ሳስታውስ!
አንድ የመለስ አብሮአደግ የነበረ የዊንጌት ት/ቤት የክፍል መምህር በአንድ አጋጣሚ ያወጋኝን ገጠመኝ አንስቼ በጥያቄ ልሰናበት፡፡ መለስ ዜናዊ በዊንጌት ት/ቤት እያለ ነው፡፡ እና የሆነ ሀገራዊ በዓል ላይ ለተማሪዎች መጠነኛ ስጦታና ግብዣ ተበርክቶላቸው ተማሪው ሁሉ ተሰብስቦ ይጫወታል፡፡ የሀገርን ስም እያነሳ ይጨፍራል፡፡ መለስ ዜናዊ ብቻ – ለብቻው ከተማሪዎች ተነጥሎ  ጥጉን ይዞ ቁጭ ብሏል፡፡ መምህሩ ጠጋ ብሎ ይጠይቀዋል ታዳጊውን መለስን፡- ‹‹ለምን ከሌሎቹ ጋር ተቀላቅለህ አትጫወትም?›› ብሎ፡፡ መለስም ይመልሳል፡- ‹‹አይይ… እዚሁ ብሆን ይሻለኛል፣ አሁን መጫወት አልፈለግኩም!››፡፡ አስተማሪው ለወትሮው የሚያውቀው መለስ እንዲያ ጭምት የሆነበት ምክንያት አልገባ ይለዋል፡፡ እና ጫን ብሎ ይጠይቀዋል፡- ‹‹ይሄ እኮ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የሚያከብሩት ብሄራዊ በዓል ስለሆነ እኮ ነው ተማሪው ሁሉ ተነስቶ የሚያከብረው፣ የሚጨፍረው… እና አንተም ደስ ባይልህም.. በል ተነስና ከሌሎቹ ጋር ተቀላቅለህ ተጫወት!›› በማለት፡፡ ጭቅጭቁ አላስቀምጥ ያለው መለስ ግን የመጨረሻውን ቁርጥ ምላሽ ነገረው ለመምህሩ፡-
‹‹አይ ይቅርብኝ! እነሱ ኢትዮጵያውያን ስለሆኑ ለበዓሉ ይጫወቱ!
እኔ ግን ኤርትራዊ ነኝ እንጂ፣ ትዮጵያዊ አይደለሁም!
ስለዚህ ከእነርሱ ጋር አልጫወትም፣ ይቅርብኝ እዚሁ ሆኜ
እነርሱ ሲጫወቱ ብመለከታቸው ይሻለኛል!››፡፡
መምህሩ ይህን ከታዳጊው መለስ አንደበት ሲሰማ – በወቅቱ የቱን ያህል ድንጋጤ እንዳደረበት (‹‹ሾክድ›› እንደሆነ) ነበረ ያወጋው፡፡
እንግዲህ ከዚህ እውነተኛ ተሞክሮ ተነስተን መናገር የምንችለው ነገር ቢኖር – በወቅቱ መለስ በት/ቤት ጓደኞችና ጓደኝነት መሐል እንዲህ ዓይነት ያገነገነ አመለካከትን በራሱ አውቆ በውስጡ ለማስረፅ ገና ታዳጊ ነበረ፡፡ እና – ይህን ዓይነቱን አመለካከት በራሱ ሊያዳብረው እንደማይችል እንረዳለን፡፡ ምናልባትም – መለስ ዜናዊ በልጅነት አስተዳደጉ፣ በቤተሰቡ፣ ወይም በቅርብ ዘመዶቹ ዙሪያ እንዲህ ዓይነቱን ኢትዮጵያዊ እንዳይደለ፣ በኢትዮጵያዊነቱ ‹‹ቢሎንጊንግነስ›› ወይም እኔነትና አብሮነት የምንለውን፣ ወገንተኝነት የምንለውን ጤናማ የፍቅር ስሜት፣ በኢትዮጵያዊነቱ የመኩራትና አካባቢዬ፣ የምራመድበት ሥፍራ፣ የቆምኩበት ምድር የእኔ ነው፣ ብሎ እንዳይሰማው የሚያደርግ አስተሳሰብ ገና በጊዜ እንደተዘራበት ያሳያል፡፡
እና በ‹‹ዴቨሎፕመንታል ሳይኮሎጂ›› እንደሚታወቀው በእርሱ ዕድሜ ላሉ ሁሉ ጤናማ ግላዊና ሀገራዊ ሰብዕና ለመገንባት እጅግ አስፈላጊ ሆኖ የሚወሰደውን ‹‹ሴንስ ኦፍ ሰኪዩሪቲ›› (አጠቃላይ የደህንነት ስሜት፣ ለኔ ሀገር አማን ነው ብሎ የማሰብ ስሜቱን) የሚጎዳ – እና ከፍ ሲልም ኢትዮጵያዊነትን እንደ በታችነት ቆጥሮ የተቀበለን – ባላንጣዊ ፉክክር በውስጡ የታከለበትን – አመለካከት መለስ ያዳበረው ገና ከልጅነት ዕድሜው ነው ብለን ብንደመድም ስህተታችን ምን ላይ ይሆን??!
ይህን ሁሉ ስናስተውል የምናገኘው የመለስ ስዕል በውስጡ፣ በሀገሩ፣ በወገኑ፣ በማንነቱ እፍረት አድሮበት ያደገን ልጅ ነው፡፡ ይህ ኤክስፕላኔሽን ፀረ – ኢትዮጵያ አጀንዳን አንግቦ የትግራይን የሺህ ዓመታት ታሪክ፣ እና የኢትዮጵያን የሺህ ዓመታት ታሪክ ሊማጥፋት ቀን ከሌት ሲዳክር የኖረውን መለስ አስተሳሰብ ከምንጩ ያስረዳናል፡፡ ይሄው ትንተና – ምናልባትም በመሪነት ወንበር ላይ ተቀምጦ – የታሪክ ክስረትን፣ የሀገር እፍረትን ሲሰብክ የኖረው መለስ ስለምን ያን ዓይነት አስገራሚ ሰብዕና ተላብሶ ሊገኝ ቻለ? ለሚለው የማያባራ ጥያቄያችን ቢያንስ ከብዙ መልሶች እንደ አንዱ ሆኖ ምላሽን የሚሰጠን ይመስለኛል፡፡ ሀገራዊ እፍረትን እንደ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርጎ ስላውለበለበው “ጀግና” – ለጊዜው ከዚህ በላይ የምለው አይኖረኝም!
48ቱ የመለስ አጓጉል ቱሩፋቶች ገና አላበቃም፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!
( …./ ይቀጥላል )
Filed in: Amharic