>
5:33 pm - Monday December 6, 0517

የአብዮታዊ ሰራዊት ጥቁር ቀን!!! (ደረጀ ደምሴ)

የአብዮታዊ ሰራዊት ጥቁር ቀን!!!

ደረጀ ደምሴ
የግንቦት 8,1981 ዓ.ም ያልተሳካ መፈንቅለ መንግስት እና ያስከተለው ውድመት
የዛሬ 31 ዓመት ግንቦት 8,1981 ዓ.ም በእነ ሜ/ጀ/መርዕድ ንጉሴ ጠንሣሽነትና መሪነት ከፍተኛ የደርግ ባለስልጣናት የፕሬዝዳንት መንግስቱ ኃ/ማርያምን መንግስት ለመገልበጥና አዲስ መንግስት ለመመስረት መፈንቅለ መንግስት ሙከራ ያደረጉበት ቀን ነው::
የመፈንቅለ መንግስቱ መሪዎች በግንቦት 8 ቀን አዲስ አበባ አምባሳደር አካባቢ በሚገኘው የመከላከያ መስሪያ ቤት በሜጀር ጀነራል መርዕድ ንጉሴ መሪነት የዕቅዱ አተገባበር ላይ ውይይት ይዘዋል።
ሌተናል ኮሎኔል መንግስቱ ሃ/ማርያም ወደ ምስራቅ ጀርመን ለጉብኝት ለመጓዝ በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፓላን ውስጥ ገብተዋል። የመፈንቅለ መንግስቱ መሪዎች መንግስቱን ለመገልበጥ መከላከያ ሚኒስቴር መ/ቤት ውስጥ የዕቅድ አፈፃፀም ውይይት ላይ የተለያዩ እቅዶች ቀርበው ነበር።
አንደኛው “ኮሎኔሉን በአየር ላይ እንዳሉ በአየር ሃይል ይመቱ ወይም እናጋያቸው” በሚሉና “ኮሎኔሉን የያዘቸው አውሮፕላን ሳትመታ እሳቸው ከሀገር ሲወጡ ይፈፀም” በሚሉ የጦሩ ከፍተኛ መሪዎች መሃከል አለመግባባት ነበረ።
አዲስ አበባ ያሉት የጦር መሪዎች እርምጃ ሳይጀምሩ ቀደም ብሎ በታሰበው የአፈፃፀም እቅድ መሰረት አስመራ የነበረው በእነ ሜጀር ጀነራል ደምሴ ቡልቶ የተመራው ወደ ማስፈፀሙ ገብቶ ስለነበር መንግስቱ ኃ/ማርያም ከስልጣን መውረዱን በአስመራ ሬድዮ እንዲህ በማለት አስነገረ።
“ለመላው የኢትዮዺያ ጦር ኃይሎችና የፖሊስ ሠራዊት አባሎች በሙሉ አገራችንና ሕዝባችንን ማባሪያ በሌለው ጦርነት ውስጥ እንድትዘፈቅ ያደረገውና ለብዙ ሺህ ዜጎች ሕይወት አላግባብ መጥፋት ምክንያት የሆነው በመንግስቱ ኃ/ማርያም የሚመራው የደርግ መንግስት ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ ከሥልጣን የተወገደ በመሆኑ ሠራዊቱ የዚህን ለውጥ ተጠቃሚ እንዲሆንና የተገኘውም ከፍተኛ ድል በመጠበቅ አዲስ ከተቋቋመው መንግስት ጎን እንዲቆም።
በተቃራኒው ወገን ለቆማችሁት ለሕዝባዊ ግንባር ሐርነት ኤርትራና ለሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ አባሎችና መሪዎች በሙሉ የጠላትህ ጠላት ወዳጅህ ስለሆነ አምባገነኑን የደርግ ስርዓት ለማስወገድ የጀመርነውን እንቅስቃሴ በመደገፍ ከጎናችን እንድትቆሙና በአገራችን ሠላም ለማምጣት በሚደረገው በዚህ ጥረት ውስጥ የበኩላቸሁን አስተዋፅዖ እንድታበረክቱ ጥሪያችንን በሁለተኛው አብዮታዊ ሠራዊት ስም እናስተላልፋለን!”
አዲስ አበባ ያለውንም እንቅስቃሴ ለመርዳት እና ቁልፍ ቁልፍ የተባሉ ቦታዎች ለመቆጣጠር አየር ወለዱን ከአስመራ ወደ አዲስ አበባ ተላከ ።
ይሁን እንጂ በኋላ ከዳ በተባለለው የደህንነት ሚንስትሩ ኮሎኔል ተስፋዬ ወልደስላሴ አማካኝነት መፈንቅለ መንግስት ሙከራው ከሸፈ። ኮሎኔል መንግስቱም ከምስራቅ ጀርመን ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ።
የከሸፈው መፈንቅለ መንግስት በአብዮታዊ ጦር አዛዦች ላይ ያስከተለው የማይተካ ውድመት
መፈንቅለ መንግስቱ ሲከሽፍ የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኤታማጆር ሹም የነበሩት ሜጀር ጄኔራል መርዕድ መከላከያ ሚኒስቴር የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ራሱን በገዛ ሽጉጣቸው አጠፋ።
የኢንዱስትሪ ሚንስትር ነበሩት ሜጀር ጄኔራል ፋንታ በላይ ከሙከራው በኋላ ተሰውረው በደርግ የደህንነት ሃይሎች ሲፈለጉ ከርመው ከሙከራው አራት ቀን በኋላ መከላከያ ሚኒስቴር ግቢ ውስጥ የሚገኝ ኮንቴይነር ውስጥ ተደብቀው ተገኙ። ጄኔራል ፋንታ ከተያዙ ከቀናት በኋላ እዚያው የታሰሩበት ማዕከላዊ ምርመራ ግቢ ውስጥ ባልታወቀ ሁኔታ ተገደሉ።
ሜጀር ጄኔራል ደምሴ ቡልቶ የመፈንቅለ መንግስቱን መክሸፍ ተከትሎ በገዛ ወታደሮቻቸው በአሰቃቂ ሁኔታ በጥይት ተደብድበው ከተገደሉ በኋላ አንገታቸው ተቆርጦ አስመራ ከተማ ላይ ይታይ እንደነበር ተፅፏል።
ሜጀር ጄኔራል አበራ መፈንቅለ መንግስቱ ከተካሄደበት መከላከያ ሚኒስቴር ግቢ አጥር ዘሎ አምልጦ ለወራት ሲፈለግ ከቆየ በኋላ አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኝ የዘመዱ ቤት ውስጥ ተደብቆ ቆይቶ በጥቆማ ፖሊሶች ደርሰውበት ቤቱ ሲከበብ አጥር ዘሎ ለማምለጥ ሲሞክር በተተኮሰበት ጥይት ተገደለ።
ይህች መከረኛ ኢትዮጵያ ልጆቿ እርስ በእርስ እየተጠፋፉ ከድጡ ወደማጡ ትንደረደራለች። ታሪክ እንደግማለን እንጂ ከታሪክ አንማርም። በወቅቱ የጀነራሎቹን መገደል አስመልክቶ ቢቢሲ ‘Ethiopia killed her own war Engineers’ ብሎ ዘግቦት ነበር::
በዚህ መፈንቅለ መንግስት ኢትዮጵያ ያጣቻቸው የቁርጥ ቀን ልጆቿ አንዱ
ሜጀር ጀነራል ደምሴ ቡልቶ ነበሩ።
በወርሃ ነሐሴ 1953 ዓ.ምአስራ ዘጠኝ ሰዎችን ያሳፈረውና ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነው ዲሲ 3 አውሮፓላን በበረራ ላይ እንዳለ በቀድሞው አጠራር በየረርና ከረዮ አውራጃ፤ ዳለቻ በሚባል ስፍራ ላይ ተከሰከሰ።
አውሮፓላኑ ወድቋል የተባለበት ስፍራ ለነፍስ አድን ስራ የሚመች ባለመሆኑ አየር ወላዶችን በዚህ ስፍራ ላይ በፓራሾት ማውረድ ግድ ሆነ። አየር ወለዶቹ በዚህ የነፍስ አድን ስራ ላይ በመሰማራት የብዙዎችን ተሳፋሪዎች ህይወት ለማዳን ቻሉ ፤ በዚህ ካባድ ግዳጁ ላይ በመሰማራት የወገንን ህይወት ከታደጉልን አራት የአየር ወለድ አባላት መሃከል የያኔው የመቶ አለቃ የኃላው ሜጄር ጆነራል ደምሴ ቡልቶ አንዱ ነበሩ።
እኝህ ቆፍጣና ወታደር በሲውዲን መኮንኖች ስልጠናን ካገኙ የሶስተኛው ዙር የክቡር ዘበኛ ሙሩቃን መሀከል አንዱ ነበሩ። በ1946 ዓ.ም ወደኮሪያ ካቀናው የኢትዮጲያ ጦርም ጋር በመዝመት ግዳጃቸውን በብቃት ተወጥተዋል።
ሜጀር ጄኔራል ደምሴ ቡልቶ በእስራኤል ሀገር የአየር ወለድ ስልጠናን ወስደው ወደ ወደ ሀገር ቤት በመመለስ የአየር ወለድ ጦርን በኢትዮጲያ ካቋቋሙት መኮንኖች መሀከልም በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ። በ1955 በደጋሀቡር ፣ በ1957 በባሌ የሶማሊያን ጦር በማሳፈር ይታወሳሉ። ጀነራሉ እዚህ ማእረግ ላይ ለመድረስ ድፍን 38 አመታት ፈጅቶባቸዋል።
ሜጄር ጄነራል ደምሴ ቡልቶ ከ1981 ዓ.ም ኮ/ል መንግስቱ ሀ/ማሪያምን ከስልጣን ለማስወገድ በተደረገው ሙከራ የአስመራውን እንቅስቃሴ በዋናነት መርተው እንቅስቃሴው ሲከሽፍ በጥይት ተደብደበው በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል።
በአስመራ እና በአዲስ አበባ የተገደሉ የአብዮታዊ ጦር መሪ መኮንኖች 
በአስመራ ከጀነራል ደምሴ ጋር  እንቅስቃሴ ላይ ተሳታፊ የነበሩና ሁዋላ ላይ የተገደሉ የኢትዮጲያ ስመጥር ጀነሎችና ሌሎች መኮንኖች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦
1. ብ/ጀነራል አፈወርቅ ወ/ሚካኤል
2. ብ/ጀነራል ታዬ ባላኪር
3. ብ/ጀነራል ታደሰ ተሰማ
4. ብ/ጀነራል ወርቁ ቸርነት
5. ብ/ጀነራል ንጉሴ ዘርጋው
6. ብ/ጀነራል ከበደ መሀሪ
7. ብ/ጀነራል ተገኔ በቀለ
8. ብ/ጀነራል ከተማ አይተንፍ
9. ብ/ጀነራል ከበደ ወ/ጻዲቅ
10.ብ/ጀነራል ሰለሞን ደሳለኝ
11. ዶ/ር ኮሎኔል ጌታቸው አወቀ
12. ኮሎኔል መስፍን አሰፋ
13. ኮሎኔል ፈቃደ እንግዳ
14. ሌ/ኮ ዘርአይ እቁባአብ
15. ሌ/ኮ ዮሀንስ ገብረማሪያም
16.ሻለቃ ካሳ ፈረደ
17. ሻለቃ ሚካኤል ማርቦ
18. ሻምበል ጌታሁን ግርማ
በአዲስ አበባው እንቅስቃሴ ላይ የተሳተፋና ሁዋላ ላይ ከተገደሉት መሀከል ደግሞ፦
1. ሜጀር ጄነራል መርዕድ ንጉሴ
2. ሜጀር ጄነራል ፋንታ በላይ
3. ሜጀር ጄነራል ኃይሉ ገ/ሚካኤል
4. ሜጀር ጄነራል ወርቁ ዘውዴ
5. ሜጀር ጄነራል አምሀ ደስታ
6. ሜጀር ጄነራል ዓለማየሁ ደስታ
7. ሜጀር ጄነራል ዘውዴ ገብረየስ
8. ብ/ጀነራል ደሣለኝ አበበ
9. ብ/ጀነራል ሰለሞን በጋሻው
10. ብ/ጀነራል ተስፋ ደስታ
11. ብ/ጀነራል እንግዳ ወ/አምላክ
12. ብ/ጀነራል እርቅይሁን ባይሣ
13. ብ/ጀነራል ነጋሽ ወልደየስ
14. ብ/ጀነራል ገናናው መንግሥቴ
15. ብ/ጀነራል ተስፋዬ ትርፌ
ምንጭ፦ አባቴ ያቺን ሰዓት እና ጄነራሎቹ
Filed in: Amharic