>

ሕገ መንግሥታዊነት በህወሀትና በብልጽግና!?! (በፍቃዱ ኃይሉ)

ሕገ መንግሥታዊነት በህወሀትና በብልጽግና!?!

 

በፍቃዱ ኃይሉ
በኢትዮጵያ ባለው የኃይል አሰላለፍ ብልፅግና እና ሕወሓት ከበላይ ይገኛሉ። እነዚህ ሁለት ኃያላን ቡድኖች ግን አንዱ ሌላውን እንደ ባላንጣ መከታተል ከጀመረ ውሎ አድሯል። ሕወሓት በአምሳሉ የሠራው ኢሕአዴግ በብልፅግና መሪዎች ፈርሶ የዳር ተመልካች መደረጉ የእግር እሳት ሆኖበታል።

ወቅቱ የሕገ መንግሥታዊነት ሙግቶች የተጧጧፈበት ነው። ኢትዮጵያ ከገባችበት የሕገ መንግሥት ተቃርኖ ወይም ክፍተት በዚያው በሕገ መንግሥታዊ መንገድ መፍታቷ የግድ አስፈላጊ እንደሆነ ምሁራን እና ብዙዎቹ የፖለቲካ ልኂቃን ይስማማሉ። ሕገ መንግሥቱ የዚህን ያህል አስፈላጊ ሰነድ እንደሆነ በሕዝባዊ ተዋስዖ ታይቶ አያውቅም። ችግሩ በተቀናቃኞቹ መካከል ያለው የሕገ መንግሥታዊነት አረዳድ ለየቅል መሆኑ ነው።

በኢትዮጵያ ባለው የኃይል አሰላለፍ ብልፅግና እና ሕወሓት ከበላይ ይገኛሉ። እነዚህ ሁለት ኃያላን ቡድኖች ግን አንዱ ሌላውን እንደ ባላንጣ መከታተል ከጀመረ ውሎ አድሯል። ሕወሓት በአምሳሉ የሠራው ኢሕአዴግ በብልፅግና መሪዎች ፈርሶ የዳር ተመልካች መደረጉ የእግር እሳት ሆኖበታል። ብልፅግናም በበኩሉ የሁሉንም ክልሎች አስተዳደሮች የራሱ ሲያደርግ ሕወሓትን ብቻ ባለማንበርከኩ ቁጭት አለበት። በሁለቱ ኀይሎች መካከል ያለው ፀብ ፖለቲካዊ ነው፤ ነገር ግን በሁለቱም መካከል በሕጋዊ እና ሞራላዊ የበላይነት የሚመሩ ለማስመሰል እየተፍጨረጨሩ ነው። የመጨረሻው ውሳኔ ግን በሕገ መንግሥት አግባብ ከመሆኑ ይልቅ በኃይል እና ደጋፊዎች ብዛት የመሆኑ ዕድል ሰፊ ነው።

ሕገ መንግሥታዊነት በኢትዮጵያ

የመንግሥት የኃይል ምንጭ፣ ሥልጣንና ገደብ የሚወሰነው በሕገ መንግሥት ነው። ሕገ መንግሥታዊነት ደግሞ መንግሥታት በዚህ መመሪያ ሥር የመተዳደራቸው ጉዳይ ነው። ይሁን እንጂ የሕገ መንግሥታዊነት ጉዳይ ከመጤፍም ተቆጥሮ አያውቅም። እንዳጋጣሚ ሆኖ፣ ምርጫ ተራዝሞ አያውቅም። ይሁን እንጂ ሕገ መንግሥታዊ መብቶች ብዙ ጊዜ በይፋ ተጥሰዋል። በተለይም የመንግሥት ሥልጣን የሚፈትኑ ሕገ መንግሥታዊ መብቶች እንዳልነበሩ ሆነው ተዘንግተዋል። ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት ተገድቧል፣ የመደራጀት መብት ተሸርሽሯል፣ ሌላው ቀርቶ «ሕገ መንግሥቱ ይከበር» ብለው የጠየቁ ወጣቶች ታስረዋል። በምርጫ ረገድም ቢሆን በተለይም በምርጫ 2002 እና በምርጫ 2007፣ ምርጫዎቹ የይስሙላ ከመሆናቸው የተነሳ የክልሎች እና የፌዴራል ምክር ቤት ወንበሮች ሕገ መንግሥታዊነት በሰፈነባቸው አገሮች ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በገዢው ፓርቲ ፍፁም የበላይነት ሥር ወድቀዋል።

ይህ ሕገ መንግሥታዊነት የማያውቅ የፖለቲካ ታሪክ ብዙኀኑን ዜጎች እና የፖለቲካ ልኂቃኖቻቸውን በሕገ መንግሥታዊነት ሳይሆን በኃይል የበላይነት እንዲያምኑ አድርጓቸዋል። የቅርብ ጊዜ የፖለቲካ ለውጥ ሒደትም የዚህ ትልቅ አካል እንጂ ግንጥል ክስተት አይደለም።

የብልፅግና አጭር ታሪክ

ኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥት የቱንም ያህል ሕዝባዊ ተቀባይነት ቢያጣ በምርጫ ተለውጦ አያውቅም። በዚህም የተነሳ የፓርላማ ወንበሮችን መቶ በመቶ ያሸነፈው እና በሕወሓት የበላይነት ይመራ የነበረው ኢሕአዴግ በዓመቱ ሕዝባዊ አመፅ ተጋፍጧል። ሕዝባዊ አመፁን የሕወሓት የበላይነት ያስቆጫቸው የነበሩ የኢሕአዴግ አባላት ከውስጥ ተቀላቅለውት ሕወሓትን ከመሐል አገር ፖለቲካ አሰናብተዋል። አልፎ ተርፎም፣ ነባሩን መዋቅር እና አካሔድ ተከትለው ኢሕአዴግን አፍርሰው ብልፅግና ፓርቲን በመቃብሩ ላይ ገንብተዋል። በዚህ መንገድ ብልፅግና ፓርቲ የፌዴራሉ እና የስምንቱ ክልሎች ገዢ ፓርቲ ሲሆን፥ አንድም ምርጫ በሥሙ መወዳደር አላስፈለገውም ነበር።

የሕወሓት አጭር ታሪክ

ሕወሓት ሥልጣኑን አሐዱ ብሎ የጀመረው በምርጫ ሳይሆን በትጥቅ ትግል ባገኘው ድል ነው፤ ለሦስት ዐሥርት ዓመታት የክልሉ መሪ የሆነውም ሕገ መንግሥታዊ በሆነ አመራር አይደለም። ሕወሓት በትግራይ ሕዝብ እና በድርጅቱ መካከል ልዩነት እንደሌለ ደጋግሞ ሲናገር ከርሟል። በክልሉ ጠንካራ ተቃዋሚዎች አንዲኖሩ በፍፁም አይፈቅድም። ሕወሓት ከገዢው ግንባር ከተገለለ በኋላ መቐለ ሲከትም፣ ተስፋ ቆርጦ አልተቀመጠም። ክልሉን በበፊቱ ፀጥ ለጥ የማድረግ ባሕሪው ቀጥሎበታል። ማዕከላዊ መንግሥቱን ጠላት አድርጎ በመሣል ከበፊቱ የበለጠ ድጋፍ አሰባስቧል። የጎደለበት ነገር፣ ባለፈው ምርጫ አማካይነት ፌዴራል መንግሥቱ ውስጥ አግኝቶት የነበረው የገዢ ፓርቲ አካልነት፣ ሌላ ምርጫ ሳይደረግ መነጠቁ ነው።

ከምሁራኑ ትንታኔ ባሻገር

ምሁራኑ ሕገ መንግሥታዊ አመራጮችን እየተነተኑ ነው። ብልፅግና እና ሕወሓት ግን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ጨዋታ ከሕግ ይልቅ ከኃይል አሰላለፍ መሆኑን ስለሚያውቁ ፖለቲካውን እያጦዙት ይገኛሉ። ነገር ግን ሁለቱም ሕገ መንግሥታዊነትን ለዓመል ያነሳሉ። ብልፅግና ፓርቲ ሕገ መንግሥቱን አስተንትኖ ሲያበቃ፥ የሕገ መንግሥት ትርጓሜ ብቸኛ አማራጭ ነው ብሏል፤ ትርጓሜውም ሥልጣኑን እንደሚያስቀጥልለት እርግጠኛ ነው። ሆኖም ሕወሓት ትክክለኛው ሕገ መንግሥታዊ አማራጭ ባላደራ መንግሥት መመሥረት እንደሆነ በሥራ አስፈፃሚ አባሉ (ጌታቸው ረዳ) በኩል ሲናገር ሰንብቶ ነበር። የኋላ ኋላ በክልላችን ምርጫ እናካሒዳለን ብሎ የወሰነው የሕወሓት መንግሥት፥ የትግራይ ክልል ሕገ መንግሥት የሚሰጠውን አማራጭ ግን ማስተንተን ላይ ምንም አልሠራም። ይህም ጉዳዩ የፌዴራሉን መንግሥት ማስጨነቅ ላይ እንጂ ሕገ መንግሥታዊነት ላይ እንዳልሆነ ያሳብቅበታል።

ሕወሓት እና ብልፅግና ከሕገ መንግሥታዊነት ዲስኩራቸው በስተጀርባ ደጋፊዎቻቸውን ለማሰባሰብ እየተፍጨረጨሩ ይገኛሉ። ይህ ግን ለሕወሓት እምብዛም አልሠራለትም። ብዙዎቹ ምርጫው በሚራዘምበት ጊዜ ብልፅግና ፓርቲ እየመራ ይቆይ ብለዋል። ሌላው ቀርቶ በሕወሓት መሪነት የተሰባሰቡት «ፌዴራሊስት ኃይሎች» የተባሉ የፖለቲካ ቡድኖች ሳይቀሩ ይህንኑ የሚደግፍ መግለጫ ትላንት ሰጥተዋል። ሕወሓት ብቻውን የቀረ ይመስላል፤ የፈለገውን ያህል ግፊት ቢያደርግ ምርጫ ማድረግ የሚችለው ክልሉ ውስጥ እንጂ የፌዴራሉን መንግሥት ማስገደድ አልሆነለትም። በዚያ ላይ ምርጫ ማሰናዳት በሕዝብ ተወካዮች ምርጫ ቤት ተጠሪነት ሥር ያለው ምርጫ ቦርድ ሥልጣን ነው። ስለሆነም፣ ሕወሓት የጠላውን የፌዴራሉ ንዑስ አባልነት ፈቅዶ ካልተቀበለ ውጤቱ ማንም የማያተርፍበት ፖለቲካዊ ቀውስ ብቻ ነው የሚሆነው።

Filed in: Amharic