>

የመለስ አጓጉል ትሩፋቶች!(- ክፍል አራት) አሰፋ ሀይሉ

የመለስ አጓጉል ትሩፋቶች!

አሰፋ ሀይሉ
(ክፍል አራት)
8ኛ/ ለፖለቲካ ትርፍ ብሔርን ከብሔር፣ ዘርን ከዘር እየሰነጠቀ ያንድ ሀገር ዜጎችን ያናከሰ (እና ገና የሚያናክስ) ጀግና!
በመለስ ዜናዊ ዘመን እጅጉን ጎልታ የወጣች አንዲት ቃል አለች፡፡ ‹‹መቻቻል›› የምትባል፡፡ ይህች መቻቻል የምትሰኝ ቃል ገና ከመነሻዋ በብዙዎች ተቃውሞ ገጥሟት ነበር፡፡ ይገርመኝ ነበር፡፡ ጤነኛ አዕምሮ ያለው የሰው ልጅ እንዴት ‹‹መቻቻል››ን (‹‹ቶለራንስ››ን) ይቃወማል? በመቻቻል ፋንታ ‹‹መበላላት›› የሚል ቃል የመንግሥት መመሪያ ሆኖ እንዲወጣ ነው ማለት ነው ፍላጎታቸው? እያልኩ እገረም ነበር፡፡ ኋላ ነው የተቃውሞው እውነትነት የተገለጸልኝ፡፡ ለካንስ የመለስ ዜናዊ ‹‹መቻቻል›› የተሰኘች ፖለቲካ እርስ በእርስ በሰላም ሲኖሩ የነበሩ ዜጎችን በዘርና በብሔር፣ በሐይማኖትና በጎሳ ልዩ ልዩ መሆናቸውን እንዲገነዘቡ – እና ልዩነታቸውን እንዲያውቁና ከተኙበት የአብሮነት ሰመመን እንዲነቁ የምትነፋ የማንቂያ ፊሽካ ነበረች፡፡
መቻቻል – የመለስ ዜናዊ የእብድ ገላጋይ ፖለቲካ ፊሽካ ነበር፡፡ አማራና ኦሮሞ ተቻቻሉ፡፡ ኦሮሞና ሶማሊ ተቻቻሉ፡፡ እስላምና ክርስትያን ተቻቻሉ፡፡ ስልጤና ጉራጌ ተቻቻሉ፡፡ አኙዋክና ኙዌር ተቻቻሉ፡፡ ይህ ነበር መለስ በየቦታው የሚያስነፋው ፊሽካ፡፡ ፊሽካው በተነፋበት ቦታ ሁሉ ከተኛበት የዘመን የመስማማት እንቅልፍ ተነስቶ እርስበርሱ ያልተናከሰ ዜጋ አይገኝም፡፡ ይህን የመለስን የተንኮልና የክፋት መለከት ሳስብ አንድ የአባቶቻችን አነጋገር ይመጣብኛል፡- ‹‹ወንዝ ዳር መቀደስ፣ የተኛን ሰይጣን መቀስቀስ!›› የሚል፡፡ እውነታቸውን ነው፡፡ የመለስ ዜናዊ የመቻቻል ፊሽካም እንደዚያ ዓይነት የወንዝ ዳር ቅዳሴ ነበረች፡፡ የተኛን ሰይጣን ለመቀስቀስ ሆነ ተብላ – ተጎራብተው ተዋህደው በሚኖሩ ሕዝቦች መካከል በመለስና ጎሰኛ ጭፍሮቹ አማካይነት የምነሰነስ በማር የተለወሰች እርስበርስ የማናከሻ መርዝ፡፡
በዚህ የመለስ ዜናዊ የዘር ጥላቻ ፖለቲካዊ ቅስቀሳ የተነሳ ‹‹የአማራ ነፍጠኛ ብሔር ተወላጆች ናችሁ፣ ሠፋሪዎች ናችሁ፣ መጤዎች ናችሁ፣ ወዘተ ›› በሚሉ የወያኔ-ኢህአዴግ የጎሳ ሥርዓት በፈለፈለላቸው የተለያዩ ጥላቻ ቅስቃሽ መጠሪያዎችና አመለካከቶች የተነሳሱ የተለያዩ ብሔር ተወላጆች… በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ‹‹የአማራ ተወላጅ›› ናችሁ የተባሉ ሠላማዊ ኢትዮጵያውያውያንን… ከምዕራብ ሐረርጌ፣ ከምዕራብ አርሲ፣ ከአርባጉጉ፣ ከጅማ፣ ከጉራፈርዳ፣ ከወለጋ፣ ከአፋር፣ ከቤኒሻንጉል፣ ከምዕራብ ሸዋ፣ እና ከአዲስ አበባ ዙሪያ አፈናቅለዋል፡፡ አሁንም ድረስ እያፈናቀሉ ነው፡፡
ማፈናቀል ማለት በአንድ ጀንበር የሚፈጸም ድርጊት አይደለም፡፡ በመቶዎችና በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ቤት ንብረታቸውና ሕይወታቸው ላይ አደጋ ጥለህ – የህግ ከለላ እንደሌላቸው በተግባር አሳይተህ – በጉልበት ከኖሩበት ቀዬ ያለምንም ፍትህ በጅምላ ማባረር፣ ማሳደድ ማለት ነው፡፡ ማፈናቀል ቀናትን፣ ሳምንታትን፣ ወራትን አሊያም ዓመታትን ሊወስድ ይችላል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን የመለስ ዜናዊ ዘረኛ ሥርዓት ጋሻጃግሬዎችና የታጠቁ ኃይሎች እጃቸውን አጣጥፈው መቀመጥ ብቻ ሳይሆን፣ ከአፈናቃዮቹና ከወንጀለኞቹ ጋር እየተባበሩ ዘር-ተኮር የጅምላ ግፍን ሲያነሳሱ፣ ሲፈጽሙና ሲያስፈጽሙ ኖረዋል፡፡
/በነገራችን ላይ ይህ ሁሉ ዘር ተኮር ጥቃትና ጭፍጨፋ፣ ዘር ተኮር ማፈናቀልና የመንግሥት ድጋፍ የታከለበት ግፍ እንዲሁ ዜና ብቻ ሆኖ ያለፈና የሚያልፍ ብቻ ሳይን በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ የሀገር ውስጥና ዓለማቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ተቋማት በማስረጃ ጭምር የተረጋገጠ አሳዛኝ የመለስ ትሩፋት ነው፡፡/ 
በመለስ ዜናዊዋ ኢትዮጵያ የመንግሥት ሥልጣንና የተፈጥሮ ሀብት የብሔር ቅርፅና ድንበር ተበጅቶለት መቀመጡ የሥርዓቱ ዓይነተኛ መፎከሪያ ገጽታ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በተለያዩ የሀገሪቱ መዳረሻዎች ብሔርና ብሔርን እየቀሰቀሱ ማናከስን የሥርዓቱን ዕድሜ ማስረዘሚያ ዓይነተኛ መንግሥታዊ ፖሊሲ ሆኖ ለቆጠረው የመለስ ዜናዊ ዘረኛ አስተዳደር ደግሞ – ይህ የፖለቲካ ቅርፅ ተሰጥቶት የመንግሥት መዋቅር ሆኖ በሀገሪቱ ሁሉ የተዘረጋ የዘርና ብሔር ፖለቲካ – ዓይነተኛ የከፋፍለህ ግዛው ፖለቲካዊ መሣሪያ ሆኖለት ቆይቷል፡፡ ልክ ክፋትን የተላበሱ አናሳ ቅኝ ገዢዎች ብዙሃኑ አፍሪካዊ በጋራ ቆሞና ተደራጅቶ ያሰፈኑትን የጭቆና ሥርዓት እንዳይዋጋና ራሱን ነፃ እንዳያወጣ ‹‹ያገሩን ሰው እርስበርሱ ማጣላትን፣ ማናከስን፣ ከፋፍሎ መግዛትን›› ሁነኛ የቅኝ ግዛት ዕድሜያቸውን ማስረዘሚያ መሣሪያ አድርገው እንደተገበሩት ሁሉ – የመለስ ዜናዊም በአናሳ ዘረኞች የሚመራ አምባገነናዊ ሥርዓት – ኢትዮጵያ የብሔሮች ሀገር ነች በማለት – እና ብሔሮችን የፖለቲካ ቅርፅ ሰጥቶ ሥልጣን በማከፋፈል ሰበብ እርስ በእርስ በመከፋፈልና በማናከስ – ስልጣኑን ለመቶ ዓመት አራዝማለሁ ብሎ የቆረጠ ሥርዓት ነበረ፡፡ እና ለመለስ በብሄርና ብሔር መካከል፣ በጎሳና ጎሳ፣ በነገድና በነገድ፣ በህዝብና በህዝብ መካከል የሚነሳ ክፍፍልና ግጭት ሁሉ – የሥልጣኑን መራዘም የሚያበስረው የእፎይታ ደወል ነበረ፡፡
በመሆኑም በርካታ መከሰት የሌለባቸው ግጭቶች መለስ ዜናዊ ሆነ ብሎ ባሰፈነው የከፋፍለህ-ግዛው የብሔር ፖለቲካ የተነሳ በየቦታው እዚህም እዚያም ተከስተዋል፡፡ ብዙ ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በወላይታና ሲዳማ፣ በወላይታና ሀድያ፣ በጉራጌና በስልጤ፣ በመስቃንና ማረቆ፣ በሱሪና በዲዚ፣ በቤኒሻንጉልና በጋምቤላ የተለያዩ ስፍራዎች፣ ለምሳሌ በበርታና በጉሙዝ፣ በኙዌርና በአኝዋክ፣ በሶማሊ የተለያዩ ጎሳዎች መካከል፣ በሶማሊና በኦሮሞ፣ በአፋር የተለያዩ ጎሳዎች መካከል፣ በሌሎችም ብዙ የኢትዮጵያ ሥፍራዎች ብዙ የጎሳና ብሔር ግጭቶች የተከሰቱት በመለስ ዜናዊ ሆነ ተብሎ በተጎነጎነ ብሔርና ብሔረሰብን ለፖለቲካዊ ፍጆታ ጠቀሜታ ሲባል እርስ በእርስ እንዲሻኮቱና እንዲናከሱ ‹‹በመቻቻል ስም ለፀብ እየባረከ›› በሩን ወለል አድርጎ በለፈተው መንግሥታዊ ዜጋን እየሰነጠቁ የማበላላት ፖሊሲ በመተግበሩ የተነሳ እንደሆነ በርካታ ጥናቶች ያረጋገጡት ጉዳይ ነው፡፡
ልክ ቅኝ ገዢዎች በአፍሪካ ላይ የዘሩት ዘር ለይቶ የመቧጨቅና የመበላላት ፖሊሲ እነርሱ ከአፍሪካ ከተባረሩም በኋላ ልክፍቱ በአፍሪካውያን መካከል እንደቀጠለ ሁሉ – የሚገርመውና የሚያሳዝነው ነገር – የመለስም የከፋፍለህ ግዛው ዜጎችን እርስበርስ የማጠላላት፣ የማናከስ፣ የማበላላትና የማጋጨት ቱሩፋቶች – ከመለስም ሞት በኋላ የቀጠሉና ገና የሚቀጥሉ መሆናቸው ነው፡፡ መለስ ዜናዊ በተለያዩ የኢትዮጵያ ግዛቶች ህዝብን ከህዝብ እየለየና እየሸነሸነ የደገሳቸው የግጭት ፈንጂዎች በሕይወት እያለም ብቻ ሳይሆን ከሞቱም በኋላ ሲፈነዱ ታይተዋል፡፡ ያገራችን ሰው ሲተርት ፡- ‹‹ነገረኛ ሰው፣ ከሞትኩ በኋላ ሬሳዬን መንገድ ዳር ቅበሩልኝ ብሎ ይናዘዛል›› ይላል፡፡ የመለስም ነገር እንደዚያ ነው፡፡ ከሞተም በኋላ እያገረሸ የሚፈነዳ ግጭትን ነው ጠምቆልን የሞተው፡፡
ሌላ ሌላውን ጊዜ ጠብቆ የሚፈነዳ የግጭት ‹‹ፖቴንሺያል ስፖትስ›› ትተን – ራሱ መለስ ዜናዊ ‹‹ወርቅ ሕዝብ›› እያለ ሲያሞካሸው የኖረውንና በስሙ እየማለ ሌሎችን ሲገዛበት የኖረውን የፈረደበትን የትግራይ ሕዝብ እንደ ምሳሌ መውሰድ እንችላለን፡፡ የትግራይን ሕዝብ ‹‹የፈረደበት›› ብዬ የጠራሁት ያለምክንያት አይደለም፡፡ ይህ ህዝብ ከጥንት ቅኝ ገዢዎች ጀምሮ በኢትዮጵያ ላይ ዕጢያቸውን የሚጥሉ ኃይሎች ሁሉ የመጀመሪያው ቀዳሚ ሰለባ የሚሆነው ይኸው የፈረደበት የትግራይ ሕዝብ ስለሆነ ነው፡፡ ባለፉት የ150 ያገራችን ታሪክ ውስጥ የትግራይ ሕዝብ በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት ጦርነት ተለይቶት አያውቅም፡፡ ወደፊትም መለስ ደግሶለት ያለፈውን የግጭት ድግስ ሲያስቡት ልብን ያደማል፡፡ ስለዚሁ ከመናገሬ በፊት ግን – ስለ አንድ ሁልጊዜ ስለሚከነክነኝ ነገር ላንሳ፡፡
መለስ ዜናዊና ጭፍሮቹ ስለምን የትግራይን ወጣት በደርግ የጦርነት እሳት ውስጥ ጨመሩት? ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተለይቶ የትግራይ ህዝብ የግድ ጦርነት ውስጥ እንዲገባ የሚገፋው – እና በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ልጆቹን ያደማ – እና ከእነርሱ ጋር የተዋጉ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሌሎች ኢትዮጵያውያንን ያደማ – በዚያ አሰቃቂ ጦርነት ውስጥ እንዲገባ የትግራይን ህዝብ የሚገፋው – ከሌላው ኢትዮጵያዊ የተለየ ልዩ እና አስገዳጅ እና አንገብጋቢ ምክንያት ነበረው ወይ?
በበኩሌ በደርግ ሥልጣን ማግሥት የመለስ ዜናዊ የወያኔ ጭፍሮች ወደ ጫካ (እነርሱ ‹‹በረሃ›› ወደሚሉት) እንገባለን ብለው የሚያስወስናቸው – እና በትግራይ ሕዝብ ላይ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ተነጥሎ የደረሰበት የተለየ ግዙፍ በደል ወይም ሌላ ጠላትነት በፍፁም አልነበረም ባይ ነኝ፡፡ ለዚህ ብዙ ማስረጃዎች አሉ፡፡ የደርግ መንግሥት ከትግራይ ሕዝብ ጋር ጠላትነትም ሆነ የተለየ ተቀናቃኝነት አልነበረውም፡፡ ለኤርትራ ተገንጣዮች – አዎ እነርሱን ተፋልሞ ለማጥፋት ደርግ ተንቀሳቅሷል፡፡ ወያኔም በወቅቱ መንግሥት ሆኖ ቢሆን ኖሮ – እቅፍ አበባ አበርክቶ እሺ ተገንጠሉልኝ ብሎ እንደማይሰጥ ሳይታለም የተፈታ ነው! እና መለስ ዜናዊ – ሻዕቢያ እንዲገነጠል ለመርዳት ሲል ብቻ – በማያገባውና በማይመለከተው ጉዳይ – ያን ሁሉ ሺህ የትግራይ ህዝብ ደም በሰው ጦርነት ውስጥ ከትቶ ያፈሰሰ ግፈኛ አረመኔ ነው፡፡
አሁን በትግራይ ህዝብ መካከል በወያኔ ትግል ስም የሰፈነው ‹‹አምልኮተ መለስ›› በነገሰበት የአስተሳሰብ ሁናቴ ላይ ሆነን – ይሄንን እውነት የሚቀበል ሕዝብ እንዳይፈጠር ተደርጎ ይሆናል፡፡ የብዙ ዓመታት ሸፍጥ የተሞላ ውሸት ሲደጋገምም እውነት መስሎ ተቀባይነት አግኝቶ ሊሆንም ይችላል፡፡ በበኩሌ ግን የታሪክ ሀቅ በፍፁም ተሸፍኖ አይቀርም፡፡ እናገራለሁ፡፡ እውነት የቱንም ያህል ዘመን ተሸፍና ትቆይ ይሆናል እንጂ ተደብቃ አትቀርም፡፡ እና ይህን መለስ ዜናዊ ለኡርትራ ተገንጣዮች ወግኖ የትግራይን ሕዝብ በውሸት ሰበካ አታልሎና አወናብዶ የጦርነት ማገዶ በማድረግ በከንቱ ያፈሰሰውን የዚያን ሁሉ ኢትዮጵያዊ ወገናችን ደም በእጁ ያለበት ግፈኛ አረመኔ እንደነበረ የሚረዳ አንድ የወደፊት ትውልድ መምጣቱ እንደማይቀር እርግጠኛ ሆኜ እናገራለሁ፡፡
ወደ ተነሳሁበት ነጥብ ልመለስ፡፡ እና መለስ ዜናዊ እንዴት ያለ የጥላቻ፣ የመለያየትና የግጭት አጀንዳ ለአሁኑም ሆነ ለወደፊቱ የትግራይ ህዝብ ቀብሮለት እንዳለፈ ጥቂት ልናገር፡፡
ቀደም ባለው ክፍል የገለጽኩት እውነት ቢሆንም – በመለስ ዜናዊ ‹‹ብሔር ብሄረሰቦች›› እየተባለ በሚሰበክባት ኢትዮጵያ – ክፉ ስም ካልሆነ በስተቀር የትግራይ ሕዝብ የተረፈለት ምንም ነገር የለም! አሁንም የትግራይ ህዝብ በአስከፊ ድህነት ውስጥ ነው፡፡ አሁንም የትግራይ ህዝብ በጭለማ ውስጥ ነው፡፡ አሁንም የትግራይ ህዝብ የሚጠጣው ውሃ የለውም፡፡ አሁንም ቢሆን 98 በመቶው የትግራይ ህዝብ በየዕለቱ ከደረቅ አፈር ጋር አፈር መስሎ ሲታገል የሚኖር ምስኪን ለፍቶ አዳሪ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን የትግራይ ህዝብ እንዲያውም ለምና ደጋ ሥፍራ ላይ ከሚኖሩት የተቀሩት የሀገሪቱ ሕዝቦች አንፃር ሲተያይ ‹‹ዲስአድቫንቴጅድ ሂዩማን ከንዲሽን›› ላይ የሚገኝ ሕዝብ ነው፡፡
የመለስ ዜናዊ የጥቅም ቱሩፋት የደረሳቸው ጥቂት የአድዋ ጭፍሮች ናቸው፡፡ እነርሱም ጥቂት፡፡ እና ሌሎች ጥቂት የወያኔ ካድሬዎች፡፡ ጥቂት በመለስ ዜናዊዋ ጠባቧ ኢትዮጵያ የብሄር ታርጋ እያውለበለቡ የጥቅም ፍርፋሪ የተቃመሱ ጥቂት በጣም ጥቂት የትግራይ ተወላጅ ባለሀብቶች ናቸው፡፡ ከእነዚህ የመለስ ፍርፋሪ በሊታዎች መሐል በራሳቸው ጥረት ጥረው ግረው ሀብት ያፈሩትን አላካትትም፡፡ እና የተቀረው 98 ፐርሰንቱ የትግራይ ሕዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የባሰ እንጂ የተሻለ ኑሮም፣ የኑሮ ተስፋም ያለው አይደለም፡፡ ይሄንንም እውነት ቢሆን የመለስ በትግራይ ስም የተነዛው የፕሮፓጋንዳ ውሸት ስለሚሸፍነው ብዙው ሰው ለመቀበል አይፈልግም፡፡ የሚገርመው የወያኔ ተቃዋሚዎችም ይህን አይቀበሉትም፡፡ ራሳቸው ወያኔዎቹም ደግሞ ሕዝቡን ባለበት ትተው በስሙ እየገዙ ጥቂቶችን በጥቅም አንቀልባ ላይ አዝለው መቆየታቸውን ከሕዝብ ሰውረው ዘለዓለም የሚዘልቁ ስለሚመስላቸው አይቀበሉትም፡፡ እውነቱን የሚያውቀው ብቻ ያውቀዋል፡፡
እንዲያም ሆኖ – ባልበላበትና ባልዋለበት – የጥቂት የመለስ ጭፍሮችንና አምቻ ጋብቻዎች ጥቅምና የሥልጣን ብልግና ለመጠበቅ ሲባል – የትግራይ ሕዝብ ለባለፉት ዘመናት ቀዳሚ የጦርነት ገፈት ቀማሽ ሆኖ የመገኘቱ አስከፊ የታሪክ ቱሩፋት ሳያንሰው – በአሁኑ ወቅትም ሆነ በወደፊቱ የሀገራችን የፖለቲካ ሂደት ደግሞ ከፍ ያለ የግጭት አደጋ ያንዣበበት ሕዝብ ለመሆን በቅቷል፡፡ ይሄ ደግሞ የሌላ የማንም ሥራ ሳይሆን የዚያው የአረመኔው የመለስ ዜናዊ እጅ ሥራ ውጤት ነው፡፡ መለስ ዜናዊ የትግራይን ህዝብ ከተጎራባች ሕዝቦች ጋር ለማቃቃር ያደረገው ምንድነው? ያለምንም የህዝብ ምክክርና ይሁንታ በታጣፊ ክላሽና ታንክ ኃይል የጎንደርን፣ የወልቃይት ፀገዴን፣ የፀለምት መሬት ከጎንደር ላይ ቆርሶ – እና የሥራ ቋንቋውን ከአማርኛ ወደ ትግርኛ ቀይሮ – እነዚህን ያካተተ ምዕራባዊ ትግራይ የተሰኘ ክልል ወደ ትግራይ አካልዬአለሁ በማለት – ትናንትም ሆነ ዛሬ የትግራይ ህዝብ በወያኔ ስምና እኩይ ተግባር የተነሳ በብዙው የጎንደር ህዝብ ዘንድ የተፈጠረውን ሰፊ ቁጭት፣ መቀናቀንና ከፍ ሲልም ጥላቻና ምሬት አትርፎለት አልፏል፡፡
ከኤርትራስ ጋር? መለስ ዜናዊ – ኤርትራን ለማስገንጠል ሲል የትግራይን ምሁርና ገበሬ አሰልፎ በጦርነት እሳት ውስጥ ሲማግድ መቆየቱ ሳያንስ – ወያኔን አምኖ የተከተለው የትግራይ ህዝብ ለሻዕቢያ ሲል ያንን ሁሉ ደም ካፈሰሰም በኋላ ደግሞ – መለስ ደም የበቃው አይመስልም፡፡ እና ከኤርትራ ጋር አዲስ የድንበር ውዝግብ ፈጠረለት፡፡ አወዛጋቢ የሆኑ የባድመና ኢሮብ እና ሌሎች ጥቃቅን አካባቢዎችን መሠረት አድርጎ ከኤርትራ ጋር ጦርነት ገባ፡፡ የትግራይ መሬት ዳግም በሰላም ዘመንም ወደ ጦርነት እሳት ተቀየረ፡፡ ከዚያ በኋላ የስንት ሺህ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ደም ከፈሰሰ በኋላ ደግሞ – መለስ ሆነ ብሎ በገባበት ስምምነት የነሳ – በዓለማቀፍ ፍርድቤት ውሳኔ መሰረት ለኤርትራ ስጥ የተባለውን መሬት ‹‹አልሰጥም›› ብሎ ሩጫውን አገባደደ፡፡ ይኸው እስከዛሬም ድረስ በሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ከሚገኝ ሕዝብ በተለየ መልክ የትግራይ ሕዝብ ካሁን ካሁን ከኤርትራ ጥቃት ይመጣብኛል ብሎ የሚሳቀቅ ሕዝብ ሊሆን በቅቷል፡፡ /እንዴ!? ኤርትራ ሚሳኤል ተኩሳ አውሮፕላን ትመታለች ተብሎ እኮ – የትግራይ አየር ማረፊያ ተሰርቶ የምናገኘው ከኤርትራ ድንበር 70 እና 80 ኪሎሜትር ርቆ እኮ ነው!!/
ይሄ የወረራ ስጋት፣ ይሄ የጦርነት ስጋት፣ ይሄ ሁሉ የትግራይን ክልል የግጭት ቀጣና በማድረግ የተደመደመው የስጋትና የጦርነት ቅንቅን በማን የተዘራ ነው? በራሱ በመለስ ዜናዊ የተዘራ ነው! ያን ሁሉ የትግራይ ወጣት ደም ለሻዕቢያ ጦርነት ግብዓት አድርጎ ገብሮ ኖሮ፣ ሲሞትም ደግሞ ከሻዕቢያ ጋር ጦርነትንና ግጭትን ሥጋትን ደግሶለት ሞተ፡፡
ከወሎስ በኩል? መለስ ዜናዊ የአካባቢውን ሕዝብ ሳያማክርና ከአጎራባች ሕዝቦች ጋር በቂ ውይይት ሳያካሂድ ባገነገነ የዘር ጥላቻ ተለክፎ ቀደም ሲል በወሎ አስተዳደር ስር ሲተዳደሩ የኖሩ አካባቢዎችን በብሄርና በቋንቋ በመሸንሸን ከፊሎቹን (የራያ አካባቢዎች) ወደ ትግራይ ክልል አካለለ፡፡ እና ዛሬም ድረስ ይኸው የትግራይ ሕዝብ በዚያም በኩል ሌላ ግጭትና መጪ የግጭት ሥጋት ውስጥ ተደንቅሮ ይገኛል፡፡ መለስ ለትግራይ ሕዝብ ጠምቆለት ያለፈው እነዚህን ግጭቶች ብቻ አይደለም፡፡ አምባገነንነትንና ጭቆናን፣ ሙስናንና ሀገራዊ ምዝበራን፣ የቡድን ዝርፊያን – ይህ ሁሉ ዓይን ያወጣ ተግባር – የአንድ የመለስ ዜናዊ የተከለው የዘራፊ አምባገነን ሥርዓት የእጅ ሥራ ሆኖ ሳለ – መለስ ይህን ሁሉ ግፍ የብሔር ስም እንዲሰጠው በማድረግና በማሰጠት – ዛሬ የትግራይ ልጆች በሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መካል እንደልባቸው ለማለፍና ለመተላለፍ የሚሳቀቁበትን ሁኔታ ፈጥሮ ተደምድሟል፡፡
እና መለስ ለትግራይ ሕዝብ የጠመቀለት በያቅጣጫው የተቀበረ የግጭት ፈንጂን ብቻ ሳይሆን – በዙሪያው የተጋረጠ የጥላቻ ባህርን ጭምር ነው፡፡ መለስ ዜናዊ ሕዝብና ሕዝብን በብሔር ከፋፍሎ ከማነካከሱና ከማጫረሱ በፊት መቼ ነው – ከመቼ ወዲህ ነው የወሎ ሰው – ለትግራይ ሕዝብ እህል አይጫንም ብሎ መንገድ ዘግቶ የሚያውቀው? መቼ ነው የጎንደር ሕዝብ የትግራይ ተወላጆችን መርጦ ለጥቃት ያጋለጠው? መቼ ነው የጎጃም ሕዝብ የትግራይ ተወላጆችን መርጦ ካገር ያበረረው? መቼ ነው የኦሮሞ ሕዝብ ትግሬን በትውልድ ሀገሩና በፊት ገፁ እየመረጠ የጥላቻ ሰለባ ሊያደርግ የተነሳሳው? ይሄ ሁሉ የመለስ ዜናዊ ጭፍንና ከዶሮ ጭንቅላትም የጠበበ የወደፊቱን የህዝቦች መልካም ጉርብትና ያላገናዘበ፣ ያላገናዘበ ብቻ ሳይሆን ማናቸውንም በኢትዮጵያ ጥላ ስር ዜጎች በፍቅር ተሳስረው የሚኖሩበትን ሀገራዊ ወገናዊ ትስስርና ትብብርን ጨርሶ የሚጠላና ለመበጣጠስ ቀን ከሌት እንቅልፍ አጥቶ የሠራ እኩይ መሪ በመሆኑ የተነሳ የታፈሰ ውጤት ነው፡፡ ይህን የመለስ የክፋት አዝመራ ገና ውጤቱ ሙሉ በሙሉ አልታየም፡፡ ገና አዝመራው አልታጨደም፡፡ ገና ወደፊት ብዙ ጦሱንና ግሳንግሱን ይዞ የሚግተለተል ነው፡፡
መለስ በሕይወት እያለ ብቻ ሳይሆን፣ ከሞተም በኋላ የትግራይ ሕዝብ ከሌሎች አጎራባች ሕዝቦች ጋር ለግጭትና ለመበላላት የሚዳረግበትን የወደፊት የግጭትና የመነካከስ አጀንዳ አስቀምጦ ያለፈ እኩይ መሪ ነው፡፡ የትግራይ ሕዝብን ብቻ አይደለም – የአማራን ሕዝብ – የሶማሊን ሕዝብ – የአፋርን – የጋምቤላን – የቤኒሻንጉልን – የአደሬን – የሲዳማን – የጋምቤላን – የጉራጌን – የወላይታን – የስልጤን – የኦሮሞን – እና የሌላውንም ሁሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ – እርስ በእርሱ የሚጋጭበትንና የሚበላላበትን እሾህና ፈንጂ ቀብሮ የሄደ መርዘኛ የግጭት ጠማቂ – እና በፀረ-ትግራይ፣ በፀረ-ኢትዮጵያ ተንኮሉ ተብትቦን ያለፈ እኩይ ሰው ነበር፡፡ ቦታውና የጽሑፉ ዓላማ አይፈቅድ ሆኖብኝ እንጂ ሌሎችንም በርካታ እውነታዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ ግፎቹና ጦሶቹ ተቆጥረው አያልቁም፡፡ ይህንና ይህን ሁሉ ስንመለከት ነው መለስ ዜናዊ ለጊዜያዊ የፖለቲካና የዝርፊያ ትርፍ ሲል ብሄርን ከብሄር እየሰነጠቀ ያናከሰ የዘመናችን የመጠላላትና የመበላላት ጀግና ተብሎ ቢጠራ ቢያንሰው እንጂ ፈጽሞ የማይበዛበት፡፡
የሰው ልጅ ጭንቅላት የቱንም ያህል ቢማርና ቢመራመር – ቅንነት ካልታከለበት – ሊያስከትል የሚችለውን ጥፋት ለማየት – ከመለስ ዜናዊ በላይ ሀገር ያወቀው ሕያው ምስክር ከየትም አይገኝም! እና አፈሩን ያቅልልለት ወይ? … እኔ ምን አግብቶኝ – በእግዜሩ ሥራ?! ምን ጥልቅ አድርጎኝ ደሞ!!?!!? የሰው አልቆብኝ ብዬ ብዬ በእግዜሩ ሥራ ልግባ ደግሞ…. !!!?
ለማንኛውም ተከታዩን ከተጻፈ ወደ 55 ዓመት የሚጠጋው የኢትዮጵያ ገጣሚና ቀደምት ምሁር የከበደ ሚካኤልን ግጥም ለአንባብያን ጋብዤ የዛሬን አበቃሁ፡-
“ዕውቀትና ክፋት (በክቡር ከበደ ሚካኤል)
ብዙ ሰዎች አሉ ባህርያቸው የከፋ
ዐዋቂዎች ተብለው ስማቸው የጠፋ ፡፡
በዕውቀት ተመስግነው በጣም የተማሩ
ጥበብን ዕውቀትን የተመራመሩ ፣
ግን በሕይወታቸው ባለም ላይ ሲኖሩ
ብዙ መጥፎ ሥራ በሰው እየሠሩ
ተሰድበው ተጠልተው ተንቀው የቀሩ ፡፡
(-ክቡር ከበደ ሚካኤል፣ “ዕውቀትና ክፋት”፣ ከ“ብርሃነ ኅሊና” መድብል)
በቀጣዩ ክፍል እስከምንገናኝ – መልካም ጊዜ፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
Filed in: Amharic