>

የጣና አስገራሚ እውነታዎች‼️  (ታደለ ጥበቡ)

የጣና አስገራሚ እውነታዎች‼️ 

ታደለ ጥበቡ

የኢትዮጵያ ልጆች የጉንደት፣የጉራዕ፣የአድዋ፣ የማይጨው እና የካራማራ ድል በጣና ላይ ይደግሙታል!!

•••
ጣና ከመከራው ውኃ የተረፈ፣ ከኤዶም ገነት የተጨለፈ፣ የቃል ኪዳኗን መርከብ ያንሳፈፈ፣ ፍጥረቱንም ሁሉ ያተረፈ ሐይቅ ነው፡፡ በልብ አምሳያ የተሠራ፣ ከልብ የመነጨ ሃይማኖት፣ እምነት፣ ታሪክ፣ ትውፊት፣ አርቆ አሳቢነትና ደግነትን አቅፎ ይዟል፡፡
•••
ጣና ምንጩ ከኤዶም ገነት ሚወርደው ግዮን በላዩ ላይ ይሄዳል።
•••
ጣና በኢትዮጵያ ትልቁ ሐይቅ ነው።አጠቃላይ ስፋቱ 695,885 ሔክታር ነው። ከሰሜን እስከ ደቡብ ያለው የሐይቁ ርዝመት 85 ኪሎ ሜትር ሲቃረብ ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ ያለው ስፋቱም 66 ኪሎ ሜትር ተገምቷል፡፡
•••
ጣና  በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ ከሰኔ 1 ቀን እስከ ሰኔ 5 ቀን 2007 ዓ.ም. ጉባኤውን ያካሄደውና የብዝኃ ሕይወት ጉዳይን የሚመረምረው ዓለም አቀፉ ምክር ቤት ጣና ሐይቅን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣የሳይንስና የባህል ድርጅት ዩኒስኮ በያዘው ብዝኃ ህይወት ክምችት በቅርስነት መዝግቦታል።
•••
ጣና ሐይቅ በጥንታዊ ቋንቋ (ግእዝ) አገላለጽ ‹‹ጻና ሐይቅ›› ይባላል፡፡ድንግል ማርያም በገዳሙ የነበራትን ቆይታ አጠናቃ ስትመለስ “ፀአና በደመና” በደመና ጫናት የተባለው በጊዜ ብዛት ለአሁኑ የሐይቁ መጠሪያ ስም “ጣና” መሠረት ሆኖታል ነው የሚባለው።
•••
ጣና ምድር ጥፋት ውኃ በጠፋች ጊዜ ዘር እንዲያተርፍ ቃል ኪዳን የተሰጠው የኖኅ መርከብ ማየ አይኅ መጉደል ሲጀምር በ7ኛ ወር ከወሩም በ27ኛው ቀን  በአናቱ ላይ ያረፈበት ታላቅ ሐይቅ ነው። የኖኅ መርከብ ያረፈበትም አራራት ተራራ በጣና ራስጌ (ዘጌ)  የይጋንዳ ተክለሃይማኖት ቤተ ከርስቲያን  ላይ ይገኛል።
•••
በክርስቶስ ልደት ገደማ ስለግብጽ ብዙ ምርምር ያደረገው ስትራቦ ዓባይ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኝ ትልቅ ሐይቅ እንደሚነሳ ያውቅ ነበር ይባላል፡፡ የሐይቁን ስምም ስትራቦ “ሴቦ” ብሎታል፡፡
የሁለተኛው ዘመን የግብጽ መልክዓ ምድር ተመራማሪ ገላውዲዮስ ፕቶሎሚ ደግሞ “ኮሎ” ይለዋል፡፡
የአቴናው ድራማ ጸሐፊ አስክለስ “መዳብ የተቀባው ሐይቅ የኢትዮጵያ ጌጥ” ብሎታል፡፡ ባለቅኔው ሆሜርም “ከሌሎች የተለየና ጥርት ያለ የውኃ ባለቤት ነው” ብሎ ጠርቶታል፡፡
•••
ከ3000 ዓመት በፊት የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ የኾነችው ታቦተ ጽዮን ቀዳማዊ ምኒሊክ  ከ318 ሌዋውያን እና ከ12 ነገደ እስራኤል ጋር ይዞ ወደ ኢትዮጵያ በመጣ ጊዜ ያረፈችው ጣና ቂርቆስ ገዳም ላይ ነው።ዛሬም ጣና ቂርቆስ 4 ሺህ 518 ዓ.ዓ ጀምሮ መሰዋዕተ ኦሪት ይቀርብበት የነበረ፣አራት ማዕዘን ቅርጽ ያለው ከአናቱ ላይ እንደ ሙቀጫ የተቦረቦረው ድንጋይና የኦሪት  የብረት መስዋዕት ማቃጠያ በሥፍራው ይገኛሉ።ከታቦተ ጽዮን ጋር የመጣው ሊቀ ካህናቱ አዛርያስ ጣና ቂርቆስ ገዳም ላይ  ነው የተቀበረው።
•••
ከ3000 ዓመት በፊት የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ የኾነችው ታቦተ ጽዮን ባረፈችበት ጣና ቂርቆስ ገዳም በአንደኛው መክዘ ሄሮድስ ጌታን ሊገድል በፈለገ ጊዜ
ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጇ ከዮሴፍና ከሰሎሜ ጋር 3 ወር ከ10 ቀናት የተቀመጠችበት ቦታ ነው።
•••
ጣና በአጠቃላይ በውስጡ ከ37 በላይ ደሴቶች ሲኖሩት 27 ገዳማትን አቅፎ ይዟል።ገዳማቶች በ14ኛ ምእት ዓመት አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ባመነኮሷቸው ‹‹ሰባቱ ከዋክብት›› ተብለው በሚጠሩት ቅዱሳን አባቶች የተመሠረቱ ናቸው።ከገዳማቶች
መካከል፦
•••ደብረ ማርያም
•••ክብራን ገብርኤል
•••ዑራ ኪዳነምህረት
•••መሀል ዘጌ ጊዮርጊስ
•••አቡነ በትረ ማርያም
•••አዝዋ ማርያም
•••ዳጋ ኢስጢፋኖስ
•••ይጋንዳ ተለሃይማኖት
•••ናርጋ ስላሴ
•••ደብረ ሲና ማርያም
•••ማንድባ መድኃኒዓለም
•••ጣና ቂርቆስ
•••ክርስቶስ ሳምራ ገዳም
•••ራማ መድሕኒ ዓለም
•••ኮታ ማርያም…እና ሌሎችም ገዳማቶች ይገኙበታል።
•••
ሰባቱ ከዋክብት የሚባሉት አኩስም አቅራቢያ የሚገኘው የደብረ በንኮል ገዳም መሥራች አቡነ መድኅነ እግዚእ ደቀ መዛሙርት ናቸው።እነርሱም፦
1.አቡነ ታዴዎስ~ደብረ ማርያም መሥራች
2.አቡነ ዘዮሐንስ~የክብራን እና የእንጦስ ገዳም መሥራች
3. አቡነ በትረማርያም~የዘጌ ጊዮርጊስ መሥራች
4. አቡነ  ኂሩተ አምላክ~የዳጋ እስጢፋኖስ መሥራች
 5.አቡነ ኢሳይ~የመንዳባ መድኃኔዓለም መሥራች
6.አቡነ ዘካርያስ~ደብረ ገሊላ መሥራች
7.አቡነ  ፍቁረዮሐንስ~ጣና ቂርቆስ መሥራች ናቸው።
•••
ጣና ቂርቆስ ታቦተ ጽዮን ለ800 ዓመታት ያረፈችበት፣ ሊቀ ካህናቱ አዛርያስ የተቀበረበት፣ቅድስት ድንግል ማርያም  ከልጇ ከዮሴፍና ከሰሎሜ ጋር 3 ወር ከ10 ቀናት የተቀመጠችበት ገዳም ነው።ቅዱስ ያሬድ ምልክት የሌለውን ድጓ የጻፈባትና መጽሐፉና መስቀሉ የሚገኝበት ገዳም ነው።
•••
ዳጋ እስጢፋኖስ በዐፄ ይኩኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት በአቡነ ሒሩት አምላክ የተመሠረተ ሲሆን ቤተ ክርስቲያኑ ውኃ ዘመን የሰው ዘር በኖኅ መርከብ አማካይነት መዳኑን ለማመልከት በመርከብ ቅርፅ የተሠራ ነው።የዐፄ ዳዊት (1374-1406 ዓ.ም)፣የዐፄ  ዘርዓ ያዕቆብ (1426-1460 ዓ.ም)፣የዐፄ  ሱስኒዮስ (1600-1625 ዓ.ም.) እና የዐፄ  ፋሲል (1625-1660 ዓ.ም) አስክሬን ሳይፈርስ በክብር የሚገኘው በዚሁ ገዳም ነው።
ይኼ ታሪካዊ ሐይቅ ነው  እምቦጭ በተባለ አረም ሊጠፋ የተቃረበው። 
Filed in: Amharic