>

የተከለከሉ ሕልሞች!!! (አሰፋ ሀይሉ)

የተከለከሉ ሕልሞች!!!

አሰፋ ሀይሉ
 
* 8ኛው ንጉሥ እና የትንሣዔው ፓስተር!!!
ሰሞኑን “8ኛውን ንጉሥ” በአንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርቦ ተመለከትኩት፡፡ ከ100ሺህ በላይ ሰዎች ተመልክተውታል፡፡ እና ገረመኝ በጣም፡፡ ሚዲያው፡፡ ልጁ፡፡ የማኅበረሰባችን አጀንዳ ሆነው የሚንሸራሸሩ ርዕሰ ጉዳዮች፡፡ ገረሙኝ ሁሉም፡፡ 8ኛው ንጉሥ ህልሙ እንዲቃናለት ምኞቴ ነው፡፡ ግን ልጁ በእጁ የጨበጠውን የህክምና ትምህርትና የሜካኒካል ምህንድስና ትምህርት እርግፍ አድርጎ – በህልሙ የታየውን ንግሥና ሲያሳድድ ታየኝና ከልቤ አዘንኩለት፡፡
ግን ደግሞ… ማን ያውቃል? ማን ያውቃል…. የእረኛው ዳዊት የማይመስል የንግሥና ቅባት ነገር… በዚህስ ልጅ አይደገም እንደሆን ማን ያውቃል? ወይ ሕልሙን አሳክቶ ይገኝ ይሆናል፡፡ አሊያ ግን… (ብዬም አሰብኩ በሃዘኔታ) – አሊያ ግን… ልጁ አስቸኳይ የህክምና እርዳታ ያስፈልገውም ይሆናል ፡፡ የተደጋገመ የንግሥና ህልም፣ ሥር ከሰደደ የንግሥና ምኞት ጋር ሲዋሃድ – አንዳች የሳይካትሪ ትሪትመንት የሚያስፈልገው ህመም ምልክት ተደርጎ ይወሰድ ይሆን? “ዲሉዥናል ሜንታሊቲ” – እንደሚሉት ዓይነት? አላውቅም፡፡
እርግጥ ነው ያለንባት ዓለም ከፍታለች፡፡ በእውኑ ዓለም ስትጓዝ – ገጣሚው እንዳለው – አንዱን የሕይወት ቁልፍ ታግለህ በሩን ስትከፍት የምታገኘው ሌላ ዕድል የለም፡፡ ሌላ በትልቅ ቁልፍ የተዘጋ በር ነው የሚጠብቅህ፡፡ እና ብዙዎቻችን እውኗ ሕይወት እውነተኛ በሮቿን ስትጠረቅምብን – ወደማይዘጉት የህልም በሮች እናፈገፍጋለን፡፡ ለዚህ ነው፡፡ ጊዜው የህልም ነው፡፡ በህልም የምንኖርበት፡፡ በሌት ህልም የመዓልቱን መከራ የምናመልጥበት፡፡ በህልም ህይወት፡፡ በህልም ተስፋ፡፡ በህልም ኑሮ፡፡ በህልም ንግሥና የምንመላለስበት፡፡ አብዛኞቻችን.. በህልማችን ቅቤ እየጠጣን – በድርቀት እውን የምንመላለስበት ሕይወት ሆኗል የተረፈን፡፡
አንዳንዴ ግን ተዓምር አያልቅም አይደል? እና በህልሙ የታየው የገጠር ሸበላ – 7ኛው ንጉሥ – ህልሙን በእውን ካሳካ፣ ከመሰል መቼት የበቀለው 8ኛውስ ሕልመኛ ንጉሥ – ነገ ለዙፋን የማይበቃበት ምን ምክንያት አለ? – ምንም! “ተዘነጋሽ እንዴ.. ኢትዮጵያ መሆኑ..?”፡፡ ማየትና መስማት ብቻ ነው በትዕግሥት – ይህ 8ኛው ሺህ ዘመን ምን ይዞብን፣ ወይ ምን ይዞብን እንደሚመጣ፡፡ መጨረሻችንን ያሳምርልን፡፡
ስለ ሕልመኞቹ እየፃፍኩ… በመሐል አንድ እውነተኛ ገጠመኝ ትዝ አለኝ፡፡ ይሄን እውነተኛ ታሪክ “የትንሣዔው ፓስተር” ብላችሁ ያዙልኝ፡፡ የዛሬ 3 ዓመት ገደማ የሆነ ነው፡፡ በጋዜጣ ላይ የወጣ ዜና ነበር፡፡ ካልተሳሳትኩ በከፋ አካባቢ ይመስለኛል፡፡ አንድ ፓስተር “ከ9 ቀናት በኋላ የዓለም መጨረሻ ነው – ጌታ ሊፈርድ በእዚህ ተራራ ላይ ይመጣል” – በማለት ተከታዮቹን ስንቅ አስይዞ ከነቤተሰቦቻቸው የምፅዓት ቀንን ለመጠባበቅ ጫካ ያስገባል፡፡ እና ፆም ፀሎት ያስጀምራል፡፡ እና በ3ኛው ቀን ምን ሆነ?
በ3ኛው ቀን – በወረዳዋ የሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት በሥፍራው ደርሶ – ሁሉንም አማኞች ከነፓስተሩ ወደ እስር ቤት ይከታቸዋል፡፡ ሌሎቹ ቃላቸውን ሰጥተው ሲለቀቀቁ – ፓስተሩ ግን ለፍርድ ለመቅረብ በእስር ወደ ዞኑ እንደተላከ ያትታል ዜናው፡፡ በጥቁርና ነጭ ፎቶግራፍ አስደግፎ፡፡ ሳነበው እንደለመድኩት በሳቅ ፈነዳሁ… እና ለአንድ የኢህአዴግ ተወካይ ለነበረ በጓደኝነት ለምቀርበው ባልደረባዬ… ወሰድኩለት ጋዜጣውን፡- “ይኸው ጉዳችሁን እይ!” ብዬ፡፡ እሱም አንብቦት ከትከት ብሎ ሳቀና መለሰልኝ ጋዜጣውን፡፡
እኔ ግን ልለቀው አልፈለግኩምና፡- “ቆይ ግን እኔ የምጠይቅህ… ፓስተሩ ተከታዮቹን ጫካ ወስዶ የዓለም መጨረሻ ነውና መርዝ እንጠጣ፣ ራሳችንን እናጥፋ.. ” እስካላላቸው ድረስ… መብታቸው አይደለም ወይ የዓለምን መጨረሻ መጠባበቅ? መከላከያውን ምን ጥልቅ አደረገው?” አልኩት፡፡ አሁንም እየሳቀ… ምን ቢለኝ ጥሩ ነው? :-
“ምን አለ መሰለህ..? የኛ ሰዎች ከሐይማኖት አንፃር
ብቻ አያዩትም…፤ እነሱ የሚያዩት… ዛሬ ጌታ
ይመጣል ብሎ ሰዎችን ሰብስቦ ጫካ ማስገባት
ከቻለ… ነገ ደግሞ ኑ ኢህአዴግን እናውርድ ብሎ
ሰዎችን ጫካ ሊያስገባ ይችላል.. ብለው ነው!
አየህ? ይሄ ሰውዬ አደገኛ ነው ብለው ነው
የሚያስቡት.. እና ካሁኑ መገራት አለበት..
እንደዚያ ይመስለኛል የሚያስቡት!”
ብሎኝ እርፍ!!! (በተራዬ ረ….ዥም ሳቅ!) ይሄ መንግሥት በሥልጣኑ ስትመጣበት… እንዴት ነገሮችን አርቆ እንደሚያስተውል…!! ሆሆ..!! ጉድ እኮ ነው፡፡
በነገራችን ላይ – በሕልሙ ሲነግሥ የታየውና ሕልሙን የተናገረው 8ኛው ንጉሥ – በሕልሟ ስትነግሥ ከታያትና ህልሟን በይፋ ካወጀችው 5ኛዋ ንግሥት ከእህተ ማርያም ጋር – በ7ኛው ንጉሥ  መታሰሩን ስሰማ – ግፍ አይሁንብኝና ሳቅ አመለጠኝ! ደግሞም አዘንኩ በኛ ሀገር ነገር! በእውኑ ዙፋኑን መመኘት ተወው…፡፡ በህልም እንኳ ዙፋኑን ማለም የሚከለከልባት ሀገር! በእርግጥ በትክክል 8ኛው ንጉሥ ለእስር ስለመዳረጉ እርግጠኛ መረጃው ኖሮኝ አይደለም፡፡ ግን ታሰረም አልታሰረ.. በጥቅሉ… 7ኛው ንጉሥ የዙፋን ህልም ባይታይህ የሚመርጥ ይመስለኛል፡፡ ከታየህ ደግሞ ህልምህን ኤዲት እያደረግክ መናገር ግድ ሊልህ ነው ማለት እኮ ነው!
ስለ ዙፋን ህልም ሲነሳ… መቼም ነገርን ነገር ያነሳዋል አይደል?… እነ እስክንድር ነጋ የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክርቤት መመሥረቱንና የታከለ ኡማ ህገወጥ አስተዳደር የሥልጣን ዘመኑ እንዳበቃ ለሕዝብ ይፋ ባደረጉ ማግሥት – 7ኛው ንጉሥ በንዴት ዓይኖቹ እየተንቀለቀሉ የተናገረው አሁን መጣብኝ፡- “እንዲህ ዓይነት ቀልድ የለም! ባላደራ ምናምን እያሉ የሚቀጥሉ ከሆነ በግልጽ ጦርነት ውስጥ ነው የምንገባው! በዚህች ሀገር ያለው መንግሥት አንድ መንግሥት ነው! እሱም እኔ የምመራው መንግሥት ነው! ሌላ የለም!” (አቤት በሥልጣን ለመጣ ሰው የሚመነጨው ንዴት! – አያድርስ ነው!!)፡፡
በቅርቡ ደግሞ የኢህአዴግ ፈጣሪ ወያኔ-ህወኀት – እና እነ ጃዋር ኢድሪስ መሃመድና እነ ልደቱ አያሌው – የአብይ አህመድ መንግሥት ምርጫ ካላካሄደ – ከመስከረም 30 በኋላ – ህጋዊ ሥልጣን ያለው መንግሥት የለም – ብለው ሲያውጁ – 7ኛው ንጉሥ ልክ በእስክንድር ላይ ብሎ የነበረውን ዛቻ ደገመው! “ይሄ ምርጫ ምናምን እናደርጋለን የሚባለው ነገር ከቀጠለ… አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ ነን.. እርምጃ እንዲወሰድ ትዕዛዝ እሰጣለሁ!” (ኧረ የሥልጣን ያለህ!?!!) – በእርግጥ 7ኛው ንጉሥ – በዚህ አኳኋኖቹ – ጓድ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያምን ያስታውሰኛል!!
7ኛው ንጉሥ በሥልጣኑ ስትመጣበት የሚያሳየው አኳኋንና ንግግር ሁሉ የመንጌን ንግግር ይቀሰቅስብኛል፡፡ መንጌ እንዲህ አልነበር ያለው?፡- “እኔኮ የሚገርመኝ.. ይህ ሕዝብ ገና የስንዴና የበቆሎ ቂጣ በልቶ ሳይጠግብ… ምን ሥልጣን ላይ እንደሚያንጠላጥለውኮ ነው! ደግሞ.. ይህቺን ወንበር የሚቀመጥባት አንድ ሰው ነው – እሱም እኔ ነኝ!”(ሃሃሃሃ… አይ መንጌ!! ይመችህ አቦ!! ያኛው ጣት እንቆርጣለን እያለ አለፈ፣ 7ኛው ንጉሥ ደግሞ መጣና – ወደ ግልጽ ጦርነት እንገባለን! የማያዳግም እርምጃ እንወስዳለን! ያዙኝ ልቀቁኝ- አይ ሥልጣን! አንቺ በአራት ኪሎ ያለሽ ሥልጣን ሆይ! እውን ነፍስሽ ይማራል?!!)
ድሮ ‹‹ምኞት አይከለከልም›› የሚሉት አባባል ነበር፡፡ ኖኖኖ! ያ አልፎበታል፡፡ በኛ ሀገር – በእውንህ ከተመኘህ ግልጽ ጦርነት ውስጥ ዘልሎ የሚገባ 7ኛ ንጉሥ አለ፡፡ በህልምህ ከተመኘህ – የገባህበት ገብቶ መቀመቅ የሚከትትህ 7ኛ ንጉሥ አለ፡፡ እግዜሩስ ግን ምነው እንዲህ ከፋ ግን በእኛ ላይ?!! የምሬን እኮ ነው…፡፡ የዘንድሮ እግዜር… እንደ 8ኛው ንጉሥ በህልምህ ንግሥና እያሳየ – በእውን ወደ ማረፊያ ቤት ያገባ ጀመር!? በሰው ነፍስ ይጫወት ጀመር እግዜሩም እንደ ሰው?!! እና እውነት 8ኛው ሺህ አልገባም ገና?!! (ሀሀሀ..!)
አይ ጊዜ!! አይ.. የተገለባበጠ ሕልም!! ዙፋን አይተህ ለሸቤ!?! እንዲያ ከሆነስ… ህልማችንን ያክፋልን ብሎ መለመን ነው እንጂ ፈጣሪን..! ሌላ ምን ይባላል?! የንግሥና ህልም አይተው – የእውን እስር የጠበቃቸውን የህልመኞቹን ነገሥታት – የ8ኛውን ንጉሥ እና የ5ኛዋን ንግሥት መጨረሻ ሳስብ – ምን ትዝ አለኝ? – “የህልሜ ደራሲ” – የሚለው ግጥም፡-
“የህልሜ ደራሲ
“ስስምሽ ስላደርኩ – ትላንትና በህልሜ
ዛሬ ቶሎ ተኛሁ – ልስምሽ ደግሜ፡፡
ታዲያ ምን ያደርጋል – የህልሜ ደራሲ አትታደል ቢለኝ
ህልሜን ገለባብጦ – ሲስሙሽ ኣሳየኝ!”
አበቃሁ፡፡
ሕልማችንን የሚከፍት የሚዘጋ አንድዬ – ከአጓጉል ሕልም ይጠብቀን!
Filed in: Amharic