>

ሕጋዊነት...!! (ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም)

ሕጋዊነት…!

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም

በዚህ ሰሞን ፖሊቲከኛ-ነን ባዮች ሁሉ የያዙት የመመጻደቂያ ርእስ ሕጋዊነት ሆኗል፤ የሕጋዊነቱ ንትርክ የተፋፋመው በምርጫው ዙሪያ ነው፤ ምርጫው ይካሄድ ወይስ ይዘግይ የሚለው ጥያቄ መሠረቱ ቢሆንም ሕጋዊ ነው ሕጋዊ አይደለም የሚለው ጥያቄ ዋና ሆኗል፤ እንዲህ ያለውን የረቀቀ የሕጋዊነት ክርክር ዘጠና አምስት ከመቶ የሚሆነው ሕዝብ አራት የታወጁና አንድ የከሸፈ ሕገ መንግሥት ባለቤት መሆኑን አያውቅም፤ ለመራቀቅ እየሞከሩ የሚከራከሩትም አልተገነዘቡትም፤ ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ የሕግ ያለህ! የዳኛ ያለህ! እያለ የማይጮህ ደሀ አለ? የማየጮህ አእምሮ ያለው ሰው አለ? የማይጮህ ኅሊና ያለው ሰው አለ?
የምርጫውን ጊዜ እግዚአብሔር በመቅሰፍት ስለመታው ዛሬ ማንም ሰው ምርጫው ወዲህ ይሁን ወዲያ ይሁን ብሎ መወሰን አይችልም፤ ይህንን ሁሉም ስለሚያውቀው የክርክሩ ፋይዳ ዜሮ ነው፤ ሕጋዊነትን ዛሬ የማናውቅ ሰዎች በመስከረም ይገለጥልናል ብሎ … አያዋጣም፤ ከእግዚአብሔርም ጋር የመስከረም ሠላሳ ቀጠሮ ያገኘ ያለ አይመስለኝም፤ እግዚአብሔር እንደዚህ ያለ ቦለቲካ አይጫወትም፡፡
Filed in: Amharic