>

አከራይዋ - ሽራፊ ወግ!!! {በእውቀቱ ስዩም}

አከራይዋ – ሽራፊ ወግ!!!

 {በእውቀቱ ስዩም}
 ቤቱን በተከራየሁት በማግስቱ ሴትዮይቱ
 ”ተሰማማህ?” አሉኝ።
 ‘አዎ! ጥሩ ነው !”
”እንግዲህ ፀባይህን አሳምረህ መኖር ነው ። ፀባይህን ካሳመርህ ድርሽ የሚልብህ ሰው የለም! ”
 ዝም አልኳቸው ።
”ካንተ በፊት ይህን ቤት የተከራየው ሰው ፀባዩ    ስላላማረ ነው ያባረርኩት!”
 አሉኝ ።
 ዝም አልኳቸው ።
” ይገርምሃል ። ፍፁም ስግብግብና ራስ ወዳድ ነበር ። በየቀኑ አንዳንድ ባልዲ ውሃ ይቀዳል ። ልብ አርግ! አንድ ባልዲ !…ሥራዬ መምህር ነው  ያለኝ ….የሚወስደው የውሃ ብዛት ደግሞ በሌላ እንድጠረጥረው አደረገኝ ። በየቀኑ አንድ ባልዲ !..ይሄ ሰውዬ ምን ነካው ? ትንሽ ቆይቶኮ  ”ልብስ አጥበን እንተኩሳለን ” የሚል ማስታወቂያ በሩ ላይ ሳይለጥፍ አይቀርም ብዬ አሰብኩ። አንድ ቀን ኮስተር ብዬ ”ምነው ልጄ ? ቤትህ ውስጥ አሳ ታረባለህ ንዴ?” ብዬ ብጠይቀው ” ምን ማለትዎ ነው። ለእግሬ መታጠቢያና ለምግብ ማብሰያ እንኳ የሚበቃ አልቀዳውም!” ብሎ ጮዅብኝ። እግዜር ያሳይህ የኔ ልጅ!…አሁን ሰው አዲሳባ ውስጥ እየኖረ በቀን በቀን እግሩን ይታጠባል?!…ለዚያውም በጫማ እየሄደ …ምግብ ለማብስልስ ቢሆን አንድ ጣሳ ውሃ አይበቃም ?…ወይስ ንፍሮ ና አጥሚት ነው ቀለቡ?…
እግዜር ያሳይህ ልጄ ! መብራት እስከምሽቱ ሁለት ሰዓት ተኩል ድረስ ያበራል ። እሰከ ምሽቱ ሁለት ሰዓት ተኩል !…ልብ አድርግ!…ከሥራ የሚገባው ባሥራ ሁለት ሰዓት ተኩል ነው ። ምነው እንደገባ አጠፋፍቶ ቢተኛ !…የኔ አምፑል ደመራ ነው ?..እኔኮ ቢጨንቀኝ ይሄ ሰውዬ በቤቴ ውስጥ የማታ ትምህርት ያስተምራል ንዴ? ብዬ ራሴን ጠየቅሁ። ታዲያ ሰው በጤናው እስከ ምሽቱ ሁለት ሰዓት ተኩል ድረስ አምፑል እንደ ጧፍ ያነዳል?….”
ይሄ ብቻ እንዳይመስልህ….የቤት ስልኬን ለማንም ውርጋጥ ሰጥቶ ያስበጠብጠኛል። ይገርምሃል ! አንድ ሰው በስልክ አምስት ደቂቃ ማናገር የጤና ነው ? ለዚያውም በሰው ቤት !!!…እግሩ አይንቀጠቀጥበትም? ጆሮው አይደነዝዝበትም? … እኔ እንዲያውም አንዳንዴ የኢትዮጵያ ሕዝብ በተራ በተራ የሚያናግረው ነው የሚመስለኝ !… ደሞ ስልክ እያናገረ ይስቃል !…ብልግና የመጨረሻ ደረጃ ሲደርስ በሰው ቤት ማሳቅ ይጀምራል ። የሱም እንደዚያ ነው እንግዲህ …”
”….የዚህ ሰውዬ ጉድ ማለቂያ ያለው እንዳይመስልህ …መጀመሪያ ሲከራይ መምህር ነኝ ! ብሎኛል ። እንግዲህ መምህር ተሆነ አንተው ራስህ ደሞዙን ገምት ! …የእሱ ደሞዝ ከሽሮ ና ከቲሸርት መግዣ አያልፍም ። እሱ ግን መምህር ነኝ ብሎ መጀመሪያ ቴፕ ገዛ ። ምን የመሰለ ቴፕ ! …ይግረምሽ ብሎ ቴሌቪዥን ገዝቶ አመጣ ። ያውም ባለቀለም ! ዘንግ የሚያክል አንቴና ያለው !…እንግዲህ ይሄ ሁሉ ተየት መጣ?!… እንግዲህ ዝም ካልኩት በቁሜ እያለሁ አንድስ የሚያክል ፍሪጅ ገዝቶ ሊያመጣ አይደለምን እያልሁ ስጨነቅ ቆየሁና
 ” ኪራይ ጨምር” አልኩት ። ሳያንገራግር ጨመረ። …….እና አሁን ይሄ ምኑ መምህር ነው ?…ትንሽ ቆይቶ እሳት የመሰለ ሽንጥ እየገዛ ይገባ ጀመር ። ልጄ አንተው ፍረደኝ!…በኪራይ ቤት ሽንጥ ትበላለህ ? ሽንጥ ትበላለህ ወይ ?….በዚህ ቢያበቃ ጥሩ ነበር ።
…ትንሽ ቆይቶ አንድ የኮሌጅ ማስታወቂያ ሲታይ እሱም በቴሌቪዥን ታየ ! ይታይህ የኔ ልጅ በሰው ቤት ውስጥ ሆነህ በቴሌቪዥን ትታያለህ?! …ትታያለህ ወይ ?”
 እንዲህ ሲሉኝ ዋሉ ።……
በማግስቱ የተከራየሁትን ቤት ለቀቅሁ ።
Filed in: Amharic